Saturday, 11 May 2013 11:17

የአሜሪካ “ጨካኝ አጋች”፣ ለአገራችን “ቆፍጣና ባል” ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአሜሪካ፣ “serial killer” ተብሎ በፖሊስ የሚታደን ሰው…

በኛ አገር “አርበኛ” ወይም “ጀግና” ተብሎ ሊወደስ ይችላል (በአብዮቱ አመታት ሲተላለቁ እንደነበሩት አብዮተኞች)

በፈረቃ ከምትሰራበት በርገር ኪንግ እንደወጣች ጠፍታ የቀረችው አማንዳ ቤሪ፣ “ፊቷን አየሁ፤ ድምጿን ሰማሁ” የሚል ሰው ሳይገኝ 11 አመታት አልፈዋል። የጠፉ ልጆችና ልጃገረዶች፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ተፈልገው ካልተገኙ ብዙውን ጊዜ መጨረሻቸው አሳዛኝ ነው። ተገድለው ነው የሚገኙት። ሳምንት ሙሉ ተፈልጋ ያልተገኘችው አማንዳ፣ ከዚህ ዘግናኝ ህልፈት አትተርፍም የሚል ነበር የመርማሪዎች ግምት። አስገራሚው ነገር ከሳምንት በኋላ፣ ለእናቷ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሰ። የተደወለው ከአማንዳ ሞባይል ነው። የእናቷን ድንጋጤና ጭንቀት ልክ አልነበረውም። ስልኩን ሲያነሱት ግን፣ የልጃቸውን ድምፅ አልሰሙም። ሞታለች የሚል መርዶም አይደለም። ከአማንዳ ጋር ተጋብተን ሚስቴ ሆናለች የሚል የወንድ ድምፅ ነው የሰሙት። በኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ብንተረጉመው፣ “ጠልፌ ወስጃታለሁ፤ ጠልፌ አግብቻታለሁ” እንደማለት ነው። በቃ፣ ስልኩ ተዘጋ።

የአማንዳ እናት መረጃውን ለፖሊስ ቢያደርሱም፣ የፖሊስ ምርመራና ፍለጋ ባይቋረጥም፣ ውጤት አልተገኘም። ከአመት በፊትም፣ ከዚያው አካባቢ አንዲት ወጣት ሴት ጠፍታለች። ከአማንዳ በኋላም እንዲሁ፣ ከተመሳሳይ ቦታ ሌላ የ14 አመት ሴት እንደወጣች ቀርታለች። የት ይግቡ፣ የት ይድረሱ ፍንጭ አልተገኘም። በእርግጥ አንዲት ጠንቋይ በቴሌቪዥን ስርጭት አማንዳ ህይወቷ አልፎ አስከሬኗ ጥልቅ ባህር ውስጥ ሰጥሟል ብላ እንደተናገረችውም አልሆነም። ሶስቱ ሴቶች ከነሕይወታቸው ከአስር አመት በላይ ሲሰቃዩ የኖሩት፣ አማንዳ ከጠፋችበት አካባቢ ብዙም የማይርቅ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው - በሶስት በአራት ኪሎሜትር ርቀት። በኤርየል ካስትሮ ተጠልፈው ከታገቱበት እለት ጀምሮ፣ ሶስቱ ሴቶች ከቀን ቀን፣ ከአመት አመት፣ ቤት እንደተዘጋባቸው መከራ ይበላሉ።

ለመውጣት ቢሞክሩ፣ ድብደባውና እርግጫው! አሁንም በኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ እንግለፀው ከተባለ፣ “ከቤት ንቅንቅ ብትይ እግርሽን እሰብረዋለሁ” እያለ ሚስቱን ነጋ ጠባ የሚያሰቃይ ባል እንደማለት ነው። እንዴት ብትሉ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢቲቪ በሁለት ክፍል ካቀረበው ድራማ መልሱን ማግኘት ይቻላል። “ጠልፎ ማግባት” በህግ የተከለከለ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ለማሳየትና፣ “ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ” ታስቦ የተሰራ ድራማ ነው። እንግዲህ አስቡት። “ጠልፎ ማግባት” ብዙም እንደ ወንጀል ስለማይቆጠር፣ “በሽማግሌና በእርቅ” ሊያልቅ የሚችል ቀላል ጉዳይ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታሰብ… ያን ያህልም “ጉድ! ጉድ! አቤት ጭካኔ!” የሚያሰኝ አይደለም ማለት ነው። እናም፤ “ጠለፋ ወንጀል ነው” እያሉ “በድራማ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት ማድረግ” አስፈለገ። ገና እዚህ ደረጃ ላይ ነን ያለነው። ከኢትዮጵያውያን መካከል ግማሾቹ፣ ባል ሚስቱን የመደብደብ መብት አለው ብለው እንደሚያምኑም ባለፉት አስር አመታት የተካሄዱ ሶስት ተከታታይ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

በአጭሩ፣ ጠልፎ ማግባትና ማሰቃየት፣ ብዙ ጣጣ የለውም። ድብቅነትን አይጠይቅም። በአሜሪካ ግን፣ ጣጣው ብዙ ነው። ጠልፎ ማግባት ይቅርና፣ ሚስትን “የት ወጣሽ የት ገባሽ” እያሉ ማሰቃየት እንደ ተራ ነገር አይቆጠርም። በዝምታ የሚታለፍ ቢሆን ኖሮማ፣ ኤርየል ካስትሮ ከመጀመሪያ ሚስቱ ጋር ባልተለያየ ነበር። የኤርየል ቤትና የሚስቱ ወላጆች ቤት ቅርብ ለቅርብ ቢሆንም፣ እየመጡ እንዲጠይቋት ወይም እየሄደች እንድትጠይቃቸው አይፈልግም ነበር። አንዳንዴ እሱ በማይኖርበት ሰዓት እህቷ ልትጠይቃት ስትመጣ እንኳ፣ በሩ ስለሚቆለፍ መግባት አትችልም። ኤርየል፣ ሚስቱን ቤት ውስጥ ቆልፎባት ነው የሚሄደው። ከዚያም ድብደባ ተጨመረበት። አንዴ አፍንጫዋን ሰብሯታል። ሚስቱን በመደብደቡ ሁለቴ የታሰረው ኤርየል፣ ባህሪውን ሊያሻሽል ስላልቻለ ሚስት በፍቺ ጥላው ወጣች - በፖሊስ ታጅባ። “ሚስቱን ቢደበድብ መብቱ ነው” የሚል አይነት አስተሳሰብ በስፋት የሌለበት አገር ውስጥ፣ “ውልፊት ትይና እግርሽን እሰባብረዋለሁ” እያለ እድሜ ልክ ሚስቱን እያሰቃየ መኖር አይቻልም - ማንም እንዳያውቅ ደብቆ ካላሰቃየ በቀር። ኤርየልም፣ ይህንኑን ነው ያደረገው - ጠልፎ እየወሰደ በድብቅ ማሰቃየት።

እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ በሃይማኖትና በብሄረሰብ ስም፣ በአገርና በህዝብ ስም፣ ሰውን የማጥቃትና የማሰር፣ የማሰቃየትና የመግደል… ቅስቀሳዎች ወይም ዘመቻዎች በየጊዜው በግላጭ ይፈፀሙ የለ? ይህንን የሚፈፅሙ ክፉ ሰዎች፣ ለጭካኔያቸው ሰበብና ማመካኛ አያጡም። እንዲያውም፣ “አገር ወዳድ አርበኛ፣ ቆራጥ አብዮተኛ፣ የቁርጥ ቀን ጀግና”… የሚል ውዳሴ ይጎርፍላቸዋል። ስቃይና ግድያ የሚፈፅሙትም በግላጭ ነው። እንደ አሜሪካ በመሳሰሉ በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ ግን፣ ሰውን በግላጭ ለማሰቃየትና ለመግደል የሚያስችል ሰበብና ማመካኛ ማግኘት ከባድ ነው። ክፉ ሰዎች፣ በግላጭ እንዳሻቸው ጭካኔ እየፈፀሙ በየአደባባዩ መፈንጨት አይችሉም። በድብቅ ስቃይና ግድያ ለመፈፀም የሚሞክሩ ግን አይጠፉም - ለምሳሌ ልማደኛ ነፍሰ ገዳዮች (serial killers)። ልዩነቱን አያችሁት። በኋላ ቀር አገራት ውስጥ፣ ክፉ ሰዎች ለጭካኔያቸው ብዙ አይነት ማመካኛ ማቅረብ ስለሚችሉ፣ በአደባባይ ሰውን እያሰቃዩና እየገደሉም፣ እንደ ጀግና ወይም እንደ አርበኛ ይታያሉ። በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ ግን፣ ክፉ ሰዎች “ልማደኛ ነፍሰ ገዳይነታቸውን” የሚሸፋፍኑበት እድል ስለሌላቸው በፖሊስ ይታደናሉ። እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ “ልማደኛ ነፍሰ ገዳዮች (serial killers) የሌሉ ይመስለናል። በሌላ ስም ስለምንጠራቸው ነው - አርበኛ፣ አብዮተኛ፣ ጀግና እየተባሉ ይጠራሉ። እንደ ኤርየል ካስትሮ፣ በድብቅ የእገታና የማሰቃየት ጭካኔ የሚፈፅሙ ሰዎች በአገራችንና በሌሎች ኋላቀር አገራት የሌሉ ከመሰለ ንም ተሞኝተናል። ሞልተዋል። ግን፣ ጭካኔያቸውን ያን ያህልም መደበቅ አያስፈልጋቸውም። ሳልፈቅድልሽ ከቤት ወጥተሻል ብሎ ሚስቱን ቢደበድብ ብዙም ችግር አይገጥመውማ።

Read 2509 times