Saturday, 27 April 2013 10:21

ባለ 100 ዶላር ኖት በአዲስ ዲዛይን ሊታተም ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ውስብስብነቱ ለማተሚያ ቤት አስቸጋሪ ሆኗል

ህገወጥ የመቶ ዶላር ኮፒዎችን ለመከላከል፣ በአዲስ ዲዛይን የተሰራ ባለ 100 ዶላር ኖት ከስድስት ወር በኋላ ስራ ላይ እንደሚውል የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክ (ፌደራል ሪዘርቭ) ባለፈው ረቡዕ ገለፀ። የተጠማዘዘ ሰማያዊ ጥለትና ሌሎች አስቸጋሪ ገፅታዎች ተጨምረውበት የተሰራው ዶላር፣ ከሁለት አመት በፊት ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ህትመት ላይ በተፈጠረ ችግር ሲጓተት ቆይቷል። አስመስሎ መስራትን ለመከላከል ተብለው የተጨመሩ ዲዛይኖች ናቸው ህትመት ላይ የመጨማደድ ብልሽት እየፈጠሩ ያስቸገሩት።

በተለይ በዶላሩ ውስጥ የተጠቀቀለለ የሚመዝል ስስ ሪባን ለህትመት በጣም ፈታኝ በመሆኑ፣ የማተሚያ ማሽኖች ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል። ሪባኑ ከጥቃቅን ሌንሶች የተሰራ ሲሆን፣ ዶላሩን ወደቀኝ ገፋ ሲደረግ ሪባኑ ወደ ግራ የሚንሸራተት ሆኖ ይታያል ብለዋል የማተሚያ ቢሮ ቃል አቀባይ ዳውን ሃሌ። ዶላሩን ቀና ደፋ በማድረግ፣ ሪባኑ ላይ የሚታዩት የደወል ምስሎች፣ “100” ወደሚል ፅሁፍ ይቀየራሉ። የቀለም ብልቃጥ ምስል ላይ የተጨመረው የደወል ምስል ደግሞ፣ መልኩ ከብጫ ወደ አረንጓዴ ይለወጣል።

በትልቁ የተጻፈው “100” የሚል ቁጥርም እንዲሁ ቀለሙ ይቀያየራል። ነባሩ ዲዛይን ለተወሰኑ አመታት አገልግሎት ላይ እንደሚቆይ የገለፀው የአሜሪካ ቢሄራዊ ባንክ፣ በዚህ አመት 250 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ባለመቶ ዶላር ኖት በአዲሱ ዲዛይን እንደሚታተም አስታውቋል (2.5 ቢሊዮን ኖቶች መሆኑ ነው)። የማሻሻያ ዲዛይኑ የተጀመረው ከአስር አመት በፊት ሲሆን፣ በመጀመሪያ ባለ 20 ዶላር ላይ የቀለማት ለውጥ ከተደረገለት በኋላ፣ ባለ 50፣ ባለ 10 እና ባለ 5 ዶላር ኖቶችም ተሻሽለው ወጥተዋል። የአንድ ዶላር ኖት፣ ምንም ለውጥ አልተደረገበትም።

Read 2176 times