Saturday, 04 May 2013 10:30

58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የቦንደስ ሊጋ ሆነች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለ58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጀርመንን የወከሉ ሁለት ክለቦች ለፍፃሜ ጨዋታ መድረሳቸው የቦንደስ ሊጋን የበላይነት አረጋገጠ፡፡ ከ3 ሳምንት በኋላ የቦንደስሊጋ ደርቢ የተባለውን የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታድዬም ሲያስተናግድ ቦርስያ ዶርትመንድ ከባየር ሙኒክ ይፋለማሉ፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በ70 አገራት በ40 የተለያዩ የኮሜንታተር ቋንቋዎች በሚኖረው የቀጥታ ስርጭት ከ120 ሚሊዮን በላይ ተመልካች እንደሚያገኝ ታውቋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ ሁለቱን የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ክለቦች የጀርመን ቦንደስ ሊጋው ክለቦች 11ለ3 በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈዋል፡፡ በዘንድሮ የጀርመን ቦንደስሊጋ ሻምፒዮናነት ፍፁም የበላይነት የነበረው ባየር ሙኒክ በሜዳው አሊያንዝ አሬና ባርሴሎናን 4ለ0 ካሸነፈ በኋላ በመልሱ ኑካምፕ ላይ ባርሴሎናን በድጋሚ 3ለ0 በሜዳው አንበርክኮ በድምር ውጤት 7ሎ በመርታት ወደ ዋንጫው ማለፉን አረጋግጧል፡፡

የአምናው የቦንደስ ሊጋ ሻምፒዮን ቦርስያ ዶርትመንድ በበኩሉ የአምናው የፕሪሚዬራ ሊጋ ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድን በሜዳው 4ለ1 ካሸነፈ በኋላ በሳንቲያጎ በርናባኦ 2ለ0 ቢረታም በአጠቃላይ ውጤት 4ለ3 በማሸነፉ ወደ ዋንጫው ፍልሚያ ተሸጋግሯል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የዓለም ስፖርት አፍቃሪ አራት አይነት የፍፃሜ ጨዋታዎችን ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ከአራቱ ዓይነት የፍፃሜ ፍልሚያዎች ሊከሰት የበቃው ግን ባየር ሙኒክ ከቦርስያ ዶርትመንድ የሚፋጠጡበት የቦንደስ ሊጋ ደርቢ ነው፡፡ ሁለቱ የስፔን ክለቦች ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ በሜዳቸው ባደረጉት የመልስ ጨዋታዎቻቸው ተጋጣሚዎቻቸውን ቢያሸንፉ ኖሮ ዋንጫው የኤልክላሲኮ ድግስ ነበረ፡፡ ሌሎቹ ሁለት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዋንጫ ፍልሚያዎች ደግሞ ባርሴሎና ከቦርስያ ዶርትመንድ ወይንም ሪያል ማድሪድ ከባየር ሙኒክ የሚገናኙባቸው እና ቦንደስ ሊጋን ከፕሪሚዬራ ሊጋ የሚያፋጥጡ ድራማዎችም ነበሩ፡፡

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የቦንደስ ሊጋ ደርቢ ሲያጋጥም የመጀመርያው ነው፡፡ ከዘንድሮ በፊት በውድድሩ ታሪክ የአንድ አገር ተወካይ ክለቦች ለፍፃሜ የተገናኙት በ3 የዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ነበር ፡፡ የመጀመርያው በ2003 እኤአ ላይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በፕሪሚዬራ ሊጋ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ቫሌንሽያን 3ለ0 በመርታት ዋንጫ የወሰደበት ነበር፡፡ ሁለተኛው በ2005 እኤአ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በጣሊያን ሴሪኤ ደርቢ ኤሲ ሚላን በመለያ ምቶች ጁቬንትስን 3ለ2 አሸንፎ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃበት ነበር፡፡ ሶስተኛው ደግሞ በ2008 አኤአ ላይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ደርቢ ማን ዩናይትድ ከቼልሲ ጋር አገናኝቶ ፤በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1 እኩል አቻ ከተለያዩ በኋላ ማን ዩናይትድ በመለያ ምቶች 6ለ5 አሸንፎ ዋንጫውን ያነሳበት ነበር፡፡ በዘንድሮው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ምእራፍ ላይ ከጀርመንና ከስፔን የተወከሉ አራት ክለቦች ሲገኙ ከ13 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መካከል የነበረው የሃይል ሚዛን ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በመሸሽ ወደ ጀርመን ቦንደስ ሊጋ መጠጋቱን አረጋግጧል፡፡

የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አንጀላ ማርያ የግማሽ ፍፃሜው ትንቅንቅ ከፕሪሚዬራ ሊጋው እና ከቦንደስ ሊጋው የትኛው እንደሚልቅ ምላሽ ይሰጣል በማለት ተናግረው የነበረ ሲሆን ጀርመኖች ስታድዬሞች ቢኖራቸውም ምርጥ ውድድር ያለን ስፓንያርዶች ነን ብለው ፉክክሩን ለማሸነፍ ፍላጎት አሳይተው አልሆነላቸውም፡፡ የዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ እና የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ንፅፅር ውስጥ በማስገባትም አከራካሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ከቦንደስ ሊጋ እና ከፕሪሚዬራ ሊጋው የቱ ይበልጣል በሚለው ክርክር ሚዛን ከደፉ አጀንዳዎች የሁለቱ አገር ክለቦች አጨዋወት የመጀመርያው ነው፡፡ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ የመከላከል ስትራቴጂ በብሎኬት ግንብ የተመሰለና የማጥቃት ጨዋታው በከፍተኛ ወራራ የሚታጀብ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ደግሞ በሚያምር የኳስ ቁጥጥር እና ቅብብል እንዲሁም በፈጠራ በተሞሉ የግብ አይነቶቹ ተፎካካሪነቱ ተጠቅሷል፡፡ ለጀርመን ቦንደስ ሊጋ ምርጥነት ግን ብዙ ምክንያቶች እየተዘረዘሩ ናቸው፡፡ በአካዳሚዎች ጥራት፤ በስታድዬም ዋጋ መርከስ እና በተመልካች መሞላት፤ በጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ የጀርመን እግር ኳስ የአውሮፓ ደረጃ በከፍተኛ ልዩነት እየመራ ይገኛል፡፡

ለዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በደረሱት ሁለቱ የጀርመን ክለቦች ከአካዳሚዎች የወጡ ከ10 በላይ ወጣት ተጨዋቾች ይገኛሉ፡፡ በባየር ሙኒክ ፊሊፕ ላሃም፤ ባስትያን ሽዋንስታይገር፤ ቶማስ ሙለርእና ዴቪድ አላባ እንዲሁም በዶርትመንድ ማርዮ ጎትሴዜ፤ ማርኮ ሬውስ እና ኑሪ ሳሂን በየክለቦቹ ከሚገኙ አካዳሚዎች የተመለመሉ ናቸው፡፡ የጀርመን እግር ኳስ ላይ በታዳጊ እና ወጣት ፕሮጀክት በስፋት መሰራት ከጀመረ ከ10 ዓመታት በላይ አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከ713 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እድሜያቸው 19 እና 20 የሚሆናቸው ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን ለማፍራት ተችሏል፡፡ ስለሆነም ደግሞ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች በአገር ውስጥ ውድድር እና በአህጉራዊ ደረጃ በሚያሳዩት ስኬት ይሄው የአካዳሚዎች አስተዋፅኦ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ ከወጣት ተጨዋቾች ባሻገር ከጀርመን ቦንደስ ሊጋ 18 ክለቦች ካንዱ በቀር በሁሉም እየሰሩ ያሉት አሰልጣኞች አገር በቀል መሆናቸው ሌላው ለእግር ኳሱ መጠናከር ምክንያት የሆነ ነው፡፡ በትርፋማነት የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ቀዳሚ ቢሆንም ቦንደስሊጋም በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ 2013 ሲገባ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ባንድ የውድድር ዘመን በሪከርድ ስኬት ገቢ አድርጓል፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቦንደስ ሊጋው በቴሌቭዥን የስርጭት መብት የሚያገኘው ገቢ መጨመር ደግሞ የሊጉን ትርፋማነት ያሳድገዋል፡፡ የጀርመን ክለቦች የፋይናንስ ጤንነት እና የቦንደስ ሊጋው አስተዳደር 50 ሲደመር አንድ በሚለው ደንብ የክለቦች ባለቤትነት ድርሻን ለአባላት እንዲሆን ማስገደዱ ተመጣጣኝ አቅምና እና ፉክክር በውድድር እንዲኖር አድርጓል፡፡

የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ጨዋታዎችን በስታድዬም ገብቶ ለመመልከት ያለው የትኬት ዋጋም ከሌሎች የአውሮፓ ሊጎች የረከሰ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ አንድ የጀርመን ቦንደስ ሊጋን ጨዋታ ለመታደም ርካሹ የትኬት ዋጋ 12 ዩሮ ሲሆን ይህ ገንዘብ የትኛውንም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ለማየት አይበቃም፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የ58 አመታት የውድድር ታሪክ በሁለት ክለቦች 13 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ቢሆንም በ5 ክለቦች ተመሳሳይ የዋንጫ ብዛት በመሰብሰብ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል፡፡ የጣሊያኑ ሴሪኤ በ3 ክለቦች ባገኛቸው 12 ዋንጫዎች ሶስተኛ ደረጃ ሲይዝ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ3 ክለቦች 6 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን በመሆን በአራተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በክለብ ደረጃ 9 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሲሆን የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን 7፤ የእንግሊዙ ሊቨርፑል 5 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው፡፡ ባየር ሙኒክ እና ባርሴሎና እያንዳንዳቸው አራት የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድሎችን በማስመዝገብ አራተኛ ደረጃ ሲወስዱ በተከታይነት የተመዘገበው ማን ዩናይትድ በሶስት የዋንጫ ድሎቹ ነው፡፡

ዶርትመንድ በ1 የሻምፒዮንስ ሊግ ድሉ በ22ኛ ደረጃ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ታዋቂው የቢዝነስ መፅሄት ፎርብስ ይፋ ባደረገው የአውሮፓ ክለቦች የዋጋ ግምት ሪያል ማድሪድ በ2.532 ቢሊዮን ዩሮ ተመን አንደኛ ደረጃ ሲወስድ ማን ዩናይትድ በ2.429 ቢሊዮን ዩሮ ሁለተኛ ነው፡፡ በዚሁ የክለቦች የዋጋ ተመን ደረጃ ባርሴሎና በ1.995 ቢሊዮን ዩሮ ሶስተኛ ደረጃ ሲያገኝ ባየር ሙኒክ 1.017 ቢሊዮን ዩሮ በሚተመነው አርሰናል ተበልጦ በ1.005 ቢሊዮን ዩሮ የዋጋ ግምት አምስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሚሰጠው ነጥብ መሰረት ባለፈው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ታላቅ ሊጎች በወጣላቸው ደረጃ 84.10 በማስመዝገብ የሚመራው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ነበር፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ በ84.08፤ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ በ75.18 እንዲሁም የጣሊያኑ ሴሪኤ በ59.81 ነጥብ እስከ አራት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡

በስታድዬም የአንድ ጨዋታ አማካይ ተመልካች የሚመራው የጀርመን ቦንደስሊጋ 45116 አስመዝግቦ ሲሆን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 34601 እንዲሁም የስፔን ላሊጋ 28403 ተመልካች በአንድ የሊግ ጨዋታ በማግኘት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን በሚያስገኘው የገቢ መጠን የሚመራው የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ከ2.5 ቢሊዮን ዩሮ በላይ በመሰብሰብ ነው፡፡ በገቢ መጠን ሁለተኛ ደረጃ የሚወስደው 892 ሚሊዮን ዩሮ በአንድ የውድድር ዘመን የሚያስገባው የጣሊያኑ ሴሪኤ ውድድር ሲሆን የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ በ560 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ422 ሚሊዮን ዩሮ ገቢያቸው ተከታታይ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

Read 5440 times