Saturday, 01 June 2013 13:28

“አባዬ በሞባይል መታኝ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰውየው መኪና እያሽከረከረ ነበር፡፡ አራትና አምስት ዓመት የሚሆነው ልጁን ኋላ መቀመጫ ላይ በመናው ቀበቶው አስሮ አስቀምጦታል፡፡ እናላችሁ ድንገት አንድ የትራፊክ ፖሊስ ያስቆመዋል፡፡ “ጌታዬ መንጃ ፍቃድ…” (ስሙኝማ…የሆነ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ…በትራፊከ ፖሊስና በአሽከርካሪ መካከል ያለው መንጃ ፈቃድ የመጠየቅና ላለመስጠት የሚደረገው ክርክር ሶርያ ላይ የመሣሪያ ማዕቀብ ይጣል/አይጣል ከሚለው እሰጥ አገባ እኩል ጊዜ የሚወስደው ለምንድነው? የትራፊክ ፖሊስ ከአንድ አሽከርካሪ ጋር ሲከራከር አንዳንድ ጊዜ ሀይ ባይ እየጠፋ ትራፊኩ እንዴት እንደሚጨናነቅ ልብ ብላችሁልኛል!) “ምን አደረግሁ?” ሲል ሰውየው ይጠይቃል፡፡

የትራፊክ ፖሊሱም፣ “ሞባይል እያወሩ ሲሄዱ ነበር” ይለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ጸጉሩ ሊለወጥ ወደሚችልባቸው ቀለሞች ሁሉ ተለውጦ “እንትን ያላለበት ዳገት…” የሌለው ባለመኪናው “እኔ በጭራሽ በሞባይል አላወራሁም!” ብሎ ድርቅ ይላል፡፡ ድርቅ ማለት ብቻ ሳይሆን እንደውም “እንዴት እኔን የሚያክል ሰው እንዲህ ትደፍረኛለህ!” አይነት ቃና ነበረው አሉ፡፡ እናላችሁ…ትራፊክ ፖሊሱም “በዓይኔ በብረቱ አይቼዎት!” አይነት ክርክር ያደርጋል፡፡ ሰውየው ግን ጭራሽ የ‘ምኒታ ተቆጢታ’ አይነት ሆነ፡፡ “አይደለም በሞባይል ላወራ ሞባይሌንም ከቤት ይዤ አልወጣሁም…” ይላል፡፡ ይሄኔ ትራፊክ ፖሊሱ ግራ ይገባውና ሊለቀው ወስኖ “እሺ በሉ…” ምናምን ነገር ይላል፡፡ ይሄን ሁሉ ጊዜ ኋላ መቀመጫ ላይ የተቀመጠው ልጅ እየተወራጨ እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡

አባቱ ዝም በል ቢለው ጭራሽ ባሰበት፡፡ ይሄኔ ትራፊክ ፖሊሱ እንደ ማባበል “ማሙሽ ምን ሆነህ ነው?” ይለዋል፡፡ ትንሹ ልጅ ምን ቢል ጥሩ ነው…“አባዬ በሞባይል መታኝ!” ለካስ ሰውየው ሞባይሉን ከትራፊክ ፖሊሱ ለመደበቅ ወደኋላ ሲወረውር ልጁን ቀውሮታል! እናላችሁ ዘንድሮ ነገርዬው “አባዬ በሞባይል መታኝ!” እየሆነ ነው፡፡ እናላችሁ…ምስጢር እየወሰዱ በመዘክዘክ ብዙ ወዳጅነቶች እየፈረሱ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…በደህናው ጊዜ የሆድ የሆዳችሁን “እሱ ማለት እኔ ማለት ነኝ…” ብላችሁ ለሆነ ወዳጃችሁ ያወራችሁት ነገር ሁሉ…አለ አይደል… ለእናንተ ይወራላችኋል፡፡ እናማ…እንደ ‘አገር ጉዳይ’ በከፍተኛ ምስጢርነት ያወራችሁት ነገር…በሦስተኛው ቀን ዞሮ፣ ለእናንተው ይነገራችኋል፡፡

“ስማ ያቺ አጅሬ የሆነ ነገር ሠራችህ የሚሉት እውነት ነው?” “የት ሰማህ?” “ሰማኋ! የሆነ ሰው ምስጢር ብሎ የነገረኝ ነው።” እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ምን የሚባል ነገር አለ መሰላችሁ…የሆነ ወሬ እንዲናፈስ ከፈለጋችሁ “ከፍተኛ ምስጢር ነው…” ብላችሁ አውሩ የሚሉት ነገር አለ፡፡ ደግሞ ዘንድሮ እንደዛ ‘የሚሸቱ’ መአት ነገሮች እየሰማንና እያነበብን ነው፡፡ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ ‘ምስጢር’ ካወራን ይቺን ስሙኝማ፡፡ የእራት ግብዣ ላይ ነው አሉ፡፡ ተጋባዦቹ ከወንዶችና ከሴቶች ይበልጥ ታማኝ ማን ነው በሚል ርዕስ ዙሪያ ነበር እየተከራከሩ የነበሩት፡፡ አንድ ሰውዬ በንቀት “አንዲቷም ሴት ምስጢር መጠበቅ አትችልም!” ሲል ተናገረ፡፡ ይሄኔ አንዲት ቆንጅዬ ሴት እንዲህ አለች፡፡ “ባልከው አልስማማም፡፡

ለምሳሌ እኔ ሃያ አንድ ዓመት ከሞላኝ ጀምሮ ዕድሜዬን በምስጢር ነው የያዝኩት፡፡” ሰውየውም “ምን አለ በዪኝ አንድ ቀን ትዘረግፊዋለሽ…” አላት፡፡ እሷ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው… “በጭራሽ አልዘረግፈውም፡፡ አንዲት ሴት ለሀያ ሦስት ዓመት ምስጢር መያዝ ከቻለች ዕድሜ ልክ መያዝ ትችላለች ማለት ነው፡፡” አሪፍ አይደል.. ለክፉም ለደጉም ሃያ አንድ እና ሀያ ሦስት ይደመርልንና በ‘ሰርቲፋይድ’ የሂሳብ ባለሙያ ተረጋግጦ ይምጣልንማ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አሁን፣ አሁን ‘ዜና’ ተብለው የሚወጡ ነገሮችን (በተለይ ‘ቦተሊካ—ተች’ የሆኑትን) ለመቀበል በጣም እየቸገረን ነው፡፡

እነ ‘ፌስቡክ’ የጥቅማቸውን ያሀል አንዳንዴ እኛንም ‘ጦጣ’ ለማድረግ የተመቹ እየሆኑ ነው፡፡ እናላችሁ…በሆነ ወገን አካባቢ ትንሽ “አደባለቀውና እርጥቡን ከደረቅ…” ቢጤ ለመፍጠር እንደ ሰበር ዜና ‘የሚረጩ’ ነገሮች በአጠቃላይ ‘ሶሻል ሚዲያው’ ላይ ብቻ ሳይሆን ‘ሜይንስትሪም ሚዲያ’ የሚሏቸው ላይ ያለንን እምነት እየሸረሸረብን ነው። እናላችሁ…አንዳንድ ዜናዎችን ሰምተን ወይም አንብበን “ይቺ ነገር ከእነእንትና የመጣች መሆን አለባት…” ለማለት እየተገደድን ነው፡፡ ልክ ነዋ…ዘንድሮ ጠርጥረን ከሚያመልጡን ነገሮች ይልቅ ሳንጠረጥር አደናቅፈው የሚጥሉን በዝተዋል፡፡ አባቶቻችን “ሽንብራውን ዘርተን እሸቱን ስንበላ አወይ የእኛ ነገር ሁልጊዜ ጥርጠራ” ያሉት ነገር ዘንድሮ ነው የምር እውነት የሆነው፡፡ እናላችሁ…ትንሽዬዋን ምስጢር እንኳን መነጋገር የማንችልበት ደረጃ ላይ መድረሳችን የምር አሳዛኝ ነው፡፡

ምስጢር የሚያካፍሉት ወዳጅን ያህል ‘ናቹራል ሬመዲ’ አልነበረማ! ‘ምስጢር’ ብላችሁ የተነጋገራችሁት ‘ምስጢር’ እየተባለ እንደ ቀለበት መንገድ ህዝቡ መሀል ሲሽከረከር አሪፍ አይደለም፡፡ ይቺን የ‘ምስጢር አጠባባቅ’ ስሙልኝማ… “ለእሷ እንዳትነግራት ያልኩህን ምስጢር እንደነገርካት ነገረችኝ፡፡” “እንደነገርኳት እንዳትነግርህ ነግሬያት ነበር፡፡” “እንግዲያው እሷ እንደነገረችኝ ለአንተ መንገሬን እንዳትነግራት፡፡” እና…እንዲህ ሆኖላችኋል፡፡ ይቺን ከሆነ መጽሔት ቢጤ ነገር ያገኘኋትን ስሙኝማ…አቶ ባል ለጓደኛው እንዲህ ይለዋል፡፡ “ጎረቤቶቻችን የምንጋገረውን እንዳይሰሙ ሚስቴ የሬድዮኑን ድምጽ በሰፊው ትለቀዋለች፡፡” ጓደኝዬውም “እና እንዳሰበችው ሆነላት?” ሲል ይጠይቃል፡፡ “እንዳሰበችውም፣ እንዳላሰበችውም ሆነ፡፡”

“ምን ማለት ነው?” “ጎረቤቶቻችን እኛ የምንለውን አይሰሙም። ችግሩ እነሱ የሚሉትን እሷም እንዳትሰማ ድምጹ ከለከላት፡፡” ማርክ ትዌይን የሚባለው አሜሪካዊ ደራሲ እንዲህ ብሏል አሉ፡፡ “ሁሉም ሰው እንደ ጨረቃ ነው፡፡ ለማንም የማያሳየው ጨለማ ወገን አለው፡፡” ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘የስኬታማ ትዳር ምስጢሮች’ ተብለው የሆነ ድረ ገጽ ላይ የለጠፏትን የሆነ ባል የተናገረውን አንብቡልኝማ! እኔና ሚስቴ መልካም ትዳራችንን ለማቆየት የራሳችን ምስጢሮች አሉን፡፡

1) በሳምንት ሁለት ጊዜ ጥሩ ሬስቱራንት ሄደን ጥሩ ምግብ እንበላለን፣ ጥሩ ወይን እንጠጣለን ከሰው ጋርም እንቀላቀላለን። እናም… እሷ ማክሰኞ ቀን ትሄዳለች እኔ ደግሞ ዓርብ ቀን እሄዳለሁ፡፡

2) ደግሞም በተለያዩ አልጋዎቸ እንተኛለን— እሷ ፍሎሪዳ ትተኛለች፣ እኔ ኒው ዮርክ እተኛለሁ፡፡

3) እኔ ሚስቴን ሁሉም ቦታ እወስዳታለሁ፣ እሷ ግን ከሁሉም ቦታ እኔ ሳላስፈልጋት በራሷ ተመልሳ መምጣት ትችላለች፡

4) ሚስቴን “ለትዳራችን ዓመታዊ መታሰቢያ የት መሄድ ትፈልጊያለሽ?” ብዬ ጠየቅኋት፡፡ እሷም “ለረጅም ጊዜ አይቼው የማላወቀው ቦታ” አለችኝ። እኔም “ማብሰያ ቤት ቢሆን ምን ይመስለሻል?” አልኳት፡፡

5) ሁልጊዜ እጅ ለእጅ እንያያዛለን፡፡ እጇን ከለቀቅኋት የሆነ ነገር ትገዛለች፡፡ እናላችሁ…የግልና እዛው በእዛው መቅረት ያለበት ምስጢር ሁሉ እየተበተነ አይደለም ሌላውን ራሳችንን መጠርጠር ልንጀምር ምንም አልቀረን። ሰውየው ምን አለ አሉ መሳላችሁ…“ሁሉም ሰው ሲያወራው ምስጢር መሆኑን አወቅሁ፡፡” “አባዬ በሞባይል መታኝ!” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5013 times