Saturday, 11 May 2013 11:33

“ጉራማይሌ ቋንቋ፤ ጉራማይሌ ማንነት ይሆናል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ባለፈው ሳምንት በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት አካባቢ በርካታ ወጣቶች “ጉራማይሌ ቋንቋ፣ ጉራማይሌ ማንነት ይሆናል” የሚል ጥቅስ የታተመበት፤ ወይንጠጅ ቀለም ያለው ተመሳሳይ ቲሸርት ለብሰው በጋራ ሲጓዙ ትኩረቴን ሳቡት። እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች መንገደኞችም በነገሩ መሳባቸው አልቀረም፡፡ አንዳንዶች እንደውም ቀረብ ብለው ሲጠይቁ ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ ቲ-ሸርቱ ላይ የሰፈረው ጥቅስ መልዕክት ምንድነው? ሃሳቡን ካመነጩት ስድስት ወጣቶች ጋር ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ በቲ-ሸርት ላይ መልእክት ለማስተላለፍ መነሻና ምክንያት የሆናችሁ ምንድነው? የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የማታ ተማሪዎች ነን፡፡

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል ለሦስት ዓመታት የተሰጠንን የአማርኛ ቋንቋ አጠናቀን የዚህ አመት ተመራቂዎች ስለሆንን ደስታችንን በምን እናድምቅው ብለን ስናስብ፣ በአማርኛ ቋንቋ ዙሪያ የሚታይ ችግርን የሚያመለክትና የሚያወያይ መልእክት ማስተላለፍ ስለፈለግን “ጉራማይሌ ቋንቋ፣ ጉራማይሌ ማንነት ይሆናል” የሚል ጥቅስ በቲ-ሸርት ላይ አሳትመን በመልበስ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ምን ያህል ተማሪዎች ናችሁ ለዚህ ዓላማ በጋራ እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት? በእኛ ዲፓርትመንት በማታው ክፍለ ጊዜ የምንማር ተማሪዎች ብዛት 116 ስንሆን በሦስት የተለያዩ ክፍሎች ነው የምንማረው፡፡ በምረቃችን ዋዜማ በጥቅስ መልእክት የማስተላለፉ ሀሳብ የመነጨው በአንደኛው ክፍል በምንገኝ ስድስት ጓደኛሞች ቢሆንም አሁን ሁሉም የማታው ክፍለ ጊዜ ተመራቂ ተማሪዎች ደግፈውት በጋራ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ ላይ ተጋርጧል የምትሉት ችግር ምንድነው? ቋንቋው ላይ ችግር ተከስቷል ብለን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በጋራ እየተንቀሳቀስን ካለነው ተመራቂ ተማሪዎች መሀል አንዳንዶቻችን በግልም፣ በመንግሥትም ትምህርት ቤቶች ስለምናስተምር በተግባር ብዙ ችግር በየእለቱ እናያለን፡፡

ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ወስጥ አማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ የሚከለክሉ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የሚናገር ተማሪ ሀፍረት እንዲሰማው የሚያደርግ ተግባር ሲፈፀምባቸው ይታያል፡፡ አማርኛ ቋንቋ ከትምህርት ቤቱ ግቢ በ200 ሜትር ርቀት ብቻ ነው መናገር የሚቻለው የሚል ሕግ ያወጡ ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ ወላጆች የትኛው ትምህርት ቤት ነው እንግሊዝኛ ጥሩ የሚያስተምረው እያሉ ነው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገቡት፡፡ ይህ ልማድ በጊዜ ካልተቀጨ በጥቂት አመታት ውስጥ ወጣቶች ለማንነት ቀውስ ችግር መጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ይህ አደጋ መነጋገሪያ እንዲሆን በመሻት ነው እኛም ጥቅሱን አሳትመን በመልበስ በመንቀሳቀስ ላይ ያለነው፡፡ ቋንቋው በንግግር ብቻ ሳይሆን ለፅሁፍም ከማገልገሉ ጋር በተያያዘ ተከስቷል የምትሉት ችግር አለ? አማርኛ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋ እያሳደረበት ባለው ጫና ምክንያት ለችግር መጋለጡን ለሕብረተሰቡ እያመለከቱ ያሉ ሌሎች አካላትም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን የቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ በጌታቸው በልዩ የተሰራ ጥናት አለ፡፡

ከሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች በተሻለ ሁኔታም በአማርኛ ቋንቋ ዙሪያ ብዙ ጥናት ተሰርቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ የአውሮፓውያን አስተሳሰብ በተለያየ መልኩ ጫና እያሳደረብን እንዳለው ሁሉ፣ ቋንቋችን ዋነኛው ሰለባ እየሆነ መምጣቱ በትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ እለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ይታያል፡፡ “ጉራማይሌ ቋንቋ፣ ጉራማይሌ ማንነት ይሆናል” የሚለው መልእክታችን አማርኛ ቋንቋን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም ሌሎች የአገራችን ቋንቋዎችንም ይመለከታል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን ባህል፣ እምነት፣ ወግ፣ ልማድ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ ሀዘን ደስታ… መግለጫ ነው፡፡ የራስን ቋንቋ እንደሚገባው አለማወቅ ለማንነት ቀውስ ችግር ይዳርጋል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ አማርኛ የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ነው፡፡ በአገራችን ልጆች አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ እንዲማሩ ተወስኗል፡፡ በአዲስ አበባ የሚወለድ ልጅ አፉን የሚፈታው በአማርኛ ቢሆንም በትምህርት ቤቶች ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የላቀ ችሎታ እንዲኖረው እየተሰራ ወይም የወላጆች ፍላጐት እንደዚያ እንዲሆን የመፈለግ አዝማሚያ በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ጅማሬ በዚሁ መልኩ እያደገ ከሄደ በማንነታችን ላይ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም፡፡

በየእለቱ ቅላፄያቸው ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተለወጡ የአማርኛ ቃላትን እንሰማለን፡፡ በሙዚቃችን ውስጥ እንዲህ አይነቱ ነገር እየበዛ መጥቷል፡፡ የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ፊደል ያልቆጠሩ እናቶቻችንም በንግግሮቻቸው መሀል ብዙ የእንግሊዝኛ ቃላት ሲጠቀሙ እየሰማን ነው፡፡ ቋንቋ የሚፈጠረውና የሚያድገው አንዱ ከሌላው እየወሰደና እየሰጠ ስለሆነ እንዲህ መሆኑ ምን ይገርማል? ችግሩ መቀባበሉ ላይ ሳይሆን አወሳሰዱ ላይ ነው፡፡ ሁሉም ቋንቋ ሀሳብን ለመግለፅ በራሱ ምሉዕ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ አማርኛ ቋንቋ በአባባል፣ በተረት፣ በእንቆቅልሽ፣ በሥነቃል የዳበረና ሀሳብን ለመግለፅ ምንም ችግር የሌለበት ሆኖ ሳለ፣ በንግግር መሐል እንግሊዝኛ ቃላትን መጠቀም አዋቂና የተማረ ያሰኛል ስለሚባል፤ ፋይዳቸው ምንም የሆነ የእንግሊዝኛ ቃላት በአማርኛ መሀል መጨመር ተለምዷል፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎቻችንን ለፈተና እየተዘጋጃችሁ ነው? ብለን ስንጠይቃቸው “ዌል ዝግጁ ነን” የሚል መልስ ይሰጡናል፡፡ በዚህ መልስ ውስጥ “ዌል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መጨመሩ ያስገኘው ምንም ጥቅም የለም፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ከሌሎች ቋንቋዎች ወስደን የምንገለገልባቸው ብዙ ቃላት አሉ፡፡ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የሚሉትን ቃላት እንደምሳሌ መጥቀስ እንችላለን፡፡

የቴክኖሎጂ ስያሜዎች ወደ አገራችን ሲገቡ በአገራችን አባባል የሚተረጉም አካል አለመኖሩ ለችግሩ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ጀርመኖች የቴክኖሎጂ ቃላትን በራሳቸው አባባል ተርጉመው የቋንቋቸው አካል ያደርጋሉ፡፡ በእኛ አገር ሲሆን የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ ማደግ ጋር የሚፈጠሩ ስያሜዎች በየእለቱ ወደ ቋንቋዎቻችን ይገባሉ። ከዚህም ባሻገር ከበድ ያሉ ፅንሰ ሀሳቦችን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማያስፈልጋቸው አባባልና አገላለፆች ሁሉ የእንግሊዝኛ ቃላትን መጠቀም እየበዛ መጥቷል፡፡ የተቀላቀለ ቋንቋ የሚናገር ሰው በበዛ ቁጥር ቅይጥ ማንነት ያላቸው ሰዎች ይበረክታሉ፡፡ የአማርኛ ቋንቋም የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ይነገራል፡፡ በእኛም አገር “እንግአማ” ላይ ይወድቃል፡፡ ሂንዱ የሚባለው የሕንዶች ቋንቋ በእንግሊዝኛ ተፅእኖ ስር ወድቆ የመጥፋት አደጋ እየተፈጠረ ስለሆነ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚባለው መፍጠን ይኖርብናል፡፡ “እንግአማ” ምንድነው? እንግሊዝኛና አማርኛ ከሚሉት ሁለት ቃላት ተውጣጥቶ የተገኘ ቃል ሲሆን በሁለቱ ቃላት የተመሰረተ አዲስ ቋንቋ ለማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ማንነት ሊኖረው አይችልም፡፡ “እንግአማ” ሁለት ማንነት ይፈጥራል፡፡ አማርኛ ቋንቋ በዘይቤ የወሎ፣ የጐንደር፣ የጐጃም፣ የሰሜን እና የሸዋ በሚል በአምስት የተለያዩ ክፍሎች ይመደባል፡፡ የገጠር አማርኛ ተናጋሪዎች ሁሉ የእንግሊዝኛ ቃላትን እየደረቱ ሲጠቀሙ መስማት ተለምዷል፡፡ ቋንቋችን ጉራማይሌ ከሆነ ማንነታችንም ጉራማይሌ ይሆናል። አንድ የሬዲዮ ጋዜጠኛ “Part of the body” የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ ተናግሮ አብሮት ለሚወያየው የሥራ ባልደረባው “በአማርኛ ምንድነው የሚባለው?” ብሎ ትርጉም ሲጠይቀው ሰምተናል፡፡

ችግሩ እስከዚህ ድረስ ሰፍቶ የሚታይ ነው፡፡ እኛ እንግሊዝኛ ቋንቋን እያጥላላን አይደለም። እንግሊዝኛን ማወቅ የለብንም አላልንም። እንግሊዝኛን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአገርና የዓለም ቋንቋዎችንም ማወቅ ብንችል አንጐዳም፡፡ ማንነታችን ላይ ቆመን ሌላውን ለማወቅ ካልጣርን ግን ጉራማይሌ ማንነት ነው የሚኖረን፡፡ በአገር ውስጥ በሌሎች ቋንቋዎች ጫና ምክንያት ጉዳት ሲደርስበት የሚከላከልለት የሌለ የሚመስለው አማርኛ ቋንቋ፤ አሜሪካንን በመሳሰሉ ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሚኖሩባቸው አገራት እንግሊዝኛን አሸንፎ ለመነጋገሪያነት መዋሉን እንሰማለን፡፡ ቻይናም በአገሯ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ዜጐቿ እንዲማሩ እያደረገች ነው፡፡ ሌሎች ይህን ያህል ዋጋ ከሰጡት እኛ ከነሱ በላይ ልናከብረውና ልንጠነቀቅለት ይገባል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በአገር ውስጥ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ይሰጣል፡፡ የተለያዩ መፃህፍትም ይታተማሉ፡፡ ቋንቋውን ለመጠበቅና ለማዳን በተለይ ሕብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ሰፊ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ለዓላማችሁ ድጋፉን የሰጠ ማን አለ? ተቃውሞስ አልገጠማችሁም? ያለውን አደጋ መከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ለማስጨበጥ ስንነሳ መምህር ደብሬ “ጉራማይሌ ቋንቋ፣ ጉራማይሌ ማንነት ይሆናል” የሚለውን ጥቅስ በመስጠት ተባብራናለች፡፡

መምህር የሻው ተሰማን መሰል መምህራንም ጥሩ ነው በማለት አበረታተውናል፡፡ ጥቅስ የታተመበትን ቲ-ሸርት ለብሰን በየአደባባዩ ስንንቀሳቀስ የሚያዩን ሰዎች ዓላማችንን እየጠየቁን ስንነግራቸው እንድንበረታና ሀሳቡን ለሚመለከታቸው አካላት እንድናደርስ በርቱ ይሉናል፡፡ ተቃውሞ ግን እስካሁን አልገጠመንም፡፡ ተመርቃችሁ ከወጣችሁ በኋላስ ለዚህ ዓላማችሁ ለመንቀሳቀስ ምን እድልና ተስፋ አላችሁ? አብዛኞቻችን አስተማሪ ስለምንሆን በተማሪዎቻችንና በትምህርት ቤታችን አካባቢ የምንሰራው ነገር ይኖራል፡፡ ስብስባችንም ሳይበታተን ለዚሁ ዓላማ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የእግር ጉዞን መሰል የቅስቀሳ መድረኮች የማሰናዳትም እቅድ አለን። የምረቃችንን ዋዜማ በጭፈራና ሆይ ሆይታ ሳይሆን እንዲህ ባለ ቁምነገር ላይ ማሳለፋችንም እያስደሰተን ነው፡፡

Read 4256 times