Saturday, 11 May 2013 13:12

የጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር፣ ምክትላቸውና ባለሃብቶች ታሰሩ

Written by 
Rate this item
(41 votes)

ተጨማሪ የሙስና ተጠርጣሪዎች ዛሬ እንደሚታሰሩ ምንጮች ተናግረዋል

የጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንቴና ምክትል ዳሬክተሩ አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም የ“ኬኬ” ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደን ጨምሮ አስራ ሁለት ግለሰቦች በሙስና ተጠርጥረው አርብ ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ባለሥልጣናትና ባለሃብቶች አርብ ጠዋት ከያሉበት በፖሊስ ተይዘው እንደተወሰዱ የገለፁ ምንጮች፤የቤት ብርበራ ሲካሄድ ማምሸቱንም ተናግረዋል፡፡ የፀረሙስና ኮሚሽን ማታ ሁለት ሰዓት ላይ በኢቴቪ በሰጠው መግለጫ፤ የጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተርና የሚኒስትሮች ካቢኔ አባል አቶ መላኩ ፈንቴ እና ምክትል ዳሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በሙስና ተጠርጥረው እንደታሰሩ ተገልጿል፡፡ ከሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ባለሃብቶችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ኮሚሽኑ ገልፆ፤ ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ጋር በመተባበር ምርመራ ማካሄዱን ተናግሯል፡፡

ከበርካታ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች የቀረቡ አቤቱታዎችና ጥቆማዎች ለምርመራው እንዳገዙት ኮሚሽኑ ጠቅሶ፤ ተጠርጣሪዎቹን ወደ ፍ/ቤት በማቅረብ ክስ እመሰርታለሁ ቢልም ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉት ባለሃብቶች መካከል የሚጠቀሱት አቶ ከተማ ከበደ፤ ተጠርጥረው ከታሰሩት ባለሃብቶች አንዱ ሲሆኑ በበርካታ የኢንዱስትሪና የንግድ መስኮች የተሰማራው “ኬኬ” ኩባንያ ባለቤት ናቸው፡፡ ከ20 ዓመት በፊት የተመሠረተው “ኬኬ” ኩባንያ፤ አጀማመሩ ከትንሽ ደረጃ ላይ የተነሳ ስለነበር ሥራው የሚመራውና አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው በድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ እንደነበር የድርጅቱ ይፋዊ መረጃ ይገልፃል፡፡

በልብስና በቀለም ምርት የተሰማራው “ኬኬ”፤ የከባድ ማሽነሪዎች አስመጪ በመሆንም በስፋት ይታወቃል፡፡ ከጊዜ በኋላም በቡና ኤክስፖርት እንዲሁም በእርሻ ኤክስፖርትና በማዳበርያና ተባይ ማጥፊያ ምርቶች አስመጪነት በመሰማራት ሥራውን እንዳስፋፋ የድርጅቱ መረጃ ይዘረዝራል፡፡ የሚኒስትሮች ካቢኔ የሆኑት አቶ መላኩ ፈንቴ ከሥልጣናቸው ይነሳሉ ተብለው ለወራት ሲወራ የነበረ ሲሆን ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ደግሞ ባለፈው የካቲት ወር በፓርቲው ውስጥ ከነበራቸው ሃላፊነት መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ በተያያዘ ዜና፣ አርብ እለት ከተፈፀመው እስር እንዲሁም ሌሊቱን ሙሉ ከተካሄደው የተጠርጣሪዎች ቤት ብርበራ በተጨማሪ፣ ዛሬ ቅዳሜ እለትና በቀጣዮቹ ቀናት በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሎሎች ተጠርጣሪዎች እንደሚኖሩ ምንጮች ጠቁመዋል።

Read 9473 times Last modified on Monday, 13 May 2013 08:51