Saturday, 22 June 2013 11:14

የፍንዳታ መሣሪያዎችን የመለየት ብቃት ያላቸው የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች!

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

የአዲስ አበባ ህንፃዎች ለአሸባሪዎች ፍንዳታ የተጋለጡ ናቸው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ፎሬንሲክ ምርመራ ዳይሮክቶሬት ፍንዳታ ዲቪዥን በስሩ ከሚያስተዳድራቸው ክፍሎች አንዱ የዛሬ አምስት ዓመት የተቋቋመው የፍንዳታ ምርመራ ዲቪዥን ክፍል ተጠቃሽ ነው። በኢንስፔክተር ታመነ ግርማ የሚመራው ይሄ ክፍል፤ ፍንዳታ ከመድረሱ በፊትና ከደረሰ በኋላ ምርመራ በማካሄድ ስለተፈፀመው ወይም ሊፈፀም ታስቦ ስለነበረው አደጋና የፍንዳታ መሣሪያ ዓይነት አስተማማኝ መረጃ ይሰጣል፡፡ በአገራችን ብዙ ጊዜ የተለመደው ፍንዳታ የእጅ ቦንብ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንስፔክተር ታመነ፤ አልፎ አልፎ ግን በአሸባሪዎች የሚፈፀሙና ሊፈፀሙ የታሰቡ ሌሎች የፍንዳታ ዓይነቶች እንደሚገጥሟቸው ይገልፃሉ፡፡

በ19ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ከኤርትራ ሰልጥነው የመጡ አሸባሪዎች አዲስ አበባን እንደባግዳድ ማድረግ የሚል ዓላማ አንግበው በተለያዩ አካባቢዎች ለማፈንዳት ያቀዱት C4 (Composition four) ወይም ልቁጥ ፈንጅ የተባለውን የፍንዳታ መሣሪያ እንደነበር ኢንስፔክተሩ ያወሳሉ። ደግነቱ ግን በህብረተሰቡ ጥቆማ አሸባሪዎቹ ጥቃቱን ከመፈፀማቸው በፊት በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡ ይህ የፈንጂ አይነት እንደ ቅቤ የመቅለጥ ባህሪ ስላለው በማንኛውም ነገር ውስጥ በመክተት ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ እንደሚመች እና በፍተሻ ባለሙያዎች ዘንድም ጥርጣሬ እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡ ፈንጂው ከሞባይል ጋር በመደወል ወይም በተሞላ ሰዓት አማካኝነት ሊፈነዳ እንደሚችል ጠቁመው ፈንጂው የተሰራው ለኮንስትራክሽንና ለመንገድ ስራዎች አገልግሎት ቢሆንም በአሸባሪዎች እጅ ሲገባ ግን ለከፍተኛ የህይወትና ንብረት ውድመት ይውላል ብለዋል - ኢንስፔክተሩ፡፡

እስካሁን በአገራችን ከተገኙ የፈንጂ አይነቶች መካከል ለመርማሪም ሆነ ለፖሊስ አስቸጋሪው ሆነው የተገኙት ቤት ውስጥ የሚሰሩና ሰው በራሱ ጥበብ የሚፈጥራቸው ፈንጂዎች ሲሆኑ እነዚህ ፈንጂዎች ከሲሊንደር ጋዝ ወይም ከድራፍት ሲሊንደር ጋር በማገናኘት እንዲፈነዱ የሚደረጉ ናቸው ያሉት ኢንስፔክተሩ ፤ በምሳሌነትም በቅርቡ በአሜሪካ የቦስተን ማራቶን ላይ የደረሰውን አደጋ ይጠቅሳሉ፡፡ “ሌላው TNT (Tin Nitro Toluen) ወይም ሳሙና ፈንጅ እያልን የምንጠራው ሲሆን ይህንንም በፈለግነው መጠን በመሰባበር ከቦታ ቦታ ልናንቀሳቅሰው እንችላለን፤ በተረፈ RDX፣ PTX፣ HMN፣ አሞኒየም ናይትሬት፣ TMX የመሳሰሉ ፈንጂዎችም በአገራችን የተገኙ ናቸው” ብለዋል፡፡ የአገራችን የፍተሻ መሳሪያዎች በአብዛኛው ብረት ነክ ነገሮችን የሚለዩ መሆናቸውን የገለፁት ኢንስፔክተሩ ፤ የጠቀስናቸው የፈንጂ ዓይነቶች ግን በአብዛኛው ከብረት ጋር ንክኪ ስለሌላቸው የሚያመልጡበት እድል መኖሩን በመጠቆም ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል፡፡

የአገራችን ህንፃዎች አሰራርም ለአደጋዎች የተጋለጡ መሆናቸውን ነው ሃላፊው የሚናገሩት፡፡ እዚህ አገር አጥፍቶ ጠፊዎች ባለመኖራቸው ነው እንጂ ህንፃዎቹ ለፍንዳታ ምቹ ናቸው፤ በቀላሉ በመኪና ላይ ወይም በመግቢያው በር ላይ ባሉ ምሰሶዎች ፈንጂዎችን በማጥመድ ጉዳት ማድረስ ይቻላል የሚሉት ኢንስፔክተር ታመነ፤ ህንፃዎቹን ከእንደዚህ ዓይነቱ አደጋ ለመታደግ የፕላን ስራ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በፌደራል ፎሬንሲክ የፍንዳታ ምርመራ ዲቪዥን የፍንዳታ መሣሪያዎችን በቀላሉ በሚለዩና ፈጣን የምርመራ ውጤት በሚሰጡ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች የተደራጀ ሲሆን በብቃታቸው ለየት ከሚሉት ውስጥ ጥቂቶቹን እንያቸው፡፡ “ቫፐር ትሬሰር 2” “ቫፐር ትሬሰር 2” የተባለው መሣሪያ እጅግ ዘመናዊ እና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡ ይህ መሳሪያ ምንድን ነው? ለምንስ አገልግሎት ይውላል? “ቫፐር ትሬሰር”፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ፎሬንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ፍንዳታ ዲቪዥን ውስጥ ትልቅ አገልግሎት እንደሚሰጥ ኢንስፔክተር ታመነ ይናገራሉ፡፡

“ቫፐር ትሬሰር”ን የፈጠረው የአሜሪካ የሀገር መከላከያ እና የአደገኛ ዕፅ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ሲሆን መሳሪያውን እየተጠቀሙበት ከሚገኙት አካላት መካከልም የአሜሪካ ጉምሩክ አገልግሎት፣ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ በፕሬዚዳንቱ ቢሮ የብሄራዊ አደገኛ እፅ ተቆጣጣሪ እና ሌሎችም የጥበቃና የደህንነት ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም በኤርፖርት፣ በኤምባሲ፣ በማረሚያ ቤቶችና ከፍተኛ ጥበቃና ክትትል በሚያስፈልጋቸው ቦታዎችና ተቋማት ይሄ መሣሪያ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከፍንዳታ በፊት በማንኛውም አጋጣሚ በተጠርጣሪዎች በተነካኩ እቃዎች ለምሳሌ ጠረጴዛ፣ የመኪና ማንኛውም አካል ፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎች እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ላይ በቀላሉ ናሙና በመውሰድ ብቻ በመሳሪያው በመመርመር ወዲያውኑ ውጤቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ ከፍንዳታ በኋላ ደግሞ ከተጎጂዎች አልባሳት ወይም ድንጋይ ላይ ናሙና በመውሰድና ምርመራ በማካሄድ ውጤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማወቅ እንደሚቻል ነው ኢንስፔክተሩ የሚናገሩት፡፡ በቀላሉ በእጅ ተይዞ የሚንቀሳቀሰው “ቫፐር ትሬሰር”፤ ክብደቱ 3.2 ኪ.ግ ሲሆን የተሰጠውን ናሙና ለመለየትም ከስምንት ሰከንድ እስከ አንድ ደቂቃ በቂ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

መሳሪያው በፈንጅነት የተጠረጠረን ዱቄት መሰል ነገርና ስኳር እንዲሁም ቅባት መሰልና ከሌላም ነገር ጋር ተመሳሳለው ለፀረ-ሰላም ተግባር ሊውሉ የሚችሉ ፈንጅዎችን በቅፅበት እና በአስተማማኝ ሁኔታ በመለየት ውጤቱን ከማሳወቁ በተጨማሪም በማንኛውም አይነት እቃ ተጠቅልሎ የተቀመጠን ነገር በማሽተት በውስጡ ያለውን ነገር የመለየት አቅም አለው፡፡ በፋብሪካ ውስጥ በኬሚስትሪ ተቀምሞ የሚሰራን የፈንጅ አይነት ለይቶ በማሳወቅና የአደገኛ ዕፅ ዓይነቶችን በመለየት ረገድ መሳሪያው ትልቅ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ከፈንጅ አይነቶች TNT (Tin Nitro Toluen) ወይም ሳሙና ፈንጅ እያልን የምጠራውን እንዲሁም C4 (Composition four) ወይም ልቁጥ ፈንጅ፣ RDX፣ PTX፣ HMN፣ አሞኒየም ናይትሬትና TMX የተሰኙትን ጨምሮ ሌሎችም በአለም ላይ ያሉ በርካታ ፈንጅዎችን በቀላሉ ይለያል፡፡ “ኤኤል-6ዲ” ኤኤል-6ዲ (AL-6D) የሚባለው ዘመናዊ የኤሌትሮኒክስ መሳሪያ፣ ኤሌክትሮ ማግኔቲክ መልዕክት በፍጥነት በማስተላለፍና ቦታዎችን በመጠቆም የተዋጣለት ዘመኑ ያፈራው መሳሪያ ነው፡፡ ከተቀመጠበት ቦታ እስከ 20 ኪ.ሜ ርቀት 360 ዲግሪ በማካለል ጋራ፣ ህንፃ እና ምንም አይነት ከለላ ሳያግደው ፈንጅ፣ የጦር መሳሪያ፣ የሚፈነዳ ነገር፣ የኒውክለር አረር፣ ተተኳሽ ነገር፣ ባሩድ እና ማናቸውንም የሚፈነዱ ነገሮች ጨምሮ ማዕድንም መኖሩን በቅፅበት ማመላከት ይችላል፡፡

ምን ይሄ ብቻ … ወደ መሬት እስከ 8 ሜ. ጠልቆ በማንበብ የተጠቀሱት ነገሮች መኖራቸውን ለመግለፅም ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ባህር፣ ውቅያኖስ፣ አሸዋማ ይሁን ኮንክሪት AL-6Dን አይበግረውም፡፡ ተሽከርካሪን ጨምሮ ባቡርም ይሁን መርከብ ላይ ጥቆማ ለመስጠት አይሳነውም፡፡ “ኤኤል-6ዲ” በቀላሉ በእጅ ተይዞ መንቀሳቀስ የሚችል ሲሆን ከኮምፒዩተር (ላፕቶፕ) ጋር በብሉቱዝ ተገናኝቶ በጎግል ኧርዝ አማካኝነት የተለያዩ መስመሮችን በማስመር ፈንጂው ወይንም ማዕድኑ የሚገኝበትን ቦታ ያሳያል፡፡ ከዚያም ወደ ቦታው በማምራት የተባለውን ነገር ማግኘት ይቻላል። እነዚህን ሥራዎች ያለ ምንም እንከን በማከናወን “ኤኤል-6ዲ” እጅግ የተዋጣለት በመሆኑ በርካታ የአውሮፓ ሀገሮችና ከሦስት የማይበልጡ የአፍሪካ ሀገራት መሳሪያውን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ይህንን ዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ በአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታንና ሌሎችም ፍንዳታ በሚበዛባቸው ሀገሮች ስራ ላይ አውለውት ባለውለታነቱን አስመስክሯል፡፡ “ኤኤል-6ዲ” ስቴድየሞችን፣ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያዎችን፣ ወደቦችን፣ የአውቶብስ መናኸሪያዎችንና ሆቴሎችን እንዲሁም ሌሎች ቦታዎችን ከፍንዳታ አደጋ ነፃ እንዲሆኑ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ከአደጋ የመጠበቂያ መሳሪያ ሆኗል፡፡

ይህንን መሳሪያ የሚሸጠው ዳዮድቢል ኮርፖሬሽን፤ ኤኤል -6ዲን “ለእያንዳንዱ ዜጋ የተፈጠረ ነፍስ አድን” በማለት ድንቅ የዘመናችን ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህንን ዋጋው እጅግ ውድና ጠቀሜታው ጉልህ የሆነውን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ከሚጠቀሙበት ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። መሳሪያው በውድ ዋጋ ተገዝቶ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት የፍንዳታ ዲቪዥን አማካኝነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አገራችን ኤኤል 6ዲ ቴክኖሎጂን መጠቀም በመጀመሯ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ሊፈነዱ የሚችሉ ነገሮችን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ መንግስታትና ትልልቅ ባለስልጣናት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት፣ መንግስታዊና ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ እግር ኳስ ጨዋታዎችና የሃይማኖት በዓላትና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች በሚኖሩበት ጊዜ መሳሪያው ያለ ምንም ስጋት እንዲከናወን ያስችላል፡፡ በኤርፖርቶችና ሌሎችም ቦታዎች ቢሆን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ የፍንዳታ ስጋትን ማስወገድ ተችሏል ብለዋል - ኢንስፔክተር ታመነ፡፡

Read 2847 times