Saturday, 20 April 2013 11:37

ከመሠረት ጋር አትጣላ ለሁልጊዜ ይሆንሃል። ካብ ጋ አትጠጋ እላይህ ላይ ይፈርሳል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ሰዎች ወንጀል ፈፅማችኋል ተብለው የፐርሺያ ሱልጣን ፊት ቀረቡ፡፡ ሡልጣኑ የመጀመሪያውን አስጠርተው “ወንጀሉን ለመፈፀም ያነሳሳህ ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ የመጀመሪያው ሰውም፣ “ሡልጣን ሆይ! መቼም ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም፡፡ በተለይ በሴት የማይሳሳት የለም፡፡ አንዲት ቆንጆ ሴት የሰጠችኝን ምክር አምኜ ነው ጥፋትን የፈፀምኩት!” ሲል መለሰ ሡልጣኑም፤ “ይሄማ የወንጀል ወንጀል ነው! ከጥፋትህ የከፋው ደግሞ የአሳሳች ምክር ማዳመጥህ ነው! ከቆንጆ ሴትም ይምጣ ከአስቀያሚ ሴት ምክሩን ሳትመረምር ወንጀል መፈፀም ከፍተኛ ጥፋት ነው፡፡ ዋጋህን ልታገኝ ይገባል፡፡ እንዲያውም የሰው ምክር ሰምቼ ከምትል ራሴ በራሴ ፈፀምኩት ብትለኝ ይሻል ነበር!” አሉና ማረፊያ ክፍል ሆኖ ፍርዱን እንዲጠብቅ አዘዙት፡፡ ሁለተኛው ወንጀለኛ የመጀመሪያውን ተከሳሽ ሡልጣን ሲያናግሩት ሰምቷል፡፡ “ሁለተኛው ወንጀለኛ ይግባ” ሲሉ አዘዙ፡፡ ተጠርቶ ቀረበ፡፡

ሡልጣኑ፤ “አንተስ፤ ምን ሆነህ ነው ወንጀል የፈፀምከው?” ሁለተኛው፤ “ሡልጣን ሆይ! እኔ ማንም ቆንጆ ወይም አስቀያሚ ሴት አላሳሳተችኝም፡፡ ራሴው በራሴው የፈፀምኩት ወንጀል ነው፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ!” ሲል አስረዳ፡፡ ሡልጣኑም፤ “ያንተ ደግሞ ከመጀሪያውም የባሰ ነው! የሠራኸው ወንጀል ሳያንስ፤ ጭራሽ ከዚህ ችሎት በሰማኸው ክርክር ችሎቱን ለማሳሳት ትሞክራለህ! አንተ እጥፍ ቅጣት መቀጣት አለብህ፡፡ ማረፊያ ቤት ቁጭ በልና ፍርድህን ጠብቅ” አሉት፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወንጀለኞቹ ወደ ሱልጣኑ ተጠሩ፡፡ ሱልጣኑ፤ “የፈፀማችሁት ወንጀል ከፍተኛ ነው፡፡ ይኸውም አንተ የመጀመሪያው ምክር በመስማትህ ወንጀለኛነትህ የተረጋገጠ ሲሆን፤ አንተ ሁለተኛው ደግሞ የምክር ምክር በመስማትህ ወንጀለኛነትህ ተረጋግጧል፡፡

ስለዚህ ሁለታችሁም ሞት ተፈርዶባችኋል” አሉ፡፡ ይሄኔ የመጀመሪያው፤ “ሱልጣን ሆይ ፍርዴን የሚያስነሳልኝ አንድ ሀሳብ ላቅርብ?” ሲል ጠየቀ፡፡ “ሀሳብህን እንስማ ተፈቅዶልሃል” አሉ ሱልጣኑ፡፡ “ሱልጣን ሆይ! የሚወዱት ፈረስዎ በአንድ ዓመት ውስጥ ክንፍ አውጥቶ መብረር እንዲችል እንዳስተምረው ይፈቀድልኝ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ሱልጣኑ ፈረሳቸው ክንፍ አውጥቶ ተቀምጠውበት ከዓለም በላይ ሲበሩ ታያቸውና፤ “መልካም፤ እስከዚያው የሞት ቅጣቱ ይዘግይ” ብለው አሻሻሉት፡፡ ወንጀለኞቹ ወደማረፊያቸው እንደደረሱ ሁለተኛው ተከሳሽ ጓደኛውን ጠየቀው፡፡ “ስማ፤ ፈረሶች ክንፍ አውጥተው እንደማይበሩ ታውቃለህ፡፡ እንዲህ ያለ የዕብድ ሀሳብ ለምን ታቀርባለህ? የማይቀርልንን ሞት ማዘግየትስ ምን ይጠቅማል?” ሲል ጠየቀው፡፡ አንደኛው ተከሳሽም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንደሱ አይደለም ወዳጄ፡፡ ነፃ ለመውጣት አራት ዕድል እየሞከርኩ ነው፡፡ አንደኛ - ማን ያውቃል እስከ አንድ ዓመት ንጉሱ አንድ ነገር ይሆኑ ይሆናል፡፡

ሁለተኛ - እኔም እራሴ እሞት ይሆናል ሦስተኛ - ወይ ፈረሱ ይሞት ይሆናል አራተኛ - ወይ ምናልባት ተሳክቶልኝ ፈረሱን መብረር አስተምረው ይሆናል!”

                                                  * * *

ጊዜ መግዛት የብልሆች ዘዴ ነው፡፡ ብዙ ዕድሎች እያሉን ጊዜ መግዛት ባለመቻላችን ብቻ የሚይመልጡን አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ያለ ዲሞክራሲ ኃይሎች መገንባት አንችልም፡፡ ዲሞክራሲን የሚያራምድ ኃይል እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ የሚሸከም አካልም ሊኖር ያሻል፡፡ ያ ደግሞ በፈንታው መልካም መደላድልን ይጠይቃል፡፡ ከመደላደሎቹ አንዱ ባህሉን በቅጡ ማወቅ፣ ተዛማጅ ትርጉም መስጠትና ማዋሃድ፤ ሶሲዮ-ኢኮኖሚውን መመርመርና አብሮ ዕሳቤ ውስጥ ማስገባት፤ ከሁሉም በላይ ግን፤ አስተሳሰባችንን የምንቀርፅበት ወሳኝ መሠረት ትምህርት መሆኑን መረዳት ነው፡፡ የዕውቀት ሰዎቻችንን ካላከበርን አገራችንን አናከብርም የሚባለው ለዚህ ነው! ለነዚህ ሁሉም መጠንጠኛቸው ጊዜ ነው! ጊዜን ለቅፅበትም ለዘለዓለምም አብዝቶ መጠቀም የሚችል ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ አዕምሮውን በቀለም ያነፀ “እንደወዶ-ገባ ኮርማ፣ ተነስ ሲሉት የማይነሳ፣ ተኛ ሲሉት የማይተኛ”፣ ልበ-ሙሉና በራሱ የሚተማመን ወጣት ካለን ወይም ካፈራን፤ ጊዜ የእሱ ናት፡፡

ስለ ሀገር የመቆርቆሪያ፣ ስለ ዕድገት የማሰቢያ ጊዜ ሊገባው የሚችል ተረካቢ ትውልድ አለን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ወጣት እንደኛ ያለችው ደሀ አገር ከቶም ሜዳ አትሆንለትም፡፡ አቀበቷ፣ አባጣ ጐርባጣዋ፣ ጠመዝማዛ አንጋዳዋ ስለሚበዛ፤ ሁሌ በቀለበት መንገድ የሚሄድባት አገር አትሆንለትም፡፡ የቀደሙትን ቢከተልም፣ እነሱም በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ተኝተው ያደሩባት አገር እንዳልሆነች ይረዳል፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተባሉ የሀገራችን የትምህርት ሊቅ፤ ታዋቂውን ገጣሚ ዳንቴን ጠቅሰው አንድ ግጥሙን እንዲህ ያቀርቡልናል፡፡ “ወጣቶች አነሱ ግንባራቸውን፤ ሊጠይቁ (እ)ኛን “ታውቁት እንደሆነ እስኪ ንገሩን ባቀበቱ ዙሪያ መንገድ ይኖረን፤ ቪርጂልዮ መለሰ እንዲህም አላቸው መስሎአችሁ ይሆናል እኛ የምናውቀው ምንገደኞች ነነ እኛም እንደናንተው ትንሽ ቀደም አልንይ የደረስን አሁን ነው መንገዳችን ሌላ፤ የባሰ ከናንተው (ቀጥ ያለ አቀበት ነው እንቅፋት የመላው) እንግዲህስ መውጣት ለኛ መቅለሉ ነው፡፡

(መካነ ንስሐ፤ መዝሙር 2) ወጣቱ የራሱ ጊዜ ይኑረው ሲባል ያባቱን ሞት ጠባቂ፣ ቅርስ ናፋቂ የማይሆንበት አትሁን ማለታችን ነው አገሩን አገር በራሱ እጅ ያንጽ፣ በራሱ ወቅት ይጠቀም ማለት ነው፡፡ “ካላለፍነው ትላንት የለም፣ ካልኖርነው ዛሬ የለም፡፡ ካላቀድነው ነገ የለም” የሚሉት ፀሐፍት ለአፍ አመል አይደለም፡፡ የማያስብ፣ የማይሰራ፣ ችግሩን አስቦ፣ መላ መትቶ የማይፈታ ትውልድ ነገ የለውም፡፡ ጠያቂ ትውልድ መፈጠር አለበት፡፡ ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን፣ ባህሉን፣ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚመረምር፣ ንቃተ - ህሊናው የዳበረ ትውልድ ሊኖር ይገባል፡፡ የአበውን ቁምነገር የማይዘነጋ፣ የሚጥል - የሚያነሳውን ኑሮ የተገነዘበ ወጣት ትውልድ፤ አገር አለኝ የማለት አቅም ይኖረዋል፡፡ “ከመሠረት ጋር አትጣላ ለሁልጊዜ ይሆንሃል፡፡ ካብ ጋ አትጠጋ እላይህ ላይ ይፈርሳል” የሚለውን የአበው አነጋገር ልቡ ላይ ሊያትም ይገባዋል፣ የምንለው፤ ያን መሳይ ወጣት ይኖረን ዘንድ አበክረን በማሰብ ነው፡፡

Read 5153 times