Saturday, 22 June 2013 10:53

የወሰን ማስከበር ስራዎች የባቡር ፕሮጀክቱን እያጓተቱ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

       የውጪ ድርጅቶች በልማቱ ላይ እንቅፋት እየሆኑ ነው

          ከፈጣን ባቡር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ለመንገዱ የሚያስፈልገውን መሬት ለማግኘት ከሚተገበረው የወሰነ ማስከበር ስራ ጋር በተገናኘ አድሎ እንደሚፈፀምና ተለዋዋጭ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ነዋሪዎች ሲናገሩ፤ ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚመራው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የወሰን ማስከበሩ ስራ ለኔም የራስ ምታት ሆኗል፤ ስራዬንም እያጓተተ ነው አለ፡፡ ከሲኤምሲ አካባቢ እስከ ጦር ሃይሎች ለሚደርሰው የ8 ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ፕሮጀክት በሚያስፈልገው የማስተር ፕላን ቦታ ውስጥ የተገኙ የመኖሪያ፣ የንግድ ቤቶችና ትላልቅ ህንፃዎች እየፈረሱ ሲሆን በአካባቢው ያሉ ንግድ ቤቶች በማፍረስ ሂደቱ በተለይ ከልኬት ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ተለዋዋጭ የሆኑ ውሣኔዎች እየተላለፉ መሆኑ ቋሚ ወሰናችንን እንዳናውቅ አድርጎናል፤ ይህም የንግድ ስራችንን እያወከብን ነው ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ቀን ልኬት መሠረት አፍርሱ ከተባልን በኋላ በተወሰነልን ድንበር ላይ ራሳችንን አቋቁመን ስራችንን ስንጀምር በድጋሚ የተወሰኑ ሜትሮች አፍርሳችሁ ወደ ውስጥ አስጠጉ እንባላለን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከዚህም ባሻገር በተመሳሳይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቤቶችና ህንፃዎች መካከል አድሎ ይፈፀማል፣ አንደኛው ሲፈርስ አጠገቡ ያለው ሣይፈርስ ይቀመጣል በማለት ችግሩን ይገልፃሉ፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፍቃዱ ሃይሌ በበኩላቸው፤ በህብረተሰቡ የሚነሱት ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን በመግለጽ በተለይ ተለዋዋጭ የልኬት ስራዎች ላይ የሚሰነዘረው ቅሬታ እሣቸውንም በተደጋጋሚ ከባለሙያዎች ጋር የሚያጋጫቸው ተገቢ ያልሆነ አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዎቹ በማስተር ፕላኑ የተፈቀደውን 40ሜትር ስፋት ለማግኘት በሚያከናወኑት የልኬት ስራ ውስጥ ለስራው ትኩረት ሠጥቶ ሃላፊነትን ካለመወጣት ጋር የሚፈጠር ችግር እንዳለ የጠቆሙት ኢንጂነር ፍቃዱ፤ አንዴ ቁርጥ ያለ የድንበር ልኬት አለመከናወኑ በተለይ በንግድ ስራ በሚተዳደሩ ግለሰቦች ላይ ተጽእኖ እንዳለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደሚገነዘብና ችግሩን ለመፍታት ከከተማዋ ፕላን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት መፍትሄዎችን ለመዘየድ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለባቡር ፕሮጀክቱ ተብሎ የማስተር ፕላኑ ከሚያዘው 40 ሜትር ውጪ ተጨማሪ መሬት እንደማይወሰድ የሚናገሩት ኢንጂነሩ፤ በዚህ ክልል ውስጥ ያሉ ህንፃዎች እና ቤቶች ግን ሙሉ በሙሉ ተነሺ ናቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ “ለም ሆቴል” አካባቢ ባሉ ቦታዎች ለመንገዱ በሚገነባው ማሳለጫ ምክንያት ከ40 ሜትር ሊወጣ ይችላል፡፡ ተመሳሳይ በ22 አካባቢ፣ በመገናኛ፣ በዘሪሁን ህንፃ አካባቢ፣ በሜክሲኮ እና በለገሃር ስፖርት ኮሚሽን አካባቢም መንገዱ የውስጥ ለውስጥ እና የላይ ማሳለጫዎችን አካትቶ ስለሚሰራ ከ40 ሜትር ተወጥቶ ሊሠራ እንደሚችል ኢንጂነር ፍቃዱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ህንፃዎችና ቤቶች ሲፈርሱ እንደ መስፈርት የሚታዩ ጉዳዮች እንዳሉ የሚገልፁት ሃላፊው፤ በዋናነት ህንፃው ቢፈርስ ያለው የኢኮኖሚ ጉዳት፣ የሚያስከትለው ውድመት እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከግምት ይገባል ብለዋል፡፡

ይህ ከተጠና በኋላ ትንሽ ወጪና ጉዳት ያለው ቤት ወይም ህንፃ እንዲፈርስ ሲደረግ የማፍረሱ ስልጣንም የክፍለ ከተሞች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህ መሠረት በመንገዱ 40 ሜትር ክልል ውስጥ ያረፉ ህንፃዎችና ቤቶች ተገቢው ካሣ እየተከፈላቸው ይፈርሳሉ የሚሉት ኢ/ር ፍቃዱ፤ የመንግስት ንብረቶች የሆኑት እንደ የፍትህ ሚኒስቴር እና ልደታ ፍርድ ቤት አጥር የመሳሰሉት የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ባስተላለፈው ውሣኔ መሠረት፤ ያለምንም የካሣ ክፍያ እንዲፈርሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የካቢኔው ውሣኔ በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ተቀባይነት ካላገኘ በማፍረስ ሂደቱ ላይ መጠነኛ መዘግየት እንደሚያጋጥምና ችግሩ በአጭር ጊዜ ተፈትቶ የማፍረስ ስራው እንደሚሰራ የገለፁት ኢንጂነሩ፤ በዚህ ሳቢያ ጉዳዩ እንደ አድሎአዊ አሠራር መታየት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡

ከኤምባሲና ከውጭ ድርጅቶች ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው የነገሩን የስራ ሃላፊው፤ ከሲኤምሲ እስከ ጦር ኃይሎች በሚሰራው መንገድ ላይ ውሃ ልማት አካባቢ የሚገኘው የቡልጋሪያ ኤምባሲን ጨምሮ ልደታ አካባቢ የሚገኘው ደጅ አዝማች ባልቻ ሆስፒታል በሩሲያ መንግስት ከመተዳደሩ ጋር በተያያዘ፣ ጉዳዩ ከአለማቀፍ ስምምነት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ በስራው ላይ መዘግየት አጋጥሟል ብለዋል፡፡ ከ6 ኪሎ እስከ ጉራራ በሚሰራው መንገድ ላይ የሚገኘው የፈረንሣይ ኤምባሲም አጥሩ ከ3-5 ሜትር ወደ ውስጥ መግባት እያለበት ኤምባሲው ለማፍረስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ስራው እንደተጓተተ የገለፁት ኢንጂነር ፍቃዱ፤ የውጭ ድርጅቶች የሚፈጥሩት ችግር በልማቱ ላይ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ ጉዳዩን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሣውቀን ምላሹን ለማግኘት እየተጠባበቅን ነው ያሉት የስራ ሃላፊው፤ የቡልጋሪያ ኤምባሲ አጥር ወደ ውስጥ ፈርሶ መሠራቱ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል አስተዳደርም መንገዱ በኛ በኩል ማለፍ የለበትም፤ ድንበራችንንም አናፈርስም ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑንና ይህም በፕሮጀክቱ ላይ የመዘግየት ችግር መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

በመስመሩ ላይ የሚፈርሱ ህንፃዎችና ቤቶች ሁሉ መታወቃቸውንና እየፈረሱ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂነር ፍቃዱ፤ ለገሃር አካባቢ የሚገኙት የመድህን ህንፃና የባህር ትራንስፖርት ቢሮ ህንፃ መሃንዲሶች፤ ህንፃዎቹ ሳይነኩ የባቡሩ መንገድ የሚሰራበትን አማራጭ በማመላከታቸው ከመፍረስ መዳናቸውን ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል በመንገዱ ላይ የተቀበሩ የውሃ የመብራትና የስልክ መስመሮችን የማዛወር ስራ እየተሠራ እንደሆነ የተናገሩት ሃላፊው፤ እስካሁን አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ለዋናው ስራ በሚያስፈልግ ዝግጅት ደረጃ 80 በመቶው ተጠናቋል ብለዋል፡፡ “እስከዛሬ በከተማዋ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ከባዱና ውስብስብ የሆነው ከሲኤም ሲ እስከ ጦር ሃይሎች የሚገነባው አዲሱ የባቡርና የመደበኛ መንገድ ፕሮጀክት ነው” የሚሉት የስራ ሃላፊው፤ በ8 ኪሎ ሜትር ውስጥ ብቻ በአምስት ቦታዎች ላይ ወሎ ሠፈርና ኦሎምፒያ አካባቢ የተሰሩትን አደባባዮችና ማሳለጫ መንገዶችን የመሰሉ ይሰራሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሁለት ቦታዎች የላይ መሸጋገሪያ ድልድይ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎችም መገናኛ አደባባይ፣ 22 አካባቢ፣ ኡራኤል፣ ሜክሲኮ፣ ልደታ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ለም ሆቴልና ዘሪሁን ህንፃ አካባቢ ደግሞ የላይ መሸጋገሪያ ድልድዮች ይሰራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ነባሩ የእግረኛና የመኪና መንገድ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መልክ እንደገና ይሰራል ብለዋል ኢንጂነር ፍቃዱ፡፡ ሌሎች መንገዶችም በቀጣይ እየተዘጉ እንደሚገነቡ ጠቁመው፤ በዘንድሮ ክረምትም ከሜክሲኮ እስከ ልደታ ያለው መንገድ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

Read 11190 times