Saturday, 06 July 2013 10:58

ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ “ይቅርታን የደፈሩ መሪ”!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(20 votes)
  • ሃይ ባይ ያጣውን የመብራት መቆራረጥ “እያስመዘገብኩ ነው” (ለታሪክ!!) 
  • በአባይ ላይ የተደረገው የኢህአዴግና የተቃዋሚዎች ውይይት “የጨበራ ተዝካር” ተብሏል!
  • የአገር ፍቅር መለኪያ ቴርሞሜትር የሚያስፈልግበት ዘመን ላይ ደርሰናል! (አባቶቻችን እንዳይሰሙ)

ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣውን የመብራት መቆራረጥ በየጊዜው ስፅፍ “እህ” ብሎ የሚያደምጠኝ አግኝቼ አንዳች ነገር ይሻሻላል ወይም ይለወጣል በሚል ተስፋ እንዳልሆነ ለውድ አንባብያንም ሆነ ለኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች በትህትና ላስታውቃቸው እወዳለሁ፡፡ (እንዲሳሳቱብኝ አልፈልግማ!) ይሄኔ የመ/ቤቱ ሃላፊዎች “ታዲያ ምን ለመፈየድ ነው በየጊዜው የምትሞነጭረው ?” ብለው ሊናደዱብኝ ይችላለሉ (የእነሱ ብሶ!) እኔ ግን መልሴ በጣም አጭር ነው - በየጊዜው የመብራት ኃይልን ጥፋቶች እየነቀስኩ የምፅፈው ለሌላ ሳይሆን “እያስመዘገብኩ ነው” ለማለት ያህል ነው፡፡ “ወይ አዲስ አበባ” በተሰኘ ውብ ልብወለዱ እውቅናን ያተረፈው ተወዳጁ ደራሲ አውጎቾ ተረፈ፤ “እያስመዘገብኩ ነው” በሚል ርዕስ በፃፈው ድንቅ አጭር ልብወለዱ ውስጥ የቀረፀው ገፀባህርይ፣ በደርግ ዘመን የቀበሌ አብዮት ጠባቂዎችና ካድሬዎች የሚያደርሱበትን በደል በህጋዊ መንገድ ተጋፍጦ መከላከል ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት፣ ጠጅቤት ውስጥ ላገኘው ጠጪ ሁሉ የሰሩትን በደል እየዘከዘከ “ይሄንንም እያስመዘገብኩ ነው!” ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ማድረግ አለመቻሉን እናስተውላለን፡፡ እኔም አሁን ምንም የማድረግ አቅም የሌለውን መብራት ቦግ ድርግም የሚልበት ነዋሪ ወክዬ “እያስመዘገብኩ ነው” እያልኩ ነው፡፡ (እንጂማ ተስፋ ከቆረጥንማ ብዙ ክረምቶች ጠቡ!)

እናላችሁ --- ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ላይ እንደተለመደው መብራት ተቋርጦ ነበር - ለአንድ ሰዓት ያህል፡፡ (ይሄንንም እያስመዘገብኩ ነው!) የአሁኑን ሳምንት የመብራት መቋረጥ ልዩ የሚያደርገው ምን መሰላችሁ? ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመልሶ ሲመጣ በከፊል ነበር - በአንድ ቢሮ ውስጥ ከነበሩ ሶስት አምፑሎች አንዱ ብቻ ነበር የሚበራው። ኮምፒውተሮችም ሙሉ በሙሉ አይሰሩም - በኃይል አቅም ማነስ፡፡ (ይሄንንም እያስመዘገብኩ ነው!) የሚገርማችሁ ግን እሱም ከአንድ ሰዓት በኋላ ድርግም ብሎ ጠፋ - “ይለይላችሁ” በሚል፡፡ ከዚያ በኋላ ከአራት ሰዓት በኋላ ነው ተመልሶ የመጣው። “ይሄንንም እያስመዘገብኩ ነው” (ለታሪክ!!) እስቲ አስታውሱኝ ----የትኛው ገጣሚ ነው “አገርህ ናት በቃ” የሚል ከሃሳብ ድካም የሚገላግል ቅኔ የተቀኘው? አሁን ያማረኝ መብራት ሳይሆን እሱን ግጥም በሻማ ወይም በፋኖስ እየኮመኮሙ መቆዘም ብቻ ነው፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ትንሽ ፈገግ የሚያሰኝ ወግ እናውጋ፡፡ መብራት ባይኖርም እኮ ማውጋት ይቻላል፡፡ የፈገግታን ጧፍ አቀጣጥለን። ይኸውላችሁ በመዲናችን አንድ ጥግ ላይ የነዋሪዎችን ልብስ እየጠቀመ ኑሮውን የሚገፋ አንድ ብርቱ ኢትዮጵያዊ አለ፡፡ በተረት ዓለም ሳይሆን በገሃዱ ዓለም፡፡ እዚህችው አዲስ አበባችን - ሸገር እምብርት ላይ፡፡ ልብሳቸውን ለሚጠቅምላቸው ደንበኞቹ ታዲያ ቀልድ ይመርቃል አሉ - መራራ ኑሮን ማጣፈጫ ፡፡ ይሄ ልብስ ሰፊ ከመዲናዋ በርካታ ልብስ ሰፊዎች የሚለይበት ነገር አለ ከተባለ በኑሮ ፈተናና ውጣ ውረድ አለመማረሩ ነው፡፡ ይልቁንም እንደዘበት ቀልዶበት ያልፋል፡፡ ቀልዱ ታዲያ ከራሱም አልፎ በየራሳቸው የግል ህይወትና ችግር ምርር ያሉ ደንበኞቹን በሳቅ ይሸኝበታል፡፡
የዚህን ልብስ ሰፊ ታሪክ የማወጋችሁ ደንበኛው የሆነች ወዳጄ ከነገረችኝ ነው፡፡ ልብስ ሰፊው ሥራውን የሚከውንበት ዳስ ቢጤ እንኳን የለውም - ፈረንጆቹ እንደሚሉት “ኦፕን ኤር” ላይ ጭንቅላቱን ከጠራራዋ ፀሃይ በሚጠቅማቸው ልብሶች እየተከላከለ ሲጠግን፣ ሲጠቅም ይውላል። የደንበኞቹን ልብስ - የደንበኞቹን ኑሮ፡፡ በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ሊከበር ጉድ ጉድ ሲባል፣ ከዚህ ቀደም አይቷቸው የማያውቅ ቁጣ ቁጣ የሚላቸው ካድሬዎች ካለበት ተነስቶ ወደ ውስጥ--- በጣም ውስጥ--- እንዲገባ በማስፈራርያ የታጀበ ትዕዛዝ አስተላልፈው ሄዱ - ምክንያቱን እንኳን ለማስረዳት ሳይጨንቃቸው፡፡ (“ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ” አለ አሉ) መቼም ሰው አይደል --- “ምን አጥፍቼ ነው አስፈራርተውኝ የሄዱት? አብሉኝ አጠጡኝ አላልኩ?” እያለ ትንሽ መብከንከኑ አልቀረም፡፡ በኋላ ግን “ለመንግስት ስንትና ስንት ሺ ብር ግብር እንከፍላለን” እያሉ ይመፃደቁበት የነበሩ የግሮሰሪዎችና ጠጅቤቶች የበረንዳ ዳሶች ሳይቀሩ መፍረሳቸውን ሲመለከት ግን ተረጋጋ፡፡ ውስጥ በጣም ውስጥ ገብቶ አንድ ጥግ ላይ የደንብኞቹን ልብስ መጥቀሙን ቀጠለ። የአፍሪካ ህብረት ምስረታ በዓል ተከብሮ ከተጠናቀቀ በኋላ (በነገራችሁ ላይ የአፍሪካ የነፃነት አባቶች እየተባሉ የሚሞካሹት መሪዎች ጭምብል ያጠለቁ አምባገነኖች መሆናቸውን አያችሁልኝ አይደል?) ወዳጄ የምታስጠግነው ልብስ ኖሯት ወደዚህ ልብስ ሰፊ ደንበኛዋ ትሄዳለች፡፡ በሰው ሰው ተጠቁማም ውስጥ ድረስ ዘልቃ ታገኘውና ጥያቄ ታቀርብለታለች-
“አንተ ጉደኛ ፤ ደግሞ እዚህ ውስጥ ምን ከተተህ እባክህ?” ትለዋለች - መልሱን በጉጉት እየጠበቀች፡፡
ቀልደኛው ልብስ ጠቃሚም ፈገግታውን በማስቀደም፤ “እድሜ ለፀሃዩ መንግስታችን----ፀሃይ እንዳይነካህ ብሎ ወደ ውስጥ አስገባኝ--- ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ምን አግኝተህ ነው ያማረብህ ብሎ ወደ ፀሃዩ መልሶ ያወጣኝ ይሆናል” ብሎ እንዳሳቃት አውግታኝ አስቃኛለች፡፡ ኑሮአቸውን ነጋ ጠባ እያማረሩ ከሚነጫነጩና የጨጓራቸውን እድሜ ከሚያሳጥሩ የእኔ ቢጤዎች የእዚህ ልብስ ሰፊ የኑሮ ስትራቴጂ አይመረጥም ትላላችሁ? (አረ በስንት ጣዕሙ!)
አንድ በቅርቡ የሰማሁትና ኮፒራይቱ የህዝብ የሆነ ቀልድ ደግሞ ልንገራችሁ (ጠያቂውም ተጠያቂውም ህዝብ ነው እያልኳችሁ እንደሆነ ይታወቅልኝ) ኢህአዴግ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምትክ የሾማቸው አዲሱ ጠ/ሚኒስትር፣ በአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ የአፍሪካ መሪዎች ውስኪና ሻምፓኛቸውን ሲራጩ እሳቸው ግን በራሳቸው የግል ምክንያት ለስላሳ ያዛሉ፡፡ ያዘዙት መጥቶላቸው ሲጠጡ የተመለከተ አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራር ደንግጦ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ጠጋ ይልና “ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትራችን እኮ ወይን ነበር የሚጠጡት” ይላቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ድንግጥ ብለው “በል ይሄን ውሰድና ወይኑን አስመጣልኝ” ይላሉ - ለስላሳውን በመመለስ፡፡ ወይኑ እንደመጣላቸውም እየመረራቸውም ቢሆን መጎንጨት ይጀምራሉ፡፡ ቀደም ሲል ለስላሳ ይዘው እንደነበረ ያስተዋለ አንድ የአፍሪካ አገር መሪ “ክቡር ጠ/ሚኒስትር ምን ያዙ?” ሲል ይጠይቃቸዋል - ከለስላሳ ወደ ወይን የመሻገራቸውን ሰበብ ለማወቅ በውስጡ ጉጉት ተፈጥሮበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም በብርሃን ፍጥነት “መለስ የጀመረውን---” ሲሉ ይመልሱለታል፡፡ (የቀልዱ ኮፒራይት የህዝብ መሆኑ እንዳይረሳ በድጋሚ አሳስባለሁ!)
ከጀመርኩ አይቀር ሌላ የህዝብ ቀልድ ልጨምራ - አሁንም በኢህአዴግ ዙሪያ ነው ቀልዱ (የህዝብ ፓርቲ ስለሆነ በህዝብ ቀልድ አይቀየምም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ!) በዘንድሮው የ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር ላይ ተሳትፋ “ጉድ ሰራችን” የተባለችው ወጣት ኢትዮጵያዊት “የወሲብ ቅሌት” በፌስቡክ ዋና የአገር አጀንዳ (እናት አገሯን አስደፍራለች እስከመባል መደረሱን ያስታውሷል) የሆነ ሰሞን፣ በመንግስት ደረጃም ለውይይት ቀርቦ ነበር ይላሉ - የቀልዱ ምንጮች፡፡ (ኮፒራይቱ የህዝቡ ነው ማለቴ ይሰመርበት) እናም የአገሪቱ ከፍተኛው የመንግስት ባለሥልጣን የሆኑት ጠ/ሚኒስትሩ አንጋፋ የኢህአዴግ መሥራችና ሚኒስትር የሆኑ የሥራ ባልደረባቸውን እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ -
“እኔ የምለው የዚች ልጅ ጉዳይ --- የአገርን ገፅታ አያበላሽም እንዴ?”
ሚኒስትሩም “ህግመንግስቱን የሚንድ ተግባር እስካልፈፀመች ድረስ የሚያሳስብ ነገር የለውም” በማለት እንዳረጋጓቸው የቀልዱ ምንጮች ያወሳሉ፡፡
ይሄ እንግዲህ ቀልዱ ነው፡፡ ወደ እውነቱ ስንመጣ ግን በ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ላይ የተሳተፈችውና የወሲብ ቅሌት ፈፅማለች የተባለችው ወጣትና ድርጊቱን በቲቪ የቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል የተባለው ጣቢያን ፍርድቤት እንገትራቸዋለን የሚል በወኔ የታጀበ መረጃ ሰምቻለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ ምክንያቱ ደግሞ የአገርን ገፅታ ማበላሸታቸው ነው። ለእኔ ግን ከዚህ ይልቅ የአገርን ገፅታ የሚያበላሸው ከኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን ጋር ተያይዞ በሚከሰተው የሥልጣን ሽኩቻ ሳቢያ የሚደርሰው የነፃነት አፈናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይመስለኛል (ተረት ለማድረግ የዛትንበት ድህነታችንም ሳይረሳ!) እናም ጉልበታችንን፣ አቅማችንና ገንዘባችንን በተጨባጭ ለሚጠቅመን ጉዳይ ብናውለው ይሻላል ባይ ነኝ (ለምሳሌ የነፃነትና የሰብዓዊ መብትን ፋይዳ በሚያስገነዝብ ትምህርትና ስልጠና ላይ!)
እኔ የምላችሁ ---- ሰሞኑን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በአባይ ወንዝ ዙሪያ ያደረጉትን ውይይት (የፖለቲካ ተንታኞች ግን የጨበራ ተዝካር ብለውታል) ተከታትላችሁልኛል ? እኔ ግን ከሁሉም በፊት አንድ ጥያቄ መሰንዘር እፈልጋለሁ፡፡ “አገር ወዳዱን” እና “ከሃዲውን” ፓርቲ መለየት የሚቻልበት መንገድ የተቀመጠበት መፅሃፍ አለ እንዴ? መቼም ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች በሚያውቁት የጋራ ህገመንግስታችን ላይ ይሄ ነገር እንዳልሰፈረ “መከራከር” እንችላለን፡፡ (የኢህአዴግ ተወካዩ “በአባይ ጉዳይ ላይ ኮንሰንሰስ ስለመኖሩ መከራከር እንችላለን” እንዳሉት!) መቼም ይሄንን ማለት በምንም መመዘኛ “ከሃዲ” እንደማያስብል እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከማንኛውም በሥልጣን ላይ ያለም ሆነ ከሥልጣን ውጭ የሆነ ፖለቲከኛ ያነሰ የአገር ፍቅር እንደሌለኝ ልገልፅ እወዳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የአገር ፍቅር መለኪያ ቴርሞሜትር የሚያስፈልግበት ዘመን ላይ መድረሳችንን ልገልፅ እወዳለሁ! (የጥንት አባቶቻችን ይሄን ቢሰሙ ከልባቸው ማዘናቸው አይቀርም! )
ከምሬ እኮ ነው --- በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል በአባይ ጉዳይ ላይ ብሄራዊ መግባባት (ኮንሰንሰስ) ያመጣል ተብሎ የተገመተው የኢቴቪ ውይይት፤ በሚያሳዝን የእርስ በእርስ “ፍረጃ” ተጠናቀቀም አይደል፡፡ ደግነቱ ግብፆቹ በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደዋል እንጂ እንዴት ይታዘቡን እንደነበር አልነግራችሁም! እንደውም ኢትዮጵያውያን በግድቡ ጉዳይ አንድ አቋም የላቸውም የሚል አቋም የሚይዙት የኢቴቪን ውይይት ካዩ በኋላ ነበር የሚሆነው፡፡ እንዴ --- የኢህአዴጉ ተወካይ እኮ እስካሁን ኢህአዴግ ሲል የቆየውን ነው ያፈራረሱት። ሌላው ቀርቶ ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ለጋዜጠኞች ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “አባይን በተመለከተ በህዝቡ ዘንድ ብሄራዊ መግባባት አለ--- ተቃዋሚዎችን ጨምሮ” ማለታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ለነገሩ እኮ ራሳቸው በውይይቱ የተሳተፉት የኢህአዴግ ተወካይም መጀመርያ ላይ “ከታላቁ ህዳሴ ግድብ በፊት አገራዊ መግባባት ያስፈልጋል” በማለት የተሟገቱትን ተቃዋሚዎች ለመርታት “በአባይ ጉዳይ ኮንሰንሰስ የለም የሚል ካለ መከራከር እንችላለን” ሲሉ ሰምተናቸዋል፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን (ወደ ውይይቱ መጠናቀቂያ ላይ ይመስለኛል) ራሳቸው “ኮንሰንሰስ” እንደሌለ አሳይተውን ቁጭ አሉ - መድረክና አንድነት የተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአባይ ጉዳይ ላይ በክህደት የሚያስጠረጥር መግለጫ ሲያወጡ መቆየታቸውን በመዘርዘር፡፡ (በነገራችሁ ላይ ጋዜጠኛው በውይይቱ ላይ የነበረውን ሚና ለተመልካችና ለታሪክ ትቼዋለሁ!) እኔ የምለው ግን ---- የኢህአዴግ የፓርቲ ባህል ተቀይሯል እንዴ? (ግራ ገባን እኮ!) እንግዲህ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ከሁነኛ የፓርቲው ሰዎች በአደባባይ ስለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የሰማነው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ተወካይ ከተናገሩት ፍፁም የተለየ ነገር ነው (ኢህአዴግ ሳይነግረን አቋሙን ለውጦ ይሆን እንዴ?) ወይስ ተወካዩ በውይይቱ ላይ ሳያውቁት በስሜት ተወስደው የራሳቸውን አቋም ይሆን ያስተጋቡት? (አንዳንዴ ፖለቲካ እኮ አቅል ያስታል!) እርግጠኛ ነኝ ተወካዩ በስሜት ተወስደው ከሆነ ያንን ሁሉ የተናገሩት ገና ሳይጠይቁን እኛ ራሳችን ይቅርታ እናደርግላቸዋለን (“ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም ” የሚለውን ጥንታዊ ብሂል በመጥቀስ ) እንዲያም ሆኖ ግን እሳቸውም ይቅርታ መጠየቃቸው አይቀርም - እኛን ሳይሆን አውራ ፓርቲያችንን ኢህአዴግን! (እኛ ማለት ኢህአዴግ ፤ ኢህአዴግ ማለት ደግሞ እኛ መሆናችንን ልብ ይሏል!) በዚህ አጋጣሚ በዚያው ተመሳሳይ ውይይት ላይ ኢህአዴግ (መንግስት) የግብፆችን ድንፋታ ተከትሎ “ህዝቡን ለአገርህ ዘብ ቁም!” በሚል ለጦርነት ቀስቅሷል ሲሉ የተናገሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፣ ነገሩን ከየት እንዳመጡት አናውቅምና እሳቸውም ተረጋግተው ካሰቡ በኋላ ኢህአዴግንና ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባቸው የሚያጠራጥር ነገር ያለ አይመስለኝም (የጦርነት አዋጁን የሰሙት በህልማቸው ከሆነ ግን ሳንከራከር እንቀበላቸዋለን!) በነገራችን ላይ --- ለእውነት ዋጋ መስጠትን እንዲህ ቀስ በቀስ ብንለማመድ ሸጋ ይመስለኛል (ከእውነት ጋር ለመታረቅ እኮ ከአንድ ትውልድ በላይ ፈጅቶብናል!)
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትሩ ከአክስዮን ማህበራት የዲቪደንድ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለተሰራው ጥፋት ነጋዴዎችን ይቅርታ ትጠይቃላችሁ ወይ በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ሰምታችኋል ብዬ አምናለሁ (ካልሰማችሁት ግን አምልጧችኋል!) መጀመርያ ጉዳዩ መጣራት አለበት ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ተጣርቶ ጥፋተኛ ከሆንን ግን ይቅርታ የማንጠይቅበት ምክንያት የለም” ነው ያሉት፡፡ በዚህም “ይቅርታን የደፈሩ መሪ” የሚል ክብርና ሞገስ ተቀዳጅተዋል ሲባል ሰምቼአለሁ። የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር “አባይን የደፈሩ መሪ” እንደተባሉት ማለት ነው፡፡ (የጦቢያን ሥር የሰደደ የይሉኝታ ባህል አሽቀንጥረው በመጣልና ያመኑበትን በመናገር አዲስ የድፍረት አብዮት የለኮሱት አንጋፋው የኢህአዴግ ታጋይ አቦይ ስብሃት ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ እንዴት ቢሉ ---- “አባይን የደፈረው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ኢህአዴግም ሆነ ጠ/ሚኒስትሩ አይደሉም” ባይ ናቸው) እናላችሁ ወዳጆቼ ---- በዚህች ይቅርታ መጠየቅ አቀበት የመውጣት ያህል ፈተና በሆነባት ጦቢያችን፤ የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ተጣርቶ ስህተት ከሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለው በአደባባይ መተንፈሳቸው የሽንፈት ምልክት ሳይሆን የበሳልና ስልጡን ፖለቲከኛ ምልክት መሆኑን ልብ ማለት የአባት ነው፡፡ ይሄ አጋጣሚ የብዙዎቹ ፖለቲከኞች ዓይነጥላ መግፈፊያ ይሆንልን ዘንድም ከልባችን እንፀልይ! (የአሜሪካ ፖለቲከኞች ለትንሽ የምላስ ማዳለጥ ሳይቀር ይቅርታ እንደሚጠይቁ ልብ ይሏል!)

Read 4019 times