Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 November 2011 08:38

የኢራንና የአሜሪካ ውዝግብ አይሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ክምችት የዓለማችን ስጋት ነው፡፡ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ከ2500 በላይ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ያላት ሲሆን፣ ሩሲያ ደግሞ 2200 የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ አከማችታለች፡ ከአሜሪካና ከሩሲያ በተጨማሪ በፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ መሻር የሚችሉት (Veto power) አገሮች የሆኑት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ቻይናም እያንዳንዳቸው ከፍተኛ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ናቸው፡፡ ዋሽንግተንና ሞስኮ በ2010 ዓ.ም ባደረጉት ውይይት እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ 1550 የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ቅነሳ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1945 ዓ.ም በጃፓን ከተሞች በሂሮሺማና በናጋሳኪ ላይ አሜሪካ ካደረገችው ጥቃት ውጪ አምስቱም አገሮች በሰብዓዊ ኅብረተሰብ ላይ እስካሁን የኒውክሊየር መሣሪያ አልተጠቀሙም፡፡

በጃፓን ከደረሰው አሰቃቂ እልቂት በኋላ በኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ላይ ከአምስቱ አገራት ውጪ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ጥብቅ ቁጥጥር ተካሂዷል፡፡  
ነገር ግን በ1960ዎቹ አካባቢ አንዳንድ አገራት የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ግንባታ በሚስጢር እያካሄዱ መሆናቸው በመታወቁ በ1970 ዓ.ም የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ መዛመትን (Nuclear Non prolifration treaty) ተፈራረሙ፡፡ ነገር ግን ሰሜን ኮሪያ ፣ እስራኤል፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና የመሳሰሉ አገሮች ውሉን ለመፈራረም ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥም አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት የኒውክሊየር መሣሪያ ባለቤት እንደሆኑ ይታመናል፡፡
የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ የሰውን ዘር ከምድረ ገጽ የሚያጠፋ አስፈሪ የጦር መሣሪያ በመሆኑ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊያን፤ ለሰው ዘር ኃላፊነት የማይሰማቸው አገሮች ይህንን የጦር መሣሪያ በእጃቸው ማስገባት የለባቸውም በማለት ሲናገሩ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ዘልቋል፡፡
ከሁሉም በላይ አሜሪካ በዋነኛነት አፈንጋጭ አመለካከት አላቸው የምትላቸው ሰሜን ኮሪያና ኢራን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሰሞኑን ደግሞ የዓለምአቀፉን መገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሳበው የአሜሪካና የኢራን እሰጥ አገባ ነው፡፡ አሜሪካ ኢራን ለኒውክሊር መሣሪያ የሚሆነውን ዩራኒየም የተባለውን ከባድ ማዕድን እያበለፀገች ትገኛለች በማለት የጀመረችው ወቀሳ፣ ከኢራንም ጠንካራና ድፍረት የተሞላበት ምላሽ እየተሰጠው ይገኛል፡፡ አሜሪካ ያቀረበችው ክስ ሀሰት መሆኑን የገለፀችው ኢራን፤ የምታካሂደው የኒውክሊየር ግንባታ ለኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ሳይሆን ለሃይል ማመንጫ ነው ብትልም አሜሪካ ግን አልተቀበለችውም፡፡
አለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በመጪው ሳምንት የኢራንን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ግንባታ ፕሮጀክት አስመልክቶ ሪፖርት ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት፣ ከኤጀንሲው ያፈተለኩ መረጃዎች ኢራን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን መቃረቧን የሚገልጽ ነው፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ሰሞኑን ጉዳዩ በአለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በተለይ አሜሪካና እስራኤል ከወዲሁ ከኢራን ወደ እስራኤል ለመወንጨፍ የሚችሉ የረጅም ርቀት ባለስቲክ ሚሳየሎችን (Long-Range Ballastic missile) መመልከት የሚችሉበትን ፕሮጀክት ቀዳሚው እርምጃ መሆኑን አምነውበታል፡፡
አሜሪካና እስራኤል “Austere Challenge” የሚል መጠሪያ የሰጡት እና ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደር የማይገኝለት የፀረ - ባለስቲክ ሚሳየል ፕሮጀክት በሁለቱ አገሮች መካከል ከተደረጉ ታሪካዊ የትብብር ግንኙነቶች ትልቁ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ከአቶሚክ ኤጀንሲው በሚስጢር ያፈተለከውን መረጃ ተከትሎ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆይ ካርኔይ እንደተናገሩት፣ ከዚህ በፊት ኢራን ለአለም አቀፍ ህግ መገዛት እንደማትፈልግና ለዓለም ሰላም አስጊ የሆነ ባህሪ እንዳላት በተደጋጋሚ ስንገልጽ የነበረውን መረጃ የሚያጠናክርልን ነው ብለዋል፡፡
የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካርኔይ፣ የኦባማ አስተዳደር አለምቀአፉን ማህበረሰቡን በስፋት በማስተባበር፣ በኢራን ላይ ከፍተኛ ግፊት የሚፈጥሩበትን እና ከአለም ማህበረሰብ የምትገለልበትን ሁኔታ በመፍጠር አጥብቆ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢራን ላይ ከባድ የሆነ እና አገሪቱን ከኒውክሊየር ፕሮግራም እንድትገታ ሊያደርግ የሚችል ማዕቀብ በፀጥታው ምክር ቤት የተጣለባት መሆኑን ያስታወሱት ካርኔይ፣ ማዕቀቡ በአገሪቱ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ ከባድ መሆኑን ፕሬዚዳንት አህመዲን ነጃድ ሳይቀር ተናግረዋል በማለት ገልፀዋል፡፡
የኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም፤ መካከለኛው ምስራቅን ወደሌላ የጦርነትና የእልቂት አዙሪት እንዳያስገባው የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በጆን ካርኔይ አገላለጽ ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን እርምጃ ተከትሎ፣ በአገሪቱ ላይ ጦርነት አትከፍትም በማለት ቀዳሚ እርምጃዋን በዲፕሎማሲ መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ስጋት ዙሪያ እየተጋጋለ የመጣው የአካባቢው ፖለቲካን በተመለከተ “ፎሬይን ፖሊሲ” መጽሔት ”Trouble over Tehran” በሚል ርዕስ ባቀረበው ሰፊ ዘገባ፤ ላይ አሜሪካና እስራኤል በቀጣይነት የኢራንን ስጋት ፈጣሪነት መና ለማስቀረት የኒውክሊየር ፕሮጀክቷን እስከመደምሰስ ሊያደርሱ የሚችል እርምጃ መውሰድ ጥሩ አማራጭ አለመሆኑን አምስት ምክንያቶችን በማስቀመጥ ለመተንተን ሞክሯል፡፡
በፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ጽሑፉን ያቀረበው አሮን ዴቪድ ሚለር ሲያብራራ፣ አሜሪካና እስራኤል በጋራ የተጠናከረ የአየር ድብደባ ለማድረግ መሞከራቸው ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ የገለፀ ሲሆን፤ በቀዳሚነት ኢራን የጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ ባለቤት ብትሆን ከፍተኛ ስጋት የምትፈጥረው በእስራኤል ላይ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ ይልቅ እስራኤል የኢራንን የኒውክሊየር ፕሮጀክቶች በአየር ድብደባ ለማውደም ከፍተኛ ፍላጐት አላት ይላል፡፡ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሁለቱ አገሮች በኢራን ላይ የአየር ድብደባ ቢፈፅሙ ለጊዜው ኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራምዋን እንድትገታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ተከታታይና መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባ መጨረሻው “ሳሩን” ሊያቃጥለው የሚችል ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ሣሩ መልሶ ማቆጥቆጡ አይቀርም” ይላል ጽሑፉ፡፡
በተጨማሪም የአየር ድብደባው አማራጭ ተደርጐ ቢወስድም፣ በስኬት ላይጠናቀቅ የሚችልበት በርካታ ምክንያቶችም አሉ፤ በተለይም የኢራን የኒውክሊየር ፕሮጀክት ሚስጢራዊነት፣ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ለማወቅ የሚያዳግት መሆኑ ቀዳሚው መሰናክል ነው፡፡
በሌላ በኩል ከአየር ድብደባው በኋላ ሁሉንም ነገር ወደነበረበት ተመልሶ የሚያመጣ ከመሆኑ በተጨማሪ አለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚከፋፍልና እስራኤልና ኢራን አሁን ከሚገኙበት ፍጥጫ ወደ እውነተኛው የጦርነት ግብግብ የሚያስገባ ስለሆኑ ለቀጣይ አመታትም መካከለኛውን ምስራቅ አዲስ በሆነ የጦርነት እሳት ሊያጋይ የሚችል እንደሆነ ፀሐፊው ይገልፃል፡፡
በተከታይነት የቀረበው ምክንያት ደግሞ ኢራን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ሊያግዳት የሚችል አንድም አገር የለም የሚለው ነው - ከራስዋ ከኢራን በስተቀር፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ሰሜን ኮሪያ የመሳሰሉ አገሮች (እስራኤልም ሳትቀር) በአለማችን ላይ ለሰላም ስጋት የሚፈጥረውን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ በጥብቅ ሚስጢር ማበልፀግ በመቻላቸው ነው፡፡ የነዚህን አገሮች ፈለግ ኢራቅ እና ሶሪያም ተከትለውት ነበር፡፡
ኢራን በንጉስ ሻሃ በምትመራበት ወቅት ቁርጠኛ አቋም የነበራት ቢሆንም፣ ጊዜው ያለቀበት የሻህ አገዛዝ ውጥኑን ከዳር ሳያደርስ ሊቀር ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ኢራንን ከኒውክሊየር መሣሪያ ግንባታ ውጪ አድርጐ ማሰብ ልክ በአሻንጉሊት እንደመጫወት ነው፡፡
ለኢራን የመሣሪያው ባለቤት መሆን ትልቅ እይታና የአገሪቱን የብሔራዊ ማንነት ቀመር የሚያስተካክልና በታሪክ ውስጥ ያላትን የታላቅ አገር ስሜትን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ይህንን አላማ በአየር ድብደባ ፀጥ ለማድረግ መሞከር ከሚፈጥረው ሰብዓዊ ዕልቂት ጋር ተያይዞ ኢራን ጠንካራ ፕሮፖጋንዳ በመፍጠር፣ የአረቡ አለም እስራኤልን መጥፎ ኢላማ ውስጥ እንዲያስገባት ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡
በኢራን ላይ ሊቃጣ የሚችለው የአየር ድብደባ አሜሪካን ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም የሚለው ፀሐፊው አሮን፣ በቀውስ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ በይበልጥ አጋርዋን እስራኤልን ለመታደግ ብላ የምታሰማው ወጪ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል የአየር ጥቃት በኢራን ላይ ከተፈፀመ፤ 40 በመቶ የሚሆነው የአለማችን የነዳጅ ፍጆታ መጓጓዣ የሆነው የሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ በኢራኖች ሊዘጋ የሚችል በመሆኑ፣ ለነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር በር የሚከፍት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደጋ ውስጥ ባለው የአሜሪካ ኢኮኖሚ እና በተቀረው ዓለም የሚፈጥረው ቀውስ ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡
ሌላው ስጋት የሚሆነው ኢራን በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ ውስጥ ባልተጠናቀቀው የአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት ለማድረግ መሞከሯ አይቀርም የሚለው ነው፡፡
በዚህ ምክንያት አልቃይዳ አመቺ የመስፋፊያ ቦታዎችን እና ከባቢዎች እንዲፈጠሩለት ምክንያት ይሆናል፡፡
በኢራቅ የሚገኘውን ጦርዋን ሙሉ በሙሉ አውጥታ ለመጨረስ ፕሮግራም የያዘችው አሜሪካ፤ ከኢራን ጋር ግጭት ውስጥ ብትገባ የኢራቅን ቆይታዋን ከማራዘሙም በላይ፣ በአካባቢው ላይ ያላት ጥቅሞች በሙሉ በኢራን ኢላማ ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ነው የሚሆነው፡፡ የኢራን ወታደራዊ ብቃት አሜሪካን ለማጥቃት ያለው አቅም የተወሰነ ቢሆንም፤ ኢራን በአሜሪካ ላይ የምትከፍተው ጦርነት በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ አሜሪካ ባላት ይዞታዎች ላይ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
አሜሪካና እስራኤል በአማራጭነት የሚያብላሉት የአየር ድብደባ ጥቃት ከብዙ ነገሮች ጋር የተሳሰረና የተወሳሰበ መሆኑ ዋናው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡
የትልቁ ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር እስራኤልን ከኢራቅ ስከድሚሳየል ለመከላከል ረጅም ርቀት የተጓዘ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም የባህረ ሰላጤው ጦርነት ከዚሁ ጋርም ተያያዥነት አለው፡፡
በኢራን ላይ የተካሄደው ማዕቀብ አገሪቱ ከአለም ማኅበረሰብ እየተነጠለች እንድትመጣ ሊያደርግ ቢችልም፤ የኢራንን የኒውክሊየር መሣሪያ ለማውደም የሚደረገው ጥቃት ግን ከዚህ በፊት አሜሪካ በኢራቅ ያገኘችውን መልካም ስራዎች መና ሊያስቀር የሚችል ነው፡፡ በተለይም በኢራን ላይ የሚደረገው ጥቃት በአረቡ አለም የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ፀረ - አሜሪካ አቋም በመያዝ ተቃውሞ እንዲያሰሙ በማድረግ በአካባቢው የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሂደት ጥላሸት ሊቀባ እንደሚችል ፀሐፊው ተንትኗል፡፡

 

Read 7255 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:47