Saturday, 30 March 2013 13:47

ባህርዳር - በጉባኤው ዋዜማና መክፈቻ ወቅት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ (ከባህርዳር)
Rate this item
(7 votes)

የአማራ ክልል ርእሰ ከተማ ባህርዳር የብአዴንን ጉባኤ አስተናግዳ የአፍታም እፎይታ ሳታገኝ ነበር፤ ዘጠነኛውን የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ለማስተናገድ ደፋ ቀና ማለት የተያያዘችው፡፡ ከአባይ ወንዝ ወዲህ በቻይና ባለሙያዎች የተሰራው አዲሱ የብአዴን አዳራሽ፤ ግንባታው ባይጠናቀቅም የጉባኤውን ተሳታፊዎች ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል፡፡ ከተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የመጡ ጉባኤተኞች እንዲሁም ከአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ከዋዜማው ቀደም ብለው ባህርዳር ውስጥ ከትመዋል፡፡ የከተማዋ ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች የጉባኤውን ተሳታፊዎች ሸክፈው ለመያዝ አቅም አጥሮአቸዋል፡፡ በሼክ መሀመድ አሊ አልአሙዲን ባለቤትነት የሚተዳደረው አቨንቲን ብሉናይል ሆቴል የከፍተኛ ባለስልጣናት ማረፊያ ሆኗል፡፡ከጉባኤው መክፈቻ አንድ ቀን ቀደም ብሎ (በዋዜማው) የጉባኤው ቃል አቀባይ በሆኑት አቶ ሴኮቱሬ፤ በብአዴን ፅ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠን፡፡

አቶ ሴኮቱሬ ከአምስት ደቂቃ ያልበለጠ ጊዜ በወሰደው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፕሮግራሙን አጠቃላይ ይዘትና የፕሮግራሙን ቅደም ተከተል ከገለፁልን በኋላ ቀጥሎ “off the record” የምንነጋገረው ጉዳይ ስላለ መቅረፀ ድምፃችሁን አጥፉ ካሜራችሁንም ዝጉ ብለው አዘዙን፡፡ ትእዛዙ ያልተዋጠላቸው ጥቂት ጋዜጠኞች፤ መቅረፀ ድምፃቸውን ከአቶ ሴኮቱሬ ፊት ቢያነሱም፣ ለማጥፋት ወይንም ቀረፃውን ለማቋረጥ አልፈለጉም፡፡ ጉባኤው፣ በድርጅቱ ብሎም በአገሪቱ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ ጉባኤ ነው በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ሴኮቱሬ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች በጉባኤው ወቅት ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን እየዘረዘሩ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አቀረቡ፡፡ ጋዜጠኞች በዚህ ጉባኤ ላይ እንዲገኙ የተደረገው በድርጅቱ ፈቃደኝነትና ግብዣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ያለ ድርጅቱ ፍቃድና ፍላጐት ያገኛችሁትን መረጃ ሁሉ መዘገብ አትችሉም አሉ፡፡ ግራ የተጋቡ በርካታ ጋዜጠኞች ጉዳዩ እንዲብራራላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አቶ ሴኮቱሬ አንድ ሲሉ ጀመሩ፡፡ የጉባኤውን ውይይቶች በድምፅም ሆነ በምስል መቅረፅ አይቻልም፡፡

የጉባኤውን ሙሉ ሂደት መቅረፅ የሚችለው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ብቻ ነው፡፡ ይህም ዋልታ ከድርጅቱ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ነው፡፡ የጉባኤው መልእክትና አቋም የሚተላለፈው በቃል አቀባዩ በኩል ነው፡፡ ቃል አቀባዩ በየጉባኤው እለት ምሽት ላይ የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ነው እንደመረጃ ሆኖ ዘገባ ሊቀርብለት የሚችለው፡፡ ባለስልጣናትን እየተከታተሉ በሻይ እረፍትና በየስፍራው ፎቶግራፍ ማንሳት አይቻልም፡፡ የፎቶ ጋዜጠኞች በጉባኤው አዳራሽ ተገኝተው ለጥቂት ደቂቃዎች ባለስልጣናቱንም ሆነ ተሰብሳቢውን ፎቶግራፍ ማንሳት ይችላሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ቢፈጠርና ጉዳት ቢደርስ እኛ ኃላፊነት የለብንም፡፡ ኢህአዴግ ጋባዥ ነው እንጂ፣ ተከላካይ አይደለም፡፡ ጉባኤው አንዳንዴ በዝግ ሊካሄድ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ማንኛውም የሚዲያ ባለሙያ ወደ አዳራሹ መግባት አይፈቀድለትም፡፡ የጉባኤውን ሂደት መቅረፅ ወይንም በሰነድነት መያዝ አይቻልም፡፡ አይደለም ጋዜጠኛው ጉባኤተኛውም ሙሉ ሰነድ መያዝ አይችልም፡፡

የማሳሰቢያው ብዛት፣ በበርካታዎቹ የሚዲያ ባለሙያዎች ዘንድ መደናገጥን ፈጠረ፡፡ ታዲያ ጉባኤውን በአግባቡ መከታተልና መዘገብ ካልቻልን እዚህ ድረስ መምጣታችን ለምን አስፈለገ? የብዙዎች ጥያቄ ነበር፡፡ ጋዜጠኛው ወደ ጉባኤው አዳራሽ ለመግባት የይለፍ ካርድ ያስፈልገው ነበር፤ በጉባኤው መክፈቻ እለት ካርዱ የደረሳቸው ጋዜጠኞቹ ወደ አዳራሽ ገብተው በተመደበላቸው ስፍራ ተቀመጡ፡፡ በቻይና ባለሙያዎች የተገነባው የተንጣለለ አዳራሽ ከ3ሺ በላይ እንግዶችን ያስተናግዳል፡፡ ጉባኤተኞቹን በስርዓት ስፍራ የሚያስይዝ ስላልነበረ ጉባኤተኛው በአዳራሹ ውስጥ የፈለገበት ስፍራ ላይ መቀመጥ ጀመረ፡፡ የድርጅቱ ታላላቅ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባስልጣናቱ ገና ወደ አዳራሹ ባይገቡም አዳራሹ እየሞላ ሄደ፡፡ ከፊት ካሉት ጥቁት ወንበሮች ውጪ አብዛኛዎቹ ስፍራዎች በጉባኤተኛው ተይዘዋል፡፡ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና የድርጅቱ መሪዎች ከስፍራው ደረሱ፡፡ ከፊት ለፊት በቂ ክፍት ወንበር የለም፡፡ የአቀማመጥ ስርአቱ መስተካከል እንደሚገባው የገለፁ የጉባኤው አጋፋሪዎች፤ የፊተኞቹ ወንበሮች ለአመራር አካላት የተያዙ ቦታዎች ስለሆኑ እንዲለቀቁ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተናገሩ፡፡ ግን አፋጣኝ ምላሽ አልተገኘም፡፡ ማሳሰቢያው ሲደጋገም ጥቂቶች ስፍራውን እየለቀቁ ወደ ኋለኛው መቀመጫ ሄዱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አዳራሹ ሲገቡ የነበረው ሁኔታም ለብዙዎች ግርምትን ፈጥሯል፤ የፕሮቶኮል ጉዳይ እምብዛም አይስተዋልበትም፡፡ ምናልባት የኢህአዴግ ባህል ስለሆነ ይሆን? ለማንኛውም፣ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጉባኤው፤ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ከየአገራቱ የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ባደረጉት አጠር ያለ ንግግር ተጀምሮ፤ የጉባኤው በይፋ መከፈት በጠ/ሚር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተበሰረ፡፡ በዚሁ የጉባኤ መክፈቻ እለት በመአዛ ኃይለማርያም ተደርሶ የተዘጋጀ “አሻራ” የሚል ሙዚቃዊ ድራማ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል መድረኩን ተቆጣጥሮታል፡፡ የትጥቅ ትግሉን አጀማመርና ኢህአዴግ ያሳፈውን ውጣ ውረድ የሚያሳይ ድራማ ነበር፡፡

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን (እሁድ ምሽት) የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ህዝብ ለጉባኤተኞቹ ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ በተመሳሳይ መልኩ የፕሮቶኮል ጉዳይ ተዘንግቶ የግብዣው ታዳሚ በሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወንበራቸው ከመነሳታቸው በፊት ከግብዣው ስፍራ ሲሄድ ተስተውሏል፡፡ በጉባኤው መጠናቀቂያ እለትም ለጉባኤው ተሳታፊዎች የተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት የባህላዊ ጭፈራው ምሽቱን በደስታ አሳልፈውታል፡፡ ባህርዳርም እንግዶቿን እንደ አቀባበሏ ሸኝታ እፎይ ብላለች፡፡ እናም በዋዜማው እንደተነገረን ማስጠንቀቂያ ሳይሆን፣ ጋዜጠኞች አስፈሪ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል የሴኪዩሪቲ (የደህንነት) ችግር ሳያጋጥመን ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

Read 5020 times