Monday, 15 April 2013 08:17

የመብራት፣ የውሃና የስልክ ችግር በመንግስት አይፈታም - መቼም ቢሆን!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

መንግስት ከላያችን ላይ እጁን እንዲያነሳ ማድረግ ነው መፍትሄው - ማርጋሬት ታቸር እንዳደረጉት። የችግሩ ስረመሰረት እንዲነቀልና ትክክለኛው መፍትሄ ተግባራዊ እንዲሆን ፈፅሞ የማንፈልግ ከሆነስ? በ“አንዳች ተአምር” መፍትሄ እንዲመጣ እንጠብቃለና - ለ30 አመት በከንቱ ስንጠብቅ እንደኖርነው።

በኤሌክትሪክ፣ በውሃ እና በስልክ ችግር መማረር ሰልችቷቸው፣ “ኧረ ይሄስ፣ መላም የለው!” ብለው በተስፋ ቢስነት የተቀመጡ ሰዎች ይኖራሉ። ይፈረድባቸዋል? “ተስፋ መቁረጥማ ደካማነት ነው” ብለን እንዳንፈርድባቸው፤ “እናንተስ የትኛውን ተስፋ ይዛችሁ ነው?” በሚል ጥያቄ መልሰው ሊያፋጥጡን ይችላሉ። ይሄውና ስንት አመታችን! ከዛሬ ነገ፣ “ይሻሻላል” እያልን፣ እምነታችንን መንግስት ላይ ጥለን፣ ተዝቆ በማያልቅ ተስፋ ስንጠባበቅ ምን አተረፍን? ምንም! አንዳች ተጨባጭ መፍትሄና ማሻሻያ ሳይሆን፣ ቁጥር ስፍር የሌለው የማሳበቢያና የማመካኛ መዓት ነው ስንሰማ የኖርነው። አሁንም ጭምር። እንዲያም ሆኖ፣ ዛሬም ተስፋቸው ሳይሟጠጥ “አንዳች ተአምር” እንዲፈጠር የሚጠብቁም ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው - መንግስትን እንደ አባት ወይም እንደ ሞግዚት እንዲሆንላቸው የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች! የብዙ ፖለቲከኞችና የብዙ ምሁራን አስተሳሰብም ተመሳሳይ ነው።

የመንግስት ባለስልጣናትም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፤ “በአንዳች ተአምር” መፍትሄ እንዲፈጠር ይጠብቃሉ። በተለይ የዘንድሮ ባለስልጣናት ለዜጎች የሚሰጡት መፅናኛና ተስፋ ምን አይነት እንደሆነ ተመልከቱ። ከአስር አመት በፊት፣ የባለስልጣናት ዋነኛ የማመካኛ ሰበብ የደርግ ስርዓት ነበር - “ካለፈው ስርዓት ሲንከባለልና ሲከማች የመጣ ችግር ነው” የሚል መፅናኛ ንግግር እያስቀደሙ፤ “ትንሽ ታገሱ እንጂ ሁሉም ችግር በአምስት አመቱ የልማት እቅድ መፍትሄ ያገኛል” ብለው የተስፋ ቃል ይመግቡን ነበር። “ግድብ የመገንባት እቅድ… ኔትዎርክ የማስፋፋት እቅድ… ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን የመቆፈር እቅድ…” እያሉ ሲዘረዝሩት አጃኢብ ሊያሰኝ ይችላል። በእርግጥ፣ አንድም እቅድ ባለስልጣናት እንዳወሩለት በጊዜው አይጠናቀቅም።

ለአመታት ይጓተታል፣ ብዙ ገንዘብ ይባክናል። መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ፣ ስራ መጓተቱና ገንዘብ መባከኑ የተለመደ ቢሆንም አብዛኛው ሰው በትእግስት ይጠብቃል። ትእግስቱ እየሳሳ ሲሄድም፣ የመንግስት ባለስልጣናት ተጨማሪ ሰበብና የተስፋ ቃል አያጡም። በድህነት ላይ ያሳብባሉ። “የችግሩ ዋና ምንጭ ድህነታችን ነው። አሁን ግን አይዟችሁ። የተጀመሩት ግድቦች ተገንብተው ይለቁ እንጂ፣ ኔትዎርኮቹ ይስፋፉ እንጂ፣ ጥልቅ ጉድጓዶቹ ተቆፍረው ይጠናቀቁ እንጂ… በቃ ከዚያ በኋላ፣ ሁሉም ነገር በሽበሽ ይሆናል” ብለው ይደሰኩራሉ። ኢትዮጵያ፣ በሞባይል ስልክ ስርጭት ከሌሎቹ የአፍሪካ አገራት፣ ከሶማሊያ ሳይቀር ወደ ኋላ መቅረቷ ሳያንስ፣ የኔትዎርክ ጥራቱም እጅግ አሳፋሪና ትእግስት አስጨራሽ በመሆኑ ብዙ ሰው በየጊዜው ምሬቱን ይገልፃል። ታዲያ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ አያጡም፤ “የአቅም ችግር ስለሆነ፣ የኔትዎርክ ማስፋፊያው በጥቂት ሳምንታት ተጠናቅቆ ችግሩ ይወገዳል” ብለው ሲነግሩን፣ ብዙዎቻችን እንደአዲስ እንደገና ተስፋ እናደርጋለን። ለበርካታ አመታት የተለያየ ሰበብና እቅድ እየሰማን በጉጉት ስንጠብቅ፣ ተስፋችን እውን ሳይሆን እየቀረ አልጨበጥ ቢለንም፤ በአዲስ ሰበብ የታጀበ የባለስልጣናት ቃል ስንሰማ እንደ አዲስ ተስፋ ያድርብናል።

ከሁለት ከሶስት አመት በፊት ስለኤሌክትሪክ እጥረት ስንማረር ትዝ ይላችኋል? “ችግሩ የመነጨው ከኢኮኖሚ እድገቱ ነው፤ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ስለጨመረ ነው” የሚል ሰበብ ያቀርቡ ነበር ባለስልጣናት። እስቲ አስቡት! “በኢኮኖሚ እድገት ሳቢያ ደንበኞቼ ብዙ ሸቀጥ እየሸመቱ አስቸገሩኝ” በሚል ሰበብ በየሰአቱ ሱቁን የሚዘጋና ደንበኞቹን ሳያስተናግድ የሚያሰናብት ነጋዴ አይታችሁ ታውቃላችሁ? መክሰር የማይፈልግ ከሆነ፣ ደንበኞችን አያንገላታም። ገበያው ይድራለት እንጂ፣ ነጋዴ በቂ ሸቀጥ ለደንበኞቹ ማቅረብ አያቅተውም - ለራሱ ትርፍ ሲል። ምን ዋጋ አለው? ትርፍ ለማግኘት ተብሎ ለሚከናወን ስራ ብዙም ክብር የለንም። ለማትረፍ ሳያስብ የሚሰራ ሰው ነው የምንፈልገው - መስዋዕትነትን እንደቅድስና እየቆጠርን። በእርግጥም የመንግስት ባለስልጣናት ትርፍ ለማግኘት አይሰሩም። ደንበኛ ቢበዛላቸውና ገበያ ቢደራላቸው ምንም ትርፍ አያገኙበትም። ከመደበኛው ደሞዝ ያለፈ ወደ ኪሳቸው የሚገባ ሽልማት የለም።

በሌላ በኩልም ባለስልጣናት፣ ደንበኞችን ሳያስተናግዱ ቢመልሱና ቢያጉላሉ አይከስሩም፤ ምንም አይጎድልባቸውም። መደበኛ ደሞዛቸውን ማንም አይከለክላቸውማ። ለዚህም ነው፤ ከነጋዴ በተለየ ሁኔታ፣ የመንግስት ባለስልጣናት “ገበያተኛ በዛብኝ” ብሎ መናገር በቂ ማመካኛ ሆኖ የሚታያቸው። ከማመካኛው ሰበብ ጋርም፣ እንደተለመደው የተስፋ ቃል ያዘንባሉ - “ከእንግዲህ አትጨነቁ! የተከዜና የበለስ ግድብ ስለተጠናቀቀ በአጭር ጊዜ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተረት ይሆናል” ተብሎ ባለፉት ሁለት አመታት ተደጋግሞ ሲነገረን የስንቶቻችን ስሜት በተስፋ እንደተጥለቀለቀ አስታውሱ። በእርግጥ፤ ከዚያ በፊትም እንዲሁ፤ “ግልገል ጊቤ 1 ስለተጠናቀቀ፣ ስራ ሲጀምር የኤሌክትሪክ እጥረት መፍትሄ ያገኛል” ተብለን ነበር - እንደተጠበቀው አልሆነም እንጂ። የውሃ እጥረትም ላይም ተመሳሳይ ነው። ከሃረር እስከ አዳማ ናዝሬት፣ ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ፣ ከደብረማርቆስ እስከ ነቀምት… በውሃ ምንጭ የማትታማው አርባ ምንጭ ሳትቀር፣ በውሃ እጥረት ያልተሰቃየ ከተማ የለም ማለት ይቻላል። እጥረቱ ስለተባባሰም፣ የመንግስት ባለስልጣናት እንደወትሮው፣ “የንፁህ ውሃ አቅርቦት በእጥፍ አድጎ 90 በመቶ ደርሷል” ብለው ራሳቸውንና ሌላውን ዜጋ ማታለል አስቸጋሪ መሆኑ ገብቷቸዋል።

ለዚህም ነው፤ “የከርሰ ምድር፣ የገፀ ምድር ውሃ… የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የመስመር ዝርጋታ፣ የግድብ ጠረጋ… ሲጠናቀቅ ችግሩ መፍትሄ ያገኛል” እያሉ በየጊዜው የተለያየ የተስፋ ቃል የሚመግቡን። ብዙዎቻችንም፣ ተስፋ ቁርስና እራት ሆኖልን ለበርካታ አመታት ጠብቀናል። ግን የመፍትሄ ጠብታ አልተገኘም። የመንግስት ባለስልጣናት ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ፣ ሰበብና ማመካኛ ሊያልቅባቸው ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ትክክለኛና ተጨባጭ መፍትሄ የመፍጠር ችሎታ ባይኖራቸው እንኳ፣ አስገራሚ ሰበቦችንና ማመካኛዎችን የመፈብረክ ልዩ የፈጠራ ችሎታ አላቸው። “የውሃ እጥረት ከመባባሱም በተጨማሪ፣ እየቆየ የሚመጣው ውሃ የተበከለና የቆሸሸ ነው” የሚል አቤቱታ ሲቀርብ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ምን አይነት ምላሽ እንደሰጡ ታውቃላችሁ? አሉባልታ ነው ብለው አስተባበሉ። እንዴት አትሉም? “ከግድብ ወይም ከጥልቅ ጉድጉድ ተጣርቶ የሚወጣው ውሃ ንፁህ እንደሆነ በላብራቶሪ የተመሰከረለት ነው። የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች አርጅተው ስለተበሳሱ ነው ቆሻሻ እየገባ ብክለት የሚፈጠረው። ስለዚህ የተበከለ ውሃ ታቀርባላችሁ የሚባለው ወሬ አሉባልታ ነው” … የመንግስት ባለስልጣን እንዲህ “ማብራሪያ” ሲያቀርብ፣ “ማመካኛ ሰበብ የመፍጠር ችሎታው” አያስደንቅም? “የውሃ ምንጩ የብክለት ችግር የለበት፤ የማሰራጫ ባንቧዎቹ ላይ ነው ችግሩ”… ብለው ባለስልጣናት ሲነገሩን፤ “እንደዚያ ከሆነስ ችግር የለውም” ብለን እንድንረካ የሚያደርግ “ተአምራዊ መፍትሄ” የሰጡን ይመስላል።

እስቲ አስቡት፤ የሰፈራችሁ ነጋዴ የተበከለ ዘይት ሲሸጥላችሁ፤ “ከፋብሪካው ሳመጣው ንፁህ ነበር፤ እዚህ ሱቅ ውስጥ ነው ብክለት የተፈጠረው” ብሎ ሊያሳምናችሁ ይሞክራል? “ያምሃል? ወይስ ትቀልዳለህ?” ብላችሁ እንደምትቆጡት ስለሚያውቅ፣ እንዲህ አይነት “ማመካኛ ሰበብ” ለማቅረብ የሚሞክር ነጋዴ አይኖርም። የመንግስት ባለስልጣንን ግን ልንቆጣው አንችልም - አስገራሚ “የማመካኛ ሰበቦችን” እየቀያየረ ሲደሰኩር በዝምታ እንሰማለን። “የሃይል እጥረት የለም። ችግሩ የማከፋፈልና የማሰራጨት ጉዳይ ነው” በማለት ባለስልጣናት ሲናግሩስ አልሰማችሁም? በቃ! “የስርጭት ችግር እንጂ የሃይል እጥረት የለም” ብለው ስለተናገሩ፣ ተአምረኛ መፍትሄ የሰጡን ይመስላሉ። “የድህነትና የእጥረት ችግር ሳይሆን የአስተዳደር ችግር ነው” … ሲባልም አድምጣችኋል። እናስ? አብዛኛው ሰውምኮ፣ በየጊዜው ላለፉት አመታት ሲያማርር የቆየው፣ “የአስተዳደር ችግር” … ብሎ እየጮኸ ነው። ያው እንደተለመደው… ውይይት፣ ግምገማ፣ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ ካይዘን፣ የመዋቅር ለውጥ፣ ሹም ሽር… በየጊዜው ይሞከራል፤ እናም ብዙ ዜጎች ተስፋ ያሳድራሉ። ግን የውሸት ተስፋ ነው። የእውነት ተስፋ ቢሆን ኖሮ፣ ውሎ አድሮ እንደጠበቅነው መፍትሄ ሳይመጣ መቅረቱን ስንመለከት… “እንዴት? ለምን?” ብለን ከምር እናስብበት ነበር። ከመነሻውም፣ የባለስልጣናት ቃል ስንሰማ የሚፈጠርብን ተስፋ፣ ስስ የውሸት ተስፋ ስለሆነና ብዙም ስለማናምንበት፣ የህልም ምኞት ሆኖ መቅረቱን ስናይ ብዙም አይገርመንም፣ ብዙም አንቆጣም። በፀጋ እንቀበለዋለን። ለምን በሉ። እኔ ደግሞ በሁለት ምክንያቶች ብዬ እመልሳለሁ። አንደኛው ምክንያት፤ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የስልክና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በመንግስት ስር እስከተያዙ ድረስ መፍትሄ የማያገኙ መሆናቸው ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ ትክክለኛውን መፍትሄ ለማየትና ለመሞከር የማይፈልግ ሰው መብዛቱ ነው - እነዚያን ስራዎች በሙሉ በቢዝነስ ድርጅቶች እንዲከናወኑ ማድረግ ነው ትክክለኛው መፍትሄ። በ10ሺ ብር ደሞዝ የ30 አመት ችግር መፍታት? የቴሌ ወይም የኤልፓ ስራ አስኪያጆች የወር ደሞዛቸው ስንት ይሆን ብለን አስበን እናውቃለን? ብዙዎቻችን አናስብም። ግን፤ በወር 10ሺ ብር የማይደርስ ደሞዝ የሚከፈለው ሰው፣ የ30 አመታትን ችግር አስወግዶ፣ በየእለቱና በየሰዓቱ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ያለማቋረጥ ኤሌክትሪክ እንዲያቀርብ እንጠብቃለን። ሰውዬው፣ ኤሌክትሪክ ሳይቋረጥ በትክክል ማቅረብ ከቻለኮ፣ በየፋብሪካውና በየቦታው በከንቱ የሚባክን የስራ ሰዓት አይኖርም፤ እናም በየወሩ በቢሊዮን ብሮች የሚገመት ተጨማሪ ምርት ይፈጠራል። ኤሌክትሪክ ሳይቋረጥ ማቅረብ ማለት ትርጉሙ የዚህን ያህል ትልቅ ነው። ታዲያ ይህንን ትልቅ ስራ ለማከናወን የቻለ ስራ አስኪያጅ ምን ጥቅም ያገኛል? ምንም! እንደወትሮው 10 ሺ ብር የማትደርስ ደሞዝ ብቻ! በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት እንድንፈጥር በር የሚከፍት መፍትሄ ሲያመነጭልን፣ የስራ አስኪያጁ ደሞዝ 1 ሚሊዮን ብር ቢሆንለት ይበዛበታል?

በሌላ አነጋገር፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እንዲከናወኑ ማድረግና፣ እንደ አገልግሎታቸው ጥራት ትርፋማ የሚሆኑበት የነፃ ገበያ ስርዓት ማስፋፋት ማለት ነው። ይሄኔ፣ ምን ያህል ኡኡታ እንደሚፈጠር አስቡት። አንድ ሺ ብር ተጨማሪ ሃብትና ትርፍ እንድፈጥር የሚያደርግ ሰው፣ የአንድ ብር ትርፍ ቢወስድ ይበዛበታል? አይበዛበትም። ነገር ግን፣ “ዘረፈን” እየተባለ አገር ሙሉ ሲጮህበት አይታያችሁም? አንድ የግል ድርጅት ወይም አንድ ስራ አስኪያጅ ሚሊዮን ብር ትርፍ ከሚያገኝ፣ እኛ የቢሊዮን ብር ተጨማሪ ሃብት ይቅርብን? ኤሌክትሪኩ እንደወትሮው እየተቆራረጠ እንኑር? በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ ስራ እየተስተጓጎለ፣ በየወሩ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት እንክሰር? በየወሩ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር የሚያስችል ከባድ ስራ አለ፤ እስከ ዛሬ ለበርካታ አመታት ተሞክሮ አልተሳካም። ማን ይስራው? በ10ሺ ብር ደሞዝ ብቻ ምንም ጥቅም ላያገኝበት ከባዱን ስራ የሚያከናውንልን ሰው እንፈልጋለን።

ጥቅም ላያገኝበት ለምን ይሰራል? የተለመደው አይነት መልስ ልትሰጡ እንደምትችሉ እገምታለሁ - “ለራሱ ጥቅም ብሎ ሳይሆን፣ ለአገር እድገትና ለህዝብ ጥቅም ብሎ መስራት አለበት” በማለት። “ከራስ ጥቅም በፊት ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው” የሚለው የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ ጥንታዊና የተለመደ አስተሳሰብ ነው - ከአገራችን ባህል ጋር ለዘመናት የተሳሰረ። በ60ዎቹ ዓ.ም ደግሞ፣ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ እንደ አዲስ በሶሻሊስት (ወይም በኮሙኒስት) ተማሪዎች ይበልጥ እየተራገበና እየተስተጋባ የአገሬውን ሰው ሁሉ አዳርሷል። የዘመናችን መሪዎችና አንጋፋ ምሁራን፣ በአብዛኛው የያኔው ተማሪዎችና ግርፎች ናቸው። እናም፤ የአብዛኛው ዜጋ አስተሳሰብና የብዙዎቹ መሪዎች አስተሳሰብ ተመሳሳይ ነው። “ለራሱ ጥቅም በማሰብ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ እየሰጠ የሚሰራ ሰው”፤ እንዲሁም “ለራሱ ትርፍ ለማግኘት በማቀድ ሳይሆን፣ የአገርን ልማት እያስቀደመ የሚሰራ ድርጅት” ለማግኘትና ለመፍጠርም፣ መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የሚደረገው።

ግን ምን ዋጋ አለው? የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሶቭየት፣ በኩባም ሆነ በእንግሊዝ… ድሮም ሆነ ዛሬ፣ ከውድቀት ያለፈ ውጤት አላስገኘም። በሁለት ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ነው፣ ይሄ አስተሳሰብ ስህተትና መጥፎ የሚሆነው። አንደኛ ነገር፤ “በጥረትህ ራስህን ለመጥቀም ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል አስብ” ብለን ሺ አመት “መስዋዕትነትን” ስንሰብክ ብንኖር፤ ተከታይና አማኝ ብናገኝ እንኳ፣ በፈቃደኝነት ይህን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ የሚተገብር ሰው ብዙም አናገኝም። በፈቃደኝነት ራሱን ለመስዋዕትነት የሚያቀርብ ሲጠፋ፣ በአዋጅና በጠመንጃ ወደ ማስገደድ እንሄዳለና። በአእምሮ ብቃትና በእውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚባሉ የአገራችን ሃኪሞች፣ ሁለት ክፍል ቤት ተከራይቶ ለመኖር በማያስችል ደሞዝ “ህዝብ እንዲያገለግሉ” ስንጠብቅባቸው ምን ተፈጠረ? አብዛኞቹ ሃኪሞች “ምን በወጣን!” ብለው ጥለውን ሄደዋል። በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ የህክምና ዶክተሮች ቁጥር ከሁለት ሺ ብዙም አይበልጥም።

አሜሪካ ውስጥ፣ በዋሺንግተን ዲሲና በሜሪላንድ ብቻ የኢትዮጵያውያን ዶክተሮች በቁጥር ግን፣ እዚህ አገር ውስጥ ካሉት ይበልጣል።በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ አገራት የሚገኙ፣ እዚሁ አገር ውስጥም የህክምና ሙያቸውን ትተው በሌላ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ዶክተሮችን ሳንቆጥር ነው። በአጭሩ፣ “ለአገር ልማት፣ ለህዝብ ጥቅም!” የሚባለው የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ በተግባር አይሰራም። ልማትና ጥቅም አይገኝበትም። በደርግ ዘመን የአገሪቱ ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ከአመት አመት እያሽቆለቆለ፣ በ17 አመታት ውስጥ ድህነት በእጥፍ የጨመረው በሌላ ምክንያት አይደለም - “አገር ትቅደም፤ ህዝብን አስቀድም!” በሚል የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ምክንያት ነው። ግን በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። “ከራስህ በፊት አገር ትቅደም” ብለው የፎከሩ የ”አገራዊነት” ወይም የ”ብሄረተኝነት” አቀንቃኞች (እንደ ሞሶሎኒና ሂትለር፣ እንደ ሞቡቱና ኢዲአሚን የመሳሰሉ መሪዎች) የየአገራቸውን ህዝብ ለእልቂትና ለድህነት ዳርገዋል። “ከራስህ በፊት ህዝብ ይቅደም” ብለው የጮሁ የ”ህዝባዊነት” ወይም “የሶሻሊዝም” ሰባኪዎች (እንደ ሌኒንና ስታሊን፣ ሞኦና መንግስቱ የመሳሰሉ መሪዎች)፣ የየአገራቸውን ህዝብ በማደህየት ሚሊዮኖችን ለረሃብ እልቂት ዳርገዋል። ሚሊዮኖችን ረሽነዋል።

ሶሻሊዝምን ወይም ፋሺዝምን የዘመሩ አገራት ሁሉ፣ በየጊዜው በኢኮኖሚ ድቀት ሲፈራርሱ አላየንም እንዴ? የትም አገር፣ በየትኛውም ጊዜ በተግባር የብልፅግና ውጤት አስገኝቶ አያውቅም - የድህነትና የውድቀት ውጤት እንጂ። ታዲያ እንዲህ በየአገሩ ከቅርብ እስከ እስከ ሩቅ፣ በየዘመኑ ከጥንት እስከ ዛሬ በተግባር ተሞክሮ መጥፎነቱ የተረጋገጠ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ላይ ሙጭጭ የምንለው ለምንድነው? ዛሬም እንደ ድሮው፤ “ለራሱ ጥቅም በማሰብ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም አስቦ የሚሰራ ሰው” ችግሮችን ሁሉ ይፈታል ብለን አንዳች ተአምር እንዲፈጠር የምንጠብቀውስ ለምንድነው? እንዲሁ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሰሙት የነበረና የለመዱት አስተሳሰብ ስለሆነ ብቻ፤ በ”ደመነፍስ” እንደበቀቀን እየደጋገሙ የሚናገሩ ይኖራሉ።

ወይም፤ “አዋቂ” ብለው የሚያከብሩት ሰው ሲናገር ሰምተው፣ እንደ ገደል ማሚቶ መልሰው የሚያስተጋቡ ሰዎችም ሞልተዋል። ብዙ ሰዎች ግን፣ “ከራስ በፊት ለአገር ልማት፣ ለራስ በፊት ለህዝብ ጥቅም!” ብለው መስዋዕትነትን የሚሰብኩት፣ “የቅድስና ዋና ምሶሶ ነው” ብለው ስለሚያምኑበት ነው። በተግባር ለኑሮ የማይበጅ እንደሆነ ቢገባቸውም፣ በተጨባጭ ችግሮችን እንደማይፈታ ቢያረጋግጡም፣ በግላቸው ሁልጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጉት ከሞከሩ ህልውናቸውን እንደሚያጠፋባቸው ቢያውቁም… ያንን “የመስዋዕትነት አስተሳሰብ” አሽቀንጥረው ሊጥሉት አይፈልጉም፤ ወይም አይደፍሩም። ለምን? የ”ቅድስና ዋና ምሶሶ ነው” ብለው ያምኑበታላ። ሁልጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጉት ባይችሉ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሊሰብኩለት ይፈልጋሉ። ባይሰብኩለት እንኳ፣ ሊቃወሙት አይፈልጉም። ነገር ግን፣ “መስዋዕትነት ለምን ቅዱስ ይሆናል?”፣ “የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ለምን ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል?” … ለዚህ ጥያቄ አንዳችም አሳማኝ ምላሽ እንደሌለ የምትገልፀው አየን ራንድ፤ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ለዘመናት የሰውን ልጅ ለድህነትና ለረሃብ፣ ለእልቂትና ለባርነት የዳረገ ክፉ አስተሳሰብ ነው ትላለች። ለምን? “ጎረቤቴ፣ የራሱን ህይወት ሳያሻሽል፣ የራሱን ኑሮ እያጎሳቆለ፣ የኔን ህይወት ለማሻሻልና ኑሮዬን ለማሻሻል መስዋዕት ይሁንልኝ” ብሎ ማመን እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል? የቀማኛና የ”ጥገኛ ተባይ” አስተሳሰብ ነው። “የራሴን ህይወት ሳላሻሽል ኑሮዬን እያጎሳቆልኩ፣ እንደ ጋማ ከብት ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል በመስዋዕትነት መቅረብ አለብኝ” ብሎ ማመንስ እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል? ባርነትንና እንሰሳነትን በፀጋ የሚቀበል አስተሳሰብ ነው።

ይሄ የተጋነነ አገላለፅ እንዳይመስላችሁ። “አገርንና ህዝብን ማስቀደም ያስፈልጋል” እያሉ የሚሰብኩ የመንግስት ባለስልጣናትና ምሁራን፣ ስለ ኢንቨስተሮችና ስለ ቢዝነስ ሰዎች ሲናገሩ ሰምታችሁ አታውቁም? “ወርቅ የምትጥል ዶሮ”፤ “የምትታለብ ላም” እያሉ ነው የሚጠሯቸው። እንስሳነትንና ባርነትን በፈቃደኝነት እንድንቀበል የሚያደርግ አስተሳሰብ ተጠናውቷቸዋላ! አንዱ ሰው ባርያና አገልጋይ ከሆነ፣ በዚህኛው መስዋዕትነት “ተጠቃሚ” የሚሆን ሌላ ሰው መኖሩ አያጠራጥርም - ቀማኛ ተገልጋይና ጥገኛ ተባይ። “ለአገር ልማት፤ ለህዝብ ጥቅም” በሚል መፈክር ብዙዎች ንብረታቸውን ተቀምተዋል - በመንግስት ተወርሶባቸዋል። የአገራችን ሃኪሞች ወደ ውጭ አገራት እንዳይጓዙ የተለያዩ እገዳዎች የሚጣልባቸውስ ለምን ይሆን? “እንዲያገለግሉን ልናስገድዳቸው ስለምንፈልግ ነዋ” ብላችሁ እቅጩን መናገር ባትፈልጉ እንኳ ሌላ ትርጉም የለውም። “መንግስት ያንን ይደጉምልን፣ ይሄንን በነፃ ወይም በቅናሽ ያቅርብልን” ብለን የምንጮኸውስ ለምንድነው? ከሌሎች ሰዎች በታክስ መልክ እየቀማ ለኛ ይስጠን እንደማለትኮ ነው። “በሌሎች ሰዎች ላይ ጥገኛ ሆነን እንድንኖር አመቻችልን” እንደማለት ነው። ታዲያ፤ በሌሎች መስዋዕትነት ላይ የመኖር ምኞትን የሚያንቆለጳጵስ የቀማኛና የጥገኛ ተመፅዋች አስተሳሰብ፤ እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል? ሰውን እንደቀማኛ ወይም እንደ ባርያ፣ እንደ ጥገኛ መዥገር ወይም እንደ አገልጋይ እንሰሳ የሚቆጥር አስተሳሰብ ይዘን፤ እንዴት በፍቅር መኖር ይቻለናል? በጠላትነትና በምቀኝነት፣ በግፈኛነትና በተለማማጭነት እንጂ! የመስዋዕትነት አስተሳሰብ እኩይና ክፉ ከሆነ፤ ቅዱስ የሆነው አስተሳሰብ የትኛው ነው? ራስን የመውደድና የመከባበር አስተሳሰብ ነዋ። “ለሌሎች ሰዎች መስዋዕት አልሆንም፤ ሌሎች ሰዎችም ለኔ መስዋዕት እንዲሆኑልኝ አላደርግም” ብሎ ሰው የመሆን ክብሩን የሚጎናፀፍ፣ ቀማኛና ጥገኛ ተባይ መሆንን የሚጠላ፣ ባርያና አገልጋይ እንሰሳ መሆንን የሚፀየፍ አስተሳሰብ ነው፣ ቅዱስ አስተሳሰብ።

የራሱን ህይወት የሚያፈቅርና በጥረቱ ኑሮውን ለማሻሻል የሚተጋ፤ የሌሎችን ህይወት የሚያከብርና ለኑሯቸው መልካሙን ሁሉ የሚመኝላቸው፤ እርስ በርስ ለመጠቃቀም የሚገበያይ ኩሩ ስብእና የሚፈጠረውም በዚህ መንገድ ነው። በዚህ አስተሳሰብ ላይ በመመስረትም ነው፤ የነፃ ገበያና የቢዝነስ ስራ ቅዱስነትን መገንዘብ የምንችለው። በዚህ አስተሳሰብ አማካኝነትም ነው፤ ለዘመናት የዘለቀው የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የውሃ እና ሌሎች ችግግችን መፍታት የምንችለው። ማርጋሬት ታቸርን በአርአያነት መጥቀስ ይቻላል። ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ወደ ሶሻሊዝም ስታዘግም በቆየችው እንግሊዝ ውስጥ፣ ቀስ በቀስ የቢዝነስ ስራዎች በመንግስት እጅ እንዲገቡ እየተደረገ በዚያው መጠንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ ገደል አፋፍ ላይ የደረሰው በ1970ዎቹ ገደማ ነው። የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የስልክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በርካታ የኢንዱስትሪ መስኮችም በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ በመደረጋቸው በየአመቱ እየተዳከሙ፣ አትራፊነታቸው እየቀነሰ፣ ታክስ መክፈል እያቆሙ፣ በመጨረሻ ያለ መንግስት ድጎማ የማይንቀሳቀሱ አክሳሪ ድርጅቶች ሆነው አረፉት። በየአመቱ ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጎማ ይመደብላቸው ነበር - ከዜጎች በሚሰበሰብ ታክስ። ይህም ብቻ አይደለም። የአገልግሎት ጥራታቸውም ተንኮታኩቷል። የቤት ወይም የቢሮ ስልክ ለማስገባት እንደድሮ በአንድ በሁለት ቀን የሚሳካ መሆኑ ቀረ። ተመዝግቦ ለወራት ያህል ወረፋ መጠበቅ የግድ ሆነ። ኤሌክትሪክም እንደድሮው፣ ቀን ከሌት፣ በጋ ከክረምት መቼም የማይቋረጥ የማይጠፋ አስተማማኝ አገልግሎት መሆኑ ቀረ። በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚካሄድ ስብሰባ ሳይቀር፣ ሻማ መጠቀም የግድ ሆነ። ይሄኔ ነው፣ ማርጋሬት ታቸር “ይብቃን!” ብለው የተነሱት።

በመስዋዕትነት አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አጥፊ የሶሻሊዝም ኢኮኖሚን በመቃወም፤ በራስ ጥረት የመበልፀግ ቅዱስነትን የሚያንፀባርቅ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚን ለማስፋፋት የተነሱት ማርጋሬት ታቸር፤ ግማሽ የአለም ህዝብ ቢያወግዛቸውም፣ የአገራቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ቢኮንኗቸውም፣ በፍርሃት ሳቢያ ከአቋማቸው ለማፈንገጥ አልፈቀዱም። በመንግስት ተይዘው የነበሩ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎቶችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ግል የቢዝነስ ድርጅትነት እንዲተላለፉ አደረጉ - 10 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት እንዲሆኑ በሚያደርግ ዘዴ። ብዙም ሳይቆይ የእንግሊዝ ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ማንሰራራት ጀመረ። በድጎማ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አክሳሪ ድርጅቶች ትርፋማ በመሆን፣ በአመት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ታክስ የሚከፍሉ የብልፅግና ድርጅቶች ለመሆን በቁ። በየደቂቃውና በየሰዓቱ ይቆራረጥ የነበረው የስልክ፣ የውሃና፣የኤሌክትሪክ እጥረት መፍትሄ ያገኘው በዚህ መንገድ ነው።

Read 4409 times