Saturday, 30 March 2013 14:24

አፍሪካን ቫኬሽንና “የጊዜ መጋራት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የከተማ ኑሮ በጣም አድካሚና አሰልቺ ከመሆኑም በላይ በውጥረት የተሞላ ነው፡፡ በእኛ አገር ያልተለመደና በሙጪው ዓለም የሚዘወተር የመዝናኛ ፕሮግራም አለ - ቫኬሽን መውጣት፡፡ የማያውቁትን፣ የሚያደንቁትንና የሚጓጉለትን … ነገር፣ በማየትና በመጐብኘት መደሰት አዕምሮን ከማዝናናቱም በላይ ሰውነትን ዘና ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው በሥራ የደከመ አዕምሮውን ከቤተሰቡ ጋር ቫኬሽን በመውጣት ቢያዝናና ረጅም ዕድሜና ጤናማ ሕይወት መምራት ያስችለዋል፡፡ ይህን ባህል በእኛም አገር ለማስለመድ እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አፍሪካን ቫኬሽን ክለብ ተጠቃሽ ነው፡፡ “ታይም ሼሪንግ” የተባለ ፕሮግራም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ክለቡ ይህን አዲስ ባህል ለማስለመድ ምን እያደረገ ነው? የፕሮግራሙ ይዘትስ ምንድነው? ምን ችግሮችስ አሉበት? ችግሮቹንስ እንዴት እየተወጣ ነው? … በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ መስራችና ባለቤት ወ/ሮ ሶኒያ ፓስኩዋ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡ እስኪ ሥለ ራስዎ ትንሽ ያጫውቱኝ? ሶኒያ ፓስኩዋ እባላለሁ፡፡

ግማሽ ጣሊያን ግማሽ ኢትዮጵያዊ ብሆንም ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በሊሴ ገ/ማሪያም ጨርሼ፣ ከዚያ ወደ ጣሊያን ሄድኩኝ፡፡ እዛም 13 ዓመታት በማርኬቲንግ ስሠራ ቆየሁ፡፡ ለምን እና እንዴት ነበር ወደ ጣሊያን አካሄድዎ? ወደ ጣሊያን የሄድኩት የዛሬ 35 ዓመት ገደማ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ሥርዓት ትንሽ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት እዚህ አስጊ ነገሮች ስለነበሩ ጣሊያን ሄድኩና ማርኬቲንግ ተማርኩኝ፡፡ ይህ ትምህርት በዚያን ወቅት አዲስ ነበር፡፡ ብዙ የማርኬቲንግ ፍላጐት የታየበት ስለነበር፣ እኔም ከታወቀ ዩኒቨርስቲ በማርኬቲንግ ኤክሠለንስ በሠርቲፍኬት ተመረቅኩኝ፡፡ በወቅቱ ዘርፉ አዲስ በመሆኑ በዲግሪ ደረጃ አይሠጥም ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማርኬቲንግ ነው ስሠራ የቆየሁት፡፡

ጊዜን መጋራት (time Sharing) የተሠኘ ቢዝነስ ነው እዚህ አገር ያመጣችሁት፡፡ በዚህ አገር ይሄ ቢዝነስ አልተለመደም፡፡ እንዴት በዚህ ዘርፍ ተሠማሩ? ጣሊያን በነበርኩበት ወቅት ጊዜን መጋራት በጣም ፋሽን የሆነ ቢዝነስ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ማርኬቲንግ ላይ ባተኩርም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ቱሪዝም ላይ ትልቅ ነገር እሠራለሁ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም “ታይም ሼሪንግ” ከቱሪዝምም ከማርኬቲንግም ጋር ስለሚገናኝ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ “ታይም ሼሪንግ” ምንድነው? አሠራሩስ? ጊዜን መጋራት ማለት በአመት ውስጥ 52 ሳምንታት አሉ፡፡ አንዱን ቤት ሀምሳ ሁለት ሰዎች ይገዙታል፡፡ ስለዚህ ለአንድ ሰው አንድ ሳምንት ነው የሚደርሠው፡፡ አንድ አባል በዓመት ውስጥ ከ51 ሌሎች የድርጅቱ አባሎች ጋር ጊዜን ይጋራል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ዜጐች እንድትጐበኝ፣ መልካም መሆኗ እንዲነገር እፈልግ ነበር፡፡ ለዚህም ቆንጆ ሪዞርት፣ ቆንጆ የጉብኝትና የመዝናኛ ቦታዎችን ለመገንባት እቅድ ነበረኝ፡፡

ይገርምሻል ለቱሪዝም ፍቅር ያደረብኝ በልጅነቴ አባቴ ከከተማ የመውጣትና ከከተማ ውጭ ያለውን ነገር እንዳደንቅ ያደርገኝ ሥለነበር ነው፡፡ በእርግጥ ከጣሊያን እንደመጣሁ ባሠብኩት ፍጥነት አይደለም ይሄንን ቢዝነስ የጀመርኩት፡፡ ለምን? እንደመጣሁ አባቴም እንዳግዘው ይፈልግ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ “ፓስኩዋጁሴፔ” የተሠኘ የብረታ-ብረት እና አሉሚኒየም ማምረቻ ድርጅት ሥለነበረው እዛ ውስጥ እየሠራሁ ቢዚ ሆኜ ቆየሁ፡፡ ይህ የአባቴ ድርጅት አሁንም አለ፡፡ በቅርቡ 50ኛ ዓመቱን ልናከብር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ስሠራ ብዙ ነገሮችን እያጠናሁና እየተዘጋጀሁ ቆይቼ፣ ቱሪዝሙን የዛሬ ስምንት ዓመት እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመርኩ፡፡ አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ እንዴት ተመሠረተ? ጊዜን መጋራት (time sharing) ጣሊያን እያለሁ በስፋት የማውቀው ሥራ ነው፡፡ አውሮፓም አሜሪካም በጣም የሚሠራበት ቢዝነስ ነው፡፡ ለቤተሠብ መዝናናት በጣም አመቺ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡

በውጭ አገር በጣም ከመለመዱ የተነሳ ጥንዶች ተጋብተው የቤት ዕቃ ሁሉን ነገር ሲያሟሉ ጊዜን መጋራትንም ለመግዛት እንደ አንድ ፕሮግራም እቅዳቸው ውስጥ ያካትቱታል፡፡ አንዱ የጋብቻው አካል ያደርጉታል ማለት ነው፡፡ ለምን መሠለሽ በውጭው አለም በዓመት አንዴ ቫኬሽን መውጣት በጣም የተለመደ ነው፡፡ ለ15 ቀናት ያህል የማይዘጋ ድርጅት የለም፡፡ ሁሉም ቫኬሽን ይሄዳል፡፡ የአፍሪካ ቫኬሸን ክለብ ሠራተኞችም እረፍት ይወጣሉ? በትክክል! እናደርጋለን፡፡ ይኼ አጠቃላይ ፅንሠ ሐሣቡ ሁሉም ከቫኬሽንና ከእረፍት ሲመለሱ በአዲስ ኃይልና መንፈስ ጥሩ ሥራ ይሠራሉ ነው የሚባለው፡፡ ለድርጅቱም ውጤት ያስገኛል፡፡ ያኔ ታዲያ በቫኬሽን ጊዜ ሁሉም መጐብኘት ስለሚፈልግ ሪዞርት፣ ጥሩ ጥሩ የመዝናኛ ቦታዎች ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ትንሽ ውድ ስለሚሆን በተለይ ለደሞዝተኛ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ለማረፊያና ለመዝናኛ ለ20 ዓመት የሚያገለግል አንድ ጊዜ ኢንቨስት ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ አባል የሚኮነው እንዴት ነው? የአባልነት ስምምነት ይፈርምና ግዢ ይፈጽማል፤ እኛም ሰርቲፊኬት እንሰጠዋለን! ለ20፣ ለ15 አሊያም ለ12 ዓመት አባልነት ሊገዛ ይችላል፡፡ እናንተ ስትጀምሩ ለ45 ዓመት ሁሉ ትሸጡ ነበር ይባላል፡፡

እውነት ነው? ትክክል ነው ስንጀምር ለ45 ዓመት ነበር፤ አሁን ለ20 ዓመት አድርገነዋል፡፡ ከ45 ዓመት ወደ 20 ዓመት ያሻሻላችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? በጀመርንበት ጊዜ 45 ዓመት ስንለው ሰው ይደነግጣል፡፡ ምክንያቱም 45 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ እኛም እናስተዋውቀው ብለን እንጂ ለአሠራር አመቺ አልነበረም፡፡ 45 ዓመት ሙሉ ተከታትሎ ሰው አንድ ቦታ ላይቀመጥ ይችላል፡፡ ወደ 20 ዓመት ሲሻሻል ግን ዓመቱ አጠር ያለ ስለሆነ እስከዛ ድረስ ያለውን ጠቀሜታ አይቶ ለመቀጠልም ላለመቀጠልም ሊወስን ይችላል፡፡ ወደ 20 ዓመት ስናሳጥረው ያየነው ለውጥ ብዙ ነው፡፡ ሰው 20 ዓመቱን ከእኛ ጋር ቆይቶ ሌላ መቀየር ሊፈልግ ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ነው ያሳጠርነው፡፡ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ የአባልነት ግዢዎች አሏችሁ፡፡

ልዩነቱ ምንድን ነው? በዋናነት የሚለየው የምትጠቀሚበት ጊዜ ነው። ለምሣሌ የወርቅ አባልነትን እንውሰድ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ቫኬሽን መውጣት የሚፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተሰቦች የልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚዘጋበት፣ በአንድ ላይ ለመዝናናትና ለማረፍ ምቹና ውድ ጊዜ በመሆኑ በዋጋውም ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ በተለይ የበዓላት ጊዜ የሚወጣው ቫኬሽን ሁሉም የሚፈልገው ጊዜ ስለሆነ የወርቅ ነው፡፡ የብር ደግሞ ትንሽ መካከለኛ ነው፡፡ ይኼ ማለት ቫኬሽን የሚኬድበትም የማይኬድበትም ጊዜ ነው፡፡ የነሐስ ደግሞ የሚመቸው ውስን የቫኬሽን መውጫ ጊዜ ለሌላቸው ነው፡፡ ለምሣሌ ጡረተኞች የሚጠቀሙበት ወቅት ነው፡፡ በውጭው ዓለም የነሐስ አባልነትን የሚጠቀሙት ጡረተኞች ናቸው፡፡ አባልነቱን የሚገዙትም ከወርቅና ከብሩ በጣም በወረደና በረከሠ ዋጋ ነው፡፡ በአብዛኛው ልጅ የሌላቸውና ጡረተኞች በጣም ይጠቀሙበታል፡፡ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ የአባልነት ግዢ ምን ያህል እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉ? የማረፊያው ቤቱስ ምን ምን ነገሮችን ያሟላ ነው? ቤቱ የመኖሪያ ቤት መልክ ያለውና በሁሉም ነገር የተሟላ ነው፡፡ መኝታ፣ መታጠቢያ፣ ሳሎን፣ ኪችን … ሁሉም አለው፡፡

የሆቴል ክፍል ሳይሆን የመኖሪያ ቤት መንፈስ ያለው ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ አብስሎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቤቱን ብቻ ነው የሚጠቀሙት። “ለእረፍት መጥቼ መቀቀል አልፈልግም” ካሉ ከቤቱ ውጭ ባለው ሬስቶራንት ከፍለው መጠቀም ይችላሉ። እኛ ቤቱን ያዘጋጀነው ሰው ቫኬሽን ቢወጣም የራሱ ቤት እንደሆነ እንዲሰማው ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ለአንድ ሳምንት መጠቀም ይችላሉ፡፡ በቃ ለ20 ዓመት ከፍለውበታል፡፡ የራሳቸው ነው፡፡ የራሣቸውን ቤት እንዲመለስላቸው ሶፋ፣ ቴሌቪዥን ሁለት መኝታ ቤት ሁሉን ያሟላ ነው፡፡ የላንጋኖው ሪዞርታችን ከቤቱ ወጣ ሲባል የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሁሉንም ያሟላ ነው ፡፡ እዚህ ላይ አያይዤ የምነግርሽ ለቤቱ በአባልነት አንዴ ከገዛሽ በኋላ በየዓመቱ ደግሞ ለአስተዳደር የምትከፍይው አለ፡፡

በአባልነት ክፍያው ውስጥ የማይካተት ማለት ነው? በአባልነት የምትከፍይው የቤቱን ብቻ ነው፡፡ የአስተዳደር ክፍያው ሌላ ነው፡፡ አንቺ አንዴ ለቤቱ ከፍለሽ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምትመጪው። ቤቱ በየጊዜው መጽዳት አለበት፡፡ ለዚህ የፅዳት ሠራተኛ ያስፈልገዋል፡፡ የጥበቃ ሠራተኛ አለ፣ የጓሮ እና የጊቢ ፅዳትና ውበት እንክብካቤ ያስፈልገዋል፡፡ በአጠቃላይ የሪዞርቱ ሠራተኞች ደሞዝተኞች ናቸው። ይህን መክፈል ያለበት አባልነት የገዛው ሰው ነው። እነዚህ ነገሮች በእንክብካቤ ተይዘው ካልጠበቁት በዓመቱ ሲመጣ የሚያዝናናውና የሚያስደስተው ነገር አያገኝም፡፡ በውጭው ዓለም በአሮጌው ዓመት መጨረሻ አሊያም በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የዓመቱን የአስተዳደር ክፍያ ይፈፅማሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ለመዝናናት ሲሄዱ ወጪያቸው የሚሆነው የመዝናኛና የቀለብ ብቻ ይሆናል፡፡ ቆይታቸውም በጣም አስደሳች ይሆናል፡፡ የአባልነት ክፍያው ምን ያህል ነው? ስንጀምርና አሁን ያለው ክፍያ የተለያየ ነው፡፡ እኛ ቢዝነሱን ለማስተዋወቅና ቶሎ ወደ ስራው ለመግባት ስንል በጣም በትንሽ ዋጋ ጀምረነው ነበር፡፡ ለምሣሌ 20ሺህ ከፍሎ ለ45 ዓመት አባልነት የገዛ ሁሉ ነበር፡፡ አሁን እንደዛ አይደለም፡፡ ያኔ ለፕሮሞሽን ከ20 ሺህ ብር እስከ 120ሺህ ከብር እስከ ወርቅ ለ45 ዓመት ሸጠናል። አሁን በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ስለሆነ ዋጋው ውድ ነው አዲስ እያስገነባን ላለነውና ለማስፋፊያው አዲስ ዋጋ ነው ያወጣነው፡፡

አንድ አባል በዓመት ቫኬሽን መውጣት ባይፈልግ ማከራየት ወይም ለሌላ ቤተሠብ እንዲዝናና መፍቀድ ይችላል? አባሉ፣ ለቤተሰቡ ሊያስተላልፈው ወይም ሊያከራየው ይችላል፡፡ አሊያም ክፍት ሆኖ ሊቆይ ይችላል፡፡ የምናከራየው እኛ ሳንሆን ራሳቸው የቤቱ ባለቤቶች ናቸው ማከራየት የሚችሉት፡፡ በማከራየት ጉዳይ ከአባሎቻችን ጋር አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ ማከራየት ትችላላችሁ ስንል እኛ የምናከራይላቸው መስሏቸው ነበር፡፡ እኛ ይህንን ማድረግ አንችልም በሥራ ፈቃዳችንና በታክስ አከፋፈላችን ላይ ችግር ያመጣብናል፡፡ ራሱ ቤቱን ለ20 ዓመት የገዛው ሰው ለፈለገው የመስጠት፣ የማከራየት አሊያም በቫኬሽን ጊዜ ሳይመጣ ጊዜውን ዝም ብሎ ማሳለፍም የራሱ የባለቤቱ ውሳኔና ምርጫ ነው፡፡ ቤቱን የገዛ አባል ከአገር ቢወጣ፣ በአጠቃላይ ከጊዜ መጋራቱ መልቀቅ ቢፈልግ ለሌላ ቤተሰብ አሳልፎ የመስጠት፣ የመሸጥ ወይም የማከራየት መብት አለው? በሚገባ! እንደገዛው የዓመት መጠን ከላይ የጠቀስሻቸውን ነገሮች የማድረግ መብት አለው፡፡ 45 ዓመት የገዛ ከሆነ ዓመቱ እስኪያልቅ ለሌላ የማውረስ፣ የማከራየትና የመሸጥ መብት አለው፡፡

ውላችን ይህንን ግልፅ ባለ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ በእናንተ አሠራር ላይ የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች አሉ፡፡ አንዱ ቅሬታ፣ ገንዘብ መሰብሰብ የጀመራችሁት ሪዞርቱን ከመገንባታችሁ በፊት ነበር፡፡ እንደውም “ተጭበረበርን፣ ውሸት ነው” እያሉ ሰዎች ሲያማርሩ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ስለዚያ ጊዜ ባታነሺብኝ ጥሩ ነበር፡፡ ያ ጊዜ ብዙ ስቃይ ያየሁበት ጊዜ ነበር፡፡ ታምሜ ሁሉ ነበር፡፡ እኛ በውጭው ዓለም እንዳለውና እንደተለመደው መስሎን በአንድ ዓመት ውስጥ ሠርተን እንጨርሠዋለን ብለን ነበር፡፡ ስንጀምር በእጃችን ካለው ብር በተጨማሪ ለአባልነት ከሚከፈለው ጋር አንድ ላይ አድርገን ልንገነባ እንዳሠብን ግልፅ አድርገናል፡፡ ችግሩን የፈጠረው በአንድ ዓመት ውስጥ እንከፍታለን ብለን የፈጀብን ግን ሦስት ዓመት ተኩል መሆኑ ነው፡፡ ያኔ ሰው ሁሉ በጣም ደንግጦ ነበር፡፡

ችግራችሁ ምን ነበር? ችግራችን ብዙ ነበር፡፡ አንደኛው ሥራው የሚጀመረው ጫካ ውስጥ ነው፡፡ ጫካ ገብተሽ ስትሠሪ፣ አሠራሩና ሲስተሙ ሁሉ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የተቀናጀ ነገር የለም፣ ሠራተኛውም “ከከተማ ውጭ ሥራ” ስትይው ደስ ብሎት አይሄድም፡፡ ጥሩ ሠራተኛም ማግኘት ሌላው ፈተናችን ነበር። ጫካ ስለሆነ ለሠራተኛ የምንከፍለው ከኖርማሉ ሦስት እጥፍ ነበር፡፡ ለስራ ከወሰድናቸው በኋላ ሠልችቷቸው ሥራ አቋርጠው የሚመለሱ ነበሩ። ሌላው ችግር የአካባቢው ሰው እዚያ ቦታ ላይ ስንጀምር ደስተኛ አልነበረም፣ የጥበቃ ችግርም ነበረብን፡፡ የአካባቢው ሰው ደስተኛ ያልሆነበት ምክንያት ብዙ ሰው ሪዞርትና መዝናኛ ለመስራት ብዙ መሬት ወስዶ አልሠራም። እኛንም “መሬታችንን ቀምተው ወይ አይሠሩ ወይ እኛ አልተቀመጥን፣ በከንቱ ነው” የሚል ጥርጣሬ ነበረባቸው፡፡

እኛንም መሬት ገዝተው ዝም እንዳሉት የመቁጠር ችግር ነበረብን፡፡ በኋላ እየተሠራና እየተስፋፋ ያካባቢው ሰው የስራ እድል እያገኘ መጠቀም ሲጀምር፣ ተቀይረው በጣም ደጋፊያችን ሆኑ፡፡ ምክንያቱም ቋሚ ስራ ያገኙ አሉ፤ ስልጠና ያገኙ አሉ፤ በአጠቃላይ ብዙ የአካባቢው ህዝብ ህይወቱ ተቀይሯል፡፡ ክስ የመሠረቱ ደንበኞች እንደነበሩም ሰምቻለሁ። ችግሩን እንዴት ፈታችሁት? እርግጥ ነው፤ ብራችንን ሰብስበው ጠፉ፣ ምንም አይሠሩም፣ የሚል በርካታ ወሬና ክስ ነበር። እኛም በተቻለን መጠን ሠውን ለማሳመን ብዙ ጥረት ሥናደርግ ነበረ፡፡ አምነውንና ታግሰውን የቆዩ አሉ፡፡ ያላመነንም ብዙ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሠርተን ጨርሠን ስንከፍት እንኳን አምኖን የመጣ ሰው በጣም ጥቂት ነበር፡፡ በኋላ ግን በጣም ጥሩ ሪዞርት መሠራቱ ሲወራ ነው መምጣት የጀመሩት።

በተለይ በተከፈተ በመጀመሪያው ዓመት ተጠቃሚ የነበሩት አባላት ጥቂት ነበሩ፡፡ ግን እኮ ሁሉም መከፈቱን ሠምተዋል፤ እኛም አስተዋውቀናል። ግን አልመጡም አላመኑበትም ነበር፡፡ ክስን በተመለከተ በቀጥታ የከሰሰን ባይኖርም፣ በአሠራሩ ላይ ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በተለይ ከዓመታዊ የአስተዳደር ክፍያ ጋር ጭቅጭቆች አሁንም አሉ፡፡ ለምሣሌ “ስሄድ ነው እንጂ ለምን ቀድሜ እከፍላለሁ፣ በዚህ ዓመት ሄጄ ስላልተጠቀምኩ አልከፍም” የሚሉ አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ደግሞ አይሠራም፡፡ አሁን ምን ያህል አባላት አሏችሁ? ወደ 1900 ያህል አባላት አሉን፡፡ ከእነዚህ አባላት መካከል አብዛኞቹ ደስተኞች ቢሆኑም አንዳንዶቹ እስካሁን ያልረኩና አሠራሩ ያልገባቸው አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአባልነታቸውን እንጂ የአስተዳደር ክፍያ እስካሁን አልከፈሉም፡፡ በዚህ የተነሳ አለመግባባቶች አሉ፡፡ “እኛ እንደሚከፈል አናውቅም” ነው የሚሉት፡፡ ይኼ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እኛ ኮንትራት ውሉ ላይ አስቀምጠናል። አንዳንዶቹ “ኮንትራቱን አላነበብኩም” የሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ሌላው መክፈል እንዳለበት ያውቅና “ከሄድኩኝና ከተጠቀምኩኝ ነው የምከፍለው” የሚል አለ፡፡ በዚህም በኩል ሌላ ችግር አለብን ማለት ነው፡፡ የአስተዳደር ክፍያው ምን ያህል ነው? በየዓመቱ ሶስት ሺህ ብር ነው፡፡ ይኼ ሶስት ሺህ ብር እንግዲህ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ለጥበቃ፣ ለፅዳት፣ ለአትክልተኛና ለጥገና ሠራተኞች የሚከፈል ነው፡፡ በላንጋኖ 114 ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ ለእነሱ ደሞዝ እንከፍላለን፣ በተጨማሪም መብራትና ውሃ አለ፡፡

ውሃው በደንብ ተጣርቶ፣ ንፁህ ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡ ውሃው የጫካ ስለሆነ በደንብ መታከም አለበት፡፡ ማከሚያው ደግሞ ውድ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ እናወጣለን፡፡ ሰው ኖረ አልኖረ መብራት ይበራል፡፡ ሠራተኛው ይሠራል፤ ማኔጅመንቱም አለ፤ ለዚህ ሁሉ መከፈል አለበት፡፡ መጀመሪያውኑ የወርቅም የብርም የነሀስም የአባልነት ክፍያ ሲከፍሉ ለምን አልተደመረም? ድጋሚ የአስተዳደር ብሎ መጠየቁስ ለምን አስፈለገ? በዓለም ላይ ባለው የጊዜን መጋራት ቢዝነስ ውስጥ አሁን ያልሽው ነገር አይደረግም፡፡ ምን መሠለሽ የሚደረገው? የቤቱ ክፍያ (የአባልነቱ ክፍያ) የታወቀ ወጪ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሠራ ቤት ነው። ይኼኛው ግን በየጊዜው እየበዛና እያደገ የሚሄድ ወጪ ነው፡፡ ለምሣሌ ዛሬ የምትከፍይው የሠራተኛ ደሞዝና የዛሬ ዓመት የምትከፍይው እኩል አይደለም። የመብራት ክፍያም ይጨምራል፣ ለጥገና የሚወጣው ወጪና የሚቀየሩ የቤቱ እቃዎች ወጪም እንዲሁ ብዙ ነው፡፡ መብራት አለ ቢባልም በአብዛኛው የምንጠቀመው ጀነሬተር ነው፡፡ የናፍጣውን ወጪ አስቢው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የአስተዳደሩ ወጪ ከአባልነት ክፍያው ጋር ይካተት ማለት ተገቢ አይደለም፤ አይደረግምም፡፡

በዓመት ሶስት ሺህ ብር ደግሞ በጣም ፌር የሆነ ክፍያ ነው፡፡ ለምሣሌ የሲሊንደር ጋዝን ከአስተዳደር ወጪ አውጥተን አባሎች ለአንድ ሳምንት ሲመጡ ብቻ የሚጠቀሙበትን አሳውቀን ማቅረብ ጀመርን። ለምን? ቢባል፤ በየጊዜው ዋጋው እየናረ ስለሆነ መገመት አቃተን፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦችም ለእረፍት መጥተን ለምን ምግብ እናበስላለን? በሚል ሬስቶራንት የሚጠቀሙ አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ ባልተጠቀሙት ጋዝ ለምን የአስተዳደር ወጪ ውስጥ እንከታቸዋለን በሚል ነው ያወጣነው፡፡ ሪዞርታችሁ ባለ ሥንት ኮከብ ነው? አጠቃላይ ይዘቱስ ምን ይመስላል? ሪዞርቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆኖ ነው እውቅና የተሠጠው፡፡ 40 ቤቶች አሉት፡፡ 30 ቤቶች ስድስት ስድስት ሰው ነው የሚይዙት፡፡ 10 ቤቶች ደግሞ ስምንት ቤተሠብ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ በቅርቡ ስምንት ያህል ሲንግል ክፍሎች ሠርተናል፡፡ አሁን ደግሞ ባልና ሚስት እና ሁለት ልጆች በአጠቃላይ 4 የቤተሠብ አባላት የሚችል እንዲሁም ለባልና ሚስት ብቻ የሚሆኑ ቤቶችን እየገነባን እንገኛለን፡፡ የማስፋፊያው እቅዳችን ይሄ ነው፡፡ እስካሁንም አልተቀረፈም ከሚባሉ ችግሮች ውስጥ የሽያጭ ሠራተኞቻችሁ በየሞሉ፣ በየሱፐርማርኬቱ ወይም ባለሀብቶች ይገኙባቸዋል በተባሉ ቦታዎች እየሄዱ ሰዎችን ያናግራሉ፡፡

ብዙ ሰዎች አቀራረባቸው ምቾት አይሠጥም፣ ነፃነትን ይጋፋል የሚሉ ቅሬታዎችን ያሠማሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በደንብ ያውቁታል ብዬ አስባለሁ… እርግጥ ነው አሁንም ቅሬታዎቹ አልፎ አልፎ አሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ሠራተኞቻችንን ስናሠማራ የሚያግናሩትን ሰው እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው፣ ትህትናቸው ምን መምሰል እንዳለበት በደንብ እናሠለጥናቸዋለን፡፡ ነገር ግን የሁሉም ሰው ምላሽ እኩል አይሆንም፤ ግማሹ “ኦ! አዲስ አሠራር ነው፤ እንዴት ጀመራችሁ” ብሎና ተገንዝቦ፣ ጊዜ ሰጥቶ ከተስማማው ይቀጥላል፤ ካልተስማማው አመስግኖ ይለያል፡፡ ምክንያቱም ያኔ ይህን ቢዝነስ የጀመርነው የመጀመሪያዎቹ እኛ ነን፡፡ አሁን እንኳን ሼር የሚሸጡ፣ ቤት ሠርተው የሚሸጡ በርካታ ድርጅቶች እየሠሩበት ነው፡፡ እና ከላይ እንዳልኩት ስራው አዲስ እንደመሆኑ አድንቀው የሚሄዱ እንዳሉ ሁሉ ተሳድበው የሚሄዱም አሉ፡፡ ስድቡ አሁንም አለ፡፡ አሁንም “ሰው መረበሽ አታቆሙም እንዴ?” የሚሉና የሚበሳጩ አሉ፡፡ ይህንን ስትራቴጂ ካልቀየርን በስተቀር ያሉት ችግሮች መቀጠላቸው አይቀርም፡፡

ምክንያቱም በዚህ መንገድ ካልሆነ ሰውን ማግኘትና አባሎቻችንን ማብዛት አንችልም፡፡ ስለዚህ በየመንገዱ እየዞርን ነው የምንሠራው፡፡ ካልሆነ ሥራችን መቆሙ ነው!! ይህ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ በእኛ በኩል ሠራተኞቻችን በአግባቡና በትህትና ሠዎችን እንዲያናግሩና በአግባቡ ውጤት እንዲያመጡ በስልጠናና በመሠል ጉዳዮች አቅማቸውን ማሣደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የምናናግራቸው ሰዎች ፈቃደኛ ሲሆኑ ፎርም ይሞላሉ፤ ስልክ ይሰጣሉ፡፡ በቢሯችን የቴሌ ማርኬቲንግ አገልግሎት አለ፡፡ ማርኬተሮቹ ደውለው ቀጠሮ ይይዙና ሰውየው ወደ ቢሯችን መጥቶ ጠቅላላ ስለ አፍሪካ ቫኬሽን፣ ስለ ቱሪዝም ስራችን፣ ስለ ምንሰጠው አገልግሎት ሠፊ ማብራሪያ ይሰጠዋል፡፡ ከዚያ በኋላ አባልነቱን መግዛትና አለመግዛት እንደሰውየው ሁኔታ ይወሠናል፡፡ ሠራተኞቻችሁ መንገድ ላይ የማያውቁትን ሰው ሲያናግሩ “ሰርፕራይዝ፤ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ የመሄጃ ሎተሪ ወጥቶልሃል” በማለት ሰውን ያስደነግጡ ነበር፡፡ በዚህ አሠራር ግማሹ ይስቃል፤ ሌላው ተበሳጭቶ ይሄድ እንደነበር ከብዙዎች ሰምቻለሁ፡፡

ይህን ነገር እርሶ ያውቁት ነበር? ምንስ ማለት ነው? አዎ አውቀዋለሁ! ያ የእኛ የማርኬቲንግ ሲስተም ነው፡፡ ሰዎችን ለመሳብ ስንል ሎተሪ ደርሶሀል ነበር የምንለው፡፡ ሎተሪው ቫኬሽን ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ኢንቨስት ያደረግነው በዛ ላይ ነው፡፡ እንደምታውቂው ስራውን ስንጀምር በዚህ መልኩ የሚሠራ ሆቴል ስለሌለ ጊዜን መጋራት የሚለውን ነገር ማስረዳት እንፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህ ኬንያ ቅርብ ጐረቤታችን በመሆኑ ከአንድ ሆቴል ጋር ተነጋግረን ወደዚያ ሰዎችን እንልክ ነበር፡፡ ሰው እዛ ሄዶ የጊዜ መጋራት ሆቴል እንዴት እንደሚሠራ፤ በአገራችን ሲጀመር አባል እንዲሆን የሚያደርገውን ግንዛቤ እንዲያገኝ እናደርግ ነበር፡፡ በእርግጥ ሰው አያምንም ነበር፡፡ እኛ አድርገነዋል። ሆቴል አይሠሩም ብለውን ነበር፤ ሠርተን አሳይተናቸዋል፡፡ በዚህ ሎተሪ አማካኝነት ብዙ ሰው ኬንያ ሄዷል፡፡ ቅርብ በመሆኑ የአውሮፕላን ቲኬቱም ብዙ አያስከፍልም፡፡ በራሱ ምርጫ ደቡብ አፍሪካ ይሁንልኝም ካለ አማራጭ እንሰጥ ነበር፡፡ ማረፊያ በነፃ ነበር የሚያገኙት፡፡ እግረ መንገዳቸውን ስለ ጊዜ መጋራት ስራ ተገንዝበው መጥተዋል፡፡ አሁን ግን የዚህ ፍላጐት ላለው ሰው ላንጋኖ ወዳለው ሪዞርታችን እንልካለን፡፡ በአንድ ወቅት የላንጋኖውን ዓይነት ሪዞርት በባህርዳር እና በጐንደር እንገነባለን ብላችሁ ነበር፡፡ ከምን አደረሣችሁት? ገና አልጀመርነውም፡፡ ነገር ግን እቅዱ አለን፡ በጐንደርና ባህርዳር ብቻ ሳይሆን ሌላም ቦታ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን የላንጋኖው ሪዞርታችን በ45ሺህ ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ ነበር፡፡

አሁን ወደ 70 ሺህ ሜትር ካሬ ለማስፋፋት ይሁንታ አግኝተን ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የማስፋፊያ ግንባታዎች ጀምረናል። በዚህ ምክንያት ትኩረታችንን እዚህ ላይ ስላደረግን እንጂ የተያዙት እቅዶች ጊዜ ጠብቀው እውን ይሆናሉ፡፡ ባለፈው ዓመት “ዘና ብዬ” የተባለ ፕሮጀክት ከፍታችሁ “Resort Condimenuim International” (RCI) ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የጋራ ቢዝነስ እየሠራችሁ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ… RCI የሆቴል ባለቤቶች ሳይሆኑ የኤክስቼንጅ ሥራ የሚሠሩ ማርኬተሮች ናቸው፡፡ ምን ማለት ነው? እነሱ ማርኬቲንግ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለምሣሌ አንቺ ላንጋኖ የአባልነት ከፍለሽ ገዝተሻል፤ ሌላው ታይላንድ ውስጥ እንደዚህ የገዛ ካለ፣ እሱ ኢትዮጵያ መጥቶ በአንቺ ቤት ሲያርፍ አንቺ ደግሞ ታይላንድ ሄደሽ ሰውየው የገዛው ቤት ውስጥ ቫኬሽን ታሳልፊያለሽ ማለት ነው፡፡ ይህን የማለዋወጥ ሥራ ኤጀንት ሆነው የሚያገናኙት RCI የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ አንቺ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ላንጋኖ መሄድ ሊሠለችሽ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ሄደሽ ተመሣሣይ ቤት ካላቸው ጋር እነሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አንቺ ቤት ያርፋሉ፤ አንቺም እነሱ ቤት ታርፊያለሽ፡፡ ስለዚህ RCI ይሄንን ስራ የሚሠራው በዓለም ላይ የጊዜ መጋራት ሆቴል ካላቸው ጋር ነው፡፡ አሁን በእነርሱ በኩል የእኛም አባላት ወደተለያየ አገር በልውውጥ እየሄዱ ነው፤ ከሌላውም ዓለም ወደ ላንጋኖ ይመጣሉ፡፡

ይሄ በተለይ ለአገራችን የቱሪዝም ኢኮኖሚ መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ “ዘና ብዬ” ከአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ተለይቶ ከRCI ጋር የሚሠራ ሌላ ቢዝነስ ነው፡፡ RCI የታወቀ ዌብ ሳይትና ካታሎግ አለው፡፡ አዲስ የጊዜ መጋራት ሆቴሎች ሲከፈቱ እየተከታተለ ያስተዋውቃል፤ ያለዋውጣል፡፡ የእኛን ደረጃ ከሌላው ዓለም ጋር ተመጣጣኝ ነው ወይ? የሚለውን በየጊዜው ይፈትሻሉ፤ ያረጋግጣሉ፡፡ በአጠቃላይ RCI በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የቱሪዝም ኤጀንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእኛ እንኳን እስካሁን ወደተለያየ ዓለም 300 ያህል ሰዎች በልውውጥ ሄደዋል፤ ወደፊትም ብዙ ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡

Read 5135 times