Saturday, 06 July 2013 10:40

ቤቲ ጥፋተኛ ከተባለች የ5 ዓመት እስር ይጠብቃታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(121 votes)
  • በፌስቡክ ላይ እርቃን ፎቶግራፍ መለጠፍ በህግ ያስቀጣል

 በ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የሪያሊቲ ሾው ውድድር ላይ የተሳተፈችው የ26 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ቤተልሄም አበራ፤ በቅርቡ በተለያዩ ድረገፆች በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ ወሲብ ስትፈጽም መታየቷ በወንጀል የሚያስከስሳት መሆኑን የገለፁ የህግ ባለሙያዎች፤ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ብይን ከወሰነባት የ5 ዓመት እስር እንደሚጠብቃት ተናገሩ፡፡ 

በወጣቷ ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ለአዲስ አድማስ የገለፁት የህግ ባለሙያዎቹ አቶ ጳውሎስ ተሰማ እና አቶ ተስፋሁን ፀጋዬ፤ ቤቲ የፈፀመችው ተግባር የህብረተሰቡን ባህል የሚቃረን በመሆኑና ይህም በሚዲያ በመተላለፉ በኢትዮጵያ ህግ ያስከስሳታል ብለዋል፡፡
እንኳን ድርጊቱን በአደባባይ የፈፀመ ቀርቶ ለመፈፀም ሙከራ ያደረገም በወንጀል እንደሚጠየቅ የገለፁት ጠበቆቹ፤ ቤቲ በአደባባይ የኢትዮጵያውያንን ባንዲራ ይዛ መልካም ገጽታችንን ማሳየት ሲገባት ባህላችን ሀይማኖታችንና ህጋችን የማይፈቅደውን ነገር በአደባባይ ፈጽማለች ብለዋል፡፡
ክሱን መመስረት ያስፈለገው ሌሎች በተመሳሳይ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ አካላትን ለማስተማር ታስቦ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ እንደ ህግ ባለሙያነታቸው የማንም ውክልና ሳያስፈልጋቸው ክሱን በቅርቡ እንደሚመሰርቱና በወቅቱም በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል፡፡
እርቃን ምስሎችን በኢንተርኔት መለጠፍ በሕግ ያስከስሳል ብለዋል - ባለሙያዎቹ፡፡
ቤቲ የፈፀመችው ድርጊት በተለያዩ ድረ ገፆች መለቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ጐራ ለይተው በመደገፍና በመንቀፍ አስተያየታቸውን ሲሰጡበት የነበረ መሆኑን ያስታወሱት የህግ ባለሙያዎቹ፤ እኛ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ስናስብ ምን አገባችሁ ያሉንም አሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ግን በህጉ መሠረት ይህን የማለት መብት የላቸውም ብለዋል። ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን መፈፀም ከ1 ዓመት እስከ 5 አመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል ያሉት ባለሙያዎቹ፤ የቤቲ ጉዳይም እስከ 5 አመት እስር ሊያስቀጣ ይችላል ብለዋል፡፡
ዋናው አላማችን ቤቲን እንደማሳያ ወስደን እንዲህ አይነት ድርጊቶችም እንደሚያስቀጡ ለማሳየት ነው የሚሉት ጠበቆቹ፤ ዛሬ በፌስቡክና በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች ላይ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው የተነሱትን ፎቶ እየለጠፉ መሆኑ ከዚህ የህግ ግንዛቤ ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“ከቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር የተባረረችው ቤቲ፤ በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጠችው ቃለምልልስ፤ ድርጊቱን አለመፈፀሟንና የታየው ነገር ለውድድሩ አስፈላጊ በመሆኑ በትወና የተደረገ እንደሆነ ገልፃለች፡፡

Read 53949 times