Monday, 27 May 2013 13:55

በእውነትና በልቦለድ መሀል የሚዋልለው ‹‹የመንጌ ውሽሚት››

Written by  ባህሩ ጀማል
Rate this item
(3 votes)

ተከታዮቹ ሁለት ሥነ ጽሑፋዊ እሳቤዎች ፤ ደጋፊ እና ነቃፊ አግኝተው በመላው ዓለም የሚገኙ ጸሐፍትን ፤ ሀያሲያንን እና አንባቢያንን ሲያሟግቱ ኖረዋል፡፡ ሙግቱ አሁንም የተቋጨ አይመስልም፡፡ ወደፊትም መቋጨቱን እንጃ፡፡ የመጀመሪያው እሳቤ በደምሳሳው ‹‹እውነት ልቦለድ ስትሆን የሥነ ጽሑፍ ሞት ተቃርቧል›› የሚል ነው። ይህ እሳቤ በዚያው በሥነ ጽሑፉ ክበብ በርካታ ደጋፊዎችና አቀንቃኞች አሉት፡፡ ሁለተኛው እና ተቃራኒው እሳቤ ‹‹ በሥነ ጽሑፍ እውነትን እንዳለች ማቅረብ ፎቶ ከማንሳት ምንም አይለይም›› የሚል ነው፡፡ ይኸኛው ሀሳብም እንዲሁ በርካታ ደጋፊዎች አሉት፡፡ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች እውነትን ኪናዊ ለዛን ፤ ውበትንና ጣእምን ተላብሳ ሲያነቧት ነው ሀሴት የሚያደርጉት፤እውነትን በደራሲው ውብ ቃላት፤ በሳል ዕይታ ፤ማራኪ የህይወት ትዝብትና ምትሀታዊ ትረካ ስጋ ለብሳ ፤ነፍስ ዘርታና ሙሉ ህልውናዋን ተጎናጽፋ ማግኘት ነው የሚፈልጉት።

ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥኩት ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የልቦለድ መጽሐፍ በነዚህ ሁለት ምድቦች አማካይ መንገድ ላይ የሚዋልል ይመስላል፡፡ ዐቢይ ጭብጡን አብዝተን በምንወደው የልጅነት ሕይወት ላይ ያደረገውን ይህን ማለፊያ የረጅም ልቦለድ የመጀመሪያ ሥራውን ጀባ ያለን ተስፋዬ አለነ አባተ ነው፡፡ ልክ በልጅነት ዘመን እንዳነበብነው በማክሲም ጎርኪ ‹‹ ልጅነት ›› ውስጥ እንዳሉት ገጸ ባህሪያት ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በዘነበ ወላ ‹‹ ልጅነት›› ልቦለድ ውስጥ በእጅጉ በሳቅ እንዳፍነከነኩን እነ ቀጢሳው፤ በአዳም ረታ ተወዳጅ የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ውስጥ ንፋስ መውጫ ጉብታ ላይ ሆኖ ሕይወትንና ዓለምን በሕፃን አዕምሮው እንደሚታዘበው መዝገቡ ዱባለ እንዲሁም ‹‹ እንጀራዬን››፤ ‹‹ ዘላን››፤ ‹‹ ጢቦ›› እና ‹‹ከሰማያዊ ወደ ቦቢ›› በተሰኙት የአዳም ረታ አጫጭር ልቦለዶች ውስጥ እንደሚገኙት ሕፃናት፤ በእንዳለጌታ ከበደ የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ‹‹ከጥቁር ሰማይ ስር›› ውስጥ እንደሚገኘው አዝናኝ ሕፃን አቦቸር ሁሉ በ‹‹ በመንጌ ውሽሚት›› ውስጥ የሚገኙት አበይት ሕፃናት ገፀ ባሕሪያት ‹‹ጭንቅሎ››፤ ‹‹ጠይሜ›› እና ‹‹ጠምቤ››ም በመጽሐፉ ደራሲ መቼም ከአእምሮ እንዳይወጡ ሆነው ተቀርጸዋል ፡፡

ደራሲው ተስፋዬ አለነ ‹‹መንደርደሪያ›› በሚል ርእስ ባቀረበው መግቢያ ላይ ‹‹የመንጌ ውሽሚት የኔና የጓደኞቼ የነጭንቅሎ ፤ ጠይሜ ፤ጠምበለልና የመሳሰሉት ሕይወት ብቻ አይደለም - የናንተም ያኔ ልጅ የነበራችሁ ሰዎች ሁሉ ጭምር እንጂ …›› ይላል ፡፡ ያንን ሲለን እንዲያው ‹‹ለራስ ሲቆርሱ…›› ብለን ደራሲው ራሱን እየሸጠ ነው ብለን በትዝብት ገርፈነው እናልፈዋለን፤ኾኖም ታሪኮቹ የእውነትም እንደሚመለከቱን የምናውቀው ጥቂት ገጾችን እንደገለጥን ነው፡፡ በእርግጥም በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት ታሪኮችና ገጸ ባህሪያት ውስጥ የልጅነት ሕይወታችንን የወከለልንን ሕጻን ፈልገን ማጣት አይቻለንም፤ የሕይወት ትወናችንን እንመለከትበታለን፡፡ በገዛ ልጅነታችን እንስቃለን፣ ፎቶ ባልነበረበት ዘመን የተወለድን ጭምር እንስቃለን፣ እድሜ ለዚሁ ደራሲ ራሳችንን በፊደል ቀርጾ በመጽሐፍ ገጾች አትሞ፣ የልጅነት ፎቶዎቻችንን ያድለናልና፡፡ እስኪ መጸሐፉን በወፍ በረር እንቃኘው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ለዚህ ዳሰሳችን በማጣቀሻነት የተጠቀምኩት የመጽሐፉን ሁለተኛ እትም እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙት ሀያ አንድ ታሪኮች ውስጥ ለመጽሐፉ ርእስነት የተመረጠው ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የሚለው ታሪክ ፤በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ጭንቅሎ የተባለው ገጸ ባህሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለማርያም በወጣትነት ዘመኑ ሐረር፤ ቀላድ አምባ ውስጥ በጥገና ሥራ ተሰማርቶ ሳለ፣ አጎቱና የሰፈር ሰዎች የነገሩትን ይዞ፤ በመንጌ የከንፈር ወዳጅነት የሚታሙትን እማማ ትሁኔን ስለሰማው ሀሜት ይጠይቃቸዋል፡፡ እማማ ትሁኔ አረቄ ሻጭ ናቸው፡፡ በእማማ ትሁኔ አረቄ ቤት ግድግዳ ላይ ‹‹ዱቤ ከመንግሥቱ ወዲህ….›› የሚለውን የጽሑፍ ማስገንዘቢያ ወንድሙ አረቄ እንዲገዛ ሲልከው የተመለከተው ጭንቅሎ፣ እግረ መንገዱን የማስገንዘቢያውን ምንነት ለማወቅ እማማ ትሁኔን ይጠይቃል፡፡ ጭንቅሎ በሕጻን አንደበቱና አእምሮው በሀሜት መልክ የሰማውን ወሬ እውነትነት ለማጣራት የሚያደርገው ጥረትና ትህትናው አስደማሚ ነው፡፡

እማማ ትሁኔም እንዲህ ሲሉ ይመልሱታል፡- ‹‹…መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ያኔ ገና ወታደር ሳለ እዚህ ጥገና የሚባለው የወታደር መሥሪያ ቤት ውስጥ ነበር የሚሠራው፡፡ እንዴት ያለ ጎበዝ መካኒክ ነበር መሰለህ …ታዲያ አንድ ጊዜ ደምወዝ እስኪወጣ በዱቤ ጠጣልህ፡፡ ከዚያ ከዛሬ ነገ ይከፍለኛል ስል ሲቀር፤ ስጠብቅ ሲቀር ኋላ ላይ እኝያን ደግ አባት ከመንበረ ስልጣናቸው ገልብጦ ገድሏቸው ነገሰ። ግሪሱን ጠራርጎ ዙፋን ላይ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድራት እሱ ነው›› የሚል ወሬ ሰማሁ። ያን ቅንነቱ አውቅ ስለነበር መንጌ መቼም ጨክኖ ብሬን በልቶ አይቀርም። እጥፍ አድርጎ ይመልስልኛል ብዬ በተስፋ ጠበቅኩት፡፡ ለአንድ ሀገር አስተዳዳሪ አረቄ በብድር ያጠጣሁ መሆኔን በኩራት ለሀረር ሕዝብ እያወራሁ ከረምኩ፡፡ በመጨረሻ ምላሴ ሌላ እዳ ይዛብኝ መጣች ›› መንጌን የተመለከቱት ትርክቶች ታሪክ ቀመስ በመሆናቸው ልቦለድ ይሁኑ ፈጠራ እንዲሁ እንደተወዛገብን ታሪኩ ይፈጸማል፡፡ ደራሲው የሀረር ልጅ መሆኑና ለልቦለድ የራቁ፣ ለእውነታ የቀረቡ ታሪኮችን ይዞልን ስለቀረበ፣ ‹‹የመንጌ ውሽሚትን›› ታሪክ እውነት ይሁን ስነጽሁፋዊ ኩሸት የምናውቀው ነገር አይኖረንም፤ ደራሲውም ውዝግባችንን የፈቀደ ይመስል ምንም ፍንጭ አይሰጠንም፡፡

ለቤተሰባቸው እና ለእናት አገራቸው ሟች ናቸው ብለን የምንዘክራቸው ቆራጡ መንጌ የጉርምስና ህይወት ደራሲው እንደነገረን አይነት ላይሆን እንደሚችል ልባችን መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ ‹መንጌ ዉባንቺን ከማግኘታቸው በፊት በእርግጥም የጭን ገረድ ነበራቸውን?› ብለንም እንጠይቃለን፡፡ ደራሲው ይህንን ክፍል በታሪክ ላይ ተመስርቶ መጻፉ ነው ለዚህ ሁሉ የሚዳርገን፡፡ በሌላ ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ በህጻንነታችን የቃለ መሀላን ክብደት ሳንገነዘብ የተናገርነው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የምንፈጽማቸውን አስገራሚ መሀላዎች ያስታውሰናል፡፡ የመሀላ ታሪኮቹን ደራሲው የጻፈበት ክፍል ፈገግታን ማጫሩ የግድ ነው፡፡ በእናቶቻችን ስም እንፈጽም የነበረውን የመሀላ ብዛት ያስታውሰናል፡፡ በታሪኩ ውስጥ ጭንቅሎና ጠምቤ በእድሜ በጥቂቱ የሚተልቃቸው ጠይሜ በብይ ጨዋታ በቁማር የሚያገኘውን ሳንቲሞች አባቱ እንዳያገኙበት ቆፍሮ ከሚደብቅበት የገዛ ግቢያቸው ውስጥ አውጥተው ይወስዱበታል ::

ጠይሜ ጓደኞቹ ሳንቲሞቹን አለመውሰዳቸውን የሚያረጋግጠው እንዲምሉለት በማድረግ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ጭንቅሎ እንዲህ ሲል ይተርከዋል:: ‹‹የልጅነት አበባዬን ይቅጨው!›› እያልኩ በውሸት ብዙ ጊዜ ምያለሁ፡፡ አንዴም ግን ተቆጥሮብኝ አያውቅም፡፡ እናቴ ሳትሞትብኝ ቤት እያለች ‹የእናቴ አጥንት እሾክ ሆኖ ይውጋኝ!› ብዬም አውቃለሁ። እናቴ ግን እስካሁን በህይወት አለችልኝ፡፡ ረጅም እድሜ ለሷ! ረጅም እድሜና ጤና ለእናቴ! አምላክ በልጅነታችን የመሀላን ክብደት እንደማንረዳ ስላወቀ መሰለኝ ይቅር ያለኝ ፤ይቅር ያለን ፡፡ ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› ዐቢይ መቼት ሀረር ነው። ደራሲው ተስፋዬ አለነ በጭንቅሎ፤ በጠይሜና በጠንቤ በኩል በውብ ቋንቋ የሚተረክልን የሀረርን የልጅነት ህይወት ነው፡፡ እነዚያን ሁሉ የልጅነት ታሪኮች ከደቂቃ በፊት የተከሰቱ ያህል ፤ደራሲው የልጅነት ዘዬአችንን አንድም ሳይቀር ማስታወሱ በእጅጉ አስደምሞኛል፡፡ ቦታ፤ አገርና ርቀት ሳይወስናቸው የልጅነት መልኮቻችን ተመሳሳይ እንደሆኑ ይህ መጽሐፍ አጠናክሮልኛል፡፡

ማክሲም ጎርኪ የተረከው የራሺያ ልጅነት፤ ዘነበ ወላ በ‹ልጅነት› የተረከው የጨርቆስ (አዲስ አበባ ) ልጅነት ፤ አዳም ረታ በ‹ ግራጫ ቃጭሎች ›ውስጥ ያቀረበልን የንፋስ መውጫ ( ጎንደር) ልጅነት፣ ተስፋዬ አለነ ‹‹በመንጌ ውሽሚት› ካቀረበልን የሐረር የልጅነት ሕይወት ጋር የሚያስተሳስራቸው አንድ ክር ያለ ይመስላል፤ በሁሉም ውስጥ አብዝተን የምንናፍቀውን የህፃንነት ዘመን የሕይወት ትወናችንን እናገኛለን። በሕፃን አእምዕሯችን እውነት ላይ ለመድረስ፤ ሕይወትን ለመረዳት፤የአዳዲስና እንግዳ ነገሮችን ምንነት ለማወቅና ለመገንዘብ የምናደርገው የሐሳብ አርምሞና ተመስጦ በሁሉም ውስጥ ይስተዋላል፡፡ ‹ለከፋ› በሚለው ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ አዲስና እንግዳ የሆነበትን ነገር ለመረዳት የሚያደርገውን ጥረት እንመልከት፡- ‹‹…ይሄ .. ክብረ ንጽህና የሚባለው ነገር ምን ዓይነት እቃ ቢሆን ነው በጉልበቱ የወሰደባት? ግራ ገባኝ፡፡ ‹‹ቀለበት፤ ሀብል፤ ኮፍያ፤ ፎጣ፤ ደብተር ተነጠቁ !›› እንጂ ‹ክብረ ንጽህና ተነጠቁ›› ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ እናቴን እሷም ክብረ ንጽህና እንዳላትና እንደሌላት፤ እንደተነጠቀችና እንዳልተነጠቀች ወሬያቸውን ሲጨርሱ እንደምጠይቃት ተማምኜ ማድመጤን ቀጠልኩ።… ‹‹ለከፋ›› እና ‹‹ከእብደት በስተጀርባ›› በሚሉት ታሪኮች ውስጥ ተስፋዬ አለነ የእብደትን ልዩ መልኮች ያስቃኘናል፡፡ ብሪቱ፤ ዘርፌ (ዘርፈሽዋል)፤ ቀሽቲ፤ ተወልደ እና መሊ ( ሚሊዮን) አስገራሚ የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው፡፡ ከእብደቷ በስተጀርባ ቀሽቲ ልዩ ተልዕኮ አላት፤ በአለባበስና በድምጽ ፆታዋን ቀይራ፤ ራሷን ጥላ፤ ድሪቶ ለብሳ፤ ትራፊ በልታ በኦሮምኛ እየቀባጠረች ለኦነግ ትሰልላለች፡፡

ጭንቅሎ፣ ጠይሜና ጠምቤ በድንጋጤ አፋቸውን እስኪይዙ ድረስ የቀሽቲን መጨረሻ በዐይናቸው ይታዘባሉ፡፡ በመጽሐፉ ‹‹የፈረንሳይ ካራቴ›› በሚለው ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ ለየት ያለ የቪዲዮ ቤት ገጠመኙን ይተርክልናል፤ ትንፋሻችንን ቁ-ር-ጥ-ቁ-ር-ጥ እስኪልብን ድረስ፡፡ ታሪክን በጽሑፍ በመተረክ እንደሲኒማ የሰውን ትኩረት ይዞ መቆየት መቻል ብዙ ደራሲዎች የሚታደሉት ስጦታ አይደለም፡፡ … ማሙሸት ቪዲዮ ቤት፣ የተመረጡ ጎረምሶች ብቻ ሲመሻሽ አንድ ፊልም በሽልንግ ያያሉ፡፡ማንኛውም ሙጫጭሬ መክፈል ቢችልም መግባት አይፈቀድለትም፡፡ የፊልሙ ማስታወቂያ ብዙ ጌዜ እደጅ አይለጠፍም፡፡ ፊልሙ ሚስጥር ነው፡፡ እኔና ጠንቤ አናውቅም፡፡ ጠይሜ ግን የሆነ ጭምጭምታ ሳይሰማ አልቀረም፡፡ ወንድሙ የማታ ማታውን ፊልም ማየት ስለሚፈቀድለት አውርቶለት ይሆናል፡፡.. ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ‹‹ የቢሾፍቱ ቆሪጦች›› በተሰኘው ልቦለድ ውስጥ የቢሾፍቱ ሕፃናትን ‹‹ማቲዎች›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ተስፋዬ አለነ ከላይ ከመጽሐፉ በቀነጨብነው አንቀፅ እንደተመለከትነው የሐረር ሕፃናትን ‹‹ሙጫጭሬ›› ይላቸዋል። የአዲስ አበባ ደራሲያን በበኩላቸው ህፃናትን በድርሰቶቻቸው ውስጥ ‹‹ፈልፈላዎች›› ሲሏቸው እንመለከታለን፡፡

ሕጻናት በቢሾፍቱ፣ በሐረርና በአዲስ አበባ እንዲህ በተለያየ ቃል ይገለፃሉ፡፡ አማርኛው በዚህ መልኩ ከሁሉም ቃላትን እየወሰደ ይዳብራል፡፡ ጭንቅሎ አስገራሚ የቪዲዮ ቤት ገጠመኙን መተረኩን ቀጥሏል፡፡ … …ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንሳይ ካራቴን ያየሁት ከእህቴ ከመሳይ ጋር ነበር፡፡ ታገል፤ መሳይን ይዣት ከመጣሁ ሁሌ ፊልም በነጻ እንደሚያስገባኝ ቃል ገባልኝ፡፡ ብቻዬን …እነ ጠይሜን ትቼ መግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት፡፡ ለሦስታችንም በነጻ ፈቀደልን፡፡ መሳይን አስይዤ ጓደኞቼን ፊልም ጋበዝኩ፡፡… የመጽሐፉ ደራሲ ተስፋዬ አለነ፤ በዚህ የመጀመሪያ የልቦለድ ድርሰቱ የሐረርን የልጅነት ዘመን በጥልቀትና በስፋት ማስቃኘቱ እንዳለ ሆኖ፤ እግረ መንገዱን ከሁለት ዓሥርት ዓመታት በፊት በሐረርና በዙሪያዋ የነበሩትን ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኹነቶችን ኪናዊ በሆነ መልኩ አቅርቦልናል፤ ከኪነ ጥበብ ሥራ በላይ ዘመንን ቁልጭና ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ የለምና ተስፋዬም በ ‹‹መንጌ ውሽሚት” በወቅቱ የነበረውን ሁለንተናዊ የዘመን መንፈስ በደንብ ያሳያል- የዘመኑ አስከፊ ገጽታም አይቀረውም፡፡ ለአስረጂነት በመጽሐፉ ገፅ 191 ላይ የሚገኘውን ተከታዩን ክፍል መመልከቱ በቂ ነው፡፡ …የደንገጎው ውጊያ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ‹በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ›ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣቶች አንዱ የሆነው ፊልጶስ ሰለሞንን የበላ የጦር አውድ ሆኖ አልፋል፡፡ እኚያን ኳስ ለመምታትም ለመሮጥም ፈጣን የነበሩ እግሮች ከባድ መሳሪያ ጎመዳቸው።

ፊሊጶስ በቅጽበት ያፈረሱትን መልሰው መገንባት በማይችሉ ሰዎች በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ተመትቶ ግማሽ ሰው ሆነ፡፡ ከወገብ በላይ እንጂ ከወገብ በታች አካል የሌለው አዲስ ፍጥረት። ከመሰቃየት እንዲገላገል አብረውት በውጊያው ተሰልፈው የነበሩት አባቱ ሻምበል ባሻ ሰለሞን ገብረ እየሱሰ፤ዓይኖቻቸውን ጨፍነው ‹‹ቻው! ልጄ…እጄ እንጂ ልቤ መቼም አይጨክንብህም !›› ብለው እያለቀሱ ጨረሱት፡፡ በቀጣይዋ ጥይት የራሳቸውን ጭንቅላት በራሳቸው ጣት በተሳበ ቃታ አፈንድተው የልጃቸው ሬሳ ላይ ወደቁ ፡፡… ከተስፋዬ የወደድኩለት ጫወታ አዋቂነቱን ብቻ አይደለም፡፡ የርዕስ አመራረጡንም ጭምር እንጂ፡፡ የብዙዎቹ ታሪኮች ርዕስ እንደሚያስጎመዥ ማዕድ ፍላጎትን ያንራሉ፡፡ እንደገናም ደግሞ ከአእምሮ ይቀራሉ፤ ለአፍ ይቀላሉ፡፡ ‹ የጢቢኛ ፍቅር›፣ ‹አወይ ቀላድ አምባ› ፣‹የድድ ማስጫ ልጆች›፣‹ዱርዬው ባንድ› የሚሉት እና ሌሎችም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ለዘለቄታው ከአእምሮ ውስጥ እንዳይጠፉ ተደርገው በደራሲው ብዕር ተከትበዋል፡፡

ደራሲው መግቢያ አጻጻፍ፣ ምስጋና መዘርዝር ላይ አዲስ ዘዬን ለመከተል የሞከረበትን መንገድ ግን ብዙም አልወደድኩለትም፡፡ ቀጥታ ወደ ታሪኮቹ ቢዘልቅ አልኩኝ፡፡ የ‹‹መንጌ ውሽሚት›› የሚለው ታሪክ የመጽሐፉ መጠሪያ እስከሆነ ድረስ ልቦለድ ይሁን ታሪክ ቀመስ ትርክት ቁርጡን ቢነግረን መልካም ነበር፡፡ መፅሐፉን ካነበቡ ወዳጆቼ ጋር ባደረግሁት ውይይት ‹‹ እውነተኛ ታሪክ ነው አይደለም” በሚል ብዙ ተሟግተናል፡፡ ደራሲው ሙግቱን የፈለገውና የፈቀደው ይመስላል። በመጨረሻም ይህንን መጽሐፍ የዚምባቡዌው ሰውዬአችን አንብበውት ይሆን ብዬ አሰብኩና ፈገግ አልኩኝ፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 4096 times