Monday, 27 May 2013 13:14

“አይጧ ከሌለች፣ ጉድጓዱ ከየት መጣ?” - የወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“የሠራሁት ፊልም አንድ ተጨማሪ ተመልካች ካስከፋ ሥራዬን ሠርቻለሁ ማለት ነው!” ዉዲ አለን

 አንዳንድ ዕውነቶች ሲያረጁ ተረት ይመስላሉ፡፡ በአንድ አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ አንድ ዕብድ ሰውዬ መንገድ ላይ በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ቆሞ፤ “እዚህ አገር ስኳር የለም!” “እዚህ አገር ዘይት የለም!” “እዚህ አገር ዱቄት የለም!” እያለ እየጮኸ ይናገራል፤ አሉ፡፡ ከዚያም የመንግሥቱ የፀጥታ ሠራተኞች ይይዙና ወደ እሥር ቤት ይወስዱታል፡፡ አስፈላጊውን ጥያቄዎች ያደርጉለትና ወደ አንድ ክፍል ይወስዱታል፡፡ ከዚያም፤ “እሺ፤ ስኳር የለም አደለም ያልከው፤ ና ላሳይህ” ይለዋል የፀጥታ ሠራተኛው፡፡ ወስዶ የስኳር ዶንያ ጋ ያደርሰውና ማጅራቱን ይዞ ባፍ - ጢሙ ስኳሩ ላይ ይደፋዋል፡፡ ሰውዬውም ፊቱ ስኳር በስኳር ሆኖ ይነሳል፡፡ ቀጥሎ ወደ ሌላ ክፍል ይወስደውና፤ “እህ አጅሬ! ዱቄት የለም አደለ ያልከው?” ይላል የፀጥታ ኃላፊው፡፡

“አዎ!” ይላል እሥረኛው፡፡ “በል ና አሳይሃለሁ!” ይላል ኃላፊው፡፡ ይወስድና ያንን እሥረኛ፤ ዱቄት ጆንያ ውስጥ፤ ጭንቅላቱን ይዞ ባፍጢሙ ይደፋዋል፡፡ ከጆንያው ጭንቅላቱን ይዞ ሲያወጣው ያገር ዱቄት ቅሞ ይነሳል፡፡ ደሞ ሌላ ክፍል ወስዶ፤ “አጅሬ ዘይት የለም! አደለ ያልከው? ና ላሳይህ!” ወስዶ ጭንቅላቱን ይዞ ዘይት በርሜል ውስጥ ባፍ - ጢሙ ይደፍቀዋል፡፡ በመጨረሻ በል ውጣና ሂድ ይለዋል፡፡ እሥረኛው - ከእሥሩ ቅጽር ጊቢ ሲወጣ አንድ ዱሮ የሚያውው ሰው ያገኘውና፤ “እንዴ! አያ እገሌ ተለቀቅህ?” “አዎ!” “ምን አደረጉህ?” “ኧረ ተወኝ ምን ያላረጉኝ ነገር አለ! ብቻ እንኳን በርበሬ የሌለ፤ ጉድ ሆኜልህ ነበር!” ይለዋል፡፡ ቀጥሎ፤ “እዚህ አገር በርበሬ የለም! እዚህ አገር በርበሬ የለም!!” እያለ የመንገድ ላይ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡

                                                      * * *

የተበደለ ህዝብ ጩኸቱን መቀጠሉን አይተውም፡፡ ያለውን አለኝ የሌለውን የለኝም ይል ዘንድ አንደበት ተሰጥቶታል፡፡ መብቱን ይረዳል፡፡ ነፃነቱን ያውቃል፡፡ ከተራቆተ ታረዝኩ፣ ፍትሕ ከጐደለው ተበደልኩ፣ ከተዘረፈ ተበዘበዝኩ ይል ዘንድ ልሣን አለው፡፡ እጀ - ሠባራ እንዳይሆን መሥራት፣ የታፈነ እንዳይሆን የመናገርና ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን መጠቀም፣ የሚያየውን ጉድለት ማሳየት ይገባዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የሚታዘበውን ሙስና ለአደባባይ ፀሐይ ማብቃት ይገባዋል፡፡ እርምጃ የሚወስደውን አካል በጥንቃቄ ማበረታታት ያሻል፡፡ በታሪክ እንዳየነው “ንጉሡ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ ቢጠየቁ አሻፈረኝ አሉ!” ተብሎ አይታለፍም - ስዊስ ያስቀመጡትን ገንዘብ መሆኑ ነው፡፡ ጆርጅ በናርድ ሾው የተባለው ታዋቂ የሒስና የምፀት ሰው፤ “ለማንኛውም ትንሽ ሴንሰርሺፕ ያስፈልጋልኮ” ተብሎ በባለሥልጣን ሲነገረው፤ “በትንሹ ማርገዝ የሚባል ነገር መኖሩን ካሳመንከኝ ትንሽ ሴንሰርሺፕ ያልከውን ነገር እቀበላለሁ!” ብሎ ነበረ፡፡ ይህን መንግሥታችን ልብ ይበል!! ዕውነቱን ነው የግፍ ትንሽ የለውም፡፡ የማያድግ በደልም የለም - ጊዜና ቦታ ካለ፡፡ ሰንሰለቱ ከታወቀ ስለቀለበቱ ማውራት ድካም ይሆን ይሆናል፡፡ ያላግባብ የሚሰጥ ፍርድም ሆነ ያላግባብ የተካበተ ገንዘብና ንብረት፤ ሁለቱም ለሀገርና ህዝብ በደል ናቸው፡፡ ፀሐፍት፤ “They shout at most against the vices they themselves are guality of” ይላሉ፡፡

ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ፤ እንደማለት ነው በዙር - አማርኛ፡፡ ትላንት ሙሰኞችን እናወድማለን ያሉ፣ ዛሬ ሙሰኛ ሆነው ሲገኙ ልንል የምንችለው አንድ ሁነኛ ቃል - “ጠርጥር!” ነው፡፡ ልባችን ሙስና አፋችን ፀረ - ሙስና ሲሆን፤ ጥርጣሬ ፎቁን ሲሰራ ማየት አይገርምም! “ማንኛው ይሆን ሀቀኛ?” “የቱ ይሆን ዕውነተኛ ንግግር?” ብሎ መጠራጠር ጥፋት አይሆንም፡፡ ሃሳብ አቅራቢም፣ ወሰኝም፣ አስፈፃሚም፤ የተወሰነ ሰው የሆነበት ሥርዓት ካለ ጤና አይኖርም፡፡ ፈረንጆች absolute power corrupts absolutely! የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ “ፍፁም ሥልጣን ፍፁም ሙሰኛን ይወልዳል” እንደማለት ነው፡፡ ሁሉን ማዘዝ ከቻልኩ ማን አለኝ ከልካይ! ብሎ መደገግ አይቀሬ ነው፡፡ አደባባይ ላይ ተንፈራጥጦ የቆመህን ህንፃ ካላሳዩ እርካታ አይመጣም፡፡ “እቺ ምን ሰማይ ነች፣ በዐይን የምትታይ?” እንዳለው እብሪተኛ ንጉሥ ጣራ አልበቃ ይለናል፡፡ “ጣራው ጣር እንደሚሆንብን” እንዘነጋለን፡፡ የወደቁት ያጠፉት ጥፋት በእኛ አይደገምም እያልን እንፎክራለን፡፡ ያለነው ግን እዚያው ውቂያኖስ ውስጥ ነው፡፡

እንጠንቀቅ! የውቂያኖሱ ሥርዓተ ማዕበል አንድ ነውና፡፡ ማኪያቬሊ “ሰዎች የአስቸኳይ ጥቅምና ፍላጐታቸው ተገዢ ከመሆናቸው የተነሳ አታላይና አጭበርባሪ ሰው ከመጣ ለመታለልና ለመጭበርበር ዝግጁ ናቸው” ይለናል፡፡ አጋጣሚው የፈቀደላቸው እንዳታለሉ ይኖራሉ፡፡ ያልቀናቸውና የተነቃባቸው የእሥር ቤት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ እንጂ ሥርዓቱ አልተለወጠም፡፡ ቁልፉ ጉዳይም ይሄው ነው፡፡ ሥርዓቱ በምን ይለወጥ? እስከመቼ፤ እንደወላይትኛው ተረት “አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?” እያልን ቁጭ ብለን እናያለን? የተጀመው መንገድ ከቀጠለ አይጧን ማጥመድም ሆነ፣ ጉድጓዱን መድፈን እንችላለን፡፡ “ወዳጅህን ከጐረቤት ታገኛለህ፡፡ ጠላትህን እናትህ ትወልድልሃለች” ይላል አበሻ፡፡ ከጉያችን ያለውን እንፈትሽ፡፡

የተቋጠረውን እየፈታን፣ የተዘጋ የሚመስለውን እየከፈትን፣ አደባባዩን ምሽግ ያደረገውን እየደረመስን፣ ወመቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ፣ ቱሪስቱን ከፒስኮር፣ ህንዱን ከባኒያን፣ ጭልፊቱን ከአሞራው፣ የፖለቲካ ነጋዴውን ከሀቀኛ መንገደኛው፤ ለይተንና አበጥረን መጓዝ ለሀገርና ለህዝብ የሚመች አጓጓዝ ነው፡፡ ጐረቤትንም ልብ እንበል - ዓለም አላፊ ነው፣ መልክ ረጋፊ ነው! ያኔ፤ የተሳካ ሥራ ለመሥራታችን የራሳችን ልበ - ሙሉነት ማረጋገጫ ሲሰጠን፤ እንደፊልም ተዋናዩ ኮሜዲያን እንደዉዲ አለን፤ በምፀት፤ “የሠራሁት ፊልም አንድ ተጨማሪ ተመልካች ካስከፋ፣ ሥራዬን ሠርቻለሁ” ለማለት እንችላለን!!

Read 3567 times