Saturday, 15 June 2013 10:42

ከ80 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የአውሮራ ቤተመፅሃፍት!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት የሚገኘው የአውሮራ የህዝብ ቤተመፅሃፍት ከ80 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የዕድሜ ባለፀጋ ነው፡፡ የዕድሜ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በመፅሃፍት፣በመረጃ፣በንባብና በዘመናዊ የቤተመፅሃፍት አገልግሎት አሰጣጥም የተደራጀና የበለፀገ ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ጅማሬው ነው- አነሳሱ፡፡ ይሄን የህዝብ ቤተመፅሃፍት የማቋቋም ሃሳብ የፀነሱት እ.ኤ.አ በ1925 ዓ.ም የከተማዋን ማደግ ተከትሎ የተመሰረተው የአውሮራ ሴቶች ክበብ አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ ትጉህና በአዳዲስ ሃሳቦች የተሞሉ የክበቡ አባላት ከተማዋ እየሰፋች ፤የነዋሪዋ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ለአዋቂዎችም ሆነ ለታዳጊ ህፃናት አገልግሎት የሚሰጥ የህዝብ ቤተመጽሃፍት እንደሚያስፈልጋት ያሰቡት ቀደም ብለው ነበር፡፡ ከሃሳብ በቀር ግን ቤሳቤስቲን አልነበራቸውም፡፡

የሁሉም ትላልቅ ፈጠራዎች መነሻ ሃሳብ (ህልም) ነው እንዲሉ… ሃሳባቸውን በወረቀት ላይ አስፍረው፤ዕቅድ ነድፈውና ግብ አስቀምጠው ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ ገቡ፡፡ ቤተመፅሃፍት የማቋቋም ህልማቸውንም እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መትጋት ነበረባቸው፡፡ ገቢ ለማሰባሰብ ፓርቲ አዘጋጅተዋል፤ ሻይና ደረቅ ምግቦች ሸጠዋል፡፡ የፅህፈት መሳሪያዎችን ቸርችረዋል፡፡ ትያትር አዘጋጅተው አሳይተዋል-ለአዋቂዎች 25 ሳንቲም፤ ለህፃናት 15 ሳነቱም እያስከፈሉ፡፡ የአውሮራ ሴቶች ክበብ ለአራት ዓመት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ፌብሯሪ 10 ቀን 1929 ዓ.ም ሳራ የተባለች የክበቡ አባል በፈቀደችው አንዲት ክፍል ውስጥ ቤተመፅሃፍቱ ተከፈተ፡፡ የክበቡ አባላት ቤተመፅሃፍቱን ሲከፍቱ በእጃቸው ላይ የነበራቸው ገንዘብ 171ዶላር ብቻ ነበር፡፡ በአንዲት ክፍል ፤በአንድ የቤተመፅሃፍት ባለሙያና በ171 ዶላር ለከተማዋ የመጀመሪያ የሆነው ቤተመፃህፍት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ በ1930 ዓ.ም የካፒታላቸው መጠን 200 ዶላር የደረሰ ሲሆን 3100 መፃህፍትና አንድ የቤተመፃህፍት ጠረጴዛ ነበራቸው፡፡ በዚህ ወቅት በዚህች አንድ ክፍል ውስጥ በአንድ ወር ብቻ 906 ተጠቃሚዎች መስተናገዳቸው ተመዝግቧል - በዚህችው አንዲት የቤተመፅሃፍት ባለሙያ፡፡ ከ20ዓመት በኋላ ቤተመፅሃፍቱ እያደገና እየሰፋ የመጣ ሲሆን ከተለመደው የቤተመፅሃፍት አገልግሎት በተጨማሪ አዳዲስ ዝግጅቶችም ተጀምረው ነበር፡፡ ለምሳሌ ታላላቅ የመፃህፍት ውይይቶች ከመደረጋቸውም ባሻገር፣ የበጋ የንባብ ፕሮግራም እና የህፃናት የትረካ ሰዓት የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የክለቡ አባላት ከግለሰቦች እንዲሁም ቤት ለቤት እየዞሩ የመፅሃፍት ልገሳ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ አውሮራ ቤተመፅሃፍት አሁን ከተቋቋመ 84ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

በአንዲት ክፍል ቤት ተጀምሮ አራት ቅርንጫፎችን መክፈት ችሏል- ያውም ማራኪና ዘመናዊ በሆኑ ህንፃዎች ውስጥ፡፡ በ175 ዶላር የተጀመረው ቤተመፅሃፍቱ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ዓመታዊ በጀቱ 5ሚ. ዶላር ሊደርስ ችሏል፡፡ የሰራተኞቹ ቁጥርም 118 ደግሞ 118 ደርሷል፡፡ ይሄ ግን የበጎ ፈቃድ አገልጋዮችን አይጨምርም፡፡ በነገራችን ላይ አውሮራ ቤተመፅሃፍት ለህፃናት የመዋያና የመጫወቻ ስፍራዎችን ያዘጋጃል፤ ህፃናት በነፃ የስልክ አገልግሎት ትረካ የሚሰሙበት አሰራር ዘርግቷል፡፡ አረጋዊያንንም ግን አልዘነጋቸውም፡፡ የአዛውንት መጠለያ ማዕከላት ድረስ አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ቤተመፅሃፍቱ ከመፅሃፍት፣ መፅሄቶችና ጋዜጦች በተጨማሪ የኢንተርኔትም አገልግሎት አለው፡፡ የኦንላይን መፃህፍት እንዲሁም ዲቪዲና ሲዲዎችም ያቀርባል፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ ከ80 ዓመት በፊት የተፀነሰ ታላቅ ሃሳብና ህልም ፍሬ ነው፡፡

Read 2959 times