Saturday, 22 June 2013 11:02

እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት አያ አንበሶ ከበሽታቸው መዳናቸውን ምክንያት በማድረግ ድግስ እንዲደገስ ተስማሙ፡፡ አያ አንበሶም ፈቀዱ፡፡ በቅደም - ተከተል ባለሟሎቹ ስማቸው ተዘረዘረ ተፃፈና ጮክ ተብሎ ተነበበ፡፡

“አንደኛ - ነብሮ” ተባለ፡፡ ተጨበጨበ፡፡ “ሁለተኛ - አያ ዝሆን” ተባለ፡፡ ተጨበጨበ፡፡

“ሦስተኛ - አውራሪስ” ተባለ ተጨበጨበ፡፡

“አራተኛ - አጋዘን” ቀጠለ ተጨበጨበ፡፡

“አምስተኛ - ጅብ” ተጨበጨበ፡፡

“ስድስተኛ - ዝንጀሮ” እያለ ግንባር ግንባር ቦታ፤ ዋና ዋና ወንበር ላይ የሚቀመጡቱ በዝርዝር ታወቁ፡፡ አያ አንበሶ ቀጠሉና፤ “ታምሜ ያልጠየቁኝ ወደዚህ ድግስ እንዳይመጡ” ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡

አክለውም “በተለይ ጦጣ!” አሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ለሁሉም አራዊት የድግሱ ጥሪ እንዲደርሳቸው ተባለና ተላከባቸው፡፡ ድግሱ ድል ተደርጐ ተደግሷል፡፡ ያልተጠራ የዱር አራዊት የለም፡፡ አሰላለፋቸው የታወቀ ነው፡፡ አንበሳ ሁሉንም በደምብ በሚያይበት ዙፋን - አል ወንበሩ ላይ ኮራ ብሎ ተቀምጧል፡፡ እነ ነብር፣ እነዝሆን፣ እነ አጋዘን፣ እነድብ ወዘተ በየተከታታይ ተርታ ተሰድረዋል፡፡ ጦጢት የለችም፡፡ ምክንያቱም አያ አንበሶ ታመው፤ አንድ ሁለት ጊዜ አጭበርብራ ሳትጠይቃቸው በመቅረቷ ነው፡፡ ካዩዋት አይለቋትም፡፡ ሆኖም የተለየ ልብስ ለብሳ ዋና አጋፋሪ ሆና ድግሱን ስታሞቀው ውላለች፡፡

“እዚህ ድግስ ተጠርተሻል? እንዴ?” ሲል ከተጋባዦች አንዱ ጠየቃት፡፡ ውስጥ አዋቂ ብጤ ነው፡፡ “ኧረ አልተጠራሁም” አለች ጦጢት “ታዲያ ምን ታረጊ መጣሽ?” አላት ሌላው፡፡ “ዘመዶቼ ቅር እንዳይላቸው ብዬ ነው” “ኋላ አያ አንበሶ ቢያገኙሽና አንድ ቅጣት ቢቀጡሽስ? ፀፀቱ ለዘመዶችሽ አይሆንም ወይ? ደሞም ታላላቅ ዘመዶችሽ ውርደቱን አይችሉትም፡፡ መዘዝሽ ለሁሉ ይተርፋል፡፡ “እግዜር ጥሎ አይጥለኝም፡፡ ድፍረቱን ሰጥቶ ከድግሱ ከቀቀለኝ፣ ከእሳቱ መውጪያውንም እሱ ያበጅልኛል፡፡” ሁሉም ተሳሳቁ፡፡ ከመሀል አንደኛው፤ “አይ ጦጢት፤ ዱሮ በብልጠቷ ነበር የምትተማመነው፡፡ አሁን ለአምላክ እጇን ሰጠች፡፡ አይ ጊዜ! ጊዜ ሁሉን ያጋልጣል፡፡ ጦጢትንም ቢሆን” አለ፡፡

                                                        ***

ሁሌ ብልጠት አያዋጣም፡፡ “አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አያበላም” ይላሉ አበው፡፡ በብልጠት ሸፋፍኖ ዛሬን ማለፍ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገ ግን ብልጠቱ ያረጅና ዕውነቱ እንደአዲስ ቆዳ ብቅ ይላል፡፡ ስለዚህ “ሞት ላይቀር ማንቋረር” ነው የሚሆነው፡፡ የሀገራችን እስፖርት የብዙሃን መዝናኛና የብዙሃን መፎካከሪያ ነው፡፡ ውስጥ፣ እርስ በርሱ እንደየቲፎዞው አቅም ይሟገታል፡፡ ይወራረዳል፣ ይጋጫል፡፡ ከውጪ ቡድን ጋር ግጥሚያ ሲመጣ ግን ብዙሃኑ ህዝብ የእርስ በርስ ፉክክሩን፣ ፉክቻውንና፣ ሽኩቻውን ወደጐን ትቶ የአገር ጉዳይ ነው ብሎ፤ ሥጋውንም ነብሱንም ይሰጣል፡፡ ሲሸነፍ ደግሞ ፀጉሩን ይነጫል፤ አንጀቱ ያርራል፡፡ ሲያሸንፍ ዘራፍ ይላል፡፡ ያምባርቃል፡፡ መንገድ ይሞላል፡፡ የሞተር ብስክሌት አክሮባት፣ የመኪና ሰልፍ፣ የሰው ጐርፍ… ድብልቅልቁ ይወጣል፡፡

ደስታና ሁካታው ጣራ ይነካል! (The sky is the limit እንዲሉ ፈረንጆች) አንድ ክስተት የአገር ጉዳይ ሲሆን ህዝብ ከአፍ - እስከ ገደፉ እንደሚንቀሳቀስ መገለጫው እንዲህ ያለው የስፖርት ስሜት ነው፡፡ ነፍሱን - ልቡን ገብሮ የሚቆምለት ስሜት ነው!! ይህን ስሜት ማጭበርበር አይቻልም፡፡ ይህን ስሜት ማውገርገርና ማኮላሸት ክፉ ቁጣ፣ ሐዘንና ክፉ ፀፀት ይፈጥራል፡፡ ብርድ እየፈደፈደው፣ እንቅልፉን አጥቶ የጮኸለትን ድሉን በተራ ስህተት ሲነጠቅ ማየት እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ስህተቱ የማንም ይሁን የማን አስተምሮ፣ አስምሮ፣ አመሳክሮ የመገኘትን ቁብ አጉልቶ አሳይቷል፡፡

“አንተ እኮ የእግዜር ስህተት ነህ” እንዳለው ነው ፀሐፌ - ተውኔቱ፤ በንዴት ስናጤነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ዋና ዋና ቁቦቻችንን ብንነቁጥ:- አገር ድብብቆሽ መጫወቻ፣ አየሁሽ አላየሁሽ መባባያ አይደለችም! ስህተትን መወያየት እንጂ መደባበስ የትም አያደርሰንም፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ክቡር ባህል ነው፡፡ ኃላፊነትን መቀበል የሰለጠነ መንገድ ነው፡፡ ውስጣችንን መፈተሽ፣ መረጃዎቻችንን በጥብቅ መያዝ፣ በየትንሹ ጉዳይ አለመበርገግ፣ አለመዝረክረክ ዋጋ ከመክፈል ያድናል፡፡ በመጨረሻም ህዝብ የጮኸልንን ያህል የጮኸብንና የተነሳብን ቀን ወዮልን ማለት አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ የብስለት ምልክት ነው፡፡ አመንነውም አላመንነውም፤ መዘንነውም ሸቀብነውም፤ አስፈላጊውን ቅድመ - ሁኔታ ሳናሟላ ሜዳ ውስጥ መገኘት፤ “እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” እንደሚባለው ተረት መሆኑ የነገሩ ብልት ነው!

Read 3215 times