Monday, 15 April 2013 10:12

አልማዙን ዋጥ! (ይሞታል እንዴ?)

Written by 
Rate this item
(283 votes)

ባለፈው ረቡዕ በደሴቲቷ አገር በኢንዲያን ኦሽን ትልቅ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር - ውድ ውድ የከበሩ ድንጋዮችና የአልማዝ ጌጣጌጦች የቀረቡበት፡፡ ለዚህም ከቻይና፣ ከሆንግኮንግ፣ ከታይላንድ፣ ከህንድ እና ከአውሮፓ የመጡ ገዢዎች በኤግዚቢሽኑ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ግርግር መሃል ነው ፖሊስ አንዱን የቻይና ቱሪስት በስርቆት ጠርጥሮት በቁጥጥር ሥር ያዋለው፡፡ ቱሪስቱ 171 ሺ ብር ገደማ የሚያወጣ አልማዝ (diamond) ውጠሃል በሚል ነበር የተጠረጠረው፡፡ “ዓላማው መስረቅ ነበር” ሲል ለሮይተርስ የተናገረው የስሪላንካ ፖሊስ ቃል አቀባይ አጂት ሮሃና፤ በኤክስሬ መመርመርያው በጉሮሮው ውስጥ የነበረውን አልማዝ ማየት እንደቻለ ገልጿል፡፡ የ32 ዓመቱ ቻይናዊ ቾው ቼንግ አልማዙን በኤግዚቢሽኑ ላይ እየተመለከተ ሳለ እንደዋጠው ታምኗል፡፡

ኤግዚቢሽኑ የተካሄደበት አዳራሽ ባለቤት ክሪስቶፈር ዊጅኩን በበኩሉ፤ ቻይናዊው ቱሪስት ኦሪጂናሌውን አልማዝ በሲንቴቲክ አልማዝ ለመለወጥ እንደሞከረ ለሮይተርስ ተናግሯል፡፡ “እኔ እንዳስተዋልኩት ገባውና ከመቅጽበት አልማዙን ዋጠው” ብሏል ዊጅኩን ለሮይተርስ፡፡ የኢንዲያን ኦሽን ደሴት በአልማዞችና በጌጣጌጥ ኢንዱስትሪዋ የታወቀች ስትሆን በ2011 እ.ኤ.አ የኤክስፖርት ገቢዋ 532 ሚ .ዶላር እንደነበር ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡ ይሄ የፈረደበት ቻይናዊ እንግዲህ የዋጠውን አልማዝ እስኪተፋ ድረስ መከራውን መብላቱ አይቀርም፡፡ የሌብነት መዘዝ ይሄው አይደለ!!

Read 36642 times