Monday, 27 May 2013 14:02

አስጨናቂው ጉዞ

Written by  ደራሲ አምሀየስ ታደለ
Rate this item
(8 votes)

ሰማዩ ጨልሟል፡፡ ጨረቃ ወለል ብላ ወጥታ ደማቅ ብርሃኗን ትለግሳለች፡፡ የባህሩ ማዕበል ሲጋጭ የሚፈጥረው ድምጽ ስሜትን ያነቃል፡፡ ከእኔ ጋር ተቀምጠው የሚሄዱትን ተጓዦች በዓይኔ ቃኘሁ፡፡ ሽማግሌ ሸበቶ ቄስ የጣጣፈ ልብሳቸውን ለብሰው እየተጓዙ ልብሳቸውን አሁንም አሁንም ያስተካክላሉ፡፡ አናታቸው ላይ ያደረጉት ቆብ እንኳን ሳይቀር የተጣፈ ነው፡፡ የሚንቀለቀሉት ዓይኖቻቸው ውስጥ ከፍተኛ ብልጠት ይነበባል። ከጐናቸው አንድ ወታደር መለዮውን ለብሶ ተቀምጧል፡፡ ፀጉሩን በፍጥነት እያከከ ዙሪያውን ይገላምጣል፡፡ አንዳች የሚበላው ህዋስ ሳይኖር አይቀርም፡፡ ሌሎችም ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር እየተጓዙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ካርታ እየተጫወቱ ከመሀል ድንገት ከትከት ብለው ይስቁና ተመልሰው ካርታቸው ላይ ያፈጣሉ፡፡ ማሲንቆውን እየገዘገዘ አንድ አዝማሪ እየዘፈነ ነው፡፡

ሙዚቃውን እንዲያቆም የሚለምኑት ከሚያደምጡት ይበልጣሉ፡፡ ከማሲንቆውና ከድምጹ የትኛው ይበልጥ እንደሚያስጠላ አላወቅሁም። ከሙዚቃው ጋር የማይሄድ በእስክስታና በቫልስ መካከል ባለ ስልት የምትውረገረግ አሮጊት ዙሪያውን እየተሽከረከረች ነው፡፡ ዞሬ ስመለከት የምንሄድበት ነገር ከመርከብ የተለየ እንደሆነ አስተዋልኩ፡፡ ድንጋጤ ሰውነቴን እንደ ጉንዳን ወረረኝ፡፡ የአሣ ቅርጽ ያለው ነገር ነው። አሣ ነው እንዴ? ሊሆን አይችልም፡፡ ከአጠገቤ ያለውን ሰው “የት ነው ያለነው?” ስል ጠየኩት። “ማንም የሚያውቅ የለም” መለሰልኝ፡፡ “እዚህ ስለማይነጋ ቀን መቁጠር አልቻልንም፡፡ የሁላችንም የእጅ ሰአቶች ቀጥ ብለው ቆመዋል፡፡ አንተ ለረጅም ጊዜ ከእንቅልፍህ ስላልነቃህ ብዙዎቻችን ተረብሸን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ስትነቃ ያስተዋለህም የለ!” ፊቱ ላይ የተንኮል ፈገግታ ይታያል፡፡ በሀሳብ ጭልጥ ብዬ ሄድኩ፡፡ የት ነው ያለነው? ወዴት ነው የምንሄደው? እንዴትስ ወደ እዚህ ቦታ ልንመጣ ቻልን? ማለቂያ የለሽ ጥያቄዎች ጭንቅላቴ ውስጥ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ በቀስታ ወደ ጥግ ተጠጋሁ፡፡

በእርግጥም ይህ ነገር የአሣ መቅዘፊያዎችና የአሣ ጅራት ያሉት ነው፡፡ አሣ ላይ ሆኖ መጓዝ ግን ቅዠት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ መርከባችን ምናልባት የረቀቀ የቴክኖሎጂ ውጤት ሳትሆን አትቀርም፡፡ ግን የሚገርመው ምንም የውስጥ ማረፊያ የሌላት መሆኑ ነው፡፡ ተጓዦች በሙሉ ያለነው ከውጪ ነው፡፡ ድንገት “እንደምን አደራችሁ የተከበራችሁ ተጓዦች” የሚል ድምጽ ከፊት ለፊታችን ተሰማ። ወደፊት ስንመለከት ያናገረን አሣ ኖሯል፤ ትልቅ አሣ፡፡ “ፀሐይ እዚህ ስለማትወጣ ነው እንጂ በምድር ሰአት አቆጣጠር አሁን ነግቷል” የአሣው ድምጽ ውብ ቢሆንም በውስጡ የሚያስፈራ ቅላፄ ያዘለ ነው። ቀድመን መልኩን ያላየነው ራሱን ባህሩ ውስጥ ቀብሮ ስለሚዋኝ እንደነበር ተገነዘብኩ፡፡ ሁላችንም በፀጥታ ተውጠን አሣውን እናዳምጣለን፡፡ “እስካሁን ያላናገርኳችሁ ሁላችሁም እስክትነቁ በጥበቃ ላይ ስለነበርኩ ነው፡፡

ከእናንተ ውስጥ የት እንዳለን የሚነግረኝ አለ?”

አሣው በፊት ከማውቃቸው አሦች የተለየ ነው፡፡ ዐይኑ እንደ ነብር ያበራል፣ ያስፈራል፡፡ “ይህ ህልም እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም። ብቻ ለህልም በጣም ረዘመብኝ” አሉና ቄሱ አንገታቸውን አቀረቀሩ፡፡ ግራ ተጋብተዋል፤ ልብሳቸውን አሁን አያስተካክሉም፡፡ አሣው ልቡ እስኪፈርስ በሳቅ ተንፈቀፈቀ፡፡ በጐን የሚታዩኝ ጥርሶቹ በልዘዋል፤ ሰው ቢሆን ሱሰኛ ነው የሚያስብል አይነት፡፡ “አይ መምሬ፤ ህልም ውስጥ ነን ያለነው አሉን! ህልም ቢሆን ምንኛ በታደሉ ነበር፡፡ ሌላ የሚሞክር ይኖራል?” በዝምታ ተዋጥን፤ ዝምታው እየረዘመ ሄደ፡፡ “እሺ እኔው ልንገራችሁ፡፡ ያላችሁት በአንድ የማታውቁት እንግዳ ዐለም ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ሁልጊዜ ጨለማ ነው፤ ከጨረቃ በቀር የምትወዷት ፀሐይ አትወጣም፡፡ ከላዬ ላይ ዘላችሁም ወደ ባህሩ ውስጥ መግባት አትችሉም፡፡

ሙታን ናችሁ፣ ሁላችሁም ምድር ላይ ሞታችኋል፡፡” ተጓዦች ይህን ሲሰሙ በድንጋጤ መንጫጫትና ማለቃቀስ ጀመሩ። እኔም ከአጥንቴ ውስጥ ከባድ ቅዝቃዜ ተሰማኝ፡፡ ሞት? ምኑን ኖሬ! ሚስት ልጅ እንኳን ሳይኖረኝ! ወይኔ! አስደንጋጩን ዜና በፀጋ የተቀበለ አልነበረም፤ ሁሉም ከራሱ ስሜት ጋር የሚታገል ይመስላል። ቀድሞ በሀሴት ስትውረገረግ የነበረችው አሮጊት ድንገት እየጮኸች ማልቀስ ጀመረች፡፡ እውነትም ህይወት ለካ አትጠገብም፡፡ አሮጊቷ እንደ ትንሽ ልጅ ሞቷን መቆጨቷ ገረመኝ፡፡ የኔ የአፍላው ነው እንጂ የሚያሣዝነው፤ ከተጓዦቹ በሙሉ በእድሜ ትንሹ እኔ ነኝ፡፡ “ሞታችሁን የማታስታውሱ ምስኪኖች” አለ አሣው በፈገግታ፡፡ “ሰው ከሞተ በኋላ አሟሟቱን እንዳያስታውስ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ መምሬ ግን ለምን ወደዚህ ቦታ የመጡ ይመስልዎታል?” አሣው መጠየቅ በጣም ይወዳል፤ ጥያቄዎቹን ግን መልሳቸውን እያወቀ ነው የሚጠይቀው፡፡ “እኔ ምን አውቃለሁ፤ አንተው ንገረኝ እንጂ” አሉ ቄሱ በተዳከመ ድምጽ፡፡

“ጥሩ ሌላ የሚያውቅ ሰው ይኖራል?” መልሶ ጠየቀ፡፡ “እኔ እንደሚመስለኝ ገሀነብ ውስጥ ነው ያለነው” አለ ወታደሩ መሀል አናቱን እንደለመደው እያከከ፡፡ “አንተ ከጦርነትና ከእሳት ውጭ ምንም የማታወቅ አሳዛኝ ፍጡር ነህ አለው” አሳው በምሬት፡፡ “እዚህ ያላችሁት ለገነትም ይሁን ለሲኦል የማትገቡ ነፍሶች በመሆናችሁ ነው፡፡ ወይ ፀድቃችሁ አልፀደቃችሁ፤ ወይ በሀጢአት ተዘፍቃችሁ አልቦካችሁ! ለሁለቱም ዓለማት የማትገቡ የተኮነናችሁ ነፍሶች!” ይህንን ሲሰሙ ቄሱ አማተቡ። ፍርሃት በመላ ሰውነታቸው ሰርጿል፡፡ “መምሬ” አለ አሳው በፈገግታ “ይህች የሚያማትቧትን ነገር ይተዋት፡፡

በምድር ብዙ የዋሃንን ያታለሉት አይበቃዎትም?” “ማንን ሳታልል አየኸኝ?”

የአምላክን ቃል በቅንነት ከማስተማር ውጭ፣ የእርሱን ታላቅነት ከመመስከር ውጭ ምን ክፉ ተግባር ሳደርግ አየኸኝ?” አሣው ይህን ጊዜ ከመቅጽበት ሲዞር አካባቢው በውሃ መንቦራጨቅ ተረበሸ፡፡ አሣ መዞር እንደሚችል አላውቅም፤ ይሄኛው ግን ይዞራል፡፡ “ታዲያ እኔ ነኝ የሰፈሬን ልጃገረዶች ሳባልግ የነበርኩት?” አስፈሪ ቢጫ አይኖቹን እያጉረጠረጠ አፈጠጠባቸው፡፡ “በእርግጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ሰርተዋል፡፡ ስለዚህም ደጉ በክፉ ተጣጥቶ እዚች ቦታ ተገናኘን፡፡” ቄሱ ተናደው “ወጊድልኝ አንተ ክፉ ሰይጣን” እያሉ ለረጅም ጊዜ ጮሁ፡፡ የአሣው ትዕግስት እንዳለቀ ፊቱ ላይ ይነበባል፡፡ ድንገት በብርሃን ፍጥነት ቄሱን ጐረሳቸውና ያላምጣቸው ጀመር፡፡ ብዙ ካላመጠ በኋላ ዋጣቸውና ቆባቸውን ወደ ባህር ተፋ፡፡ ይህን ያዩ ተጓዦች በሽብርና በድንጋጤ ተዋጡ፡፡ ብዙዎች እየተንደረደሩ ወደ ባህሩ ለመዝለል ቢሞክሩም ወደ አሣው ጫፍ ሲደርሱ እግራቸው እያጥለመለመለ ጣላቸው፡፡ “አይ መምሬ ለሚወዱትም ገነት ይሁን ለሚፈሩት ሲኦል ሳይበቁ ሆዴ ውስጥ ቀሩ፤ ከመኖርም ወደ ምንምነት ተሸጋገሩ” አለ አሣው በፀፀት፡፡

ድንገት እምባው ዱብ ዱብ እያለ መውረድ ጀመረ፡፡ “እኔም ተርቤ ነው እንጂ እሳቸውን መብላት አልነበረብኝም ነበር፡፡ አያችሁ እዚህ ባሕር ውስጥ የሚበላ አንዳችም ፍጡር የለም፤ ቢሆንም በድርጊቴ በጣም ተፀጽቻለሁ፡፡ ሁላችሁንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” አለና አሣው በሚያሳዝን ድምጽ እንደ ውሻ ማላዘን ያዘ፡፡ እኔም የአሣውን መረበሽና ከልብ ማዘን ሳይ ልቤ በሀዘን ተነካ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሣው ሀዘን እንደሚበቃንና የተከፋ መንፈሳችንን ማስደሰት እንደሚኖርብን ተናግሮ፣ አዝማሪውን ጥሩ ሙዚቃ እንዲያንቆረቁርልን ነገረው፡፡ አዝማሪውም ድምፁን ከጠራረገ በኋላ ማሲንቆውን እየገዘገዘ ማንጐራጐር ጀመረ፤ ለጆሮ በፍፁም የማይጥም ሙዚቃ፡፡ አሳው ግን ልቡ ተነክቶ፤ አይኑን ጨፍኖ በተመስጦ ይሰማ ጀመር፡፡ አብዛኛው ሰው ሙዚቃውን አልወደደውም፡፡ ተወዛዋዧ አሮጊት እንኳን በዚህ ጊዜ አትወዛወዝም፡፡ ፊቷን አኮሳትራ ሁኔታውን በመከታተል ላይ ነች፡፡ አዝማሪው ሙዚቃውን ቀጠለ፤ ቀጥሎም በግጥሙ አሳውን አሞካሸ፡፡ አሳው ፍርድ አዋቂና የሰው ልክ አዋቂ፣ ጥሩ ከሳሽና ጥሩ ዳኛ እንደሆነ ያለማቋረጥ ለፈፈ፡፡

አሳው በተመስጦ ሙዚቃውን ያዳምጣል፣ ራሱን አልፎ አልፎ ይነቀንቃል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ አዝማሪው ሙዚቃውን ጨረሰ፡፡ ፊቱ ላይ ላቡ ችፍ ብሏል፡፡ አሳውን ለማስደሰት ብዙ ታግሏል፣ ብዙ ደክሟል። “አዝማሪ ሙዚቃ አለቀ እንዴ?” ሲል አሳው ጠየቀው፡፡ አዝማሪውም በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ፡፡ አሳው በዚህን ጊዜ ከመቅጽበት ዞረና አዝማሪውን ጐርሶ አይኑን እኛ ላይ እያጉረጠረጠ ማላመጥ ጀመረ፡፡ አዝማሪውንም ውጦ ማሲንቆውን ወደ ባህሩ ተፋው፡፡ አሮጊቷ በድንጋጤ ኡኡታውን አቀለጠችውና ተዝለፍልፋ ልትወድቅ ስትል ካጠገቧ ያሉ ሰዎች ደገፏት፡፡ ከወንዶችም ብዙ ያለቀሱ አሉ፡፡ “ድንቅ አዝማሪ ነበር፤ ሆዴ ውስጥ ሆኖ እንዲያንጐራጉር ስለፈለግሁ እንጂ እሱንስ መብላት አልነበረብኝም” አለና አሳው ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ እንባው በዚህ ጊዜ የአዞ እንባ ሆነብኝ፡፡ ውስጤም በጣም ጠላው፡፡ “ዛሬ በስራዬ ስለተፀፀትኩ ከእናንተ ጋር እንደ ልቤ መጫወት አልችልም፡፡ እናንተው ተጫወቱ” ብሎ ጭንቅላቱን ወደ ባህር ውስጥ ከተተ፡፡ በአሳው ተግባር ሁላችንም በጣም ተረብሸናል፣ አዝነናል፣ ተናደናል፡፡

እኔም ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅሜ መመካከር እንዳለብን እየዞርኩ ተናገርኩና ተሰበሰብን፡፡ ወታደሩ በቁጣ እራሱን እያከከ አሳው እንደዚህ የሚቀጥልበት መንገድ መኖር እንደሌለበት ተናገረ፡፡ ወደራሱ ስመለከት መሀል አናቱ ላይ ቀዳዳ ተመለከትኩ፡፡ የሚያሳክከው ጥይት በመሀል አናቱ የገባበት ቦታ ላይ ነው፡፡ የሞቱ መንስኤ ጥይቱ ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ፡፡ “ስንት ምሽግ የሰበርኩ፣ ጠላቴን ያንበረከኩ ጀግና ነኝ፡፡ ዝም ብዬ የአሳ እራት እስክሆን የምጠብቅበት ምክንያት አይታየኝም። ”“ምን መፍትሔ አለህ?” አንድ ፊቱ የሚያሳዝን ሰው ከመካከላችን አቋረጠው፡፡ “ጥሩ ጥያቄ ነው” አለ ወታደሩ ወኔ በተሞላ መንፈስ፡፡ “ጠላትን ለማሸነፍ የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ትብብር ነው፡፡ ጠላት ይመጣብኛል ብሎ በማያስብበት ቦታና ወቅት ማጥቃትና አከርካሪውን መስበር ድልን ያጐናጽፋል።” ቀጥሎም በህይወት ሳለ እንዴት የጠላት ምሽግ እንደሰበረና የጀብድ ተግባር እንደፈፀመ ያለማቋረጥ ተናገረ፡፡ “ይህ ሁላ ከአሳው ጋር በምን ይገናኛል?” ስል ጠየቅሁት ትዕግስቴ ተሟጦ፡፡ “ምን ማለትህ ነው? በደንብ ይገናኛል እንጂ እኔ እኮ የምላችሁ ድንገት አሳው እራሱን እንዳሁኑ ባህር ውስጥ እንደቀበረ ብናጠቃው ከመጥፋት እንተርፋለን” ነው፡፡

ግማሾቻችን ጅራቱን፣ ግማሻችን መቅዘፊያውን ሌሎቻችን ራሱን ይዘን ብንቀጠቅጠው መቼም መሞቱ አይቀርም” አለ በጥርጣሬ፡፡ ወኔው ፊቱ ላይ ያበራል፤ ዐይኖቹ ላይ እልህ ይንቀለቀላል። ይህን ወደል አሳ መግደል ወታደር ቤት አይማሩት ስለዚህ አይፈረድበትም፣ ካቅሙ በላይ ቢሆን ነው እንጂ፡፡ ብዙዎቻችን ከአሳው ጋር ግብግብ መፍጠር የሚደፈር ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ እንደ አንድ አማራጭ ግን ልንይዘው ተስማማን፡፡ ሌላ ሃሳብ ያለው ሰው እንዳለ ጠየቅሁ፡፡ አንድ መነጽር ያደረገ ሰውዬ ሃሳብ እንዳለው ተናገረ፡፡ ብዙ የተማረ ይመስላል፡፡ ፀጉሩ ሽበት ጣል ጣል ያለበት ነው፡፡ “እኔ በሙያዬ ሳይካትሪስት ነኝ እናም እዚህ አሳ ላይ ያየሁት ችግር ለኔ አዲስ ያልሆነና ብዙ ታካሚዎቼ ላይ ቀድሞ ያየሁት ነው፡፡ ፈረንጆች ደብል ወይም መልቲፕል ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደር ይሉታል፡፡ ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ተቃራኒ ባህርዮች አንድ ሰው ላይ የሚታዩበት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ይህ ችግር ያለበት ሰው በአንድ ወቅት ተቆጪና አስቸጋሪ ሲሆን ሌላ ወቅት ላይ ደግሞ ለሰው ተስማሚና ፍፁም ደስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ሁለቱ ባህሪዎች አንዱን ሰው እንደ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ያደርጉታል፡፡ አሳው እንዳያችሁት ቄሱንና አዝማሪውን እንደበላ በፀፀት ሲያለቅስ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው የማንነት ግጭት በውስጡ እንደተቀበረ ነው፡፡ በልጅነቱ ሳይኮሎጂካሊ አብዩዝድ የሆነ አሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ከኔ ጋር አንድ ሴሽን ቢኖረን ያለውን ችግር በደንብ ልረዳና አብረን መፍትሄ የምንፈልግበት ጥሩ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” ሲል ጨረሰ፡፡

ሀሳቡን ብዙዎች ተቀበሉት፡፡ አሳው ለግዳዮቹ ማልቀሱ ከተለመደው ባህርይ ውጭ ነው ሲሉ መሰከሩና ይህን የሳይካትሪስቱን ሀሳብ እንደ አንድ አማራጭ እንድንይዘው ተወሰነ፡፡ ወዲያው አንድ ቅልብልብ ወጣት “እኔ ሌላ ሀሳብ አለኝ” አለ፡፡ ሲናገር በጣም ይፈጥናል፤ መላ ሰውቱ ይወራጫል፡፡ “በህይወት ሳለሁ ጠበቃ ነበርኩ። እናም ብዙ የህግ ክሶችን ረትቻለሁ፡፡ አሳው ከእንግዲህ አንድ ሰው ቢበላ በህግ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጥ ልንነግረው ይገባል፡፡ የሰው ልጅ በሰውነቱ ክቡር ነው እናም በነፃነት የመኖር መብቱን ማንም ጉልበተኛ ነኝ የሚል ሀይል በኢሰብአዊ ሁኔታ ሲገፍፈው የመቃወም መብት እንዲሁም ግዴታ አለበት፡፡” ልጁ ንግግሩን ሳይጨርስ ተወዛዋዧ አሮጊት “እኛ እኮ ሞተናል፣ አንተ የምትለው ህግ ለህያዋን እንጂ ለእኛ አይሰራም፡፡ የሙታንን መብት የሚያስከብር አንዳችም የሕግ አካል የለም” አለች ወገቧን በእጆቿ ጥርቅም አድርጋ ይዛ፡፡ ወጣቱ ጠበቃ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “መርሳት የሌለብን አንድ እውነታ አለ፡፡ እኛ እኮ ምድር ላይ ብንሞትም እዚህ አሁን ያለንበት አለም ላይ ህያዋን ነን፡፡ እየኖርን እስከሆንን ድረስ ደግሞ በምድር የምናውቀው አይነት ሕግ ሊኖረን ይገባል፡፡ አለበለዚያ አንዳንዶቻችን ሌላዎቻችንን እየጨፈለቅን ኢፍትሀዊ የሆነ አኗኗርን እንደ ትክክለኛ የኑሮ ስርዓት ልንቀበል ነው፡፡

ይህን ሆዳም አሳ ከእንግዲህ በሕግ ከሰን መጠየቅ ይኖርብናል! ነገሮች በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይችሉም!” የጠበቃው ሀሳብ ለብዙዎቻችን ባይዋጥልንም ልጁን ላለማስቀየም ያቀረበውን ሀሳብ እንደሌላ አማራጭ አድርገን እንድንወስደው ተናገርኩና ሁላችንም ተስማማን፡፡ ቀጥሎም አንድ ኩሩ ወፍራም ቦርጫም ሰውዬ መናገር ጀመረ፡፡ “በህይወት ዘመኔ በፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከመሆን ባሻገር የከተማ ከንቲባ ሆኜ ለረጅም አመታት አገሬን አገልግያለሁ፡፡ እና አንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር እናንተ ያለንበትን ችግር አሳሳቢነት ጠልቃችሁ አለመረዳታችሁን ነው፡፡ መሪ የሌለው ስብስብ ችግር ሲኖር ወዲያው ይፈረካከሳል፡፡ እናም በቅድሚያ የስልጣን ተዋረድ ሊኖረን ይገባል!” ከጎኑ ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ታላቅ ንግግር የሰሙ ይመስል አጨበጨቡ። ሰዎቹ በህይወት ሳሉ ከከንቲባው በታች የነበሩ ባለስልጣኖችና ተከታዮቻቸው እንደነበሩ ተረዳሁ፡፡

በህይወት ሳሉ ሰውዬውን መከተል አባዜ ሆኖባቸው እዚህም ተከታዮች መሆናቸውን አላቋረጡም፡፡ ከንቲባው በእርካታ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ “ስለዚህም በቅድሚያ ፍትሀዊ የመሪ ምርጫ መካሄድ አለበት። እኔን መሪያችሁ አድርጋችሁ ከመረጣችሁ ችግሩን በአፋጣኝ የምፈታበትን መንገድ አሳያችኋለሁ፡፡” ወታደሩ ድንገት አቋርጦ “ለምርጫና ለማያስፈልግ ቢሮክራሲ አሁን ጊዜ የለንም፡፡ ይልቁንስ መፍትሔ ካለህ ብትነግረን ይሻላል” አለው፡፡ ወታደሩ ስሜቴን ስለተናገረልኝ ደስ አለኝ፡፡ “አሁንም እያዳመጣችሁ አይደለም፡፡ ያለ ስርአታዊ አወቃቀር ማንኛውንም ስራ መስራት ለውድቀት የሚዳርግ ነው፡፡ እኔን ከመረጣችሁኝ አሳውን ከውጭ ሆነን ልናጠምደው እንደማይሳነን የምታዩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡” ይህ ፖለቲከኛ ባዶ ተስፋዎችን ለስልጣን ጥማቱ ሲል ሊሸጥልን እንደሚሞክር ተሰማኝ፡፡ ስልጣኑን ቢያገኝ አሁን ምን ይጠቅመዋል? ግን ማን ያውቃል፤ ከአሳው ጋር ተመሳጥሮ ቢያስፈጀንስ?

አብዛኛዎቻችን በጭንቀት ስሜት ውስጥ ሆነነ የስልጣን ርብርቦሽ ለማየት ፈፅሞ ስላልፈለግን ሀሳቡን አጣጣልነው፡፡ ደጋፊዎቹም ሆኑ ከንቲባው የሚያዳምጣቸው ሰው አጡ፡፡ “እኔ በተነሱት ሀሳቦች አልስማማም” አንድ ራሰ በራ ሰውዬ ነበር፡፡ “በሙያዬ የባዮሎጂ መምህር ነበርኩ፡፡ ተፈጥሮ የራሷ ህግ አላት፡፡ ጠንካራው ደካማውን እየደቆሰ መኖሩ ግድ ነው፡፡ አንበሳ ለመኖር ሲል ሚዳቋን ቢበላት አይገርምም፡፡ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡ ይህ አሳ ምንም ነገር በሌለበት ባህር ውስጥ የሚመገበው ነገር ስለሌለ እኛን ቢበላን ጥፋቱ ምን ላይ ነው?” ከፖለቲከኛውም የባሰ በመምጣቱ ተገረምኩ፡፡ ይህ የሁላችንንም ጥፋት በፀጋ የሚቀበል ጎጂ ሀሳብ በሁላችንም ዘንድ ተቀባይነት አጣ፡፡ እስካሁን የተነሱትን ሀሳቦች በተቀባይነታቸው ቅደም ተከተል እንዲሞከሩ ተነጋገርንና በቅድሚያ የሳኪያትሪስቱ ካልሰራ የህግ ባለሙያው፣ ያም ካልሆነ የወታደሩ ሀሳብ እንዲሞከር ወስነን ተበታተንን፡፡ እኔም ጥጌን ይዤ ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ፡፡ ከሀሳባችን አንደኛው ይሳካ ይሆን? ወይስ የአሳው መብል ከመሆን አንድንም? መልሱን ጊዜ ነው የሚያውቀው፡፡ በዝግታ ባህሩን እየቃኘሁ በሀሳብ ነጎድኩ፡፡

Read 2887 times Last modified on Monday, 27 May 2013 14:15