Saturday, 30 March 2013 14:44

የዝነኛው እጣፈንታ!

Written by 
Rate this item
(13 votes)

“ምንድነው ዝነኝነት ሰለቸኝ ብሎ ነገር? ከሙያህ ለመውጣት ሌላ አሳማኝ ምክንያት ካለህ ንገረኝና ልቀበልህ፡፡ ተራ ሰው ሆኖ መኖር አማረኝ ማለት ግን …” አለ መርዕድ የሰለሞን ነገር አልዋጥልህ ብሎት፡፡ ለሀያ አመት በዘለቀው የፕሮሞተርነት ስራው እንደዚህ አይነት እንግዳ ነገር ሰምቶ አያውቅም፡፡ አንድ ድምፃዊ ዝነኝነት ሰለቸኝ ብሎ ድምፃዊነቱን እርግፍ አድርጎ ለመተው ሲወስን የአሁኑ የመጀመርያው ነው፡፡ ለዛውም እንደ ሰለሞን ያለ ባወጣቸው ስድስት የዘፈን አልበሞቹ በሙሉ የተሳካለት፤ በየትኛውም ስፍራ ያሉ አድናቂዎቹ ሥራውን ካላቀረበልን እያሉ በየሚዲያው የሚወተወቱት አርቲስት እንዴት ዝነኝነት ሰለቸኝ ይላል? “ሌላ ምክንያት የለኝም! … ዝነኛ ሆኖ መኖር ሰልችቶኛል፡፡ ዝነኝነትን መጥላቴ ሙያዬን እንድተው እንዳስገደደኝ ስነግርህ ማመን ካቃተህ ምን አደርጋለሁ? በቃ ተራ ሰው የሚኖረው ኑሮ አማረኝ፡፡” ዝነኛው ድምፃዊ ሰለሞን እረጋ ብሎ ነው የሚያወራው፡፡ ፕሮሞተሩ መርዕድ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዝነኝነት ከፍታ ላይ ካወጣው ሙያው ለመለያየት ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡

“እኮ አስረዳኝ! … ስንቶች ዝነኛ ለመሆን እንቅልፍ አጥተው ሲፍጨረጨሩ … አንተ ግን ዝነኝነት ሰለቸኝ ብለህ… ፈፅሞ ልትገባኝ አልቻልክም፡፡ ቆይ ዝነኝነት እንዴት ይሰለቻል? ዝነኛ ስትሆን እኮ ሰው ያከብርሀል፣ ሰላም ይልሀል፣ ቅድሚያ ይሰጥሀል” …ላንተ ምን እነግርሃለሁ መርዕድ በሃፍረት ስሜት ሰለሞን ላይ አፈጠጠ፡፡ ሰለሞን ከሙዚቃው ዓለም ሲወጣ በፕሮሞተርነቱ ብዙ ነገር እንደሚያጎልበት ይውቃል፡፡ ከግሉ ጉዳት በላይ ደግም በሀገሪቷ ሙዚቃ እድገት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ያውቃል፡፡ ሰለሞን ተራ ድምፃዊ አይደለም፤ ኃላፊነት የሚሰማው ለብዙዎች አርአያ መሆን የሚችል በሳል አርቲስትም ጭምር ነው፡፡

“ዝነኝነት ይሰለቻል! እ…ዝነኝነት ማለት በተራራ ላይ መስታወት ቤት ውስጥ እንደመኖር ነው፡፡ ሁሉም ያይሃል፣ ሁሉም ይከታተልሃል … ለብቻህ በነፃነት የምታደርገው ነገር የሌለህ ፍጡር ነህ! ነፃነት አልባ ፍጡር!” ሰለሞን ዝነኝነትን በመንገሽገሽ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ “የመጀመሪያ ካሴቴን ከማውጣቴ በፊት የነበረኝን ነፃነት ሳስበው እገረማለሁ፡፡ ስፈልግ በመንገድ ላይ እጆቼን ኪሶቼ ውስጥ ከትቼ፣ አሊያም ግስላ ሲጃራዬን እያጨስኩ፣ ከሰዎች ጋር እየተጋፋሁ፣ ህብረተሰቡ የሚያወራውንና የሚያማውን እየሰማሁ … መሔድ፤ መኖር ብዙ ትርጉም እንዳለው የገባኝ ዝነኛ ከሆንኩ በኋላ ነው - አሁን!…” ሰለሞን ለአፍታ ትንፋሽ ወሰደና በስሜት መናገሩን ገፋበት፤ “አሁን ዝነኛ ከሆንኩ በኋላስ? ሽንቴን መንገድ ላይ ቢወጥረኝ እንኳ ፊኛዬ ይፈነዳታል እንጂ መንገድ ላይ እንኳ ቆሜ መሽናት አልችልም! … መንገዱ ቀርቶ የህዝብ ሽንት ቤት መግባት እንኳ አልችልም፡፡

የፈለግኋትን ቆንጆ መንገድ ላይ ተከትዬ የመጥበስ እንኳን ነፃነት የለኝም እኮ! ይኼ ሁሉ በዝነኝነቴ የመጣ ባርነት ነው!” “እነዚህ ሁሉ ትርጉም የሌላቸው! ተራ ነገሮች እኮ ናቸው!” አለ መርዕድ በማቃለል “ትርጉምማ አላቸው! ነገሩን አልኩህ እንጂ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ትክክል ነው ማለቴ አይደለም፡፡ መንገድ ላይ የማልሸናው ዝነኛ ስለሆንኩ ነው እንጂ መንገድ ላይ መሽናት ትክክል እንዳልሆነ ስላመንኩ አይደለም!” ከመርዕድ ምላሽ የፈለገ አይመስልም፡፡ “እነዚህ ሁሉ ተራ ነገሮች የነፃነት ምልክቶች ናቸው፡፡ ሰው ነፃነት ለማግኘት ጠመንጃ ያነሳል እኮ መርዕድ! የነፃነት ግንባር ብሎ ሰይሞ ድርጅት እስከማቋቋም ይደርሳል እኮ … አስበው ሰዎች ህይወታቸውን የሚገብሩለትን ነፃነት በዝነኝነት ሰበብ ስታጣው፡፡ መንገድ ላይ ቆሞ መሽናት እንኳን ብርቅ ይሆንብሀል እኮ፣ መንገድ ላይ የተጠበሰ በቆሎ እየበላህ መሔድ እንኳን አትችልም፡፡ ለምን? ዝነኛ ነሃ!” ሰለሞን ሀሳቡን በቅጡ የሚገልጡለት ቃላት ያገኘ አልመሰለውም፡፡ “ያልከው ባይገባኝም እስቲ ሙያህን አቆምክ ብለን እንውሰድ፡፡ ከዛስ ዝነኝነትህን እንደ አረጀ ኮት አጣጥፈህ ማስቀመጥ የምትችል ይመስልሀል? ሸሽተኸው ማምለጥ እንዳትችል በስድስት አልበሞች የሰራሃቸው ስራዎች ይከተሉሀል፡፡ በስድስት አልበሞች የተገነባ ዝነኝነትን እንደቀልድ ከላይህ ላይ አራግፈህ ልትጥለው… አይሆንማ! … መርዕድ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በስሜት እየተውረገረገ ተነሳ፡፡ “አይምሰልህ ዝነኝነት እንደ አበባ ነው… ሰርክ እየኮተኮትክ፣ ውሀ እያጠጣህ የምትንከባከበው፡፡ አበባን ካልተንከባከብከው እየቆየ እንደሚከስመው ዝነኝነትም በጊዜ ሒደት ቀለሙ እየጠፋ ይኼዳል፡፡

እከሌ እኮ ድሮ የታወቀ አርቲስት ነበር ብትል ታሪክ ነው የሚሆነው፡፡ ልክ ታዋቂ አትሌት ነበር እንደምትለው … ቢበዛ ከንፈር የሚመጥልህ ሰው ብታገኝ ነው እንጂ መውጫ መግቢያ የሚያሳጣህ ሰው አይኖርም” አለ ሰለሞን፡፡ “እና ታሪክ ለመሆን አቅጃለሁ ነው የምትለኝ?” መርዕድ በጥርጣሬ መንፈስ ተሞልቶ ጠየቀው፡፡ ሰለሞን በአዎንታ እራሱን ነቀነቀ፡፡ “አዎ! እኔ የማንም አርአያ የመሆን ፍላጎት የለኝም፡፡ ዝነኝነቴን ወስዳችሁ ነፃነቴን መልሱልኝ እያልኩ ነው!” አለ ሰለሞን ከተቀመጠበት እየተነሳ፡፡ መርዕድ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ተረድቶታል፡፡ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ለስንብት እጁን ዘረጋለትና ተጨባበጡ፡፡ “ዝነኝነት ሱስ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ልክፍት! እርግጠኛ ነኝ በድጋሚ ዝነኝነት ይናፍቅሃል! ተራ ሰው ሆነህ ሀምሳ አመት ከመኖር ዝነኛ ሆነህ ሀምሳ ቀን መኖር እንደምትመርጥ አልጠራጠርም! … ያን ጊዜ በሬ ክፍት ነው፡፡ እስከዛው ግን ቢያንስ የት እንደምትሔድ ንገረኝ እና እየመጣሁ ልጠይቅህ፡፡” አለ መርዕድ ሰለሞን በአሉታ እራሱን ግራና ቀኝ ወዘወዘ “ይቅርታ መርዕድ፤ ዝነኝነት ለኔ ቀንበር ነው እንጂ ሀብል አይደለም፡፡ ወደ ዝነኝነቴ የሚመልሱኝን ድልድዮች ሰብሬ መሔድ ነው የምፈልገው፡፡ አንዳንዶች ዝነኛ ሆነው ለመኖር ብርቱ ጫንቃ አላቸው፤ እኔ ግን ፈፅሞ የለኝም! ዝነኝነትን መቋቋም የሚችል ትከሻ አልተሰጠኝም!” አለና ተንደርድሮ ከመርዕድ ቢሮ ወጣ፡፡ የውጪው ነፋሻ አየር ተቀበለው፡፡ ጀንበር ወደመጥለቂያዋ እያቆለቆለች ስለነበር ወርቅማ የስንብት ቀለሟን እሱን ወክላ የምትረጭ መሰለው፡፡ ጀንበሯን ተከትሎ “ዝነኝነት ያላጎበጠው ነፃ ሰው! ዝነኝነት ያልከበበው ነፃ ማንነት!” እያለ መጮህ ናፈቀው፡፡

ጀንበሯን ቆሞ በሰመመን ሲቃኝ ከጀርባው አንድ ድምፅ ሰማ፤ “እንዴ ሰለሞን! ታዋቂው ድምፃዊ ሰለሞን! ሰሌ! ሰሌ!!!” የሚል ጩኸት ሙሉ በሙሉ ከሰመመኑ አነቃው፡፡ ህፃናት፣ ኮረዶች፣ ጎልማሶች … የአካባቢው ሰዎች ሁሉ ከየቤታቸው ወጥተው እንደ ጉንዳን እየከበቡት መሆኑን ሲረዳ መኪናውን ያቆመበትን ቦታ ተመለከተ - ለማምለጥ! “ሰሌ! ፍቅር እና ትዝታ የሚለው ዘፈንህ ተመችቶኛል!...”፣ ሰሌ! “እዚች ጋር ትፈርምልኛለህ?” “ሰሌ! እንወድሃለን!” የሚሉና ሌሎች ድምፆች ከበቡት፡፡ ጨነቀው፡፡ ለከበበው ህዝብ “እኔ ዘፋኙ ሰለሞን አይደለሁም!” ብሎ ለመጮህ፤ ለማወጅ አስቦ ነበር፡፡ ግን አይገባቸውም በሚል ተወው፡፡ ከላይ እየበረረች የምትመጣ ላዳ ታክሲ ሲያይ አስቁሞ ዘሎ ገባ፡፡ የታክሲው ሾፌር በኋላ ማሳያ መስታወቱ አየውና ፈገግ አለ፡፡ “ምነው ቢኤም ደብሊዋ ደበረችህ እንዴ?” ጠየቀው ሾፌሩ፡፡ “መኪናዬ ቢኤም ደብሊው መሆኗን እንኳ ይኼ ሾፌር ያውቃል! የኔ ብቻ የምለው ምስጢር የሌለኝ ምስኪን ሰው!” እያለ በውስጡ በምሬት ይብሰለሰል ገባ፡፡

አፉ ላይ የመጣለትን መናኛ መልስ ለሾፌሩ ሰጠውና ወደ ራሱ ሀሳብ ተመለሰ፡፡ “ዝነኝነት ታዲያ ምኑ ነው የሚያስደስተው? ሰዎች በታክሲ መሳፈር እንዳለብህ እና እንደሌለብህ ይወስኑልሀል! የምትመገብበትን ምግብ ቤት የሚወስኑልህ ሌሎች ናቸው! ነፃነት የሌለው ህይወት ሲኦል አይደለም እንዴ?!” ከራሱ ጋር እያወራና ብቻውን እየተብከነከነ ሳለ ባለታክሲው አሁንም ሳቅ ብሎ ተመለከተውና “አልጋ የያዝክበት ሆቴል ደርሰናል!” አለው፡፡ “እዚህ አልጋ እንደያዝኩ በምን አወቀ?” ንዴት በሰራ አካላቱ ተቀጣጠለ፡፡ ባለታክሲውን በንዴት ገረመመውና እጁ ላይ የገባለትን ብር ከቦርሳው መዥረጥ አድርጎ ወርውሮለት ከታክሲው ውስጥ ዘሎ ወጣ፡፡ የነፃነት እጦት ትንፋሽ ያሳጣው መሰለው፡፡ እየሮጠ ወደ ያዘው የመኝታ ክፍል ሮጠ፡፡ ፍቅረኛው ካትሪን አልጋ ላይ ጋደም ብላ መፅሀፍ ታነባለች፡፡ ካትሪን የስዊዲን ተወላጅ ናት፡፡ ከሰለሞን ጋር ድንገት ነበር በግብዣ ላይ የተዋወቁት፡፡

ያኔ ካትሪን ስለሰለሞን ዝነኝነት ምንም የምታውቀው ነገር አልነበራትም፡፡ ለዚህ ነው ከመቅፅበት በፍቅር የወደቀላት፡፡ ሰው በመሆኑ ብቻ የምትቀርበው እንስት ሲፈልግ ነው ያገኛት፡፡ ከሀገሩ እንስቶች ሊያገኝ ያልቻለው ይህንን አይነቱን ፍቅር ነበር፡፡ ሁሉም ሴቶች እሱን ከማወቃቸው በፊት ከዝነኝነቱ ጋር በፍቅር እየወደቁ በተቸገረበት ወቅት ካትሪን ባህር ተሻግራ ደረሰችለት፡፡ የሀገሩ ሴቶች “ወይኔ ሰሌ! የመጨረሻው ካሴትህ ላይ ያለውን ‘ፍቅር ይዞኝ ነበር’ የሚል ዜማ እንዴት እንደወደድኩት!” ሲሉት የፍቅር ተስፋው እንደጉም ይበናል፡፡ የካተሪን ግን የተለየ ነበር፡፡ መጀመሪያ ሰለሞንነቱን ነው የወደደችው… ወደ ክፍሉ እየሮጠ ሲገባ ካትሪን ደንግጣ ከአልጋዋ ተነሳች፡፡

“ከማበዴ በፊት አሁኑኑ ይኼን ከተማ ለቅቄ መሄድ አለብኝ!” አላት ሰለሞን፡፡ ሁኔታው ግራ ስላጋባት ምንም ነገር ልትጠይቀው አልደፈረችም፡፡ ልብሷን ቀያይራ ተከተለችው፡፡ እስከ ሀዋሳ ድረስም ሸኘችው፡፡ የሰለሞን ጉዞ ግን እዛ የሚያቆም አልነበረም፡፡ ከተማን ነበር ሽሽቱ… ቴሌቭዥን ብሎ ነገር የሌለበት፣ ኢንተርኔት ይሉት ጉድ ያልገባበት፣ ተፈጥሮ እና ተፈጥሮ ብቻ ወዳሉበት ምድር መሄድ… ለዚህ ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተሻለ… ከፀማይ መንደር የበለጠ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ፀማይ ዝነኝነቱን እንድታከሰምለት የመረጣት ምድር ሆነች፡፡ በተፈጥሮዋ ጭምቅ አድርጋ ዝነኝነት የሚባለውን አውሬ ሲጥ እንደምታደርግለት ተማምኖባታል፡፡

*** ከሁለት ወር በኋላ… ሰው መሆን ብቻ በቂ የሆነባት ምድር-ፀማይ! ማነህ? ምንድነህ? የሚል ጥያቄ የሌለባት፣ የሰው ልጅ ከቁስ አካላዊ ግብዝነቱ ተላቆ ሲኖር ምን ያህል ውብ እንደሆነ የሚታይባት ምድር! ሰርክ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ በህልም አለም እንደሚኖር ነው የሚሰማው፡፡ የስልክ ጥሪ ሳይሆን የከብቶች እንቧታ ከእንቅልፉ ሲቀሰቅሰው ደስታው ወሰን ያጣል፡፡ ፀማይ ውስጥ የፈርምልኝ ጫጫታ አያጋጥመውም! “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ሶደሬ አካባቢ በተደጋጋሚ ይታያል”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ከአዲሷ ፍቅረኛው ጋር በተደጋጋሚ ፀብ ውስጥ እየገባ ነው”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ጫማውን ለጠረገለት ሊስትሮ ሁለት መቶ ብር ሰጠ”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ በተደጋጋሚ ሽሮ መብላቱ ለድምፁ አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆን?”... ቅብርጥሶ ምንትሶ ከሚሉ የጋዜጣ እና መፅሄት አናዳጅ ዘገባዎች ተገላግሏል፡፡ አናዳጅ የጋዜጠኛ ጥያቄዎችም ፀማይ ውስጥ የሉም! “አርቲስት ሰለሞን፤ በልጅነትህ መጫወት የምትወደው ጨዋታ ምን ነበር?” (እርግጫ ቢላቸው ይወዳል ግን ዋና እወዳለሁ ይላል) የህይወት ፍልስፍናህ ምን ነበር?” (እኔ እኮ ዘፋኝ እንጂ ፈላስፋ አይደለሁም ቢላቸው ይወዳል፤ ግን ከሰው ጋር አብሮ መኖር ምናምን የሚል ፍልስፍና አለኝ ይላቸዋል) “አርቲስት ሰለሞን፤ ወደፊት ምን ለመሆን ትፈልጋለህ?” (ጋዜጠኛውን እያየ የአንተን አይነሰብ በቡጢ መነረት ማለት ይፈልጋል፤ ግን በሙያዬ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይላቸዋል)፡፡ አሁን እነዚህ ጥያቄዎች ምን ይሰራሉ? ስለዘፈኑ ሙያዊ ጥያቄ የጠየቀው አንድም ጋዜጠኛ አያስታውስም፡፡ በቀን ለስንት ሰአት ትተኛለህ? ምግብ ማብሰል ደስ ይልሃል? የመጀመሪያ ፍቅረኛህን የት ተዋወቅሃት?... ሁሉም ስለሱ ነው ማወቅ የሚፈልጉት! የራሴ የሚለው ነገር እንዲኖረው አይፈልጉም፡፡

የማስመሰል ህይወት ፀማይ ውስጥ የለም! በጫት እና በሺሻ ታጥረው እየዋሉ “እኛ አርቲስቶች ከሱስ የፀዳ ህብረተሰብ ለመፍጠር አርአያ መሆን አለብን!” የሚል ዲስኩር ማሰማት በፀማይ ውስጥ የለም፡፡ ጠዋት ስለጫት አስከፊነት አውርቶ ከሰአት “ልጄ የጥበብ ሥራ በርጫ ይዘው በፅሞና ነው! ሼክስፒር ሳይቅም እንዲህ የፃፈ ቢቅም ኖሮ የትናየት በደረሰ ነበር!…” ማለት የለም፡፡ ህዝቡን መድረክ ላይ አስር ጊዜ “በጣም ነው የምወዳችሁ!” እያሉ በመወሻከት የቁርጥ ቀን ሲመጣ “ልጄ ሁሉም ለራሱ ነው!” ብሎ ነገር የለም፡፡ ፀማይ የእውነት ምድር ነው፡፡ መውደድ እንዳይረክስ በቃል አይጠራም፤ በተግባር ነው የሚገለፀው፡፡ እነዚህን ሁሉ በረከቶች አግኝቷል፡፡ ፀማይ ሰላም ነው! በፀማይ ኮረብቶች፣ በፀማይ ሜዳዎች ላይ ቀን ከምሽት ሳይመርጥ ሲንጐራደድ፣ አፉ ውስጥ የቀረች አንዲት ግጥምን እንደ ብሔራዊ መዝሙር ይደጋግማታል፡፡

“ፍላጐት ምኞትህ ወደብ ድንበር አለው? ብለህ አትጠይቀኝ ህልሜ አንተን መሆን ነው! ያለ ስም ቅጥያ ግቤ ሰው መሆን ነው፡፡ ሰው መሆን! ሰው መሆን! በቃ ነፃ መሆን!” ግጥሟ የአንድ ፋርሳዊ ፀሃፊ ነው ብሎ ጓደኛው ነበር በቃሉ ያስጠናው፡፡ ነፃ ሰው የመሆን ስሜቱን በፀማይ አፈር፣ በፀማይ አየር፣ በፀማይ ሰዎች መካከል አግኝቶታል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከኦሞ ወንዝ ጋር የማይደበዝዝ ፍቅር አዳብሮ ነበር፡፡ ኦሞን እንደሰው እያዋራ፣ በኦሞ የቅዝቃዜ በረከት ሲረሰርስ፣ በኦሞ ፈሳሽ ውሃ ሲዳሰስ ዘላለማዊ መኖሪያው በኦሞ ዳርቻ እንደሚሆን ወስኖ ነበር፡፡ በሰለሞን ውሳኔ ግን ኦሞ የተስማማ አይመስልም፡፡ እጣውን ኦሞ እራሱ ፅፎ ሰጠው፡፡ እጣ ደግሞ የሚመርጡት ሳይሆን የሚወጣ ነው፡፡ በአንድ ወበቃማ ቀን ሰለሞን ወደ ኦሞ ሲወርድ ለሁለት ወራት ያህል ከውሀው ሲገባ ለወትሮ የሚያገኘውን ደስታ በልቡ እያሰበ ነበር፡፡ ወደ ወንዙ የሚያመራውን ጉብታ ቁልቁል እያቋረጠ ሳለ ግን የድረሱልኝ የሚመስል ድምፅ የሰማ መሰለው፡፡ እየሮጠ ወደ ወንዙ ደረሰ፡፡

ብቅ ጥልቅ የሚል ሰው ታየው፡፡ በውሀው ላለመወሰድ የሚታገል፡፡ ዘሎ ከውሀው ገባ፡፡ የውሃውን ሃይል እየታገለ ሰው ወዳየበት አቅጣጫ ተምዘገዘገ፡፡ ያየውን ሰው እጅ እንዳገኘ ሽቅብ ገፋው እና ከውሀው በላይ አደረገው፡፡ በአንድ እጁ እየዋኘ ወደ ወንዙ ዳር ተጠጋ፡፡ ኦሞ እንደለማዳ ፈረስ እሺ ብሎ የሚጋልብለት ይመስል በቀላሉ አቋረጠው፡፡ የተሸከመውን ሰው አውጥቶ ከወንዙ ዳር አስተኛው፡፡ በውሀ ሊወሰድ የነበረው ሰው ግዙፍ ወንድ ነበር - ፈረንጅ! ከአለባበሱ ቱሪስት እንደሆነ ገምቷል፡፡ ከነልብሱ ምን ሊያደርግ ኦሞ ውስጥ እንደገባ ለሰለሞን ሊገባው አልቻለም፡፡ “እንደኔ የከተማ ቱማታ ናላውን ያዞረው ይሆናል!” ብሎ እያሰበ ሳለ፣ የፈረንጁን ጩኸት የሰሙ ፀማዮች እየተጠራሩ ከቦታው ደረሱ፡፡ የሰውዬውን ደረት እየተጫኑ ከሆዱ የገባውን ውሀ ሲያስወጡለት ቀስ በቀስ ነፍስ ዘራ፡፡ ሰለሞን የሰው ነፍስ ማትረፍ መቻሉ ከፍተኛ ደስታ አጐናፅፎት ነበር፡፡ የፀማዮች ተደጋጋሚ የምስጋና ቃል ሲቸረው በሙሉ ልብ ሲቀበል ቆየ፡፡ ያረፈባት ቤት ፈረንጁን ከውሀ ውስጥ መንጥቆ ያወጣውን ጀግና ለማየት ከአቅራቢያ መንደሮች ጭምር በሚመጡ እንግዶች እስከምሽት ድረስ ተጨናነቀች፡፡ የሰለሞን ዝና በአንድ ምሽት ፀማይን አልፎ ጅንካ ደረሰ፡፡ ከጅንካ ምድር አልፎ አዋሳ ለመድረስ አንድ ቀን አልፈጀበትም፡፡ ከአዋሳ አዲስ አበባ በዚያው ቀን ምሽት ዜናው ተሰራጨ፡፡ የጋዜጠኞች ቡድን ካሜራ እና ማይኩን ደቅኖ ጀርመናዊውን ቱሪስት ያዳነውን ጀግና ለማየት ወደ ፀማይ አመራ፡፡

ሰለሞን ከከተማ የመጡ ሰዎች ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ በብሔረሰቡ አባት ሲነገረው፤ ብዙም ደስ ባይለውም እሳቸውን ላለማስቀየም ወጥቶ የመጡትን ሰዎች ማነጋገር ነበረበት፡፡ “ለመንደራችን ልዩ ሲሳይ ነው ይዘህ የመጣኸው!... አሁንም ከከተማ ትላልቅ ሰዎች አንተን ለማነጋገር መጥተዋል፡፡ እንደምታየው መንደራችን ብዙም አላደገችም፡፡ አንተ የሰራኸው ስራ መንደራችንን ለማስተዋወቅ ጠቃሚ ነው!” የሚለው ንግግራቸው ይበልጥ አሳማኝ ሆነለት፡፡ ጋዜጠኞቹ ሰለሞንን ሲያዩ አይናቸውን ተጠራጥረው ነበር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ፤ “ዝነኛው አርቲስት ሰለሞን?” አለ ባለማመን ስሜት ተውጦ ሰለሞን በአዎንታ እራሱን ነቀነቀ፡፡ የፎቶ ካሜራዎች ብልጭታ ከየቦታው ሲተኮስበት፣ የካሜራዎች እይታ እሱ ላይ ሲያነጣጥርበት አንድ ነገር ገባው፡፡ ዝነኝነት ምርጫው ባይሆንም እጣው ነበረ፡፡ ቢሸሽ የማያመልጠው! እንደ ጥላ!

Read 4677 times