Saturday, 22 June 2013 10:50

የንግድ ተቆጣጣሪ ነኝ እያለ ነጋዴዎችን ያታለለው ተፈረደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት አስቦ ባልተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት የንግድና ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ነኝ በማለት ደረቱ ላይ የተሳሳተ ባጅ አንጠልጥሎ፣ በየሱቁ እየገባ የዘይት ዋጋ በመጠየቅ “ከዋጋ በላይ ነው የምትሸጡት፤ ሱቃችሁን አሽጋለሁ” እያለ ጉቦ ሲቀበል የነበረው ወጣት በአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና በ70 ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጣ፡፡ በመተላለፍ በፈፀመው የማታለል ወንጀል በአቃቤ ህግ ተከሶ ልደታ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 12ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩ የታየው የ23 ዓመቱ ወጣት ድላየሁ ቲሮሮ ኤርጊቶ አምስት ያህል ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በአንደኛው ክስ እንደተመለከተው፤ በ10/9/05 ዓ.ም በግምት ከቀ 7 ሰአት ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01/18 “ልደታ ጠበል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የንግድና ኢንዱስትሪ የንግድ ቁጥጥር ሠራተኛ ሳይሆን ሠራተኛ ነኝ በማለት የንግድ ቁጥጥር ባለሙያ” የሚል ባጅ አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ ወደ አንድ ሱቅ በመግባትና የዘይት ዋጋ በመጠየቅ “ከዋጋ በላይ ነው የምትሸጠው፤ ስለዚህ ሱቁን ላሽገው ነው” በማለት 300 ብር በጉቦ መልክ ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በሁለተኛ ክስ ደግሞ በዚያኑ ቀን በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት ሲሆን በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 01/18 ልዩ ቦታው አባይ ምንጭ አካባቢ፣ ያንኑ ባጅ አንጠልጥሎ ወደ ሱቅ ጐራ በማለት የዘይት ዋጋ በመጠየቅ “ከዋጋው በላይ ነው የምትሸጠው፤ ሱቅህ እንዳይታሸግ” የሚሉ አሳሳች ነገሮችን በመናገር 175 ብር ተቀብሏል፡፡ በሶስተኛ ክስ በነጋታው ከቀኑ 10 ሰዓት በተመሳሳይ ስፍራ ያንኑ ሃሰተኛ ባጅ አንጠልጥሎ አንድ ሱቅ በመግባትና የዘይት ዋጋ በመጠየቅ “ከታሪፍ በላይ እየሸጣችሁ ነው፡፡ ስለዚህ አሽገዋለሁ” በማለት 500 ብር መቀበሉን ፣ በ4ኛው ክስም በዚያኑ እለት በ10 ሰአት በዚያው ክፍለከተማ እና ወረዳ ልዩ ቦታው ቤከር ፋርማሲ አካባቢ የዘይት ዋጋ በመጠየቅና በተመሳሳይ ሁኔታ በማስፈራራት 300 ብር እንዲሰጡት መጠየቁ፣ እንዲሁም በ5ኛ ክስነት በዚያኑ ቀን ቤከር መድሃኒት ፋብሪካ አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ሱቆች በመንቀሳቀስ ገንዘብ የተቀበለ በመሆኑ በፈፀመው በሃሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ተከሶ የቀረበ ሲሆን ወንጀሉ በዘጠኝ የሰው ምስክሮችና በተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለእያንዳንዱ ክስ የሶስት ወር እስራት መነሻ ቅጣት እርከን አድርጐ፣ ተከሳሹን ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በአንድ አመት ከሁለት ወር እስራት እና በብር 70 መቀጮ እንዲቀጣ ውሣኔ አስተላልፏል፡፡

Read 9808 times