Saturday, 22 June 2013 11:10

“ቢግ ብራዘር” ለአፍሪካ የቀረበላት የቅሌት ውድድር!

Written by  ግደይ ገብረኪዳን
Rate this item
(15 votes)

“ቢግ ብራዘር” ወንድም ጋሼ እንደማለት ነው፡፡ በዲኤስ ቲቪ የሚተላለፈው ይሄ የቲቪ ሪያሊቲ ሾው የሚቀርበው ከዓለም ተገልለው በአንድ ቤት ውስጥ በደባልነት የሚኖሩ ወጣቶችን እንቅስቃሴ ለ24 ሰዓት በካሜራ በመከታተል ነው፡፡ ፉክክሩ ለሶስት ወር የሚቆይ ሲሆን ሳይባረር የተመልካቾችን ይሁንታ (ድምጽ) እያገኘ እስከመጨረሻው ድረስ የዘለቀ ተወዳዳሪ እስከ 300ሺ ዶላር የሚደርስ ሽልማት ያገኛል፡፡ የአፍሪካ “ቢግ ብራዘር” አስራ አራት አገሮችን ያሳትፋል፡፡ የመጀመርያው ውድድር (እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም) አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ናምቢያ፣ ናይጀርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ የተካተቱበት ሲሆን በአራተኛ ዓመት ውድድሩ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሞዛቢክን ጨምሯል፡፡ በሰባተኛው ዓመቱ ላይ ላይቤርያ እና ሴራሊዮን ተካትተዋል፡፡ ወንድም ጋሼ እና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የዚህ ትርኢት አካል የተደረገችው በ “ቢግ ብራዘር” አራተኛ የውድድር ዘመን ያእቆብ አቤሴሎም በተባለ ወጣት አማካኝነት ነበር፡፡

ይህም እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ቀጣዩ የትርኢቱ ዘመን ከዚህ በፊት በትርኢቱ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ተመልሰው የተወዳደሩበት ሲሆን ያእቆብ ዳግም ከኢትዮጵያ ተሳትፏል፡፡ ያእቆብ እና አጋሩ በአራተኛው የውድድር ዘመን ለሳምንት ያህል በረት ውስጥ እንዲኖሩ የቀረበላቸውን ፈተና ያዕቆብ መቋቋም ባለመቻሉ ከውድድሩ እራሱን አግሏል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ፣ ዳኒ እና ሃኒ በተባሉ ወጣቶች ተወክላ ተሳትፋለች፡፡ በሰባተኛው ዘመን ኢትዮጵያ ተሳትፎ አልነበራትም፡፡ አሁን በስምንተኛው የውድድር ዘመን ደግሞ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ሰበብ የሆነችኝ ቤቲ የተባለች የ26 ዓመት ወጣት መምህርት ተወክላለች፡፡ ይህን ጽሑፍ በቤቲ ምክንያት ለመፃፍ ብነሳሳም ዓላማዬ ቤቲ ላይ በማነጣጠር እሷን መውቀስ አይደለም፡፡

እሷ የዚህ አፀያፊ ተግባር አካል እንድትሆን ተደርጋለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ዋናው ግቤ ግን ስለ ትርኢቱ ሰፊ መረዳት እንዲኖረንና ለወደፊቱ ከዚህ ሞኝነት እራሳችንንና ሃገራችንን የምንጠብቅበት አስተዋይነት እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በሚቀጥለው ዓመት ትርኢቱ ወደ ሃገራችን ለምልመላ ሲመጣ ፍቃድ ነስቶ ማባረርና ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ደግሞ በሐገራችን ፕሮግራሙ እንዳይሰራጭ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ በተረፈ ለቤቲ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማት በመመኘት ውድድሩ ሲጠናቀቅ ተመክሮዋን ለመላው ዓለም ታጋራ ዘንድ ፍላጎቴ ነው፡፡ እሷ ለእኔ የፕሮግራሙ ሰለባ እንጂ ሌላ አይደለችም፡፡ አንድ ጥያቄ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ እቺ ወጣት ፈፀመች የተባለውን የፈፀመችው ወዳና ፈቅዳ ወይስ በተፅእኖ ይሆን? ጋጠወጥነት ከወንድም ጋሼ እስከዛሬ ይሄ የሪያሊቲ ሾው ፕሮግራም ምን ዓይነት ጋጠወጥ ክስተቶችን አስተናግዷል የሚለውን ደግሞ መረጃ እየነቀስን እንመልከት፡፡

በተለይ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በ”ቢግ ብራዘር” ውድድሮች አማካኝነት የተፈፀሙ ቅሌቶችን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ አፍሪካ፣ 2003 ወንድም ጋሼ በአፍሪካ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ ነበር ውዝግብ ያስነሳው፡፡ የዩጋንዳው ተወዳዳሪ ካግዋ እና የደቡብ አፍሪካዋ ፕሌትጀት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭቱ ወሲብ እያደረጉ ያለ የሚመስል ነገር ታይቶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወቅቱ ፕሮግራሙ በማላዊ እንዲቋረጥ ተደርጎም ነበር፡፡ ብራዚል፣ 2012 ሞኒክ የተባለች ተፎካካሪ ሰክራና እራሷን ስታ አልጋዋ ውስጥ ተኝታ ሳለ፣ ዳንኤል የተባለ ተፎካካሪ የእሷን ይሁንታ ሳያገኝ አልጋው ውስጥ ገብቶ ወሲብ በመፈፀሙና እሷም “ያለ ፈቃዴ የተፈፀመ” ነው በማለቷ፣ ክብረ ንጽህናዋን (ውድድሩ ውስጥ ሲገቡ ክብር የሚባል ነገር የለም) ገስሷል ተብሎ ወዲያውኑ ከውድድሩ ተባርሯል፡፡ አሜሪካ፣ 2001 ጀስቲን ሴቢክ የተባለው ተወዳዳሪ ክሪሳት ስቴጋል የተሰኘችውን ሌላ ተወዳዳሪ ቢላ አንገቷ ስር ይዞ እያስፈራራ ሲስማት የታየ ሲሆን ይህም ተፎካካሪ ወዲያውኑ ከፕሮግራሙ እንዲባረር ተደርጓል፡፡

አፍሪካ፣ 2008 ታዋና ሌባኒ የተባለች ተፎካካሪ ታኮንዳዋ ንኮንጄራ የተባለ ተፎካካሪን ብልት በአፏ ስትነካካ ታይታለች፡፡ ይህችው ሴት ከሁለት ወንዶች ጋር የተኛች ሌላ ተፎካካሪን “ሰይጣን” ብላ ያወገዘቻት ቢሆንም እሷ ራሷ ከሁለት ተወዳዳሪ ወንዶች ጋር በአንድ ግዜ ወሲብ መፈፀሟ ተዘግቧል፡፡ ከውድድሩ ተሸንፋ ስትወጣም የሃገሯን የቦትስዋና ባንዲራ ለብሳ “ብልት እወዳለሁ!” በማለት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት አውጃለች፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ቅሌት ይኖራል? አውስትራሊያ፣ 2005 ማይክል ብሪክ እና ማይክል ኮክስ የተባሉ ተወዳዳሪዎች በፈጸሙት ወሲባዊ ጥቃት ከትርኢቱ ተባርረዋል፡፡ በዚህ ውድድር ብሪክ የተባለው ተፎካካሪ ካሚላ ስቭሪ የተባለች ተወዳዳሪን በጉልበት ከያዛት በኋላ፣ ኮክስ የተባለው ሌላ ተወዳዳሪ ብልቱን ፊቷ ላይ ሲያደርግ በቀጥታው ስርጭት ታይቷል፡፡ በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ሃዋርድ፤ የፕሮግራሙ አስተላላፊ የነበረው “ቻነል 10” ይህን “ጅላንፎ” ፕሮግራም ማስተላለፍ እንዲያቆም ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ትርኢቱ ግን እስከዛሬ ቀጥሏል፡፡

ብሪታንያ፣ 2005 ኪንጋ ካሮልክዛክ ወጣ ባለ ጋጠወጥ ባህሪዋ (በዋሾነት፣ ሰካራምነትና እርቃኗን በመሆን) በትርኢቱ ገንና ከቆየች በኋላ፣ በፉክክሩ አጋማሽ ላይ እጅግ ወጣ ያለ ድርጊት ፈፅማለች፡፡ እንደልማዷ ሰክራ እግሯን ከፍታ ተንጋላ ከተኛች በኋላ፣ ባዶ የወይን ጠርሙስ ተጠቅማ እራሷን ለማስደሰት ስትሞክር ታይታለች፡፡ ኮሮልክዛክ ከውድድሩ በኋላ ለ “ዴይሊ ሚረር” በሰጠችው ቃለምልልስ ድርጊቱን የፈፀመችው ከፕሮግራሙ ባለቤቶች በቀረበላት መደለያና በደረሰባት “ትባረርያለሽ” የሚል ማስጠንቀቂያ የተነሳ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ አፍሪካ፣ 2007 አልኮል ያለመጠን የወሰዱት ሪቻርድ ቤዙዴንሃውትና ኦፋኔካም ተመሳሳይ ጋጠወጥ ድርጊት እንደፈፀሙ ተዘግቧል፡፡ ሪቻርድ እራሷን ስታ ከተኛችው ኦፉኔካ አጠገብ በመተኛት በእጆቹ ብልቷን ሲደባብስ የታየ ሲሆን ሌላ ተወዳዳሪ ሴት የሚሰራውን እንዲያቆም ስትጮህበት ነበር ከድርጊቱ የተገታው፡፡ ይህ አሰቃቂ ድርጊት በቲቪ በቀጥታ እየተሰራጨ የነበረ ሲሆን እዚህ ጋ ሲደርስ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ወዲያው የህክምና እርዳታ አድራጊዎች ለተወዳዳሪዋ የደረሱላት ቢሆንም ድርጊቱ የአስገድዶ መድፈር ሙከራ መሆኑ እየታወቀ ጣቢያው “በፈቃዷ የተፈፀመ ነው” በሚል ትርኢቱ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ በመጨረሻም የአስገድዶ መድፈር ሙከራ ፈፃሚው አንደኛ፣ ተደፋሪዋ ሁለተኛ ወጥተው ፉክክሩ ተጠናቋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ቤቲ ወሲብ ስትፈጽም ታይቷል፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ጋጠወጥ ድርጊቶችን የሚያሰራጨው የዲኤስቲቪው ኤምኔት ቻናል ሃይ ባይ ያጣ ይመስላል፡፡ እንደ ማላዊ ያሉና የናይጄርያው ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙ እንዳይተላለፍ እገዳ ጥለውበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ የወንድም ጋሼ ፋይዳ ምንድነው? የብሪታንያው ጎልድስሚዝ ዩኒቨርሲቲ፣ የስነ ማህበረሰብ ፕሮፌሰር የሆኑት ቤቨርሊ ስኬግስ፤ [የትርኢቱን] ቅርጽ የማህበረሰቡ የኃይል አወቃቀር ከማህበራዊ ለውጥ ጋር እንዲለወጥ የሚያደርግ፣ የሰዎች ስብእናና ተግባሮቻቸው በጥሩ እና መጥፎ ምድቦች የሚከፋፈሉበት የግምገማ መንገድ ነው ይሉታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ይሄን ፕሮግራም እንደ አንድ አፍሪካዊ ባህል መፍጠርያ መድረክ ይቆጥሩታል፡፡

ለእኔ ግን አፍሪካውያንን ከእነ ባህላቸው የሚያጠፋ መድረክ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ የተጻፈው በወግ አጥባቂ ግለሰብ ነው፤ በሚል ግምት እውነታውን አያሳይም የሚል ካለ እጅጉን ተሳስቷል፡፡ ከቀረበው መረጃ አንጻር ማንኛውም ሰብአዊ ክብሩን፣ መንፈሳዊ ሰላሙንና ነጻነቱን የሚወድ ሰው ሁሉ፣ ከዚህ ጋጠወጥ ምግባር እራሱንና የሚቆረቆርለትን ወገን ሊጠብቅ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ጋጠወጥ የቲቪ ፕሮግራም በአገራችን እንዳይሰራጭ፣ ወጣቶችም በውድድሩ ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ቤተሰቦች፣ ሚዲያዎችና ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ ዘንድ እማፀናለሁ፡፡ ሥርጭቱን ከማሳገድ መለስ ያለው ሌላው አማራጭ ደግሞ መረጃን በመረጃ መታገል ነው። የሕዝብ ግንኙነት አባት እየተባለ የሚወደሰው ኤድዋርድ በርኔይስም፤ “የፕሮፓጋንዳ ምርጡ መመከቻው፣ ተጨማሪ ፕሮፓጋንዳ ነው” ብሏል። ያለዚያ ግን እንዲህ ያለው ጋጠወጥ ፕሮግራም የባህልና የማንነት ቀውስ መፍጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

Read 8911 times