Saturday, 22 June 2013 11:23

ሕይወት በባምባሲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

                    ሰላም ሰፍኖ አገሬ ስመለሰ እዚህ በቀሰምኩት የጥልፍና የልብስ ስፌት ሙያ ቤተሰቤን አስተዳድራለሁ፤ ሙያውንም ለሌሎች አስተምራለሁ ትላለች በባምባሲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በስፌት መኪና ጥልፍ ስትሠራ ያገኘናት ሱራ አደም ኢብራሂም፡፡ የተበደለና የተገፋ ሰው ወደ ሌላ ስፍራ ተዛውሮ ጥሩ ነገር ሲገጥመው፣ “የልምጭም ገድ አለው” ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ሱራ፣ የጊዘን-ሱዳን አካባቢ ነዋሪ ነበረች፡፡ እዚያ እያለች የስፌትና የጥልፍ ሙያ ቀርቶ ቋሚ መተዳደሪያ እንኳ አልነበራትም። እሷና ጐረቤቶቿ የማገዶ እንጨት ለቃቅመውና ለውዝ (ኦቾሎኒ) ገበያ ወስደው በመሸጥ ነበር የሚተዳደሩት፡፡

አሁን ግን በባምባሲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በልብስ ስፌትና በጥልፍ ሙያ ለአምስት ወራት ሠልጥና እየሠራች ነው፡፡ የባምባሲ ስደተኞች ጣቢያ በፕላን የተሠራ የጎጆ ቤቶች መንደር ነው፡፡ በገላጣ ቦታ የተሠራው ጣቢያ ከፍ ካለ ስፍራ ሲታይ፣ የመንገዶቹ ቅያስ፣ የቤቶቹ በረድፍ መደርደር … ዓይን ከመማረኩም በላይ ዘመናዊ ከተማ ይመስላል፡፡ ከሱዳን ድንበር 120 ኪ.ሜ ላይ የተሠራው ጣቢያ፣ ሦስት ዞኖች፣ 40 ብሎኮች፣ 265 ቤቶችና 5240 አባ/እማወራዎች ሲኖሩት በአጠቃላይ 12,338 የሱዳን ተፈናቃዮችን ይዟል፡፡ በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት በተፈጠረ ያለመረጋጋት ከመኖሪያቸው ለቅቀው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን ስደተኞችን በተለያዩ የመግቢያ በሮች፣ በባምዛ፣ በኩርሙክ፣ በገመድና በሸሸቆ ሲገቡ በመቀበል፣ በማጓጓዝና በመጠለያ ጣቢያዎች ለማስፈርና አስፈላጊውን ሰብአዊና አካላዊ ጥበቃ በማድረግ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ስምምነቶች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነን ያሉት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር፣ የአሶሳ ስደተኞች ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ እጅጉ ናቸው፡፡ አቶ ሞላ አክለውም፣ በሦስት መጠለያ ጣቢያዎች፣ ከ15 ዓመት በፊት በተሠራው በሸርቆሌ፣ በኅዳር ወር በተሠራው በቶንጉና የዛሬ ዓመት በሰኔ ወር በተሠራው በባምባሲ መጠለያ ጣቢያዎች በአጠቃላይ ከ32,263 በላይ ስደተኞች እንደተጠለሉና በአሁኑ ወቅትም በሳምንት በአማካይ ከ20 እስከ 30 ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ሦስቱም መጠለያ ጣቢያዎች ስለሞሉና የስደተኞችም ፍልሰት ስላላቆመ፣ አራተኛ ጣቢያ በጉሬ ለማቋቋም እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዛሬ ዓመት የባምባሲ መጠለያ ጣቢያ ሲከፈት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበሉት የስደተኞች ቁጥር 400 እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው ከ12ሺህ በላይ መሆኑን የጣቢያው አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ጣፋ ገልጸዋል፡፡

በጣቢያው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ጋባዥነት ስምንት ዓለም አቀፍና አገር በቀል ድርጅቶች በውሃ አቅርቦት፣ በሥነ ፆታ ትምህርትና ጥቃት ዙሪያ፣ በመዋለሕፃናት ትምህርትና በሕፃናት በሽታ መከላከል፣ በመፀዳጃ ቤት አቅርቦት፣ በአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ፣ ስደተኞችን ከመግቢያ በሮች ተቀብሎ ወደ መጠለያዎች ማጓጓዝና በመጠለያ ቤት ሥራ፣ በስደተኞች አካላዊ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በመሠረታዊ የጤና አገልግሎትና በሥነ-ምግብ አቅርቦት… ዙሪያ ለስደተኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ ተድላ፤ የባምባሲ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ጣቢያው 16 የሕክምና ቡድን አባላት እንዳለው ጠቅሰው፤ ሥራቸውም አገሪቷ በምትከተለው ፖሊስ መሠረት በመከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። መደበኛ የክትባት አገልግሎት ባለፉት ሁለት ወራት በስፋት የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው ወር መጨረሻ ሀገር አቀፍ ዘመቻ በማካሄድ ለ1866 ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት፣ ለ2103 ሕፃናት ቫይታሚን ኤ፣ ለ2095 ሕፃናት ደግሞ የኑትሪሽን አገልግሎት መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን በጣቢያው ያለው ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ ስላልሆነ፣ የክትትል ሥራ እያከናወኑ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከጋራ መፀዳጃ ወደ ቤተሰብ መፀዳጃ ግንባታ እየገቡ ነው፡፡ በጤና ጣቢያ፣ በት/ቤት፣ በመኖሪያ አካባቢ፣ በቡና ጠጡ ፕሮግራም የጤና ትምህርት ይሰጣሉ፡፡

ከአምስት ዓመት በታች አንድ፣ ከአምስት ዓመት በላይ ሁለት በአጠቃላይ ሦስት የተመላላሽ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ከየዞኑ በጠና የታመሙ በሽተኞች ወደ ጣቢያው ሲመጡ ተገቢውን ሕክምና ይሰጣሉ፤ ከአቅም በላይ ከሆነ ለአሶሳ ሆስፒታልና ከባሰም እስከ አዲስ አበባ ድረስ ሪፈራል ይልካሉ፡፡ በጣቢያው የላይኛው የመተንፈሻ አካል፣ የቆዳና የዓይን በሽታ ጐልቶ ይታያል፡፡ ውሃማ ተቅማጥ ደግሞ ለሦስት ወራት ሕፃናትን አጥቅቶ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ተቀናጅተው ባደረጉት ጥናት፣ ለስደተኞቹ የሚቀርበው ውሃ ንፁህ ቢሆንም በአጠቃቀም ደረጃ ስለሚበከል መሆኑን ደርሰውበታል፡፡ በጁን ወር የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ የወባ በሽተኞች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ኅብረተሰቡ አጐበር እንዲጠቀም፣ ያቆረ ውሃ እንዲያፋስስ ሰፊ ቅስቀሳ እያካሄዱ መሆኑን ዶክተሩ ገልጸዋል፡፡ ለማንኛዋም ወላድ አጐበር ከመሰጠቱም በላይ ለሁሉም ለማዳረስ ተጨማሪ አጐበር ጠይቀዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከ70 ሰዎች 41 የወባ በሽተኛ መገኘታቸው ስጋት በመፍጠሩ ነው፡፡

የወባ ወረርሽኝ ቢከሰት ግን የመላከል አቅም እንዳላቸው ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያ ያለው ት/ቤት ዘንድሮ ነው የተከፈተው፡፡ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ሲሆን በአጠቃላይ 2028 ተማሪዎች፣ 18 ስደተኛና አራት መደበኛ መምህራን አሉት፡ የመምህራኑ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አንድ መምህር ለ107 ተማሪዎች ያህል እንደሆነ የገለፀው የት/ቤቱ መምህር አቶ ጥላሁን ጓዴ ነው፡፡ አሁን የሚያስተምሩት በቆርቆሮ ዳስ ውስጥ ነው፡፡ የአዲስ ት/ቤት ግንባታ እየተፋጠነ በመሆኑ በመጪው ዓመት ወደ አዲሱ ት/ቤት እንደሚገቡ የጠቆመው መምህሩ፤ ባለፈው ሳምንት በጣቢያው በተከሰተ አውሎንፋስ አንድ ተማሪ ቆርቆሮ መትቶት እንደሞተ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከግማሽ ቀን በላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የጐላ ተፅዕኖ እንዳልተፈጠረ አቶ ጥላሁን ገልጿል፡፡ ታላታ በበክር የ14 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ታላታ አገሯ እያለች የትምህርት ዕድል ስላላገኘች በባምባሲ መጠለያ ጣቢያ የ1ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ወደ ባምባሲ የስደተኞች ጣቢያ የመጣችው ከአራት ቤተሰቦቿ ጋር ነው፡፡ ዐረብኛ፣ እንግሊዝኛና ሂሳብ እንደሚማሩና መምህራኑ ጥሩ ስለሆኑ የእውቀት ጭላንጭል እያየች ስለሆነ በፍቅር እየተከታተለች መሆኗን ገልፃለች፡፡ ሰላም ሰፍኖ ወደ አገሯ ስትመለስ እሷም መምህር ሆና ያልተማሩ ወገኖቿን የእውቀት ጥማት እንደምታረካ አስረድታለች፡፡

ቤተልሔም ጥላሁን የሳይኮሶሻል ሄልዝ ፊልድ ኦፊሰር ናት፡፡ 15 ስደተኛ ሴቶች ለአምስት ወር በሙያ (በስፌትና በጥልፍ) ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ ሥልጠና የሚሰጠው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ብቻ ሳይሆን፣ ያሉበት ስፍራ ለሴቶች ምቹ እንዲሆን፣ ሴቶች ተዋውቀውና ተቀራርበው እየተወያዩ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጐለብቱ፣ … ለማድረግ እንደሆነ ቤተልሔም ተናግራለች፡፡ ካሁን በፊት 150 ሴቶችና 60 ወንዶች በምግብ ዝግጅት፣ 30 ሴቶች ደግሞ በኪሮሽ ሥራ ማሠልጠናቸውን ገልጻ፣ ሠልጣኞቹም ምርቶቻቸውን ሸጠው ገቢ ማግኘታቸውን ተናግራለች፡፡ ወጣቶች ዝም ብለው ሲቀመጡ ለአዕምሯቸው ጤንነት መጥፎ ስለሆነ፣ ራሳቸውን እንዲያዝናኑ የተለያየ ስፖርታዊ ሥልጠናና ለስደተኞቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተለያየ የአቅም ግንባታ መስጠታቸውን፣ ለሴቶች የማኅበረሰብ ውይይት፣ ወጣቶች በሱስ እንዳይጠመዱ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች መስጠታቸውን፣ እንዲሁም የአካባቢያቸውን ባህል እንዳይረሱና ዘና እንዲሉ፣ ባህላዊ አከባበር ማድረጋቸውን ተናግራለች፡፡ የ30 ዓመቷ ማይዳ ኢብራሂም የጊዘን አካባቢ ነዋሪ ናት፡፡ ወደ ባምባሲ የስደተኞች ጣቢያ የመጣችው ስድስት ልጆቿንና አሮጊት አያቷን በአጠቃላይ ስምንት ቤተሰብ ይዛ ነው፡፡

የምትኖርበት አካባቢ በድንገት በአውሮፕላን ቦንብ ሲመታ፣ የተወሰኑ ልጆቿን ይዛ ነው ነፍሴ አውጪኝ ያለችው፡፡ ድብደባው ጋብ ሲል ነው የተቀሩትን ልጆች ተመልሳ የወሰደቻቸው፡፡ ነገሩ ቀዝቀዝ ሲል ደግሞ ተመልሳ በጣም ጠቃሚ ናቸው ያለቻቸውን ዕቃዎች ወስዳ ሸሸች፡፡ ማይዳ ከባሏ ጋር የተለያየችው በጦርነቱ ነው፡፡ ይሙት ይኑር የምታውቀው ነገር የለም፡፡ ከባለቤቷ ወይም ከሚስቱ ወይም ከወላጆቻቸው የተለያዩ ልጆች በማለት በየጊዜው እየመጡ ቢመዘግቧቸውም ማንኛውም ስደተኛ ከሚያገኘው መደበኛ ራሽን በስተቀር ምንም አላገኘችም፡፡ እንደ አንዳንድ ሴቶች መሠልጠን ብትፈልግም ዕድሉን እንዳላገኘች ትናገራለች፡፡ አቶ ሀሰን አቡና ካሪም የ49 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ የሚኖሩበት የሻንከሩ አካባቢ በአውሮፕላን ሲደበደብ ሁሉም ነፍሱን ለማትረፍ በየአቅጣጫው መበታተኑን ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም ሰባት ቤተሰባቸውን ይዘው ነው የተሰደዱት፡፡

ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ሳያንሳቸው በስደትም ጥሩ ዕድል አላጋጠማቸውም፡፡ ባምባሲ መጠለያ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ የጀርባ ሕመምተኛ ሆኑ፡፡ በየጊዜው ወደ ጤና ጣቢያው ቢሄዱም ምንም እንዳልተሻላቸው ገልጸዋል፡፡ ስደተኛው በየጎጆው ፊት-ለፊት የተከለው ዛፍ ፀድቆ የአንድ ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ስደተኞቹ ማገዶ ፍለጋ የአካባቢውን ደን እንዳይጨፈጭፉ ምድጃና ነጭ ጋዝ ይቀርብላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የስደተኛ ስሜት እንዳያድርባቸው በተቻለ መጠን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ሐሙስ ዕለት በባምባሲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የገበያ ቀን ነው፡፡ በገበያው መኻል በሁለት ቦታ ዲናሞ እየተንደቀደቀ የተለያዩ ሞባይሎች ቻርጅ ይደረጋሉ፡፡ አሮጌ ልብሶች የሚጠግኑም አሉ፡፡ ብስኩት፣ ዳቦ፣ አምባሻ፣ ሥጋ፣ ቲማቲም፣ ሙዝ፣ ሎሚ፣ የማገዶ እንጨት፣ ስንዴ፣ ምስር፣ ዘይት፣ ሽርኩርት፣ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ጨጨስ የሚባል የገንፎ ማባያ ቅጠልና ተከትፎ ሥጋ ላይ የሚጨመር ኮድራ የተባለ ቅጠል፣ … ብቻ ሁሉም ያለውን ይዞ ወጥቶ ሸማች ይጠባበቃል፡፡

Read 3519 times