Saturday, 29 June 2013 08:40

የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲና ወራሾችን ያወዛገበው መኖርያ ቤት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የካሣ ክፍያው በዝግ ሂሣብ ተቀምጧል

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ሰንጋተራ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ ለልማት ተነሺ ናችሁ ተብለን ተገቢው ካሣና ምትክ ቦታ ሳይሰጠንና በቤቱ ላይ ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ያለው ውዝግብ እልባት ሳያገኝ፣ ከ40 አመት በላይ የኖርንበት ቤታችን በግብታዊነት ፈረስብን ሲሉ የቤቱ “ህጋዊ ወራሾች” ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በቤት ቁጥር 520 የተመዘገበው መኖሪያ ቤት፣ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ካርታ ተሰጥቶት ህጋዊነቱ የተረጋገጠና በአንድ የቤት ቁጥር ስር ተጠቃሎ ሳለ፣ ከጐኑ ያለውና የወላጅ አባታችን እህት በሞት ሲለዩ ለአባታችን በስጦታ ያበረከቱትን ቤት፣ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ “የኔ ነው” የሚል ክርክር በማንሣቱ፣ በማስረጃዎች አስደግፈን የቤቱ ህጋዊ ወራሾች መሆናችንን ብናስረዳም፣ የክፍለ ከተማውና የወረዳው አመራሮች ማስረጃችንን ተቀብለው ለማረጋገጥና ውሳኔ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም - ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡

ከቤቱ ህጋዊ ወራሾች አንዱ የሆኑት አቶ ነብዩ አባተ፤ አሁን ክርክር ያስነሳው የአክስታቸው የነበረው ቤት ከአዋጅ 47/67 በፊት ለግለሰቦች ተከራይቶ የነበረ ሲሆን አዋጁ ከወጣ በኋላ ቀበሌው በጉልበት ወስዶ ለ5 ዓመት በጽ/ቤትነት ሲገለገልበት ከቆየ በኋላ፣ በ1973 ዓ.ም ተከራክረን እንዲመለስልን በማድረግ ግብር እየገበርንበት ስንኖርበት ነበር ብለዋል፡፡ የአባታችን እህት “ድርሻዬን ለእነሱ ሰጥቻለሁ ያሉበትን የሰነድ ማስረጃ አቅርበን ነበር ያሉት አቶ ነብዩ ፤ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ግን ቤቱ በአዋጅ የተወረሰ ነው፤ ስለዚህ ለኛ ይገባናል የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ክፍለ ከተማውና ወረዳው “እኛ በቤቱ ጉዳይ ላይ ያሉንን ማስረጃዎች ተቀብለው ሳይመረምሩ ክርክራችሁን ከቦታው ለቃችሁ ጨርሱ” የሚል ምላሽ በመስጠት በግብታዊነት ቤቱን ወደማፍረሱ እንደተሸጋገሩ አቶ ነብዩ ገልፀዋል፡፡

የክፍለከተማው አመራሮች ይህን ውሳኔ ያሳለፉት ለማረፊያ የሚሆን ቤትና የካሣ ክፍያ ሳይከፍሉን ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህን መብታቸውን ሲጠይቁም፤ የካሣ ክፍያችሁ በዝግ አካውንት ተቀምጧል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና ጊዜያዊ መኖሪያ ቤት ተብሎ የተሰጣቸውን ለመረከብ ወደተባለው ቦታ ሲሄዱ፣ወረዳው የተባለውን ቤት ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ገልፀዋል፡፡ “ተገቢውን አስተዳደራዊ ፍትህ አጥተናል” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በአሁን ሰአት በአፍራሽ ግብረ ሃይል ጣራው በፈረሰው ቤት ላይ የፕላስቲክ ክዳን ወጥረው ለመኖር እንደተገደዱና ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም ምን እንደሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የልደታ ክ/ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ለምለም ገ/ሚካኤል፤ ቦታው ለልማት ተፈልጐ የከተማው አስተዳደር ተገቢው ካሣና ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ከአንድ አመት በፊት መወሰኑን ጠቁመው ፣ በዚህ ውሣኔም በአካባቢው ያሉ ቤቶች በሙሉ ሲነሱ ይህም ቤት ከቦታው እንዲነሳ ቢወሰንም በቤቱ ላይ ከሁለቱ ወገኖች ቅሬታ በመቅረቡ መዘግየቱን አስታውቀው፣ ከዚህ በላይ መታገሱ ለሚፈለገው ልማት እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ በቤቱ ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ጊዜያዊ ቤት ተሰጥቷቸውና በዝግ ሂሣብ የካሣ ክፍያው ተቀምጦላቸው፣ ቤቱ እንዲፈርስ የመጨረሻ ውሣኔ መተላለፉን ገልፀዋል፡፡

የካሣ ክፍያውን በዝግ ሂሣብ ማስቀመጥ ያስፈለገውም በፍርድ ቤት አፈፃፀም የተወሰነለት አካል እንዲወስድ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ “የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲም ክርክር ያስነሳው ቤት የራሱ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አቅርቦልናል” የሚሉት አቶ ለምለም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኛ ነው የሚሉ ከሆነ አለን የሚሉትን ማስረጃ ይዘው በፍርድ ቤት ተከራክረው ማስወሰን ይችላሉ፤ እስከዚያ ግን ቤቱ የተመደበው ካሣ በዝግ ሂሣብ ይቀመጣል፤ ጊዜያዊ የቀበሌ ቤትም ውሰዱ ብለናቸዋል፤ ለመውሰድ ግን ፍቃደኛ አይደሉም ብለዋል፡፡ “እስካሁን ድረስ ችለናል፤ መንግስት ወዳዘጋጀላቸው የቀበሌ ቤት ይግቡ፤ እኛ ግን ከዚህ በኋላ አንታገስም፤ በፍጥነት እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል - አቶ ለምለም፡፡

Read 10813 times