Saturday, 29 June 2013 08:40

የአሽከርካሪዎች ማስተማሪያ “ሶፍትዌር” ተሰራ

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(112 votes)

የአሽከርካሪዎችን ግንዛቤ በማዳበር በሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያግዝ የአሽከርካሪዎች ማስተማሪያ “ሶፍት ዌር” ተዘጋጀ፡፡ ሶፍትዌሩን ከስማቸው ኮምፒዩተር ሰርቪስ ጋር በመሆን ያሰናዱት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ እና አቶ ንፁህ ካሳ ናቸው፡፡ በትራንስፖርት ባለስልጣን ጥናት በአገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 76 በመቶ የሚሆኑት በአሽከርካሪ ስህተት የሚፈጠሩ መሆኑን የጠቀሱት አዘጋጆቹ፤ ለአሽከርካሪዎች ተገቢ የሆነ ሥልጠና በመስጠትና ሃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎች እንዲኖሩ በማድረግ እየደረሰ ያለውን አደጋ መቀነስና መግታት እንደሚቻል ገፀልዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት የተደረገበት “ሶፍትዌር”፤ በሥዕላዊ መግለጫ የተደገፈ የመንገድ ሥነ ሥርዓትና ምልክት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ክፍሎች፣ የአሽከርካሪ ባህርይ፣ የተሽከርካሪ ቅድመ ብልሽት ጥገና እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ ባለሥልጣኑ ከሚሰጣቸው የመንጃ ፈቃድ ፈተናዎች ጋር የሚዛመዱ ከአንድ ሺህ በላይ የናሙና ፈተናዎችን ያካተተ ነው፡፡ ፈተናው የሚሰጠው በኮምፒዩተር እንደሆነና ከተፈታኞች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን እንደሚወድቁ የገለፁት ዋና ሳጅን አሰፋ፤ የሶፍትዌሩ መዘጋጀት ይህንን ክፍተት ያጠበዋል ብለዋል፡፡

Read 22963 times