Print this page
Saturday, 15 June 2013 10:05

በ“ፍትህ ሳምንት” ስለፍትህ ምን ተባለ?

Written by 
Rate this item
(8 votes)

                       ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘውን “የፍትህ ሳምንት” ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የህግ ባለሙያዎችን የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህ አካላትን ሃላፊዎች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አነጋግረናል - በፍትህ ዙሪያ፡፡ “የህግ የበላይነት ለመልካም አስተዳደር መስፈን በህዝቦች ተሳትፎ” በሚል መሪ ቃል የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች፣የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን ባዘጋጁት “የፍትህ ሳምንት” ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ ለመሆኑ የፍትህ ሳምንት መከበር ፋይዳው ምንድነው? በአገሪቱ ላይ ያለው የፍትህ ሁኔታስ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ያሰባሰበቻቸው አስተያየቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

“ውሳኔ ለማግኘት ሁለት አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል”
የወንጀል ጉዳዮች ቶሎ አይወሰኑም፡፡ የፍትህ ስርአቱ ጥሩ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ችሎቶች ላይ ከባድ የሚባሉ ችግሮች አሉ፡፡ 16ኛ የወንጀል ችሎት፣ 3ኛ የወንጀል ችሎትና ጠቅላይ ፍ/ቤት የፍትሃብሔር ችሎት አንድ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ደግሞ 7ኛ እና 11ኛ ችሎት አብዛኛውን ጊዜ አዳዲስ ሰዎች ስለሚመጡ ጉዳያችን ቶሎ አያልቅም፣ ውሳኔ ለማግኘት ሁለት አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ አቃቤ ህጐች ደግሞ ችግራቸው ክሶችን ቶሎ አይከፍቱም፡፡
አቶ ስሜነህ ታደሰ
(ጠበቃ)

“ፍትህ የሚከበር ሳይሆን የሚሰፍን ጉዳይ ነው”
የፍትህ ሳምንት መከበር ሳይሆን የሚያስፈልገው መበየን ነው ያለበት፡፡ ፍትህ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ ፍትህ የሚከበር ሳይሆን የሚሰፍን፣ የሚተገበር ጉዳይ ነው፡፡ ህጋዊነት ማስፈን ትንሽ ስራ ቢሆንም ለአገራችን ግን ህጉን አክብሮ መስራት በራሱ በቂ ነበር፡፡ ፍትህ የአንድ አገር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ማርኬሌሊ የተባለ የጣሊያን የፖለቲካ ፈላስፋ ሲናገር፤ “አንዳንዴ ሰዎች የምትናገረውን እንጂ የምትሠራውን አያዩም” ይላል፡፡ ስለ ፍትህ ስትናገሪ ስራሽን ያላዩ በንግግር እንዲታለሉ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የለውም፡፡ በእኔ ደንበኞች ላይ እየሆነ ያለው ነገር ይሄ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች ቶርች ተደርገው (ተገርፈውና ተደብድበው) በኢቴቪ አለአግባብ እንዲናገሩ እየተደረገና ከዚያም በዚህ ጉዳይ ላይ የፍትሀብሔር ክስ ለመመስረት ስንጠይቅ ፍ/ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አልቀበልም ብሏል፡፡ እንግዲህ “ፍ/ቤት ለሁሉም እኩል ነው” ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ግን ፍ/ቤት ራሱ ህግን ሳያከብር የፍትህ ሳምንት ማክበር ምን ይጠቅማል? በቶርች ማስረጃ ለማውጣት ሰው እየተሰቃየ ነው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁን ተቃውመን ለመንግስት አጣሪ ጉባኤ ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፡፡ የትላንት ባለስልጣናት ዛሬ ታስረው መብታችን ተጣሰ እያሉ በመጮህ ላይ ናቸው፡፡ ይሄን ሁሉ ስናይ በኢትዮጵያ ያለው ፍትህ የሚያስታውሰን የጣሊያኑን ፈላስፋ አባባል ብቻ ነው፡፡
አቶ ተማም አባቡልጎ
(ጠበቃ)

“ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ከያዘ በኋላ ማስረጃ መፈለግ የለበትም”
ፍ/ቤቶች ኮምፒዩተራይዝድ መሆናቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ በየቦታው ባሉ ህንፃዎች ላይ ፍርድ ቤቶች መከፈታቸው አንድ ለውጥ ነው፡፡ ፖሊስ ከአቃቤ ህግ ጋር መስራቱ፣ ክሱን ለመመስረት በአንድ ቦታ ስለሆኑ ጊዜን ያቆጥባል፤ በፊት የተለያየ ቦታ ስለሆኑ ክስ ለመመስረት ብዙ ጊዜ ይፈጅ ነበር፡፡ የፖሊስ ማስረጃ ፍለጋ ኋላቀር መሆን ግን አሁንም መስተካከል ይቀረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ተከሳሽን አስሮ “ምርመራ ይቀረናል” እያለ በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩትን ያጉላላል፡፡ ታሳሪና ጠበቃ በዋናነት መገናኘት ያለባቸው በምርመራ ጊዜ ቢሆንም ፖሊስ ግን ምርመራ ሳልጨርስ ተከሳሽና ጠበቃን አላገናኝም ይላል፡፡ እንደውም ተከሳሽ ቃሉን ሊሰጥ የሚገባው ጠበቃው ባለበት ሁኔታ መሆኑን ህግም ይደግፋል፡፡ ሌላው ቢቀር ተከሳሽ ቃሉን ያለመስጠት መብት እንዳለው እየታወቀ፣ ከጠበቃው ጋር እንዳይገናኝ መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ፖሊሶች ጋ ያለው የተሳሳተ አመለካከት፣ ጠበቆችን ፍትህ የሚያዛቡ አድርጐ ማየት ነው፡፡ አንድ ተከሳሽ በምርመራው ጊዜ ተገቢውን እርዳታ ካላገኘ፣ መደበኛ ክስ ሲከፈት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩ ሰዎች ቶሎ ፍ/ቤት መቅረብ አለባቸው ፤ ፖሊስም ቢሆን መጀመሪያ ማስረጃ መያዝ አለበት እንጂ ተጠርጣሪዎችን ከያዘ በኋላ ማስረጃ መፈለግ የለበትም፡፡
አቶ ደበበ ኃ/ገብርኤል
(የህግ ባለሙያ)

“የፍትህ ስርዓቱ ብዙ ይቀረዋል”
የፍትህ ሳምንት መከበሩ ምን ይጠቅማል? ምናልባት የሚመለከታቸው ተገናኝተው ችግሮችን ለመቅረፍ ከሆነ ያስኬዳል፡፡ ዳኞችና አቃቤ ህጐች አብረው ሊበሉና ሊጠጡ ከሆነ ግን ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ነገር አለው፤ በሌላ በኩል ችግር አለው፡፡ የአገራችን የፍትህ ስርአት ብዙ ይቀረዋል - ከአወቃቀር፣ ከአደረጃጀት፣ ከብቃት፣ ከሰው ሃይል ጀምሮ … የህግ እውቀት ማነስ ችግሮች ሁሉ አሉ፡፡ የፌደራል ፍ/ቤቶች በቤኒሻንጉል፣ በሱማሌ፣ በአፋር፣ በደቡብ እንዲቋቋሙ በአዋጅ የወጣው በ1995 ዓ.ም ነው፤ እስካሁን ግን አልተቋቋመም፡፡ ይሄ የሚያሳየው ተደራሽ አለመሆናቸውን ነው፡፡ የፌደራል አቃቤ ህጐችም በመላው ክልል ነው መቋቋም ያለባቸው፡፡ አሁን ያለው አዲስ አበባ እና ድሬደዋ ላይ ብቻ ነው፡፡
ዘርአይ ወ/ሰንበት
(የቀድሞ አቃቤ ህግ)

“የፍትህ ሳምንት ማክበር ማሾፍ ነው”
ፍትህ በሌለበት አገር የፍትህ ሳምንት ማክበር መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡ ፍትህ ያጣ ህዝብ እያለቀሰ፣ ፖለቲከኛና ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ ዜጐች እየታሰሩ፣ ሰዎች ከሃይማኖታቸው ጋር በተያያዘ “ሽብርተኛ” ተብለው እስር ቤት እየገቡ፣ ከዛም አልፎ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተነፍጐ ጋዜጠኞች በሚታሰሩባትና አሁንም ድረስ “አምላክ ይፈርዳል” በሚባልባት አገር የፍትህ ሳምንት ማክበር ማሾፍ ነው፡፡ ፍትህ መታየት ያለበት በተግባር ነው፡፡ ባለፈው አመት ኪሊማንጀሮ የተባለ የጥናት ተቋም ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ከማይጣልባቸው ተቋማት አንዱ የፍትህ አካላት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ለምሳሌ አንዷለም አራጌን በእስር ቤት መጠየቅ አይቻልም፡፡ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ኢቴቪ ተጠርጣሪዎችን “ሽብርተኛ” እያለ የሚፈርድበት ጊዜ አለ፡፡ በማረሚያ ቤት ደግሞ ድብደባ፣ ማንገላታት፣ ጨለማ ቤት ማሰር--- አለ፡፡ ታዲያ እዚህች አገር ላይ ነው የፍትህ ሳምንት የሚከበረው? ፍትህ የሚባለውን የምናውቀው በስም ነው፡፡
አቶ ዳንኤል ተፈራ
(የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ)

“እዚህ አገር ይግባኝ የሚባለው ለእግዚአብሔር ነው”
የፍትህ ስርአቱ የተጠናከረ ነው፤ የኢህአዴግን ፖለቲካ እንዲያገለግል የተቀመጠ ነው፡፡ እንዲህ የምንለው የፍትህ ስርአቱን ደጋግመን በሞከርነው ነገር ስላየነው እንጂ ኢህአዴግን ስለምንጠላው አይደለም፡፡ ውሳኔዎቹ ፖለቲካዊ ናቸው፡፡ በቅርቡ እኛ ላይ የደረሰ የፍትህ መስተጓጎል አለ፡፡ የወረዳ ፓርቲ ሃላፊ የሆነ ግለሰብ የአባትህን መሬት አታርስም በሚል ፍ/ቤት ተከሶና ተፈርዶበት ሆሳእና ታስሮ ነው ያለው፡፡ ማስረጃ የማይሰማ ፍ/ቤት ባለበት ሁኔታ የፍትህ ሳምንት ማክበር ጨዋታ ነው፡
እኛ ራሳችን የአገራዊ ምርጫ ጉዳይ ህገወጥ ነው ብለን የተቃጠለውንና መፀዳጃ ቤት የተወረወረውን ድምፅ የተሰጠበትን ወረቀት ሰብስበን ስንሄድ “በእለቱ ነው ክስ መመስረት የነበረባችሁ” ተባልን፡፡ በእለቱ እንዳንሄድ እሁድ ነበር፤ እነሱ ግን እሁድም እንሠራ ነበር አሉ፡፡ ይሄንን ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ይሄ የፍትህ ሳምንት ሽፋን ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እዚህ አገር ይግባኝ የሚባለው ለእግዚአብሔር ነው፡፡
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
(የመድረክ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር እና
የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ)

“መንግስት ችግሩን አሳምሮ ያውቃል”
በአፍሪካ ደረጃ በተደረገ ጥናት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እምነት የማይጣልባቸው ተቋማት ከተባሉት አንዱ የፍትህ ስርአት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዜጐች መፍትሔ እያጡ ነው፡፡ ፍትህ ማጣታቸው ገዝፎ እየታየ የመጣው ከአፄው ጀምሮ ነው፡፡ የፍትህ ሳምንት መከበሩም ከፕሮፖጋንዳ ያለፈ ነገር አለው ማለት አይቻልም፡፡ መንግስት ችግሩን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ለፍትህ መጥፋቱ ዋናው እኮ የስልጣን ክፍፍል አለመኖሩ ነው፡፡ የአስፈፃሚው አካል እንደልቡ ተንቀሳቅሶ መስራት ካልቻለ ፍትህ ይዛባል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና (የመድረክ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)
“ፍትህን ለማስፈን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል”
ይቅርታ ለጠየቁ ታራሚዎች ሁሉ ይቅርታ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ በሀገራችን ህግ እንደ መብት አልተቀመጠም፡፡ ይቅርታ ሰጪው አካል በተለያዩ ምክንያቶች ይቅርታ ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ ለሚያስባቸው ወገኖች ይቅርታ ይፈቅዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ባለው አግባብ ይቅርታቸውን አቅርበው እንዲታይላቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጠይቀው ካልተፈቀደላቸው ደግሞ ከስድስት ወር በኋላ መልሰው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ ይህንን ሚኒስትሩ ሲመጡ የሚወስኑት ይሆናል፡፡
በአገሪቱ ፍትህን ለማስፈን በተወሰዱ እርምጃዎች በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የፍትህ አካሉን የባለሙያዎች ህገመንግስታዊ አመለካከቶች ለማረጋገጥና አቅማቸውን ለማጐልበት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የፍትህ ሳምንት የሚከበረው በቀጣይ ፍትህ በማስፈን ረገድ ምን ሊከናወን እንደሚችል ለማየት እንዲሁም እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሆን ህዝቡ የፍትህ ስርአት ባለቤት በመሆኑ የአገራችንን የፍትህ ሁኔታ ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡
አቶ ልዑል ካህሳይ
(የፍትህ ሚኒስቴር፤ ሚኒስትር ዴኤታ)

“ህብረተሰቡ ካላገዘን ውጤታማ አንሆንም”
ሙስና መኖሩ በአደባባይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ይሄንን ለእናንተ የሚናገሩ ሰዎች ለእኛም መጥተው መንገር አለባቸው፤ እንጂ በአደባባይ “ፍ/ቤት ውስጥ ሙስና ይሰራል” ብሎ ብቻ ማውራት አይጠቅምም፤ በእርግጥ ሙስና የሚሰሩ የሉም አንልም፡፡ ከዳኝነት አካላት ብቻ ሳይሆን ከታችም ያሉ ሰዎች ሊፈፀሙት ይችላል፡፡ በዳኛም ስም የሚፈፀም ይሆናል፤ የተወሰኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
“ለዳኛ ብር እንሰጣለን” የሚሉ በርካታ ስራ ፈት ፍ/ቤት የሚውሉ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን፤ ግን ህብረተሰቡ ካላገዘን ውጤታማ አንሆንም፡፡ በዚህ ምክንያት ተቋሙ ተአማኝነት ያጣል፡፡ በጥቂት ሰዎች አላስፈላጊ ስራ ተቋሙ መወሰን የለበትም፡፡ በሙስና ብቻ ሳይሆን በሌላም ሊሆን ይችላል፡፡ ዳኞች ቢሆኑም ያደረጉት ከሆነ ውሳኔ እንሰጣለን፡፡ መረጃ በሌለበት ሁኔታ ግን ዳኝነት በነፃነት የሚታይ ነገር በመሆኑ ያለአግባብ መጠየቅ አንችልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመገናኘት ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል፡፡
የተከበሩ አቶ ተገኔ ጌታነህ
(የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት)

“በታራሚዎች አያያዝ በርካታ መሻሻሎች አሉ”
የታራሚዎችን መብት ለማስከበር ከህገመንግስቱ ጀምሮ ለጠባቂዎቻችን ስልጠና እንሰጣለን፡፡ በእኛ ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊ መብት ጋር ተነጋግረን ስልጠናውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅት በአንድ ወቅት ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ በዚያ መነሻነት በዝርዝር እቅድ አውጥተን ግምገማ አድርገናል፡፡ ከእኛ ባለፈ ደግሞ ፓርላማ በየ6 ወሩ ይገመግመናል፡፡ አቅም በፈቀደ መንገድ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከህጉ ውጭ በታራሚዎች ሰብአዊ መብት ላይ ችግር የሚፈጥር ካለ አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን፤ የወሰድንባቸውም አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ አድርገን በግለሰብ ደረጃ የሚፈፀሙ ጥፋቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፤ በርካታ ታራሚዎች ስላሉ ችግር መከሰቱ አይቀርም ፤ነገር ግን በርካታ መሻሻሎች አሉ፡፡
አምስቱ ተቋማት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን መነሻ በማድረግ የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህ እቅዶችም እያንዳንዱ ተቋም ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ወደ እራሱ እየወሰደ የሚሠራበት እና በጋራ የሚሰሩ ስራዎችም ለማከናወን በአጠቃላይ በፍትህ ስርአት ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች አይቶ በመነጋገር፤ የአሰራር ክፍተቶች ካሉ በመመልከትና በመቅረፍ ትኩረት ሰጥተን እየሰራናቸው ነው፡፡ ማረሚያ ቤትን ብንወስድ ከፍ/ቤት ጋር የሚያገናኙ ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ዝዋይ የታሰረ ታራሚ በቀጠሮ ጊዜ ወደዚህ በመምጣት ከሚንገላታ በፕላዛ ቲቪ በቀጥታ የፍ/ቤቱን ጉዳይ እንዲከታተል የሚደረግበት አሠራር ዘርግተናል፡፡ የአመክሮና የይቅርታ አሠራር ሁኔታንም በተመለከተ ታራሚ እንዳይጉላላ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እነዚህን ሁኔታዎች እየሰራን ሲሆን ጥምረታችን ደግሞ ይሄንን ለማከናወን ያግዛል፡፡
የፍትህ ሳምንት መከበሩ ጥቅም አለው፡፡ ስራችን ከህዝብ ውጭ አይደለም፤ እኛ ጥሩ ሰራን ብንልም በህዝብ ዘንድ ደግም እርካታን ያልፈጠሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ከህዝብ ጋር ተገናኝተን ለመወያየት እድል ይሰጠናል፡፡ ሁለተኛ የተቋማችንን ገጽታ ከመገንባት አንፃርም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
አቶ አብዱ ሙመድ
(የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳሬክተር)

“ህገመንግስቱን በማክበር እየሰራን ነው”
በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ፍ/ቤት ቀርበው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፀመብን ሊሉ ይችላሉ፣ ግን በማስረጃ አላረጋገጡም፡፡ የምርመራ ስርአታችን ህግን የተከተለ ነው፤ በተቻለ መጠን እኛ ጋ የምንመረምራቸው ወንጀሎች በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡትን ነው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች የተለያዩ ግብአቶች ይኖራቸዋል፡፡ ተጠርጥረው የሚመጡት ደግሞ ንፁህ ሊሆን ይችላል ወይም ሊወሰንበት ይችላል፡፡ እኛ ጋ ደግሞ ይህንን ሁለቱንም በማየት ነው ምርመራ የምናደርገው፡፡ በምርመራችን ድርጊቱ ለመፈፀሙ በቂ ማስረጃ ካለን፣ ፈፃሚው ማነው? የመፈፀም ደረጃው ምንድነው? የሚለውን ማግኘት፣ መፈፀሙ ጥርጣሬ ካለው ማረጋገጥ፣ የፈፀመው ሌላ አካል ከሆነ እኛ ጋር በተጠርጣሪነት ያለውን ግለሰብ ነፃነት አረጋግጠን እንሸኛለን፡፡
ከዚያ አኳያ ሳይንሳዊ ምርመራዎች የምርመራ ህጐች የሚፈቅዳቸው አርትንም ጭምር ሁሉ እንጠቀማለን፤ መርማሪዎቻችን የካበተ ልምድ አሏቸው፡፡ በሽብር በተደራጁ፣ በሙስና ወንጀሎች፣ በፋይናንስ ወንጀሎች ጥሩ ውጤቶች አሏቸው፡፡ ከፍተኞች ለጀማሪዎች እነዚህን ልምዶቻቸውን የሚያስተላልፉበት እና አዳዲሶችም የተሻለ ነገር ለማድረግ የሚጥሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሂደት በባህሪያቸው ብልጣ ብልጥ የሆኑና የማጭበርበር ባህሪ ያላቸው ፍ/ቤትን ለማሳሳት ይፈልጋሉ፡፡ የምርመራ መነሻ ላይ የመጀመሪያ ጥያቄ የዋስትና መብት፣ የዘመድ፣ የጠበቃ፣ የሃይማኖት፣ የመጠየቅ መብት ተከለከልን ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር በምርመራ ሂደት እንዲህ ተደረግን፣ ሰብአዊ መብታችን ተጣሰ የሚሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እኛ ግን ምርመራዎቻችንን የምናካሂደው ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ተጠቅመን ነው፡፡
በየደረጃው ያለን ሃላፊዎች የሚደረጉትን ምርመራዎች የምናይበት ሁኔታ አለ፡፡ ፍ/ቤት ባለው በማንኛውም ጥርጣሬ ላይ እውነቱን ማረጋገጥ ይችላል፡፡ የሰብአዊ መብት ቅሬታም ሲቀርብለት እኛን መጥቶ ማየት ይችላል፤ እኛም ህገመንግስቱን በማክበር እየሰራን ነው፡፡ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸው ነገሮች እንዳይፈፀሙ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ በትላልቅ ወንጀሎች አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አይነት ነገር ቢያነሱም የምርመራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ማረሚያ ቤት ሲሄዱ የምርመራውን ሂደት ሲኮንኑ አይታዩም፡፡ ስለዚህ እንደ ህዝብ ሰብአዊ መብቱ ተጥሷል አልተጣሰም የሚለውን መገመት ይቻላል፡፡ ይሄ ዘዴ ክሱ ሲመሰረት መጀመሪያ ለማምለጥ የሚያደርጉት ቀላሉ ዘዴያቸው ነው፡፡
የፍትህ ሳምንት ዋና አላማው፣ የፍትህ አገልግሎት የምንሰጥ ተቋማት እና በቀጥታ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ህብረተሰብ እና ባለድርሻ አካላትን በፍትህ አሰጣጥ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንወያይ ማድረግ እና ጥሩ አፈፃፀሞቻችንን ማጉላት፣ ደካማ አፈፃፀሞቻችንን ማሻሻል የምንችልበትን ውይይት እና ምክክር የምናደርግበት መድረክ ነው፡፡
ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ (የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ)

 

Read 5720 times
Administrator

Latest from Administrator