Saturday, 15 June 2013 10:17

የህዳሴው ጅምርና የአሮጌው ባህል ድብልቅ ዘመን

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የህዳሴ ግድብ አሳሳቢ ውዝግብንና የ“ቢግ ብራዘር” መናኛ ቅሌትን እኩል ያስተናገድንበት ሳምንት

1 ከስደተኛ ኢትዮጵያውያን የሚላክልንን ዶላር እንፈልገዋለን፤ ግን ስደትን በጭፍን እናወግዛለን።

2 መብት ላለመንካት ለወራት ምርመራ እንደተካሄደ በተነገረ ማግስት, ስለ“ቶርቸር” ሰምተናል።

3 የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጀምሮ መጠናቀቁን ካየን በኋላ፣ በጠላትነት ሲወነጃጀሉ ታዝበናል።

4 “የነቤቲ የቢግ ብራዘር ጨዋታ” ቅሌት ነው ባልንበት አፍ፣ የወንበዴ ዛቻ እያወረድንባት ቀለልን።

“ግራ የሚያጋባና የሚያደናብር የተደበላለቀ ሕይወት!”… በዛሬው ዘመን፣ የአገራችን ልዩ ምልክት ይመስለኛል። “መደናበርና ግራ መጋባት”፣ ጤናማ ምልክት አይደለም። ነገር ግን፣ ለሺ አመታት ከዘለቀው “ያልተበረዘና ያልተከለሰ የኋላቀርነት ታሪክ” ጋር ሲነፃፀር፣ የዛሬው ሳይሻል አይቀርም።

በትንሹም ቢሆን፣ አሮጌውን የኋላቀርነት ባህል የሚበርዙና የሚያለዝቡ፣ ነገሮች ብቅ ብቅ፣ ጎላ ጎላ እያሉ መጥተዋል። እነዚህን አዳዲስ ነገሮች፣ የህዳሴ ምልክቶች ልንላቸው እንችላለን። ጥሬ ቆርጥሞ ማደርና ዋሻ ውስጥ ተገልሎ መኖር እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠርበት ኋላቀር ባህል፣ ለስንት ዘመን ስር ሰዶ እንደቆየ አስቡት። አገራችንን እስርስር አድርጎ ለሺ አመታት አላንቀሳቅስ አላላውስ ብሎ የቆየ አሮጌ ባህል ነው። ድህነትና አቅመቢስነት ነግሶብን የቆየውኮ አለምክንያት አይደለም።

ታዲያ አሮጌው ባህል ሙሉ ለሙሉ ባይወገድ እንኳ፣ ያንን የድህነትና የአቅመቢስነት ባህል ጥቂት በጥቂት የሚሸረሽሩና የሚበርዙ ነገሮች ሲገኙ ጥሩ አይደለም? ጥሩ ነው እንጂ። የህዳሴ ምልክቶች ናቸዋ። ለምሳሴ፣ ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚፍጨረጨሩና ቢዝነስ የሚጀምሩ ወጣቶች ትንሽ ሲበራከቱ ካየን፣ የህዳሴ ምልክት ነው። በእርግጥ፣ ድክ ድክ ለማለት እንኳ ያልቻለ እንጭጭ ጅምር መሆኑ አይካድም። ቢሆንም፣ ድህነትን የሚያወድስና የሚያመልክ አሮጌ ባህልን ሊበርዝና ሊያለዝብ የሚችል ቅንጣት የቢዝነስ ባህል ለፍንጭ ያህል መፈጠሩ አይከፋም።

በራሳቸው ጥረት ሃብት አፍርተው በትልልቅ የኢንቨስትመንት መስኮች ትርፋማ የሚሆኑ ባለሃብቶች በየቦታው ብቅ ብቅ ሲሉ ካየን፣ የህዳሴ ምልክት አይተናል ማለት ነው። “የትም ሄደው፣ የሚያዋጣቸውን ሰርተው” ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚጥሩ ወጣቶችን ካየንም የህዳሴ ምልክት ነው - ወደ ውጭ አገራት የሚሰደዱትም ጭምር። በአለማቀፍ ደረጃ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስና በስፖርት ገንነው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ካጋጠሙን፣ የህዳሴ ምልክት እንዳየን ቁጠሩት - በክለብም ሆነ በብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች የምናየው ጅምር ስኬትም ጭምር። ሳይንስንና ቴክኖሎጂን፣ ብልፅግናንና ብቃትን በጠላትነት የሚያይ ኋላቀር ባህልን የሚበርዝ የስልጣኔ ፍንጭ ሲገኝ፣ እልል ባንል እንኳ ፊታችን ፈካ ማለት አለበት። የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ከተጠናቀቀ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መግለጫ በመንግስት ሚዲያዎች ከተስተናገደም የህዳሴ ምልክት ነው - ሳይወሉ ሳያድሩ አመሻሹ ላይ በጠላትነት መወነጃጀላቸው አልቀረም። አሮጌው የመጠፋፋትና የመጠላለፍ ባህል ገና ምኑም አልተነካማ።

ቢሆንም፣ በአንድ ጥግ በትንሹ ቅንጣት ያህል እንኳ ቢሆን፣ ኋላቀሩን አሮጌ ባህል የሚበረዝ ነገር ሲገኝ፣ “ጥሩ ነው” ማለት ይኖርብናል። የ“ቢግብራዘር” ቅሌትና “የወንበዴ” ዛቻ ሌላው ቀርቶ፣ በ“ቢግብራዘር” ጨዋታ ውስጥ በአህጉር ደረጃ መካፈል የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማየትም “እንደ አቅሚቲ” የህዳሴ ምልክት ነው። ቁምነገር ኖሮት አይደለም። ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ ከጥንታዊው “የሃሜትና የአተካራ ባህል” በመጠኑ እንድንወጣ ያደርገናል። ሳንጋበዝና ሳንጠራ፣ በጎረቤታችንና በስራ ባልደረባችን የግል ሕይወት ውስጥ እየገባን ከምንፈተፍት፣ በሃሜትና በአተካራ የሰዎችን ኑሮ ከምናናጋ፣ የ“ቢግብራዘር” ጨዋታ ላይ ተጥደን መዋልና ማደር እንችላለን። ሕይወታቸውን ከጥዋት እስከ ማታ እየተከታተልን፣ የፈለግነውን ያህል ውሎና አዳራቸውን እያነሳን “በሃሜትና በወሬ” እንድንፈተፍት ፈቅደው ጋብዘውናል። የ“ቢግብራዘር” ትርኪምርኪ ጨዋታ፣ ለኑሯችን የሚፈይደው ነገር ላይኖር ይችላል። ቢሆንም፣ የሃሜትና የአተካራ ሱስ ካለብን፣ ያልደረሰብንና እንድንደርስበት የማይፈልግ ሰው ላይ ሱሳችንን እየተወጣንበት ኑሮውን ከምናናጋ፣ የ“ቢግብራዘር” ውሎና አዳር ላይ ብናወራና ብንነታረክ አይሻልም? በእርግጥ፣ ለሕይወታችን አንዳች ፋይዳ ሳይኖረው፣ የሰዎችን ውሎና አዳር የምንከታተል ከሆነ፣ በዛም አነሰ “የማንወደው” ወይም “የማንስማማበት” ነገር ማየታችን አይቀርም።

ለነገሩ፣ የ“ቢግብራዘር” አዘጋጆች ከመነሻው በግልፅ ተናግረዋል። ጨዋታው… የፆታ ጨዋታንም እንደሚጨምር ገልፀዋል። የፆታ ጨዋታውና ትርኪምርኪው ገንኖ እንደሚወጣ በገልፅ አልነገሩን ይሆናል። ግን፣ እንደዚህ አይነት ዝግጅት ሄዶ ሄዶ መጨረሻው፣ ከዚህ የተለየ አይሆንም። ለምን መሰላችሁ? ሰዎች፣ በሌሎች ጨዋታዎችና ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን የሚገቡት ለምን እንደሆነ እናውቃለን - ልዩ ብቃታቸውን ለማሳየት ነው - እግር ኳስም በሉት ሩጫ፣ በጥያቄና መልስ ውድድርም በሉት በንግድ ተሰጥኦ ውድድር፣ … የተሳታፊዎቹ ዋነኛ አላማ፣ በልዩ ብቃት ብልጫ ማሳየት ነው። ጨዋታውን የምንመለከተውም፣ የሰዎችን ልዩ ብቃት ለማየት ነው። በቢግብራዘር ጨዋታስ? የተሳታፊዎችና የተመልካቾች አላማ ምንድነው? ነገርዬው የብቃት ውድድር አይደለም። ገመናን አጋልጦ የማሳየት ውድድር ነው። ከገመናዎቹ መካከል፣ የፆታ ጨዋታው ገንኖ ቢወጣ ምኑ ይገርማል? አይገርምም። መጥፎነቱ ያፈጠጠ የወሲብ ጨዋታዎችን ቀርፆ በቲቪ ማሰራጨት፣ ወሲብን የሚያረክስ ቅሌት ነው። ግን፣ ያን ያህልም የምንንጫጫበት ምክንያት አልታየኝም። ምንስ ያንጨረጭረናል? ቅሌቱን መሸከም ያለበት የቅሌቱ ባለቤት እንጂ እኛ አይደለን! እርር ድብን ሳንል፣ “ይሄማ ቅሌት ነው” ብለን ብንናገርና መናኛነቱን ብንገልፅ ተገቢ ነው።

ብዙዎች ግን፣ ከዚያ አልፈው “ከነቤቲ መናኛ ቅሌት” የባሰ፣ “የወንበዴ ክፉ ቅሌት” ውስጥ ገብተዋል። “አሰደበችን፣ ወደ አገር መመለስ አለባት፤ መቀጣጫ እናድርጋት” የሚል ዛቻ በየደረሱበት ሲያራግፉ ሰንብተዋል። “የዛቻ ቅሌት”፣ “ከነቤቲ ቅሌት” የሚብሰው ለምን መሰላችሁ? የነቤቲን ቅሌት እንድናይ፣ እንድንሳተፍ ወይም ሰለባ እንድንሆን በጉልበት ጎትቶ የሚያስገድደን ሰው የለም። ቅሌቱንም ሆነ መዘዙን የሚሸከሙት ራሳቸው ናቸው። “የወንበዴ ዛቻ” ግን፣ ከዚህ በእጅጉ ይለያል። በሰዎች ህይወት ላይ እንዳሻው ለማዘዝና ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን የሚቃጣው ሰው፣ የራሱን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሕይወት ያበላሻል።

በአጭሩ፣ ያልደረሱበት ሰዎች ላይ ይደርሳል - ምንም ሳይበድሉት ሊደበድባቸው፣ ሊያሳድዳቸው፣ ሊገድላቸው ይፈልጋል - “እረፍ” ብሎ አደብ የሚያስገዛው ህግ ከሌለ። ለእያንዳንዱ ሰው ነፃነት ቅንጣት ታክል ክብር የለውማ። እንዲህ አይነት ሰዎች በአገራችን ብዙ መሆናቸው አይገርምም። ለሕይወትም ሆነ ለነፃነት ብዙም ክብር የማይሰጥ ባህል ለዘመናት ስር የሰደደበትና በኋላቀርነት ሲዳክር የቆየ አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። አብዛኛው ሰው፣ ለግለሰብ ነፃነት ክብር ከሌለው፣ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ የመንግስት አካላትና ባለስልጣናትም እንዲሁ በአብዛኛው ለግለሰብ ነፃነት ክብር የሚሰጡ ሊሆኑ አይችሉም።

በአንድ በኩል፣ ስልጣን ሳይኖረን እንዳሻን ሰው ላይ እየዛትን፣ በሌላ በኩል ዞር ብለን፣ “ስልጣን የያዘው መንግስት ነፃነትን የሚያከብር እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለን ብንናገር ትርጉም የለውም። ለዚህም ነው፤ “ሰዎች፣ የሚመጥናቸው አይነት መንግስት ይኖራቸዋል” የሚባለው። መብታችንና ነፃነታችንን የሚያከብር መንግስት እንዲኖረን ከፈለግን፣ በቅድሚያ ለእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነት ከፍተኛ ክብር የምንሰጥ መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ያኔ በህዳሴ ጎዳና (በስልጣኔ ባህል) ላይ ትልቁን እርምጃ ተጓዝን ማለት ነው። የህዳሴን ጅምር ከአሮጌው ባህል ጋር እያደባለቅን ከመደናበር የምንላቀቀውም ያኔ ነው። የሙስና ምርመራና የ“ቶርቸር” ምርመራ ከሳምንታት በፊት፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት ላይ፣ በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናትን ከማሰሩ በፊት ለበርካታ ወራት ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል። ምርመራው ለምን ያን ያህል ጊዜ እንደፈጀ ተጠይቀው ኮሚሽነሩ ሲመልሱ፣ የአንድም ሰው መብት መነካት ስለሌለበትና አስተማማኝ ማስረጃ ማሰባሰብ ስለሚያስፈልግ የበርካታ ወራት ምርመራ መካሄዱን ተናግረዋል። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ፣ የህዳሴ ምልክት ነው። በሁሉም የመንግስት ተቋማት ውስጥ በተለይም በፍትህ አካላት ውስጥ በስፋት ልናየው የሚገባ ስልጡን አስተሳሰብ ነው፤ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር።

አሳዛኙ ነገር፣ በርካታ ተጠርጣሪዎች ከታሰሩ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ በርካታ አሳሳቢ አቤቱታዎችን አቅርበዋል - ከህዳሴ ጋር የሚቃረን አሮጌው ባህልን የሚጠቁሙ አቤቱታዎች። ከጠበቃ ጋር ለመገናኘት መቸገራቸውን የተናገሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ድብደባ እንደደረሰባቸውና “ወተር ቦርዲንግ” የሚባለው ስቃይ እንደተፈፀመባቸው የገለፁም አሉ። ሰሞኑን ደግሞ፣ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዷ፣ በውድቅት ሌሊት እራቁቴን ቀዝቃዛ ውሃ እየተደፋብኝ ምርመራ ይደረግብኛል በማለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል። አቤቱታ ሲቀርብ፣ እውነቱን ለማረጋገጥ፣ እውነት ሆኖ ከተገኘም ተጠያቂውን ሰው ለማወቅ ምርመራ መካሄድ እንዳለበት ግልፅ ነው። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝም ይህን የተከተለ ይመስላል። በስልጣናቸው አላግባብ ተጠቅመዋል (ሙስና ፈፅመዋል) ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ሲታሰሩ፣ ተጠርጣሪዎቹን እመረምራለሁ ብሎ ስቃይ የሚፈፅምባቸው ከሆነ ስልጣኑን አላግባብ እየተጠቀመ (ሙስና እየፈፀመ) ወንጀል እየሰራ ነው ማለት ነው። በእርግጥ፣ የፖሊስም ሆነ የፀረሙስና ኮሚሽን ተቋማት፣ “እስረኛን አናሰቃይም” በማለት እንደሚያስተባብሉ አይካድም። ጥሩ፤ ተጠርጣሪዎችን ማሰቃየት እንደ ትክክለኛ የምርመራ ዘዴ እንደማይቆጥሩት መናገራቸውም አንድ ቁም ነገር ነው።

ነገር ግን፣ እንዲህ አይነት አቤቱታዎችን በጠላትነት አይን ማየት የለባቸውም። አንደኛ ነገር፣ የፖሊስ ዋና አላማ፣ ህግ ማስከበርና የሰውን መብት ማስጠበቅ ነው። አቤቱታ ሲቀርብ፣ በቅንነት ተቀብለው ማጣራትና ምርመራ ማካሄድ አለባቸው። ሁለተኛ ነገር፣ ተጠርጣሪን ማሰቃየት እንደ ትልቅ ጥፋት ወይም እንደ ወንጀል የማይቆጥሩ ብዙ ሰዎች ባሉበት አገር፣ የፖሊስ አባላት በሙሉ በጭራሽ ተጠርጣሪን ለማሰቃየት የማይሞክሩ እንከን የለሽ ቅዱሳን ናቸው ብሎ መከራከር የትም አያደርስም። ሞባይል ሲሰረቅበት፣ የሚጠረጥራቸው ሰዎች ሁሉ ታስረው እየተቀጠቀጡ እንዲመረመሩለት የሚፈልግ ሰው የሞላበት ኋላቀር አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ይህንን አስተሳሰብ የሚከተሉ ፖሊሶች ቢኖሩ ምን ይገርማል? ሞልተዋል። ይህንን ለማስተባበል ጊዜ ከማባከን ይልቅ፣ አገሪቱ ከአሮጌው ባህል ተላቅቃ በህዳሴ ጎዳና እንድትራመድ የሚያግዝ ጥረት ላይ ብናተኩር ይሻላል። ለዘመናት የዘለቀውን ኋላቀር ባህል በአንዴ መለወጥ ባይቻልም፣ በየጊዜው የሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ምርመራ በማካሄድ ቀስ በቀስ ስልጡን አስተሳሰብና አሰራር እየተስፋፋ እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል።

Read 3254 times