Saturday, 20 April 2013 12:46

አበባ ደሣለኝ “የለሁበትም” ልትለን ነው!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከአብርሽ ጋር ሲያዩኝ “ኮንግራ ሙሽራው ተገኘ?” ይሉኛል…

ፈረንሳይ ትንሿ የኢትዮጵያ ሆሊዉድ ትባላለች…

የጠበሰም የተጠበሰም፤ የጠየቀም የተጠየቀም የለም (ስለትዳሯ)

በአዲስ አበባ ውስጥ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ አድጋለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ማንጐራጐር ይቀናት የነበረችው ትንሿ አበባ፤ እንጉርጉሮዋን በማሣደግ በቀበሌ ክበብ አድርጋ፣ በምሽት ክበብ አቋርጣ እስከ ትልቁ ብሄራዊ ቴአትር ቤት ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ ከድምፃዊነት በተጨማሪ በቴአትር መድረክም ላይ ችሎታዋን ያሣየችበትን “ልደት” ቴአትርና “አንድ ምሽት”ን ሠርታለች፡፡ ወደ ፊልሙም ሠፈር ጐራ ብላ “ሩሀማ” እና “ሠካራሙ ፖስታ” ላይ ተውናለች፡፡ ማስታወቂያውንም ሞክራለች፡፡ “ሙሽራዬ ቀረ” የሚል ተወዳጅ አልበም አውጥታ በጣም ተወዶላት ነበር፡፡ አርቲስቷ አምስት ዓመት ገደማ ድምጿን አጥፍታ ከቆየች በኋላ ሠሞኑን “የለሁበትም” የተሠኘ አዲስ አልበም ለማውጣት ደፋ ቀናውን ተያይዛዋለች፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአበባ ደሣለኝ ጋር በነበራት ቆይታ በአዲሱ ስራዋ፣ ጠፍታ ስለከረመችበት ጉዳይና ሌሎችንም የሥራና የህይወት ቁምነገሮች አንስታ ተጨዋውተዋል፡፡ እነሆ:-

የት ጠፍተሽ ከረምሽ?

ጠፋ ብያለሁ ግን ሥራ እየሠራሁ ስለነበር ነው፡፡ አሁን በአዲስ ስራ እየመጣሁ ነው፡፡ እስከዛሬ ቅጽል ሥም እንዳለሽ አልነገርሽንም? አንቺ ከየት ሰማሽ? እኔ ሰሞኑን ሰምቻለሁ፡፡ ከራስሽ እንስማው…

ማነው ቅጽል ስምሽ?

የሚገርመው ወደ ኪነ-ጥበብ ገብቼ ከ “እርጂኝ አብሮ አደጌ” እስካሁን ድረስ ብዙ ቃለ - ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡ እኔም አልተናገርኩም፡፡ ሰዎችም ቅጽል ስም እንዳለኝ አያውቁም፡፡ ሰምቶም የጠየቀኝ የለም፤ አንቺ የመጀመሪያ ነሽ ስለ ቅጽል ስሜ ስትጠይቂኝ ማለቴ ነው፡፡ ስሜ “ሙናና” ነው የሚባለው፡፡ ይሄንን ስም ቤተሰቤ፣ እህቶቼ፣ የቅርብ ዘመድ እና የሠፈር ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ምን ማለት ነው? ስወለድ በጣም ቀጫጫና ትንሽ ነበርኩኝ አሉ፡፡ ካደግኩም በኋላ መወፈር አልቻልኩም፡፡ እና አሁን ይህቺ ሰው ሆና ታድጋለች… የሆነች ሙንን ያለች ነገር ብላ አያቴ ስትናገር፣ በዛው ሙናና ተባልኩኝ፡፡ አንዳንዶቹ ሙኒኒ ብለው ይጠሩኛል፤ ሰፈር ውስጥ ማለት ነው፡፡

እዚህ ለመድረስ ውጣውረዶችን እንዳሳለፍሽ ይነገራል፡፡ እስኪ አጫውቺኝ?

ከሌሎች ሰዎች በጣም የተለየ ውጣ ውረድ አይደለም ግን እንደማንኛውም ባለሙያ እዚህ ለመድረስ ከፍና ዝቅ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ሲጀመር ሁሉም አልጋ በአልጋ አይሆንም፤ በየትኛውም የስራ ዘርፍ ቢሆን ማለት ነው፡፡ ፈተናዎቹ እንግዲህ ከክበብ ጀምሮ እስከ ቴያትር ቤት፣ ከዚያም አልበም እስከማውጣት ደፋ ቀና ማለት ያለ ነው፡፡ ናይት ክለብ ስሰራም እንደዚሁ ሴትነትሽን ተከትለው ከሚመጡት ፈተናዎች ጀምሮ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ ዋናው ነገር እነሱን በድል ተወጥቼ እዚህ መድረሴ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እግዚአብሔርም ተጨምሮበት ነው፡፡ ከልጅነትሽ ጀምሮ ታንጐራጉሪ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ የእነማንን ዘፈን ትዘፍኚ ነበር፡፡ የሂሩትን ዘፈኖች ለመጫወት የመረጥሽበትስ ምክንያት ምንድን ነው?

በነገርሽ ላይ ልጅ ሆኜ የወንድም የሴትም ዘፈን አይቀረኝም፡፡ ሁሉንም በቃ መዝፈን ነው፡፡ ለምሳሌ ደረጀ ደገፋውና ማርታ ሀይሉ እየተቀባበሉ የሚዘፍኑትን “አንቺ ሆዬ ሆይ” የተሰኘ ዘፈን፣ የሷንም የእሱንም ራሴን በራሴ እየተቀባበልኩ እዘፍን ነበር፡፡ ወንዱንም ሴቷንም እየሆንኩ ማለቴ ነው፡፡ የኬኔዲና የየሺመቤትን ዘፈን አሁንም ወንዱንም ሴቷንም ሆኜ እዘፍን ነበር፡፡ የጋሽ ጥላሁንንም እዘፍናለሁ፡፡ ያው ልጅ ስትሆኚ መምረጥ የለም፡፡ ሁሉንም መነካካት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መዝፈን ማለት ምን እንደሆነ፣ ሜጀር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲገባሽ፣ መድረክ አያያዝ፣ ማይክ አጨባበጥ ምን እንደሆነ ስታውቂ፣ የማንን ዘፈን ብዘፍን ለድምፄ ከለር ይስማማል በሚል መምረጥ ትጀምሪያለሽ፡፡ እኔም ይሄ ሲገባኝ የፍቅር አዲስን፣ የብዙነሽ በቀለን፣ የሂሩትን፣ የማርታ ሀይሉን እና የሌሎችንም በመዝፈን ነው ወደራሴ የመጣሁት፡፡ የሂሩትን ዘፈን የዘፈንኩት የተለየ ምክንያት ኖሮኝ ሳይሆን ዘፈኖቹን በጣም ስለምወዳቸው ነው፡፡ ናይት ክለብ (የምሽት ክለብ) ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንደመስራትሽ ብዙ ገጠመኞችና ፈተናዎች ይኖሩሻል ብዬ አስባለሁ፡፡

እስኪ ከገጠመኞችሽ ጥቂት አውጊኝ? ናይት ክለብ ስሠራ የተለየ የገጠመኝ ነገር የለም፡፡

ግን አምሽቼ ስወጣ ቤቴ ሩቅ ስለነበር ለመሄድ እቸገር ነበር፡፡ የሚያደርሰኝ ሰርቪስ የለም፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ድረስ መሄድ ለእኔ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ አንዳንዴ ጓደኛዬ ቤት ሳድር ቤተሰቤ ይጨነቃል፡፡ በግድ ነው እንጂ እንድሠራም አይፈቀድልኝም ነበር፡፡ ሌላው በወቅቱ ተማሪ ስለነበርኩኝ ደብተር ይዤ ናይት ክለብ የምሄድበት ጊዜ በርካታ ነበር፡፡ በተለይ ፈተና የደረሰ ሰሞን አንድ እዘፍንና እንደገና ደብተር ይዤ እቀመጣለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ነው 12ኛ ክፍልን የጨረስኩት፡፡ ከዛ በተረፈ ናይት ክለብ ስትሠሪ የሚወድሽ ይኖራል ወይም የሚናደድብሽ ይኖራል፡፡ በርቺ አሪፍ ነው የሚልሽ ይኖራል፡፡ የሚያመናጭቅ ይኖራል፤ ይሄን ሁሉ አልፌያለሁ፤ የተለየ ገጠመኝ ግን የለኝም፡፡

ስለ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ቆይታሽ እናውራ፡፡

ብሔራዊ ቴአትር ቤት ታሪካዊና ቀዳማዊ እንደመሆኑ እዛ በቋሚነት ለመቀጠር ብዙ እንደሚለፋ ሰምቻለሁ አንቺ እድሉን አግኝተሽ ለስምንት ወይም ለሰባት ዓመት ያህል ሰርተሽ እንደገና በራስሽ ፈቃድ መልቀቅሽን ነው የሰማሁት እንዴት ለቀቅሽ? እውነት ለመናገር ብሔራዊ ቴአትርን በጣም ነው የምወደው፡፡ ስገባም ፀልዬ ፈጣሪዬን ለምኜ እንደውም ተስዬ ብል ነው የሚቀለኝ፤ እንደዛ ነው የገባሁት፡፡ እንዳልሽው ብሔራዊ ቴአትር ቤት ትልቅ ቤት ነው፤ ብዙ ባለሙያዎችን ያፈራ ነው፤ አሁንም ብዙ ሙያተኞች አሉት፡፡ በዛን ሰዓት ከክበብ ተነስሽ በአንዴ ቴአትር ቤት መግባት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይሄ ከዛሬ ዘጠኝና አስር ዓመት በፊት ነው፡፡ እዛ በመስራቴ እና የታሪኬ አንድ አካል በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ በወቅቱ 20 ሰው ተወዳደረ፤ የሚፈለገው ግን አንድ ሰው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ማስታወቂያውን አይቼ መጀመሪያ ብመዘገብም የፈተናው ቀን ግን በጣም አረፈድኩኝ፡፡

በምን ምክንያት?

ባስ አጥቼ ሁሉም ሰው ተፈትኖ ካለቀ በኋላ ደረስኩኝ፡፡ ከዚያም ፈታኞቹን እባካችሁ ብዬ ለምኜ፣ እስኪ እንያት ተብሎ እድል ተሰጠኝ፤ ግን ፈጣሪ ተጨምሮበት ፈተናውን አልፌ ተቀጠርኩኝ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ስትቀጠሪ በድምፃዊነት ነበር፡፡ ከዚያ ቴአትርም ሰርተሻል፤ ኧረ ተወዛዋዥም ነበርሽ ነው የሚባለው፡፡ እውነት ነው?

ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትሽውን ቴአትርም በዚያው ንገሪኝ …?

እርግጥ የተቀጠርኩት በድምፃዊነት ነው፡፡ ቴአትር ስሠራ አይተውኝም አያውቁም፡፡ ነገር ግን የቀበሌ ክበብ ውስጥ ቴአትር እሠራ ነበር፡፡ ሲራክ ታደሰ ያዘጋጀው “ልደት” የተሰኘ ትርጉም ቴአትር ነበር፡፡ በወቅቱ ካስት ሲያደርጉ “ይህቺ ልጅ ያቺን ገፀ ባህሪ ታመጣታለች” ብለው መረጡኝ፤ ስፈተንም አለፍኩኝ፤ እሱን ቴአትር ስጫወት ከእነ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ፣ ተስፋዬ ገ/ሀና፣ ትዕግስት ባዩ፣ ሱራፌል ወንድሙ ጋር ነበር፡፡ እነዚህ ትልልቅ አርቲስቶች ናቸው፡፡ በቴሌቪዥን አይቼ ከማደንቃቸው ጋር በአንዴ ተቀላቀልኩኝ፡፡ ቴአትሩ ለአንድ አመት ታይቷል፡፡ ከዛም በኋላ በደብል ካስት ልምምድ አደርግ ነበር፡፡ “ልደት” ቴአትር ላይ በጣም ተሳክቶልኛል፡፡ እንደነገርኩሽ በክበብ ደረጃ ድምጽም፣ ቴአትርም፣ ውዝዋዜም እሠራ ነበር፡፡ ውዝዋዜውን የተውኩት አጭር ስለሆንኩ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ “አንድ ምሽት” የሚል ቴአትር የጐዳና ሴተኛ አዳሪ ሆኜም ሰርቻለሁ፡፡ ትንሽ ክፍል ብትሆንም ስጫወት ጥሩ ነበርኩኝ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ ነው የቆየሁት፡፡

ታዲያ እንዴት ቴአትር ቤቱን ለቀቅሽ?

እንደምታውቂው የሰው ልጅ አንድ ቦታ ላይ አይቆምም፡፡ ፍላጐት እየጨመረ ሲሄድ ነገ የተሻለ ነገር ማግኘት ይፈልጋል፡፡ እኔም የማደግ የመለወጥ ተስፋ ነበረኝ፡፡ እዚያው ቴአትር ቤት እያለሁ “እርጂኝ አብሮ አደጌ” የተሰኘው ከትዕግስት ፋንታሁን ጋር የሠራሁት አልበም ወጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ለስራ ወደ ውጭ እፈለግ ጀመር፡፡ ፈቃድ ወስጄ ወጣ ብዬ ሠርቼ እመለስ ነበር፡፡ በመሀል ነጠላ ዜማም መስራት ጀመርኩኝ፡፡ በመጨረሻ “ሙሽራዬ ቀረ” አልበሜ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ከበፊቱ የበለጠ የውጭ ጥሪዎች መብዛት ጀመሩ፡፡ አንዴ አረብ አገር፣ አንዴ አውሮፓ ማለት ጀመርኩኝ፡፡ በመጨረሻ ግን አሜሪካ የተጠራሁበት ሥራ የስድስት ወር ስለነበር ፈቃድ አልሰጡኝም፡፡ እንደነገርኩሽ መለወጥ ማደግ ስለምፈልግ፣ ለስድስት ወር የምትሄጂ ከሆነ ትለቂያለሽ የሚል ነገር መጣ፤ እሺ ብዬ ሄድኩኝ ማስታወቂያ ተለጠፈብኝ፤ በዚህ ምክንያት ነው ቴአትር ቤቱን የለቀቅኩት፡፡ እንደሰማሁት ሰሞኑን ያንቺን ህይወት የሚዳስስ፣ ግለ ታሪክሽን የሚናገር ዘጋቢ ፊልም (ቪዲዮ) እያሠራሽ ነው፡፡ ስለሱ ጉዳይ ትንሽ ብታብራሪልኝ?

እዚህ አገር የተለመደው አንድ ሰው ሲሞት ታሪኩ ከዚህም ከዚያም ተለቃቅሞ ለአንድ ጊዜ ብቻ እከሌ በዚህ ጊዜ ይህን ሰራች (ሠራ)፣ የህይወት ዘመኑ ይህን ይመስላል ተብሎ በዚያው ይረሳል፡፡ ይሄ ከሚሆን አንድ ሰው በህይወት እያለ ትክክለኛ ግለ ታሪኩ የት ተወልዶ የት አደገ፣ የት ተማረ፣ በህፃንነቱ ምን አይነት ሰው ነበር፣ መልኩስ አስቀያሚ ነበር፣ ባህሪውስ? የሚለውን ኦውቶባዮግራፊ ቢያሰራ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ፕሮሞሽንም ነው፡፡ ምናልባት አበባን ሰው የሚያውቃት “እርጂኝ አብሮ አደጌ”ን ከሠራች በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ከዚያ በፊት የነበራትን ነገር አያውቀውም፤ ምን አይነት ፈተናዎችን አልፋለች፣ አይናፋር ነበረች ወይስ በልጅነቷ ረባሽ ነበረች፣ በትምህርቷስ ውጤቷ ምን ይመስል ነበር፣ የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን ሰው ቢያውቀውና ከአሁኑ ማንነት ጋር ቢያስተያየው ደስ ይላል በሚል ቪዲዮውን እያሰራሁ ነው፡፡ አንቺ አሁን ገና ከወጣትነቱ አልወጣሽም፤ ከአንቺ ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ፤ የግለ ታሪኩ ስራ ትንሽ አልፈጠነም?

እንዳልሽው ብዙ ይጠበቃል፤ ያኔ አሁን በተሰራው ላይ እየተጨመረ ስለሚሄድ አሁንም ቢሠራ ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ አሁን መሠራቱ እንደውም ወደፊት በእኔ መንገድ መጓዝ ለሚፈልግ ብዙ ትምህርት ይሆነዋል፡፡ በአንድ ነጠላ ዜማ ተነስቶ ታዋቂ መሆን እንደማይቻል፣ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለ፣ እንዴት መታለፍ እንደሚችል ይማሩባታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተረፈ ቅድም እንዳልኩሽ በልጅነቴ ያለው ነገሬ የሚያስቅም ነገር ይኖረዋል እና የሚያዝናና ይሆናል፡፡ ለምሣሌ የዱሮ ፎቶዬን ሲያዩ “እንዴ አባባ እንደዚህ አስቀያሚ ነበረች?” አሊያም “ወይኔ ስታምር” የሚሉ ይኖራሉ እና ሊያዝናና ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

“እርጂኝ አብሮ አደጌ”ን ከዘመድሽ ከትዕግስት ፋንታሁን ጋር ሠርታችሁ ተወዶላችኋል፤ ከዚያ በኋላ አብራችሁ አላየናችሁም፡፡ ለምን ቆመ?

የሚገርምሽ የቆመ ነገር የለም፡፡ በእኔና በቲጂ መካከል ያለው ግንኙነት የቆመ ይመስላል እንጂ አልቆመም፡፡ እንሠራለን፣ በየቀኑ እንገናኛለን፣ በየጊዜው እንደዋወላለን፡፡ ነገር ግን የህይወት መንገድ አንዳንዴ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ባለ ትዳር ስትሆኚ፣ ልጅ ስትወልጂና የቤተሠብ ሀላፊ ስትሆኚ ቤቴን ቤቴን ይመጣል፣ ወይ እኔ ተነስቼ ለስራ አንዱ አገር እሄዳለሁ፣ ቲጂም ተነስታ ወይ አሜሪካ ትሄዳለች፡፡ አየሽው አሁን የህይወት ጐዳና ወዲያና ወዲህ እንደሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት እንደድሮው ተረጋግቶና ተጣምሮ ለመስራት ይከብዳል፡፡ ሩጫው አልገጣጠም ብሎን ነው ያልሠራነው፤ በሌላው ግንኙነታችን አብረን ነን፡፡ አሜሪካም በአንድ ወቅት አብረን ሠርተናል፡፡ ለምሣሌ የዛሬ ሁለት ዓመት አሜሪካ አንድ ቤት ነበርን፤ አብረን ሠርተናል፤ ቱር አብረን ነበር የምንወጣው እና ይሄን ይመስላል፡፡ “ሙሽራዬ ቀረ” የተሠኘውን ዘፈን ስትጫዎቺ ሙሽራዉ የእውነት የቀረ ያህል ስሜትን ጨምድዶ ይይዛል፡፡ ለዘፈን ብለሽ ሳይሆን የደረሠብሽ ነው የሚመስለው፡፡ ሙሽራ የቀረበት ዘመድ ወዳጅ አጋጥሞሻል ወይስ በቅርብ የምታውቂው ጉዳይ አለ?

የህዝቡስ ምላሽ ምን ይመስላል?

የሚገርምሽ ነገር “ሙሽራዬ ቀረ” በጣም ተፅዕኖ የፈጠረ ስራ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ወይ ከአብርሽ ጋር (ባለቤቷ ነው) ሲያዩኝ ወይም የጋብቻ ቀለበቴን ሲያዩት “ኮንግራ ሙሽራው ተገኘ?” ይሉኛል፡፡ በእኔ ላይ ደርሶ የዘፈንኩት የሚመስላቸው አሉ፡፡ በአጋጣሚ ሀሣቡ መጣ፣ አብርሽ ፃፈው፤ ሮማን አየለ ዳይሬክት ስታደርገው የባሠ ነፍስ ዘራና እንዲህ አነጋጋሪ ዘፈን ሆነ፡፡ በጣም ተመስጬ የእውነት አስመስዬ የሠራሁት ቁጭ ብዬ ስሜቱን አስበው ስለነበር ነው፡፡ ይሄ ዘፈን በወጣ ሠሞን ብዙ ሙሽሮች ቀርተው፣ ድግስ አበላሽተው በ“ፖሊስና ህብረተሠብ” ፕሮግራም ላይ መመልከት ጀምረን ነበር እኮ፡፡ አጋጥሞሻል?

አጋጥሞኛል፤ አይቻለሁ፡፡ እኛ ባንሠማና ባናይ በየቦታው ይሄ ነገር ይከሠታል፡፡ እስኪ አስቢው የእኛን አገር ባህል? አንድ ሴት ተዘጋጅታ ድግስ ተደግሶ፣ ወዳጅ ዘመድ ተሠብስቦ፣ ሙሽራው ሲቀር ምን ያህል እንደሚያሸማቅቅ፡፡ በዘፈኑ እኔ መንገድ ስከፍት፣ ብዙ ሠው ሙሽራው እንደቀረ በክስ መልክ መናገርና ፖሊስም ለማስተማር በቴሌቪዥን ሲያሣየን ነበር፤ ብቻ ዘፈኑ የማንንም ቤት ሊያንኳኳ የሚችል፣ ያንኳኳባቸውንም ብሶት የቀሠቀሠ ስለሆነ በጣም ተወዶ ተደምጧል፡፡

ከሙዚቃና ቴአትር ባሻገር በ “ሩሃማ” እና “ሠካራሙ ፖስታ” ላይ በፊልም ትወና ብቅ ብለሽ ነበር፤ አሁን እልም ብለሻል፡፡ ማስታወቂያም ላይ ተመልክተንሻል፤ አሁን እሱም የለም፣ እንደገና በበጐ ፈቃድ አገልግሎት እንደምትሳተፊ ሠምቻለሁ? እስቲ በዚህ ዙሪያ አውጊኝ… ከፊልሙ እንነሣ፡፡ “ሩሀማ” ፊልም ላይ ያው ሩሃማን ሆኜ ተጫውቻለሁ፡፡ ፊልሙን አይተሽው ከሆነ ሩሀማ በጣም የምታሣዝን ሴተኛ አዳሪ የነበረች ከዚያ የህይወት ብርሀን ያየችና ያ ብርሀን መልሶ የጠፋባት ሴት ናት፤ ጥሩ ተሳክቶልኝ ሠርቼዋለሁ፡፡ እኔ እንደዚህ አይነት ገፀ-ባህሪ አይከብደኝም፡፡ ለምን ብትይ በተፈጥሮዬ አልቃሻና ሆደ ባሻ ነኝ፡፡ ፊቴም ለዚያ አይነት ባህሪ ምቹ ስለሆነ መሠለኝ እዛ ቦታ ላይ የሚመድቡኝ፡ ፊልሙን ትተሽ “እርጂኝ አብሮ አደጌ”ን አስቢው፤ እዛ ላይ ተጨንቄ ፊቴ እንደሚያሣዝን ነው የሚታየው፡፡ “ሠካራሙ ፖስታ ላይም እንዲሁ አሳዛኝ ሴት ሆኜ ነው የሠራሁት፡፡ ይህቺ ሴት ኤች አይቪ በደምሽ ውስጥ አለ ተብላ፣ ራሷን ከማህበረሠቡ ለማግለል ገዳም የምትገባ ግን ከገዳም የሚመልሣት ሠው ያገኘች ሴት ናት፡፡ ሁሉም ላይ እንዲህ አሣዛኝ ክፍል ላይ ነው የሚመርጡኝ፡፡ ማስታወቂያን በተመለከተ ብዙ ባልገፋም ሞክሬያለሁ፡፡ ሁለት ወይ ሶስት ማስታወቂያ ነው የሠራሁት፡፡ አንዱ በፊት ነው፤ አለሙ ገ/አብ ነፍሱን ይማረውና መርጦኝ፣ ጋሽ ውብሸት ወርቅአለማሁ ጋ ለእንቁጣጣሽ በዓል ከጓደኞቼ ጋር ስንዘፍን፣ እኔ ከጐጆ ቤት ወጥቼ ሠንደል ሳጨስ እታያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ከሠራዊት ፍቅሬ ጋር አምባሣደር ልብስ ላይ ሠርቻለሁ፡፡ ብቻ ብዙ የሚወራለት አይደለም ማስታወቂያው፡፡ ፊልሙ አሁን ቆሟል፡፡ ብዙ ትኩረቴን ያደረግሁት አልበሙ ላይ ነው፡፡ በመሀልም ያው በስራ ምክንያት አሜሪካ ስድስት ወር እሠራለሁ፣ እመጣለሁ፡፡ እንደዚህ ሆነና ግጥም ዜማ ስሠበስብ በቃ ፊልሙ ተረሣ፤ ነገር ግን የመስራት ፍላጐት አለኝ፡፡ በጐ ፈቃደኝነትን በተመለከተ “እናት ለምን ትሙት” ዘመቻ ላይ “እችላለሁ” የሚል ዘፈን ሠርቻለሁ፡፡ ከሌሎችም አርቲስቶች ጋር የበጐ ፈቃድ ዘፈኖችን ሠርቻለሁ፡፡ ወደፊትም የበጐ ፈቃድ ሥራ የመስራት ፍላጐት አለኝ፡፡ አሁን በአልበሙ ስራ ሩጫ ላይ ስለሆንኩ እንጂ እቀጥላለሁ፡፡ በተለይ በትራፊክ ችግር፣ በእናቶች ሞት፣ በህፃናት መደፈርና በመሠል ማህበራዊ ችግሮች ላይ የመስራት ፍላጐት አለኝ፡፡ ከአልበሙ በኋላ እመለስበታለሁ፡፡ አሁን ወደ አዲሱ ሥራሽ እንምጣ በቅርቡ ከአሜሪካ የመጣሽው አዲስ አልበም ልታወጪ መሆኑን ሰምቻለሁ…

አዎ፡፡ አሜሪካ ስራ ላይ ነበርኩኝ፡፡ ከስራዬ ጐን ለጐን ለአልበሜ ግጥምና ዜማ እዛም ካሉ ባለሙያዎች ስሠበስብ ነበር፡፡ አሁን በጣም ጥሩ የሆነ የተለያየ ስብስብ፣ ባህልም ዘመናዊም፣ ጉራጊኛም ያካተተ ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ ሠውም በጉጉት እንደሚጠብቅ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የአልበምሽ መጠሪያ “የለሁበትም” ይሠኛል፡፡ ከምኑ ነው የሌለሽበት?

የለሁበትም እንግዲህ… አንቺ ከብዙ ነገር የለሁበትም ልትይ ትችያለሽ፤ ነገር ግን ይሄ ዘፈን የፍቅር ዘፈን ነው፡፡ ትክክለኛ ሀሣቡ በትዳር ወይም በጓደኝነት ብቻ በፍቅር ውስጥ ያለች ሴት ናት፡፡ ነገር ግን ባሏ ወይም ፍቅረኛዋ እሷን አይንከባከባትም፤ ጊዜ አይሠጣትም፤ ብቻ እንደ ፍቅረኛ ከጐኗ አይሆንም፡፡ የእሷን ድካም ፍቅር አይረዳም፤ ስለዚህ “እባክህ ከእኔ ጋር ከሆንክ አብረን ፍቅራችንን እናጠንክር፤ እምቢ ብለህ እኔ ሀሣቤን ብቀይር በኋላ የለሁበትም” በሚል ነው የምታስጠነቅቀው፡፡

አልበምሽ በዋናነት በምን ላይ ያተኩራል?

ሁሉንም ያካትታል፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ከከተማ እስከ ገጠር የሚዳስስ ነው፡፡ አሁን ስለ ገጠሩ ህይወት የሚዳስስ “ባጥ አሣቅሉኝ” (ጐጆ አቃልሱኝ) እንደማለት ነው፡፡ አይነት ደስ የሚል ዘፈን ሁሉ አለው፡፡ ይህ ዘፈን የአገሬው ሠው ሆ ብሎ ቤት እንዲያሳራት የምትማጠንበት ነው፡፡ ሁለት የሂሩት ዘፈኖች ተካተውበታል፣ “ተረት ተረት”፣ “ቸር ወሬ” የሚሉና ሌሎችም ምርጥ ምርጥ ዘፈኖች ተካተዋል፡፡ በአጠቃላይ 13 ያህል ዘፈኖች አሉት፡፡ አዲስ ሥራ ሲሠራ እነማን ተሳተፉ የሚል የተለመደ ጥያቄ አለ፡፡ አንባቢም ስለሚጠብቅ በግጥም፣ በዜማ፣ በቅንብር ማን ማን እንደተሳተፈ ንገሪኝ? ጌራወርቅ ነቃጥበብ፣ ተመስገን አፈወርቅ፣ አስቻለው ዲሮ በዜማ ተሣትፈዋል አብርሽም በግጥም ተሣትፏል፤ ሁለት ዜማም አለው፡፡ ሄኖክ ነጋሽ የሁለት ባህላዊ ዘፈኖች ዜማ ሠጥቶኛል፡፡ ደሣለኝ መርሻ የተሳተፈበት ጉራጊኛ አለኝ፡፡ የሂሩትን ሁለቱን ስሠራ አንዱ ላይ አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) በግጥም ተሣትፎበታል፤ ሻምበል መኮንንም ተሣትፎ አድርጐበታል፡፡ ሌሎች ባለሙያዎች ተሣትፈዋል፡፡ ሌሎች ባለሙያዎችም ተሣትፈዋል፡፡ ቅንብሩስ…? ካሙዙ ካሣ አራት ዘፈኖችን፣ አስቻለው ዲሮ ሶስት፣ ሄኖክ ነጋሽ አንድ ዘፈን፣ እያሱ እስራኤል አለ፤ ተሾመ ጥላሁን፣ አሸብር ማሞ እና ኢዮብ ፋንታሁን ያቀናበሩት ሲሆን ሚክሲንጉን አስቻለው ዲሮ ሠርቶታል፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ደክሜበታለሁ፡፡ ወጪውም ወገቤን የሚያሠኝ ነው፡፡ ከወጪው ባሻገር ከተለያየ ባለሙያ ጋር ሲሠራ ብዙ ስሜቶችን አስተናግዶ፣ ታግሶ ማለፍ አስፈላጊ በመሆኑ ፈታኝ ነበር፡፡ አሜሪካ ሲሄድ ስመጣ ብቻ ወደ ሁለት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ገንዘቡ፣ ጉልበት፣ የሠዎች ትብብር ሳይጨመር እንኳን ከባድ ነው፡፡ አሁንም ወጪ ላይ ስለሆንኩ ይሄን ያህል አውጥቼአለሁ ልልሽ ግን አልችልም፡፡ የማሣትመውም ራሴ ነኝ፡፡ ኮከብ ሙዚቃ ቤት ለማከፋፈል ስምምነት አለን፡፡

መቼ እንጠብቅ?

እኛ እግዜር ከፈቀደ ለፋሲካ ብለናል፡፡ በሩጫ ላይ ነን፡፡ እንግዲህ ማስተሪንግ የምናሠራባቸው ህንዶች ሠሞኑን ሲዲ አልቆብናል ብለውናል፤ ግን አሁን እናስመጣለን ብለዋል፡፡ እሱ ካለቀልን ለፋሲካ አሪፍ ስራ እናበረክታለን፡፡ ለአንዳንዶቹም ዘፈኖች ክሊፕ እየሠራሁ ነው፡፡ ከስራሽ ወጣ እንበልና ስለ አንቺና ስለ ባለቤትሽ አብርሀም (አብርሽ ዘጌት) ትንሽ እናውራ ይቻላል፡፡ በፊት ጥሩ ወንድምና እህት ሆናችሁ፤ ረጅም ጊዜ ቆይታችሁ በሠዎች ወሬ ባልና ሚስት ሆናችሁ ይባላል፡፡ እንደውም “ወሬውን ሠምቻለሁ” የተባለው ነጠላ ዜማሽ የተዘፈነው ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው? እንዳልሽው እኔ እና አብሪ ግንኙነታችን ክለብ ውስጥ ነው፡፡ እኔም ልዘፍን እሱም ሊዘፍን መጥቶ ማለት ነው፡፡ የሚገርምሽ ግን ሁለታችንም የፈረንሳይ ልጆች ሆነን ግን አንተዋወቅም ነበር፡፡ እሱ የአቦ ሠፈር ልጅ ነው፤ እኔ 07 ቀበሌ ነኝ ግን አንተዋወቅም፡፡ ካዛንቺስ “አልማዝ ላሊበላ” የተባለ ክለብ ነው የተገናኘነው፡፡ ከዚያ ሌሎች ቤቶችም አብረን በመስራት በወንድምነትና እህትነት ረጅም የጓደኝነት ጉዞ አድርገናል፡፡

ግን የሆነ ሠዓት ላይ ዝም ብለን ትዳር አደረግነው እና ህይወት ቀጠለ፡፡ የጠበሠም የተጠበሠም የለም እያልሽኝ ነው? (ሣ…ቅ) አዎ የጠበሰም የተጠበሠም፣ የጠየቀም የተጠየቀም የለም፡፡ እኛ ከፍቅር ግንኙነት ውጭ በጣም ጓደኛሞች ሆነን ስንኖር ሠዎች ዝም ብለው ያወሩ ነበር፡፡ ይሄም አንድ ምክንያት ነበር፡፡ እንዳልሽው “ወሬውን ሠምቻለሁ አሜን ይሁን ብያለሁ” የተሠኘው ነጠላ ዜማም ከዚሁ ጋር ግንኙነት አለው፡፡ ሠርግም ግርግርም የለም፤ ከዚያ ክርስቲያን አብርሀም ተወለደች፤ እሷው አጋባችን፡፡ አሁን አምስት አመት ሞላት፡፡ ለክርስቲያን ወንድምና እህት አልሠጣችኋትም? አዎ ገና አልመጣም፡፡ ምክንያቱም ሩጫው ትኩረት እንድንሠጥ አላደረገንም እና አላሠብንበትም፡፡ ተወልደሽ ያደግሽው እውቁ አትሌት ዋቢ ቢራቱ ሠፈር በመሆኑ ሯጭ ትሆኛለች ተብሎ ሲጠበቅ አንቺ ዘፋኝ ሆነሽ አረፍሽው… በመሠረቱ ከፈረንሳይ ብዙ ጥበበኞች ወጥተዋል፡፡ ሁሌ “ከውሀው ነው መሠለኝ” እንላለን፡፡ ትንሿ የኢትዮጵያ ሆሊውድም ትባላለች፡፡ ከያኒ፣ ጋዜጠኛ፣ ሯጭ ብቻ ጥበበኞች አሏት ፈረንሳይ፡፡ እኔ እንደ ዋሚ ቢራቱ ሯጭ ባልሆንም ዘፋኝ ሆኛለሁ ለማለት ነው፡፡ በመጨረሻ ከ “የለሁበትም” አልበምሽ ምን ትጠብቂያለሽ? እኔ ጥሩ ነገር እጠብቃለሁ፡፡ ሁሉንም ያማከለ ስራ ነውና፡፡ ወጣቱም ጐልማሣውም ሊያዳምጠው የሚችለው ስራ ነው፡፡ ከእኔ ጋር ብዙ የደከሙ ባለሙያዎች፣ ጓደኞች፣ ባለቤቴ አብርሽ በጣም ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ ቢጂ አይ ኢትዮጵያንም አመሠግናለሁ፡፡ እና አሪፍ ነገር አለ ብዬ ነው የምጠብቀው፡፡ “አንቺ የለሁበትም” እንዳልሽው፣ አልበምሽን አሪፍ አድርገሽ ባታመጪ “እኛም የለንበትም”… አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ በጣም አመሠግናለሁ ሙናና፡፡ እኔም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡

Read 8604 times