Monday, 15 April 2013 09:25

ኮ/ል አወል አብዱራሂም በደደቢት አቅጣጫዎች ላይ …

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኮሎኔል አወል አብዱራሂም በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ባመነጩት ሃሳብ የደደቢት ስፖርት ክለብን በ1989 ዓ.ም መስርተዋል፡፡ ታዳጊ ህፃናትን በማሰልጠን ከ16 ዓመት በፊት የተጀመረው ክለቡ ገና በወጣትነት እድሜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ እንደሚያኮራቸው ኮ/ል አወል አብዱራሂም ይናገራሉ፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፎ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን ለመወከል እንዲበቃም ምኞት አላቸው፡፡ ደደቢት በኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር የሆነውን ፕሪሚዬር ሊግ መሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ ገና በአራተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ቢሆንም፤ በሊጉ የሻምፒዮናነት ፉክክር ከሚጠቀሱት 3 ክለቦች አንዱ ሆኗል፡፡ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 9 ተጨዋቾች በማስመረጥም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

የደደቢት የስፖርት ክለብ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ፤ በወደፊት አቅጣጫዎቹ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከክለቡ መስራችና ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ጋር ስፖርት አድማስ ቃለምምልስ አድርጓል፡፡ - የደደቢት ስፖርት ክለብ የተመሰረተበትን 16ኛ ዓመት ከሳምንት በፊት አክብሯል፡፡ ክለቡ በዚህ ጊዜ ያለፈባቸውን ጉልህ ሂደቶች እና ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ይመለከቱታል? የደደቢት የስፖርት ክለብ በወቅታዊ የእግር ኳስ እንቅስቃሴው ጥሩ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በተለያዩ የስልጠና ፕሮጀክቶች እና ውድድሮች የሚሳተፉ የክለቡ ቡድኖች የሚያበረታታ ውጤት እያሳዩ ናቸው፡፡ የቡድኖቹን ጥንካሬ እና ውጤታማነት በብዙ መልክ መግለፅ ይቻላል፡፡ በፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆነው ዋናው ቡድን የውድድር ዘመኑ ሲጋመስ በደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ሆኖ ነው፡፡ ይህ ውጤት ድንገተኛ ክስተት አይደለም፡፡ ክለቡ በፕሪሚዬር ሊግ በተሰለፈባቸው ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ለሻምፒዮናነት ከሚፎካከሩ ሶስት ክለቦች አንዱ ነበር፡፡ ዘንድሮም ይህን ብቃት መቀጠሉ የሚያኮራ ነው፡፡ ክለባችን በአደረጃጀቱ በተለይ በተጨዋቾች ስብስቡ አስፈላጊው ጥራት እንዲኖር ያተኩራል፡፡

እንግዲህ ከ16 አመት በፊት ክለቡ ሲመሰረት የተነሳንበት መሰረታዊ አካሄድ ከ10 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን አሰባስቦ በማሰልጠን ነበር፡፡ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት በመስራት ጥራት ያላቸውን ተጨዋቾች ማፍራት አቅደን ነበር የተነሳነው፡፡ አንድ ክለብን በብቁ የተጨዋቾች ስብስብ እና ጥራት ባለው አደረጃጀት ለማቆም ከስር ተነስቶ በረጅም ጊዜ እቅድ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ከ16 አመት በፊት ክለቡን የጀመርንበት የ U-10 ቡድን በሚያገኘው ስልጠና በአገሪቱ ምርጥ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ስልጠናችንን ወደ U-15 በማሳደግ ቀጠልን፡፡ በ1992 ዓ.ም የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖቹ በአገር አቀፍ ውድድሮች ጥሩ ተፎካካሪ ሊሆን ከመቻሉም በላይ በስብስቡ ጥራት እንደሞዴል ሊታይ የበቃ ነበር፡፡ የደደቢት U-17 ቡድን በነበረው የስብስብ ጥራት እና የተሟላ የብቃት ደረጃ ለአዲስ አበባ ሞዴል ሆኖ ከመታየቱም በላይ የከተማ መስተዳደሩን ፈቃድ አግኝቶ በአገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ሊሆን የበቃ ብቸኛው የግል ፕሮጀክት ነበር፡፡ እንግዲህ ከክለቡ ምስረታ በኋላ ለሰባት ዓመታት በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ሰፊ ስራ በማከናወን ቆይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ በተመሰረተው ዋና ቡድን 2000 ዓ.ም ላይ ወደ ብሄራዊ ሊግ ውድድር ገባን፡፡ ክለቡን ከመሰረትን ከ12 ዓመት በኋላ ደግሞ ፕሪሚዬር ሊጉን ለመቀላቀል በቅተናል፡፡ ክለቡ የሚያንቀሳቅሳቸው የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ናቸው?

ደደቢት ብቁ እና ምርጥ ተጨዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች በከፍተኛ ገንዘብ አሰባስቦ የተጠናከረ ክለብ የሚባልም ነገር አለ? የተጨዋቾች ግዢ በአንድ ክለብ አወቃቀር የሚያስፈልግ አሰራር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ማንም ክለብ የሚሳተፈው በቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ያሉ ክፈተቶችን ለመሙላት እና ልምዱን ለማጠናከር ነው፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ የተጨዋቾች ግዢን እንደ ዋና ፖሊሲው ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ክለባችንን ለመገንባት የምንከተለው ፖሊሲ ከምስረታችን ጀምሮ በሰራንባቸው የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች የማያቋርጥ እድገት ላይ የተመሰረተ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደደቢት የስፖርት ክለብ 150 ስፖርተኞችን ይዘናል፡፡ በU-15 ደረጃ በአርባ ምንጭ እና በመቀሌ በሚገኙ ሁለት የፕሮጀክት ማእከሎች 55 ስፖርተኞች በመያዝ እየሰራን ነው፡፡ ለዋናው ቡድን መጋቢ እንደሚሆን የታመነበት እና በU- 17 ደረጃ የምናንቀሳቅሰው ፕሮጀክት 25 ስፖርተኞችን በማቀፍ እየሰራ የሚገኘው በአዲስ አበባ ነው፡፡

ባለፈው አመት በስራ አጋጣሚ ወደ ጋና ሄጄ ባገኘሁት ሃሳብ ደግሞ የተስፋ ቡድንም መስርተናል፡፡ በU-19 ደረጃ የምናሰለጥንበት ይህ የተስፋ ቡድን ለዋናው የቡድን መዋቅር መሰረት መሆኑን በማመን ያስጀመርነው ነው፡፡ ይህን የተስፋ ቡድን በU- 17 ደረጃ ከምንሰራበት የቢ ቡድን ጋር በማቀናጀት የምናንቀሳቅሰው ነው፡፡ በቢ ቡድን ያሉ ተጨዋቾችን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ መስራት ውጤታማ አያደርግም፡፡ ስለዚህም በU-19 የምንሰራበትን የተስፋ ቡድኑን ወደ ዋናው ቡድን ለምናሳድጋቸው ተጨዋቾች እንደመሸጋገርያ የምንጠቅምበት ይሆናል፡፡ በዚህ የተስፋ ቡድን ፕሮጀክት በየዓመቱ ያለማቋረጥ ዋናውን ቡድን የምንገነባበትን ሂደት በጥሩ መሰረት ይዘነዋል፡፡

ለክለቡ መጠናከር የሚያግዙ ወጣት ተጨዋቾች ከማፍራት ባሻገር በአገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ውድድር ተሳታፊ በሆኑ ክለቦች ለመጫወት የሚበቁ ተጨዋቾችን በዝውውር ገበያው በማቅረብ ገቢ ለማግኘት ተስፋ ያደረግንበት እንቅስቃሴም ነው፡፡ አርባ ምንጭ ላይ በምንሰራው የU- 17 ፕሮጀክት ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ለፕሪሚዬር ሊግ የሚመጥኑ ተጨዋቾችን እንደምናወጣበት በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡ በአጠቃላይ ከእነዚህ የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ፕሮጀክቶች ወደ ሌሎች ክለቦች ያዘዋወርናቸውን ስፖርተኞች ባይኖሩም ዋና ቡድናችንን በእነዚህ ፕሮጀክቶች መገንባቱ በገሃድ የሚታይ ጥቅም ነው፡፡ ዘንድሮ በፕሪሚዬር ሊግ በሚወዳደረው ዋናው ቡድናችን ላለፉት አራት አመታት በማሰልጠን ያፈራናቸውን 7 ተጨዋቾች አስገብተናል፡፡ ደደቢት የስፖርት ክለብ በአደረጃጀቱ የሚያስፈልጉትን መሰረተ ልማቶች አሟልቷል ?ወይንስ ችግሮች አሉ? እንግዲህ ለዋናው ቡድን የስፖርት ክለቡ የተጨዋቾች ካምፕ አለው፡፡ የትጥቅ አቅርቦቱም የተሟላ ነው፡፡ በመሰረተ ልማት ደረጃ ለደደቢት ክለብ ትልቁ ችግር የራሱን የልምምድ ሜዳ አዘጋጅቶ በተማከለ ሁኔታ አለመንቀሳቀሱ ነው፡፡ ደደቢት የራሱ ሜዳ የለውም ማለት ያሳዝናል፡፡ በፋይናንስ ያለው አቅም ደካማ መሆን ያለበትን የሜዳ ችግር ለመቅረፍ ዋና እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በእርግጥ ክለቡ ከአዲስ አበባ መስተዳደር የልምምድ ሜዳውን የሚያቋቁምበት መሬት አግኝቷል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና የመስተዳደሩ አመራሮች የሰጡን ትብብር ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ነው፡፡ በደደቢት የእግር ኳስ ክለብ ስር እዚህ አዲስ አበባ ላይ የሚሰሩ አራት ቡድኖች አሉ፡፡ በአርባምንጭ ያለው ፕሮጀክታችን የሜዳ ችግር የለበትም፡፡

የአርባ ምንጭ መስተዳድር የክለባችን ፕሮጀክት በመደገፍ በከተማዋ የሚገኝ ስታድዬም ቅድሚያ ተሰጥቶን ለፕሮጀክታችን እንደሜዳ እንድንገለገልበት በመፍቀዱ በዚያ ችግር የለብንም፡፡ በመቀሌ ፕሮጀክትም ከክልሉ መስተዳድር ተመሳሳይ ድጋፍ እያገኘን ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑት አራት ቡድኖች ግን መደበኛውን የስልጠና እና የልምምድ ፕሮግራም በአራት የተለያዩ ቦታዎች ተዘበራርቀው እየተገለገሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ቡድኖች ለሚሰሩባቸው ሜዳዎች ኪራይ በምንከፍለው ገንዘብም ብዙ ወጭ እያወጣን ነው፡፡ አሁን ዋናው ቡድን የሚሰራውየመድን ክለብን ሜዳ ተከራይቶ ነው ፡፡ በአንድ ልምምድ እስከ 700 ብር እየከፈለ ነው፡፡ የተስፋ ቡድናችን ደግሞ በፌደራል ፖሊስ ሜዳ ይገለገላል፡፡ የሴቶች ቡድኑ በህንፃ ኮሌጅ ሜዳ እየሰራ ነው፡፡ ሌላው የፕሮጀክት ቡድን ደግሞ የሚጠቀመው የቀበሌ ሜዳ ነው፡፡ በእነዚህ አራት የተለያዩ ሜዳዎች አራቱ ቡድኖች ተዘበራርቀው መስራታቸው በሜዳ ክራይና በትራንስፖርት ወጪ የስፖርት ክለቡ እየተቸገረ ነው፡፡ ከገንዘብ ወጪውም ሌላ ብዙ እድገትን የሚያስተጓጉሉ ችግሮች እየገጠሙን ነው፡፡ ዋናው ቡድን ከሚሰራበት የመድን ሜዳ በቀር በሌሎቹ ሜዳዎች የተመቹ አይደሉም፡፡ በፈለግነው ሰዓት እና ፕሮግራም ሜዳዎቹን ስለማንጠቀምም ተሰቃይተናል፡፡ የማይመቹት ሜዳዎች በየቡድኑ የተያዙ ተጨዋቾችን ለጉዳት መዳረጋቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡ እናም በደደቢት ክለብ ላይ በመሰረተ ልማት ረገድ አሳሳቢው ችግር የራሳችን ሜዳ ሊኖረን አለመቻሉ ነው፡፡ ይሄን ችግር በቀጣይ ዓመት ለመፍታት ፍላጎት አለን፡፡ የአዲስ አአባ መስተዳደር መሬት በሊዝ ሰጥቶናል፡፡ መሬቱን በሊዝ መግዛት ቢኖርብንም 7.5 ሚሊዮን ብር መክፈል ባለመቻላችን እስካሁን አልተረከብነውም፡፡ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ከፍለን ካልተረከብነው ሊወሰድብን ይችላል፡፡

የየፕሮጀክቶቹን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ፤ በየደረጃው የሚወዳደሩ የክለቡን ቡድኖች ማንቀሳቀሻ በጀት ለመመደብ እንዲሁም ክለቡን በመሰረተ ልማት ለማጠናከር በቂ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ የሚተዳደርበት አቅም ምን ደረጃ ላይ ነው? የደደቢት ስፖርት ክለብ በቂ የፋይናንስ አቅም የለውም፡፡ በየፕሮጀክቱ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት፤ በዋናው ቡድን የፕሪሚዬር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪነት ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ ባሳየነው አቅም እና ለብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ብዛት ያለውን የተጨዋቾች አስትዋፅኦን በመመልከት ክለቡ በከፍተኛ ፍጥነት እድገት ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይሁንና እነዚህ አበረታች እንቅስቃሴዎችን በዘላቂነት ለመቀጠል የሚያስፈልገው አስተማማኝ ፋይናንስ ግን የተጠናከረ አይደለም፡፡ ከፈጣኑ የክለባችን እድገት ተያይዞም የፋይናንስ ፍላጐቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ ከ16 አመታት በፊት ከተመሰረተ አንስቶ ዛሬም ድረስ የራሱ ገቢ የለውም፡፡ የክለቡ የፋይናንስ አቅም በአጋርነት አብረውን በሚሰሩት ግለሰቦች እና አጋር ድርጅቶች ድጋፍ የተወሰነ ነው፡፡ ክለቡ ሲመሰረት ከተወሠኑ ደጋፊዎች የምናገኘው ድጋፍ በሺዎች የተወሰነ ነበር፡፡ በየውድድር ዘመኑ ግን ክለቡ እያደገ ከመምጣቱ፤ በአህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ ከመሆኑ እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ መገኘቱ ከደጋፊዎቻችን በሚሊዮን የሚገመት መዋእለንዋይ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡

ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት አጋር ድርጅቶች በየጊዜው በሚያደርጉልን መዋጮ በጀታችንን በመሸፈን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በ1999 ዓ.ም ክለቡ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር አንዳንድ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች በገንዘብ መዋጮ ለክለቡ ድጋፍ መስጠት ጀምረዋል፡፡ የመጀመርያውን ድጋፍ ያገኘነው ለኢትዮጵያ ስፖርት ማደግ ከፍተኛ ፍላጎት ካላቸው ክቡር ሼህ መሃመድ አላሙዲ ነው፡፡ ከእርሳቸው ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 18 ሚሊዮን ብር አግኝተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ከመከላከያ ድርጅቶች ጋር የምንሰራበትን ሁኔታ በመፍጠር ስንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ ዛሬ እነዚህ የመከላከያ ድርጅቶች የክለቡ ግንባር ቀደም አጋሮች ናቸው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ የክለቡ የፋይናንስ ደጀን ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡ ከመከላከያ ድርጅቶቹ ሲሰጥ የቆየው የበጀት ድጋፍ በስፖንሰርሺፕ ስምምነት አይደለም፡፡ ለክለቡ ባላቸው ተቆርቋሪነት የክለቡ ራዕይ ዘላቂነት እንዲኖረውና ለአገር የሚሆነውን አስተዋፅኦ በማመናቸው የበጀት ድጋፍ እያደረጉልን ይገኛል፡፡ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የመከላከያ ብረታ ብረት ኢንጅነሪኒግ ኮርፖሬሽን ዋናዎቹ የክለቡ አጋሮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ክለቡ ለዘንድሮ የውድድር ዘመን የያዘው በጀት 16 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ በጀት 80 በመቶው የተሸፈነው በእነዚህ ድርጅቶች ነው፡፡

አሁን የክለቡ አመራሮች የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር በሚያስችል አቅጣጫ ለመስራት ወስነናል፡፡ ክለቡ በፋይናንስ አቅም ተዳክሞ ከሚገኝበት የዕድገት አቅጣጫ እንዳይሰናከል አጋሮቻችን የዚህ እቅድ ዋነኛ ሃይል ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት በቀጣይ የውድድር ዘመን የደደቢት ስፖርት ክለብን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ኩባንያ ለማቋቋም ወስነናል፡፡ ይህ አቅጣጫ የክለቡን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር ለህልውናው ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን አምነንበታል፡፡ የመከላከያ ድርጅቶች ከደደቢት ጋር በአጋርነት መስራታቸው ከመከላከያ ክለብ የጥቅም መጋጨትን የሚፈጥር ሁኔታ አይደለም ወይ ? የመከላከያ ክለብ ባለቤትነት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እና ሠራዊቱ ነው፡፡ ባለኝ መረጃ መሠረት ክለቡ ከሠራዊቱ በሚገኝ መዋጮ እና በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሚለቀቅ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ እኔው ራሴ በመከላከያ ሚኒስትር ሰራተኛነት እስከ ባለፈው ዓመት በቆየሁባቸው ዓመታት ለመከላከያ ክለብ በየወሩ ከደሞዜ መዋጮ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ የደደቢት እና የመከላከያ ክለቦች ከፋይናንስ ድጋፎች ጋር በተያያዘ የገቡት የጥቅም ግጭት ሆነ ቅራኔ ያለ አይመስለኝም፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሰራዊቱ ለደደቢት ክለብ የሚከፍሉት መዋጮ የለም፡፡

የደደቢት ስፖርት ክለብ አጋሮች የሆኑት የመከላከያ ድርጅቶች እንጂ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሰራዊቱ አይደለም፡፡ በእርግጥ ደደቢት በስታድዬም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ክለቡን ለመደገፍ የሚመጡ የሠራዊቱ አባላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን እንደማንኛውም የስፖርት ማህበረሰብ ቡድኑን በማድነቃቸው ብቻ የሚያደርጉት እንጅ የክለቡ ባለድርሻ ሆነው አይደለም፡፡ ክለቡ የገቢ ምንጮቹን ለማስፋት የሚያደርጋቸው ጥረቶች በምን ደረጃ ላይ ናቸው? በአገራችን እግር ኳስ ላይ የተጋረጠ አንዱ ትልቅ ችግር የስፖርት ስፖንሰርሺፕ አሠራር አለመስፋፋቱ ነው፡፡ የማልያ ስፖንሰር ሺፕ እንኳን አግኝቶ የክለብን የገቢ አቅም መጨመር ብዙ የተጠናከረ አይደለም፡፡ ደደቢት በማልያ ስፖንሰርሺፕ በፈርቀዳጅነት ሊታይ የሚገባ ጥረት አድርጓል፡፡ ለሁለት አመት በሚቆይ የውል ስምምነት የደደቢት የማልያ ስፖንሰር የሆነው የሳምሰንግ ኩባንያ ነው፡፡ ስምምነቱ ከጅምሩ ለክለቡ 1 ሚሊዮን 400ሺ ብር ያስገኘ ነው፡፡ በማልያ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሳምሰንግ ኩባንያ የሚከፍለን ገንዘብ በ300ሺ እንዲጨምር አቤቱታ አቅርበን ነበር፡፡

በጎ ምላሽ አግኝቶ ከማሊያ ስፖንሰር ሺፕ የምናገኘው ገቢ 1 ሚሊዮን 700ሺ ብር ደርሷል፡፡ የማልያ ስፖንሰርሺፕ ድጋፉን ያገኘነው በኢትዮጵያ የሳምሰንግ ኩባንያ ወኪል ሆኖ በሚሰራው የጋራድ ኩባንያ በኩል ነው፡፡ የስፖንሰርሺፕ ውሉን በፈርቀዳጅነት ስንጀምረው በቂ ጥቅም አግኝተንበት አይደለም፡፡ ከኩባንያው ጋር በዘላቂነት የምንሰራበትን መግባባት ለመፍጠር ብለን የፈፀምነው እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በርግጥ በመደበኛው አሠራር የማልያ ስፖንሰሩ ትጥቆቹን በሙሉ ለክለቡ ማቅረብ ነበረበት፡፡ እኛ ጅምር የስፖንሰርሺፕ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማበረታታት ብለን ሙሉውን ትጥቅ በመግዛት በመጠቀም ላይ ነን፡፡ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን ጀምሮ ይህን የማልያ ስፖንሰርሺፕ በአዲስ የውል ስምምነት ለማሻሻል እንፈልጋለን፡፡ የሳምሰንግ ኩባንያ ኃላፊዎችም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ሌሎች አጋር ድርጅቶችን በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በዙሪያችን እንዲሰባሰቡ ብንፈልግም በኢትዮጵያ ስፖርት በጋራ ተጠቃቅሞ የመስራት አካሄድ ባለመጠናከሩ አልተሳካልንም፡፡

በርካታ ኩባንያዎችና ድርጅቶች የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለጋራ ጥቅም ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍን ከልመና ጋር የምናያይዝበት ደካማ አስተሳሰብ አለ፡፡ የገቢ ምንጮችን የሚያጠናክሩ የስፖንሰር ሺፕ ድጋፎችን ለማግኘት የአገሪቱ እግር ኳስ ደረጃ አለማደግ እንደ ዋና ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች በየውድድር ጠንካራ ተሳትፎና ውጤት እያገኙ መምጣታቸው የብሔራዊ ቡድኖች በትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በዘላቂ ሁኔታ መሳተፋቸው የስፖንሰሮችን ፍላጎት ሊፈጥር እንደሚችል ግን ተስፋ እያደረግን ነው፡፡ መጭው ጊዜ በስፖንሰርሺፕ ድጋፎች የክለቦችን የገቢ ምንጭን ለማስፋት ተስፋ አስቆራጭ አይደለም፡፡ ደደቢት በፌደሬሽኑ በኩል በሚያጋጥሙ ምቹ ያልሆኑ አሰራሮችን በተደጋጋሚ በመጋፈጥ፤ በመቃወም እና ጠንካራ አቋሞቹን በማንፀባረቅ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር ፕሮፌሽናል የሊግ ኮሚቴ አለመመስረቱን በተመለከተ ምን አስተያየት ይኖርዎታል? ደደደቢት ብሄራዊ ሊግ መወዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፌደሬሽኑ ምቹ ያልሆኑ አሰራሮች ጋር ፊት ለፊት ሲጋጠም ቆይቷል፡፡ ክለቡ የማያምንበትን አሰራር በመተቸት እና አቋሙን በመግለፅ የሚታገል ነው፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባናገኝም ለመመርያ ተገዢ በመሆን አቋማችንን ከመግለፅ ወደኋላ አንልም፡፡ የሊግ ኮሚቴ ፌደሬሽኑን ባቀፈ ኮሚቴ የሚሰራበትን ሁኔታ በጣም የምንቃወመው ነው፡፡ የአንድ አገር ሊግ ውድድር በፕሮፌሽናል መካሄድ ካለበት የኮሚቴ አሰራር አይሆንም ፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ውድድርን ተሳታፊ ክለቦች በባለቤትነት ይዘውት እንደኩባንያ መተዳደር አለበት፡፡ በዚህ አይነት አሰራር አለመወዳደራችን ብዙ ነገር እያሳጣን ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሊግ ውድድሩ ለክለቦች በቂ የገቢ አቅም እየፈጠረ አይደለም፡፡ የክለቦች የሜዳ ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በዚያ ላይ ፌደሬሽኑ ተገቢ ያልሆነ ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከሜዳ ገቢ የፌደሬሽኑ ድርሻ 32 በመቶ መሆኑይህ በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ በዚህ አይነት ዓመቱን በሙሉ ከሜዳ የምንስበስበው ገቢ የአንድ ተጨዋች ደሞዝ እንኳን የሚሸፍን አይደለም፡፡ ፕሮፌሽናል የሊግ አመራርን በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር መከተል ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ የሊጉ ውድድር አብይ ስፖንሰር በማግኘት ከፍተኛ ገቢ ማምጣት አለበት፡፡ ለተወዳዳሪ ክለቦች በቂ የገቢ ድርሻ የማያስገኝ ውድድር ምንም አይነት እድገት ሊኖረው አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ክለቦች የተለያዩ የገቢ ምንጮች ሊፈጥሩ የሚችሉበትን አሰራር ዘርግቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በክለቦች ብቻ የሚመራ ፕሮፌሽናል የሊግ ኮሚቴ ለማቋቋም ክለቦች አቋም ነበራቸው ፡፡ ይህ አቋም እስከዛሬ ለምን ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ አይገባኝም፡፡

Read 4701 times