Monday, 08 April 2013 10:16

ለአዲስ ፊልሞች ከ1ቢ.ዶ በላይ ማግኘት ይከብዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አይረን ማን 3 ከወር በኋላ ይታያል በ2013 በመላው ዓለም ከሚታዩ የሆሊውድ ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት በተለይ ለአዲሶቹ ሊከብድ እንደሚችል ተመለከተ፡፡ በ3ዲ በድጋሚ በመሰራት ለእይታ የሚበቁ እና በተከታታይ ክፍል የሚሰሩ ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሰብሰብ ተስፋ አላቸው ተብሏል፡፡ በ3ዲ የተሰሩት ጁራሲክ ፓርክና ስታር ትሬክ ኢንቱ ዘ ዳርክነስ እንዲሁም አይረን ማን 3፣ ፋስት ኤንድ ፊውሪዬስ 6 የቢሊዮን ዶላር ገቢ ግምት ካገኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት 4 ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳስገቡ ይታወሳል፡፡ የሆሊውድ ፊልሞች በ3ዲ በተፈጠረላቸው ውድ የትኬት ዋጋ እና እንደ ቻይና፤ ራሽያ እና ጃፓን የገበያ ከፍተኛ መስፋፋት ማሳየታቸው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓለም አቀፍ ገቢ መሰብሰብን ፊልም ሰሪዎች ተስፋ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከፊልም ሰሪ ኩባንያዎች፤ በሰራው ፊልም ዓለም አቀፍ ገቢውን 1 ቢሊዮን ዶላር በፍጥነት በማሳካት ፓርማውንት ፒክቸርስ ግንባር ቀደም ነው፡፡ፐርማውንት ከ4 ዓመታት በፊት ይህን የገቢ ጣራ በ174 ቀናት በማሳካት የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡በመላው ዓለም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገቡ ፊልሞች ብዙዎቹ ተከታታይ እና እንደ ፍራንቻይዝ የሚሰሩ ሲሆኑ ይህን የገቢ ጣራ በመድረስ የተሳካላቸው ፊልሞች ብዛታቸው 15 ነው፡፡ ከእነዚህ 15 ፊልሞች መካከል 11 ያህሉ ባለፉት አምስት አመታት በመላው ዓለም ለመታየት የበቁ ናቸው፡፡

ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማስገባት የምንጊዜም ከፍተኛውን የገቢ ሪከርድ ያስመዘገበው ደግሞ አቫታር በ2.78 ቢሊዮን ዶላር ገቢው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተያያዘ ከወር በኋላ በመላው ዓለም ለመታየት የሚበቃው አይረን ማን 3 በሚኖረው ትእይንቶች ለቻይና ገበያ ተጨማሪ ቦነሶች ይዟል ተባለ፡፡ በማርቭል ስቱድዮስ በ200 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ፊልም ለቻይና ፊልም አፍቃሪያን የሚመቹ ትእይንቶች ተጨምረውለታል፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የታየው አየርን ማን 1 በመላው ዓለም 585.2 ሚሊዮን ዶላር ያስገባ ሲሆን በ2010 እኤአ ላይ የታየው አይረን ማን 2 ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በዓለም ገበያ ሰብስቧል፡፡

Read 2205 times