Saturday, 20 April 2013 14:13

የቃላት ተዓምራዊ ሃይል

Written by  ትርጉም - ሙአሊም መዋ
Rate this item
(1 Vote)

ሪፕ እና ሎሊታ፣ እመቤት እና ሎሌ ናቸው፤ ሎሊታ እመቤት፣ ሪፕ ሎሌ፡፡ ሎሊታ ደግ፣ ብልህ አሳዳሪ ስትሆን፣ ሪፕ ታማኝነት እና ሥነ-ሥርዓት የጐደለው አሽከር ነው፡፡ ሎሊታ ብዙ ጊዜ ከጥፋት እንዲቆጠብ ብትመክረውም በጄ አልል ብሏል፡፡ በምክር ልትመልሰው አልተቻላትም፡፡ ጊዜ ወስዳ ይህን ወልጋዳ አሽከሩዋን እንዴት እንደምታቀናው አሰበች፡፡ አንድ ሀሳብ ተከሰተላት፤ ውላ አላደረችም፤ ሪፕ ይስተካከልበታል ብላ ያሰበችውን ዘዴ ልትተገብር ተነሳች፡፡ ሶስት የፖም ፍሬዎችን አዘጋጅታለች፡፡

“ሪፕ!” ተጣራች፤ መልስ የለም፤ በቅርብ እርቀት እንዳለ ታውቃለች፡፡ “ሪፕ!” ምን በወጣው እሱ፤ ዝም፡፡ “ኸረ ሪፕ!” ዝም እየሰማ፡፡ “አንተ ሪፕ!” “አቤት፡፡” “ምነው ጆሮህ ተደፍኗል’ንዴ?” “አዎ፤ ተደፍኗል፡፡” በቀስታ፤ ሎሊታ ግን ሰምታዋለች፡፡ “ምን?! ምንድነው ያልከው?!” “አልሰማሁም ነበር ነው ያልኩት፡፡” “በል እሺ ልብ አድርገህ አድምጠኝ፡፡ በዚህ የስጦታ መያዣ ዕቃ ውስጥ ሶስት የፖም ፍሬዎች አሉ…” “እና…” ጣልቃ ገብቶ፡፡ “አትቸኩል፡፡ እነዚህን የፖም ፍሬዎች ያዘጋጀሁት ለምወዳት ጓደኛዬ ነው… እ…ቤቷን በምልክት እነግርሃለሁ፤ ወስደህ ትሰጥልኛለህ፡፡”

የቤቱን አቅጣጫ በምልክት ነገረችው፡፡ ሎሊታ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ሪፕ አደራውን እንደማይጠብቅ እርግጠኛ ናት፡፡ የፖም ፍሬዎቹን እርቆ ሳይሄድ መንገድ ላይ እንደሚበላቸው ታውቃለች፡፡ ሪፕ በምልክት ወደ ተነገረው ቤት እያመራ ሳለ ያው የተለመደው ሀሳቡ መጣበት፡፡ ቀስ፤ ረጋ ብሎ የስጦታ ዕቃውን ከፈተው፡፡ አንዲትዋን የፖም ፍሬ አውጥቶ አንዴ ገመጣት፡፡ ትጣፍጣለች፤ ደጋግሞ ገመጣት፤ አለቀች፡፡ እያመነታ ሁለተኛውን ደገመ፡፡ ከመጀመሪያው የበለጠ ጣመችው፡፡ ሶስተኛዋማ ልዩ ትሆናለች ብሎ ሶስተኛዋን ደገማት፡፡ እንደ ሀሳቡ ናት፡፡ የስጦታ ወረቀቱን ጨምድዶ አርቆ ወረወረና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ “ሪፕ መጣህ?” አለችው ሎሊታ እንዳየችው፡፡ “መጥቼማ ነው እዚህ ያለሁት፡፡” “ስጦታውን ለጓደኛዬ ሰጠሃት?” “አዎ፤ ሰጥቻታለሁ፡፡” “በጣም ጥሩ፤ አሁን ገና ያለፈ ቂሜን ተወጣሁ፡፡

” “ቂም?!” ሪፕ ክው ብሎ ደነገጠ፡፡ “እንዴታ! ፖሞቹን የሰጠሃት ወዳጄ አይደለችም፤ ጠላቴ ናት፡፡ የፖም ፍሬዎቹ የተመረዙ ናቸው፡፡ ይኼኔ የመጀመሪያውን የፖም ፍሬ ስትበላ ይዞርባታል” ከማለቷ ሪፕ ይዞርበት ጀመር፡፡ “እመቤቴ ሎሊታ፣ ክብርት ሎሊታ፣ ቅድስት ሎሊታ አንደኛውን የፖም ፍሬ በልቻለሁ፡፡” “አይ እርሱ ብዙም ጉዳት የለውም፡፡ በጣም መርዛማዎቹ ቀሪዎቹ ሁለት ፖሞች ናቸው፡፡ አቤት! ሁለተኛውን የፖም ፍሬ ስትበላማ ትሽከረከራለች፡፡” ሪፕ ተሽከረከረ፡፡ “እመቤቴ ሎሊታ፤ ክብር ሎሊታ፣ ቅድስት ሎሊታ አድኚኝ፤ አንደኛውን ብቻ አይደለም፤ ሁለተኛውንም በልቻለሁ፤ አድኚኝ እመቤቴ፡፡” “ሁለተኛውም ብዙ ጉዳት የለውም፤ ሶስተኛው ነው አደገኛው እና የሚገድላት፤ ሶስተኛውን ፍሬ ስትበላ መሬት ትዞራለች፡፡” ሪፕ ተዘረረ፡፡

“ኦ! እመቤቴ ባክሽ አድኚኝ፤ ሶስቱንም ፍሬዎች በልቻለሁ፤ አድኚኝ ባክሽ፡፡” “ሪፕ አሁን አትጨቅጭቀኝ፤ ይህ የራስህ ጥፋት ነው፡፡ ታማኝ እንድትሆን ደጋግሜ መክሬሃለሁ፡፡ አልሰማም በማለትህ ለዚህ በቅተሃል፡፡ አሁን እኔ ምንም ላደርግልህ አልችልም፡፡” “እመቤቴ፣ ክብርት እመቤቴ ሁለተኛ ጥፋት አልፈፅምም፡፡ የዛሬን ብቻ አድኚኝ፣ ከዛሬ ወዲህ ፀባዬን አርማለሁ፡፡ የዛሬን ብቻ… ሁለተኛ አይለምደኝም፡፡” “ምን የዛሬው የመጀመሪያህ ይመስል ሁለተኛ አይለምደኝም ትላለህ፡፡ ሚሊዮን ስህተቶች ስትሰራ እኮ ነው የኖርከው፡፡” “አውቃለሁ፡፡” ሪፕ እየተዳከመ ነው፡፡ “እና ታዲያ?” “በቃ ለወደፊቱ እታረማለሁ፤ አይለምደኝም፡፡” “በርግጥ ትታረማለህ?!” “አዎ፤ አዎ፡፡” “በምን ላምንህ እችላለሁ?” “እየሞትኩ ነውኮ እመቤቴ፡፡” ሎሊታ የተስፋ ጭላንጭል ታየት፡፡ “ዶክተር፣ ዶክተር፣ ዶክተር፡፡” ጮሃ ተጣራች፡፡ ነጭ የሥራ ልብስ የለበሰ ሰው ገባ፡፡ “ዶክተር፣ አሁን መሬት ወድቆ የምታየው ልጅ የተመረዙ የፖም ፍሬዎች በልቶ ነው፡፡ ነገሩን የፈፀመው በራሱ ጥፋት ቢሆንም እታረማለሁ ስላለ ቢታከም ምንም አይደል፡፡” አለች ሎሊታ በእርጋታ፡፡

ሀኪሙ ሪፕን ደጋግፎ አነሳው፡፡ በስራ ልብሱ ኪስ ውስጥ ያለች ብልቃጥ አውጥቶ ከፈተ፡፡ “እንደምንም ብለህ በዚህች ብልቃጥ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ባንድ ትንፋሽ ጨልጠው” አለ ሀኪሙ፤ ብልቃጡን ለሪፕ እያቀበለ፡፡ ሪፕ የተባለውን አደረገ፡፡ “ዝለል!” ተባለ፤ ዘለለ፡፡ “ቁጭ ብድግ በል” ተባለ፤ ቁጭ ብድግ አለ፡፡ “ተንጋለል” ተንጋለለ፡፡ “ዱብዱብ በል” ዱብዱብ አለ፡፡ “ይበቃል፤ ይበቃል፡፡ አሁን ምን እየተሰማህ ነው?” “ዶክተርዬ አሁን ፍፁም ጤነኝነት እየተሰማኝ ነው” “በል አሁን ገብተህ እረፍ፡፡ ለወደፊቱ እንዲህ ህይወትህን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ባትሰራ መልካም ነው” ሪፕ ለእመቤቱ እና ለሀኪሙ እጅ ነስቶ ወጣ፡፡ ሪፕ ትንሽ እንደራቀ ሎሊታ እና ሀኪሙ ተሳሳቁ፡፡ “ማስመሰላችን የተሳካ ይመስለኛል” አለች ሎሊታ ሳቁዋን ሳታቋርጥ፡፡ “እብድ ካልሆነ በስተቀር ካሁን በኋላ የእምነት ማጉደል ተግባር ይፈፅማል ብዬ አላስብም፡፡” ሶስቱ የፖም ፍሬዎች ፍፁም ንፁሆች ነበሩ፤ አልተመረዙም፡፡ ሪፕ እንዲጠጣ የተሰጠውም የተበጠበጠ ስኳር ነበር፡፡ ስለዚህም አሁን ይህ ታሪክ እንደሚጠበቀው እንዲህ ማለቅ አለበት፡- ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሪፕ በጣሙን የታረመ እና ታማኝ ሰው ሆነ፡፡

Read 3297 times