Saturday, 01 June 2013 12:56

በገንፎ የተሠራ ጥርስ አያስቅ፣ አያስፍቅ!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለአንድ በዕብደቱ ስለሚታወቅ የኢራን ሰው የሚተረት አንድ ወግ አለ፡፡ ይህ ዕብድ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ባሉ አደባባዮች ዙሪያ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ አንድ አደባባይ አጠገብ መጥቶ ዙሪያውን መዞር ከጀመረ መቆሚያ የለውም፡፡ መሽቶ ጨልሞበት ወደ ማደሪያው እስከሚሄድ ድረስ መዞሩን ይቀጥላል፡፡ “ወዴት ትሄዳለህ?” ይሉታል ሰዎች ጠዋት፡፡ “ወደ አደባባዬ ነዋ!” ይላል፡፡ “አደባባዩን ማን ሰጠህና?” “እኔ የተፈጠርኩት ለአደባባይ መሆኑን አታውቁም? አደባባይስ የተፈጠረው ለእኔ መሆኑን አታውቁም?” እያለ እየዘፈነ ይሄዳል፡፡ ዕብዱ፤ ዋንኛ ጠባዩ ሰው አለመንካቱ ነው፡፡ “ሰውን ትሰድበዋለህ እንጂ አትመታውም” ይላል፡፡

“ለምን?” ይሉታል ሰዎች፤ ሊያጫውቱት፡፡ “የሰው ልጅ ሲደበደብ ይደድባል፡፡ ሲሰደብ ግን ብልጥ ይሆናል” “እንዴት?” “ለመልስ የሚሆን ስድብ ሲያዘጋጅ ማሰብ ይጀምራል፡፡ የስድብ ትምህርት ቤት ስለሌለ፤ ኦርጅናሌው የስድቡ ባለቤት እሱ ይሆናል” ሌላው የዚህ ዕብድ ጠባይ አንድ ጠዋት መናገር የጀመረውን ነገር በጭራሽ አይለውጠውም፡፡

ለምሳሌ አንድ ጠዋት፤ “የማይጮህ ህዝብ ምላሱ መቆረጥ አለበት!” ይላል፤ ካልን ቀኑን ሙሉ፤ “የማይጮህ ህዝብ ምላሱ መቆረጥ አለበት” ሲል ይውላል፡፡ በሚቀጥለው ጠዋት፤ “ሞኝ ያሥራል ብልጥ ይማራል!” ይላል፡፡ “The smarter prisoner yet learns. The fool governer forever imprisons” እንደ ማለት) ቀኑን ሙሉ ይቀጥላል፡፡ ደሞ ሌላ ጠዋት፤ “የሚዘምሩ ወፎች አሉ፡፡ የሚያርፉበት፤ ጐጆ እሚሠሩበት ዛፍ ግን የላቸውም” ይላል፡፡ እንዲህ እንዲህ ሲል ከርሞ አንድ ቀን ጠዋት፤ “ንጉሡ ጭንቅላታቸውን በርዷቸዋል!!” እያለ እየደጋገመ መጮሁን ቀጠለ፡፡ የአገሪቱ ፀጥታ አስከባሪ ኃላፊ፤ “አሁንስ አበዛው!” ብለው አንድ ፖሊስ አስገድዶ እንዲያስረው ላኩበት፡፡ ዕብዱ መሮጥ ጀመረ፡፡ “የዕብድ ጉልበት አያልቅም” ይባላል፡፡ ፖሊሱ ግዴታው ነውና የሚፈፅመው እየሮጠ መከተሉን ቀጠለ፡፡ ዕብዱ ያደባባዩን ዳር ዳር ይዞ ዙሪያውን ነው የሚሮጠው።

እንደወትሮው ከመስመሩ አይወጣም፡፡ ወደአደባባዩ ውስጥም አይገባም፡፡ ፖሊሱ ደከመውና ቆመ፡፡ ይሄኔ ዕብዱ ከት ከት ብሎ ሳቀና፤ “ሞኝ በመሆንህ ነው እንጂ የት እሄድብሃለሁ? ከአደባባይ የበለጠ እሥር ቤት የት አለና ነው? ይልቅ ሰው ከአደባባይ እንዳይጠፋ ማረግ ነው የሚሻለው!” አለ ይባላል፡፡

                                                               * * *

አካባቢያችንን እንፈትሽ፡፡ አደባባዩ ምሽግ ያደረገውንና ዕውነት የሚናገርበትን እንለይ፡፡ አገራችንን እናጥና፡፡ ዙሪያ ገባውን ማትሮ ጣራውንም ግርጌውንም በዐይነ ቁራኛ አይቶ ነው፡፡ የዘንድሮ ጉዞ፡፡ እንኳን የካዝና ግድግዳ የአዕምሮ ሽንቁርም አደገኛ ነው፡፡ “በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች አሉ ውሻ፡፡ ሌባው ቢያዝም እንኳ አሁንም በሩ ክፍት ከሆነ ለአዲስ ሌባ ምቹ መሆኑ አይቀርም፡፡ ህጉ ወደ ኋላ አይሰራም፤ ተመስገን ነው፤ በሚል በጊዜ ሰርቄ አምልጫለሁ፤ የሚልንስ እንዴት እንደምናስተናግደው ማጤን አለብን፡፡ ከጥንት ጀምሮ በውል እንደሚታወቀው ለሀገሩ ህልውና፣ ለሉዓላዊነቱ፣ ቀናዒ ህዝብ ነው ያለን። “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የሚለው ወዶ አይደለም፡፡ ተደጋግሞ ለጥቃት አጋልጦት ነው፡፡

አለ ነገር አለ ነገር ቁልቁለቱን ወርደን ወንዙን ስንሻገር”፤ ይላል አርቆ እያሰበ፡፡ ከላይ እስከታች፣ ነገር አለ፣ እያለ እየተጠራጠረ፣ መጓዝን የመረጠ ነው፡፡ መጠራጠርን እንተው ቢባልም እሚጠራጠር ካለ መጠርጠር መጥፎ አደለም፡፡ አንዱ ጓዳ ውስጥ ሲያንጐዳጉድ ሌላው ሳሎን እንደሚወራች አሊያም በተገላቢጦሹ ሊከሰት ይችላል፡፡ የውስጥ ችግሮቻችንን ዐይተው ባላንጦቻችን እንደሚጠራሩ መቼም ቢሆን መዘንጋት አይገባም። “ለነገር ይሁን ለፍቅር” ለዩ፤ ይላሉ አበው፡፡ ስለተጠራሩብን ጆሮአችንን በየአቅጣጫው ማቅናት ይጠበቅብናል፡፡ “እዚያ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ፤ እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው፤ ጐበዝ ተጠንቀቁ፣ ይህ ነገር ለኛ ነው!!” ማለትም የአባት ነው፡፡ “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታልን” አለመርሳትም ብልህነት ነው፡፡ በጥቃቅን መብራት በበራባቸው ነጥብ - ቦታዎች፣ በተመረጡ ወንጀሎች፣ በተመረጡ ሰዎች ላይ ስናተኩር ያልተመረጡትን ማየት ይሳነናል፡፡ ከመካከላቸውም ንፁሃኑን መለየት ይቸግረናል፡፡ ሁለመናችንን እንይ ጐበዝ፡፡ ሁሉም ከተበላሸ ወይም ሁሉም ከተሳሳተ ችግር ነው “በገንፎ የተሠራ ጥርስ፤ አያስቅ፤ አያስፍቅ” ማለት ሥረ - ነገሩ ይሄው ነው፡፡

Read 3184 times