Saturday, 11 May 2013 13:04

ጊዮርጊስ በኮንፌደሬሽን ካፕ ከሌላ የግብፅ ክለብ ተገናኘ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን በመወከል እስከ 2ኛ ዙር ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ተጉዞ በግብፁ ክለብ ዛማሌክ የተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፍ ተሸጋግሮ ከሌላው የግብፅ ክለብ ኢኤንፒፒአይ ጋር ተደለደለ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ውጭ የሆነው ከሳምንት በፊት ከግብፁ ዛማዜክ ጋር አዲስ አበባ ላይ የመልስ ጨዋታውን አድርጎ 2-2 አቻ በመለያየቱ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ የሁለተኛ ዙር ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ውጤት 3ለ3 ቢሆኑም ዛማሌክ ወደምድብ ድልድል የገባው ከሜዳ ውጪ ብዙ ባገባ በሚለው ህግ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል ለመግባት ሳይችል ቢቀርም በውድድር ዘመኑ በአፍሪካ የክለብ ውድድር ያለውን ተሳትፎ ቀጥሏል፡፡

በኮንፌደሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፍ 16 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን የመጀመርያው ዙር ግጥሚያዎች ከሳምንት በኋላ ይካሄዳሉ፡፡ ጊዮርጊስ ከግብፁ ክለብ ጋር በኮንፌደሬሽን ካፑ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታውን የዛሬ ሳምንት በሜዳው ያደርጋል፡፡ በሌሎች ጨዋታዎች የማሊው ስታድ ዴማሊ ከብሩንዲው ኤልኤል አካዳሚ፤ የናይጄርያው ኢኑጊ ሬንጀርስ ከ ቱኒዚያው ሳፋክሲዬን፤ የሞሮኮው ኢፍዩኤስ ራባት ከሌላው የሞሮኮ ክለብ ኤኤስኤፍ ራባት፤ የቱኒዚያው ቤዘርቲን ከግብፁ ኢስማኢሊያ፤ የአልጄርያው ሴቲፍ ከጋቦኑ ዩኤስ ቢታም እንዲሁም የዲሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ከሞዛምቢኩ ሊጋ ሙኩሉማና ይገናኛሉ፡፡

ጊዮርጊስ ከግብፁ ክለብ ኢኤንፒፒአይ ጋር በአፍሪካ ደረጃ ሲገናኝ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በ2006 እኤአ ላይ በሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ተገናኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ የመጀመርያው ጨዋታ ካይሮ ላይ ሲደረግ ያለምን ግብ አቻ የተለያዩ ቢሆንም በመልሱ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ኢኤንፒፒአይን 1ለ0 አሸንፎ ወደ ሁለተኛ ዙር ለመሸጋገር እንደበቃ ይታወሳል፡፡2 የውጭ ፕሮፌሽናሎችን ጨምሮ 27 ተጨዋቾችን በስብስቡ የያዘው የግብፁ ክለብ ኢኤንፒፒአይ በ48 ዓመቱ ግብፃዊ ታሬክ ኤልአሽሪ ዋና አሰልጣኝነት የሚመራ ነው፡፡

Read 2867 times