Saturday, 30 March 2013 16:09

ጂም ኬሪ “ፀረ ጦር መሳርያ” የሙዚቃ ክሊፕ ሰራ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ለልጆቻችን ደህንነት ለማይጨነቁ ልበቢሶች ነው የሰራሁት” ካናዳዊው ኮሜዲያን ጂም ኬሪ የጦር መሳርያ የመታጠቅ መብትን ለመቃወም “ኮልድ ዴድ ሃንድ” የተሰኘ የሙዚቃ ቪድዮ በመስራት እንዳሰራጨ ተገለፀ፡፡ “ፈኒ ኦር ዳይ” በተባለ ድረገፅ የተለቀቀውን ይሄን ክሊፕ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው እንደተመለከተው የዘገበው ፎክስ ኒውስ፤ በኮሜዲያኑ ላይም ከፍተኛ ትችት እንደቀረበበት ጠቁሟል፡፡ ጂም ኬሪ ከአራት ዓመት በፊት ህይወቱ ያለፈውን የቀድሞ ተዋናይ እና የ“ናሽናል ራይፍልስ አሶሴሽን” ፕሬዝዳንት የነበረውን ቻርልስ ሄስተን ገፀባህርይ በመላበስ በካንትሪ ስልት ሙዚቃውን ተጫውቷል፡፡ በክሊፑ ላይ ጆን ሌነን፤ ማህተመ ጋንዲ እና አብርሃም ሊንከልንም ተተውነዋል፡፡

እስከ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ አድናቂዎቹ በሚከታተሉት የትዊተር ማስታወሻው ላይ ጂም ኬሪ በፃፈው መልእክት፤ የሙዚቃ ቪድዮውን ለልጆቻችን ደህንነት ለማይጨነቁ ልበቢሶች ነው የሰራሁት ብሏል፡፡ በአሜሪካ ጦር መሳርያ የመታጠቅ መብት እንዲታገድ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ሲካሄድ ቢሰነብትም ጦር መሳርያ የመታጠቅ መብትን የሚከለክል ህግ እንዲወጣ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ መሆኑ ያጠራጥራል እየተባለ ነው፡፡ የኒውዮርክ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ እስከ 12 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይዘው የፀረ ጦር መሳርያ እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆኑን የዘገበው ብሉምበርግ ኒውስ ፤ በተቃራኒው በአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸው 15 ዴሞክራት እና ሪፐብሊካን ሴናተሮች የጦር መሳርያ የመታጠቅ መብትን ለመከልከል የተያዘውን ዘመቻ በይፋ እየተቃወሙ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ከ32 በላይ ፊልሞችን የሰራውና በመላው አለም እስከ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ያስገባው ኮሜዲያን ጂም ኬሪ ፤ ቢያንስ 12 ያህል ፊልሞቹ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዳስገኙለት ይታወቃል፡፡

Read 3876 times Last modified on Saturday, 30 March 2013 16:13