Saturday, 30 March 2013 14:08

“ዓለም ያደነቀው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ! እኔ የምለው…የዚች ዓለም ነገር ግራ እየገባን ነው። ይሄ የኮሪያዎቹ መፋጠጥ፣ እያሳሰበን እኮ ነው! አሀ…ሁለተኛ ዙር “ክተት” ቢባልስ! ስሙኝማ…አንድ ሰሞን ጉልበተኞቹ ኃያላን ይሄ ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ የሚሉት ነገር ነበራቸው። የኪም ኢል ሱንግ አገር “አሁንስ አበዛችሁት፣ ዝም ስንል የፈራን መሰላችሁ አይነት ነገር ማለት ሲጀመሩ የምር ‘ኒው ወርልድ ኦርደር’ እየመጣ ነው፡፡ እናማ…“አሁንስ በዛ!” ማለት ደረጃ የሚያደርሱ ነገሮች በጊዜ ፈዋሽ ‘ጤና አዳም’ና ‘ጦስኝ’ ነገር ካልተበጀላቸው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ታዲያላችሁ… እዚቹ የእኛዋ የዓለም ክፍል “አሁንስ በዛ!” የሚባሉ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ እናማ…በ‘ፈረንጅ ጠበል ለመረጨት’ የመሞከር ነገር አልበዛባችሁም! ምን መሰላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ብቻ ምን አለ መሰላችሁ…ነገሮችን እንዳሉ በራሳቸው “አሪፍ ነው…” “ነፍስ ነው…” ምናምን ብለን ከማድነቅ ይልቅ…አለ አይደል… የሆነ “በመላው ዓለም…” ምናምን አይነት ማወዳደሪያ እንፈልጋለን። ለምሳሌ የታሪክ ቦታዎቻችንን ወይንም ሌሎችን መስህቦቻችንን የሚገባቸውን ከፍተኛ ቦታና ክብር ለመስጠት “የጀርመን ቱሪስቶች አደነቁ…” አይነት ‘ታኮ’ ለምንድነው የሚያስፈልገን! ስሙኝማ…የቱሪስቶችን ነገር ካነሳን አይቀር ግርም የሚሉኝ ነገሮች አሉ፡፡ በአውሮፕላኑ ሌሊት ቦሌ አርፎ ቀጥታ ወደ ሆቴል የሄደው ‘ቱሪስት’ በማግስቱ በሆነ በዓል አካባቢ ለሚጠይቁት ጋዜጠኞች ምን ቢል ጥሩ ነው…“አገራችሁ በእውነት በጣም ደስ የሚል ነው…” ምናምን ነገር ይላል፡፡

ምን መሰላችሁ…የሚገርመው የ‘ቱሪስቱ’ መናገር ሳይሆን እንደ ትልቅ ዜና ሚዲያ ላይ ሲለቀቅ ነው፤ እዚህ አገር ሲመጣ ገና የመጀመሪያ ጊዜ፣ የሚያውቀው መንገድ ከሆቴሉ እስከ መስቀል አደባባይ ያለውን…ምኑን አይቶ ነው ‘አድናቂያችን’ የሆነው! እናላችሁ…እኔ ሳስበው ቱሪስቶቹ በሆዳቸው “እነኚህን ሀበሾች ጦጣ አደረግናቸው…” ምናምን የሚሉን ይመስለኛል፡፡ እናማ… የደመራ ወይም የጥምቀት በዓላት ልዩና አሪፍ መሆናቸውን ለማወቅ የግድ በ‘ፈረንጅ አፍ’ መደነቅ የለባቸውም፡፡ የዛን ሰሞን… የአፍሪካ ዋንጫ ትዝ ይላችሁ የለ! እናማ… ያን ጊዜ “ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የኢትዮዽያና ናይጄሪያ ጨዋታ…” ምናምን የሚባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ በጉጉት መጠበቁ ይቅርብንና አሁንም እኮ አይደለም የእግር ኳስ ቡድን “አገራችሁ ህንጻ አለ እንዴ!” የሚል ‘መላው ዓለም’ ነው ያለው፡፡ እዚሁ እርስ በእርሳችን በልዩ ፕሮግራምም በምኑም የምንጯጯሃት ነገር እኮ ዞራ እኛው ጆሮ ውስጥ ነው የምትከትመው! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ቦተሊካችን’ ሁሉ ዓለም ያደነቀው ምናምን ሲባል…አለ አይደል…ትንሽ ያስቸግራል፡፡ አሀ…አይደለም ዓለም ሊያደንቀን አሁንም እኮ የት እንዳለን፣ እዚህ ዓለም ላይ መኖራችንን የማያውቁ ብዙ መቶ ሚሊዮኖች አሉ! እናማ የእኛ ‘አልፋ ኦሜጋ’ የሌለው ተከታታይ ድራማ የሚመስል ‘ቦተሊካ’ አይደለም እነሱ እኛም ማድነቁ ቀርቶ በቅጡ ባወቅነው፡፡

እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ይሄ ‘ሁሉ ነገሮቻችንን የሚያደንቅልን’ ዓለም የሚገኘው የት እንደሆነ ለማየት አትናፍቁም! አሀ…እኛ የምናውቀው ዓለም ውስጥማ፣ አይደለም የእኛና የናይጄሪያ ቡድኖች ጨዋታ በናፍቆት ሊጠበቅ የዋልያዎቹን ስም እንኳን እንደፈለጉ እየለዋወጡ…አለ አይደል… አንደኛውን የአራዊት ስሞች ‘ዲክሺነሪ’ ሊያደርጉን ምንም አልቀራቸው ነበር፡፡ ታዲያማ…ይሄ “ዓለም ያደነቀው…” ምናምን የምንለው ነገር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ‘አኔስቴዚያ’! በቃ… ስለ ራሳችን አይደለም ዓለም እኛ ራሳችንን እየረሳን በሄድንበት ዘመን በትንሽ ትልቁ ነገር “ዓለም ያደነቀው…” ምናምን አይነት ‘አኔስቴዚያ’ ብዙም አያራምድም፡፡ ታዲያማ…ሴትየዋ የሆነች የልጃቸው ጓደኛ ልታገባ መሆኑን ይሰማሉ፡፡ እና…“የእርሶ ልጅስ፣ ባል አልመጣም እንዴ?” ምናምን ብለው ይጠይቋቸዋል። ይሄኔ ምን ይላሉ መሰላችሁ… “ይኸው በየቀኑ ልጃችሁን ስጡን እያለ በሰልፍ አይደል እንዴ ወንዱ ሁሉ የሚመላላሰው!” ይላሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ “ዓለም ያደነቀው…” በሌላ መልኩ ሲመጣ ማለት ነው! እንኳን ‘ታሳቢ’ ባል በሰልፍ እየጎረፈ “ስጡኝ…” ብሎ ሊጠይቅ የአጎቷ ልጅ “እንደምን ከረምሽ?” ብሎ ከጠየቃት እኮ ይኸው መጋቢት ጊዮርጊስ ዓመት ከመንፈቅ ሊሆን ነው! የመዳዳር ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዱ ሰው ጓደኛው የሆነ ጋብሮቮያዊ “ልጅህን ለገንዘብ ያዥህ ዳርካት የሚባለው እውነት ነው እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል። ጋብሮቮያዊውም ወሬው እውነት መሆኑን ይነግረዋል።

ሰውየውም “እሱን ሰውዬ አላምነውም ስትል አልነበረም እንዴ! እንዴት አድርገህ ነው አንድ ሴት ልጅህን ለማታምነው ሰው የምትድርለት?” ይለዋል። ጋብሮቮያዊው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “አሁንም አላምነውም፣ ደግሞ እንደሚሰርቀኝም አውቃለሁ፡፡ ግን ቢያንስ ቢያንስ የሚሰርቀው ገንዘብ ወደ ልጄ ነው የሚሄደው፡፡” ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ከጠቀስነው አይቀር…ይሄ ‘ፈረንካ’ ያለውን ማሳደድ… አለ አይደል…የኦሎምፒክ ስፖርት ቢሆን ኖሮ ወርቋንም፣ ብሯንም፣ ነሀሷንም እኛው እንሰበስባት ነበር፡፡ አሀ…ያለ ገንዘብ የሚሆን ነገር እኮ እየጠፋ ነው፡፡ በፊት ‘ቮልቮ፣ ቪላ፣ ቪዲዮ…’ አይነት ነገር የባል ‘ክራይቴሪያ’ ነገር ነበር፡፡ አሁን ለውሎውም፣ ለአዳሩም፣ ለትዳሩም ‘ማስተር’ ቁልፉ ‘ፈረንካ’ እየሆነ ነው፡፡ የአገሬ ሰው “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ…” የሚለው ነገር አለ አይደል…ይስተካከልልንማ! አለ አይደል…“ገንዘብ ከሌለህ አልተፈጠርክም ማለት ነው…” ምናምን ነገር ይባልልንማ፡፡ አሀ…ብዙ ቦታ፣ በብዙ ሰዎች አካባቢ… ገንዘብ ከሌላችሁ የማትጨበጡ መንፈስ ነገር ናችኋ! ስሙኝማ… እግረ መንገዴን፣ በዛ ሰሞን በሬድዮ የሰማነው ነገር “ጉድ ነሽ…” አይነት ነገር የሚያሰኝ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ልጆች ላይ ማንን እንደሚያደንቁ በተደረገ ጥናት… ልጆቹ የእነሱ ‘ሂሮ’ ማን ነው ቢሉ ጥሩ ነው…የነጻው ትግል ተደባዳቢ ጆን ሲና! የምር… ይሄ ሊያሳስብ የሚገባ ነው፡፡

እንደው የ‘ፈረንጅ’ ነገር አልሆን ቢል እንኳን ከአእምሮ ሰው ይልቅ ተደባዳቢ ሰው ‘ሂሮ’ የሚያደርግ ትውልድ ሲፈጠር “ኧረ መላ በሉ ዘመድ ወዳጆቼ…” ምናምን ማለት የሚያስፈልግ አይመስላችሁም! እናማ፣ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እነኚህ ልጆች እያደጉ ያሉት ለ‘ፈረንጅ’ እና ‘ፈረንጅ’ ለሆነ ነገር ሁሉ አድናቆት በሚሰጥበት ‘ሶሳይቲ’ ውስጥ ነው፡፡ እናማ…የእስክሪፕቶ ጫፍ ከኮት ኪሱ ብቅ ብላ ያየበትን ሀበሻ ‘ዘቅዝቆ ፈትሾ’… የአንድ ወታደር ስንቅና ትጥቅ አበቃቅቶ መክተት የሚችል ቦርሳ ተሸክሞ የሚገባ ‘ፈረንጅ’ን ግንባሩ መሬት እስኪነካ ሰላምታ ሰጥቶ ከሚያሳልፈው የጥበቃ ሠራተኛ፣ ለ‘ፈረንጅ’ ሲሆን የፈገግታ ፏፏቴውን አፍስሰው፤ ለሀበሻ ልጅ ፊታቸውን ሦስት ጣሳ እንቆቆ የጠጣ እስከሚያስመስሉ ‘ቦሶቻች’ን ድረስ “የፈረንጅ ቡዳ ይብላኝ…” የሚሉት ሁሉ በህጻናቱ አእምሮ ላይ መጥፎ አስተሳሰብ እየፈጠሩ ነው፡፡ ታዲያማ…ይሄ ‘ፈረንጅ’ የማምለክ ነገር የምር በጣም የሚያስገርምና…አለ አይደል…የሚያስከፋ ነገር ነው፡፡ ይሄ ህዝብ እኮ ከእነ ድህነቱ፣ ከእነ ችግሮቹ አንዱ ትልቁ እሴቱ ራሱን ዝቅ አድርጎ አለማሰቡ ነው።

ሰሞኑን አንድ ፈረንጅ የጻፈው መጽሐፍ ሳነብ ምን አየሁ መሰላችሁ… በድሮ ጊዜ የገጠር ሰዎች ‘ፈረንጅ’ በአጠገባቸው ሲያልፍ “መጥፎ ጠረን ይኖረው ይሆናል…” በሚል አፋቸውን በነጠላቸው ይሸብቡ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ነገርዬው ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ ለ‘ፈረንጅ’ እጥፍ ዘርጋ ማለቱ ከእኛ ከተራዎቹ ሰዎች እስከ ‘ሰማይ ስባሪዎቹ’ ድረስ ‘መለያ ቀለም’ ነገር ሆኖ… “ምነው የእኛን ቁጥር ቀንስህ የፈረንጅን ቁጥር አሁን ካለበት ባበዛኸው ኖሮ…” የምንል መአት ነን፡፡ ዓለም የሚያደንቀውን ያድንቅ…የእኛን ልቦናችንን ይመልስልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 8434 times