Saturday, 13 July 2013 10:37

ዘዴ የሌለው ወፍ ቅርንጫፍ በሌለው ዛፍ ላይ ያርፋል!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ኤዞፕ ከፃፈልን ተረቶች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፡- ከዕለታት አንድ ቀን ብዙ ጥንቸሎች ተሰብስበው ይመካከራሉ፡፡
አንደኛ ጥንቸል - “ጐበዝ እኔ ኑሮ መሮኛል፡፡ በየአቅጣጫው ጠላት እኛ ላይ እያነጣጠረ መግቢያ መውጪያ አሳጣን፡፡ በየጊዜው መደበቅ፣ ከሰው መሸሽ በጣም ነው ያስጠላኝ” አለች፡፡
ሁለተኛዋ ጥንቸል - “እኔ ደሞ በጣም የሰለቸኝ ከውሻ መሸሽ፡፡ ድንገት ብቅ ካለ እኮ ካለእኛ ጠላት ያለው አይመስለውም፤ ክፉኛ ያባርረናል፣ ያሳድደናል” አለች፡፡
ሦስተኛዋ ጥንቸል - “እኔ ደግሞ እንደኛው የዱር አራዊት የሆኑ አውሬዎች ናቸው እረፍት የነሱኝ፡፡ ምን እንደሚበጀኝ እንጃ” አለች፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ ሁሉም ብሶታቸውን ተነጋገሩ፡፡ በመጨረሻም፤ “እንዲህ ስቃይ ከሚበዛብንና በየቀኑ የሰውም፤ የውሻም፣ የአዕዋፍም፣ የዱር አውሬም ምግብ ከምንሆንና ምንም አቅም የሌለን ፍጡራን ሆነን ከምንቀር በቃ ውሃ ውስጥ ሰጥመን ብንሞት ይሻለናል” አሉ፡፡
ከዚያም ሁሉም በአንድ ድምጽ “አሰቃቂውን ህይወታችንን ላንዴም ለሁሌም እንገላገለው” በሚል በአቅራቢያቸው በሚገኝ ሰፊ ኩሬ ውስጥ ሰምጠው ሊሞቱ ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡
በኩሬው ዳርቻ ብዙ እንቁራሪቶች ተቀምጠው ፀሐይ ይሞቃሉ፡፡ እንቁራሪቶቹ በርካታ ጥንቸሎች ወደነሱ እየሮጡ ሲመጡ ተመለከቱና፤
“ጐበዝ፣ ጥንቸሎች ሊዘምቱብን ወደኛ እየተንደረደሩ ነው፡፡ በጊዜ ብናመልጥ ይሻለናል” ተባባሉ፡፡
ወዲያው ከኩሬው ዳርቻ ወደ ውሃው ጡብ ጡብ እያሉ በጣም ወደታች ጠልቀው ተደበቁ፡፡
ይሄኔ ከጥንቸሎቹ መካከል ብልሁ፤
“ቆይ ቆይ ቆይ” ብሎ ሁሉንም ጥንቸሎች አስቆማቸው፡፡
ሁሉም በርጋታ እሱን ለማዳመጥ ዞሩ፡፡
ጥንቸሉም፤
“አያችሁ፤ ራሳችንን ማጥፋት የለብንም፡፡ ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁ፣ እነዚህ እንቁራሪቶች እኛን ፈርተው ውሃ ውስጥ ገቡ፡፡ እኛንም የሚፈራን አለ ማለት ነው፡፡ እኛ ሌሎችን ፈርተን ራሳችንን እናጥፋ አልን፡፡ በዓለም ላይ ግን ሁሉም የሚፈራው አለው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ያጠፉናል ብለን መፍራት የለብንም፡፡ እኛም የምናጠፋው አለና” ብሎ ሁሉንም መለሳቸው፡፡
                                                        ***
ተስፋ ቆርጦ፣ ህይወት አበቃለት ከማለት በፊት ከእኔ የከፋም አለ ብሎ ማሰብ ትልቅ መላ ነው፡፡ ሁሉም የላይና የበታች አለው፡፡ የህይወት ሰልፍ ይህን ልብ እንድንል ያስገድደናል፡፡ ከጅምላ ውሳኔ መጠንቀቅ ደግ ነው፡፡ የተሻለው ካልተሻለው ጋር መክሮ ዘክሮ ካልተጓዘ አገር የጥቂቶች ብቻ ትሆንና ኑሮ በምሬት የተሞላ ይሆናል፡፡
የሀገራችን አሳሳቢ ጉዳዮች አያሌ ናቸው፡፡ በለውጥ ጐዳና ላይ አሳሳቢ ጉዳዮች ከበዙ ለውጡን ማዥጐርጐራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነባራዊ ሁኔታው በፈቀደው የሚከሰቱትን እንቅፋቶች ሁሉ ግን “ፀረ ልማት፣ ፀረ ዕድገት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት” ወዘተ ብሎ ከመፈረጅ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ሩጫችን በፈጠነ መጠን “ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል”ን አለመርሳት ነው፡፡
የኦዲት ሪፖርትን በጥንቃቄ ማየት ተገቢ ነው፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ምንጣፍ ለመግዛት ከመሯሯጥ አስቀድሞ በቅጡ ማቀድ ይሻላል፡፡ ፈሰሱ ሲበዛ ሜዳ የፈሰሰ እቅድ መኖሩን እንደሚያሳይ አንዘንጋ፡፡ በስንት ቢፒ አር፣ በስንት ግምገማ ተደግፎ ከእቅድ በላይ የተባለለት አፈፃፀም ኋላ በፈሰስ ሲመነዘር “አብዮቱ ግቡን መታ” እንደማያሰኝ እንወቅ፡፡ ሌላው አሳሳቢ ነገር የተጠርጣሪዎች መብዛት ነው፡፡ በቤት፣ በመሬት፣ በኤሌትሪክ ዕቃዎች፣ በጉምሩክ፣ በአገር ውስጥ ገቢ፣ ወዘተ እየጨመሩ ያሉ ተጠርጣሪዎች የሀገራችንን የሙስና ብዛትና ከፍተኛነት እየጠቆሙ ነው፡፡
ለዚህ ለምን አልተዘጋጀንም? ሊሠሩ የታሰቡ ነገሮች ምን መዘዝ እንደሚያመጡ ከወዲሁ ማስተዋል እንደምን ያቅታል፤ ጥፋተኝነታቸው የተነቃ ብዙ ሥራ ሲሰራ ብዙ እጅ ገንዘብ ውስጥ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ባለሥልጣኖችሽ ሲነቃባቸው በቦሌ ሲወጡ ዝም ብሎ ማየት ተፈልጐ ነው ሳይታወቅ? ሄደው ቀሩ የሚባሉ ሰዎች ነገር ተድበስብሶ የሚታለፈው “ተገላገልነው” በሚል ስሜት ይሆንን?
ሙስና ከተወራ ብዙ ጊዜ ያስቆጠረ፣ ግባራዊ ገፁ ዛሬ የታየ ነው፡፡ ፀረ -ሙስና እርምጃው አለቃና ምንዝር ሳይል የሁሉንም በር ማንኳኳት ይገባዋል፡፡
ገና የሚንኳኩ በሮች ጀርባ የሚገኙ ሙሰኞች፤ “ግጥም ሞልቶን ነበር በስልቻ ሙሉ
አንዷ ጠብ ብትል ሁሉም ዝርግፍ አሉ” ዓይነት እንደሚሆን የሚያቅ ያቀዋል፡፡
ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አኳያ መታየት ያለባቸው፣ ግን እንደዘበት እየታዩ የሚታለፉ አያሌ ጉዳዮች አሉ፡፡ በጥንቃቄ ጊዜ ወስዶ ከልብ ሙስናን ፈልፍሎ ማውጣት ይበል የሚባል ቢሆንም፤ አላግባብ ጊዜ መስጠትም የዚያኑ ያህል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ጊዜው በረዘመ ቁጥር የወንጀሎች መደራረብ፣ የህዝብና የሀገር ጉዳት የዚያኑ ያህል ያበዛልና!
የትኩረት አቅጣጫ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ብቻ ሲሆን ሌሎች የተበላሹ ነገሮችን እንዳናይ ስለሚያደርግ ዕይታችን ይጠብብናል፡፡ ስለሆነም ጉዳዮች ሁሉ በአገር ዙሪያ ሲጠነጠኑ የራሳቸው ተያያዥ ድርና ማግ ይኖራቸዋልና ዘርፎቹን ሁሉ በቆቅ ዐይን አጣምሮ ማየት ይገባል፡፡ አለበለዚያ “ዘዴ የሌለው ወፍ ቅርንጫፍ በሌለው ዛፍ ላይ ያርፋል” እንደተባለው ይሆናል፡፡

Read 3974 times