Print this page
Saturday, 30 March 2013 13:32

ኢህአዴግ፤ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና የህዝብ እሮሮ አሳስቦታል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

“አክራሪነትን ለመከላከል በቅድሚያ ውስጣችንን እናጥራ” መተካካቱ በሚፈለገው ሁኔታና መጠን መሄድ አልቻለም፤ “ነባር መሪዎች እስኪጃጁበት ድረስ ወንበሩን ይዘው መቀመጥ የለባቸውም” “ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ትልቁ ፈተናችን የእርስ በርስ መተማመናችንን ማጠናከር ነበር፤ ተተኪዎች ብቃት ሊኖራቸው ይገባል” የመንግስት የሚዲያ ተቋማት ተተችተዋል፤ “የሚዲያ ሥራዎችን የምንመራበት ጥርት ያለ አሰተሳሰብ የለንም፡፡” የኢኮኖሚ እድገት እየቀነሰ ነው፡፡ “ጉባኤ ላይ ሪፖርቶችን ቀባብቶ የማቅረብ ሁኔታ ይታያል” በባህርዳር ማክሰኞ እለት በተጠናቀቀው የኢህአዴግ ጉባኤ፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦትን በሚመለከት ከህዝብ የሚቀርብ እሮሮ አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ የኢህአዴግ መሪዎች ድክመት ለዚህ ችግር መንስኤ ስለሆነ ይታረም ተብሎ ተወስኗል፡፡

የሃይማኖት አክራሪነትን በተመለከተ ከባባድ ጥፋቶችን እንደሚያስከትል በጉባኤው ተጠቅሶ በጉባኤው ሰፊ ቦታ የተሰጠው ሲሆን፤ ኢህአዴግ ውስጡን ማጥራት አለበት ተብሏል፡፡ ነባር መሪዎችን በአዳዲስ ለመተካት ባለፉት ሦስት አመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የመተካካት ሂደት ከአዲስ አመራሮች ብቃት ጋር ተያይዞ ውይይት ከመካሄዱም በተጨማሪ፣ የመንግስት ሚዲያ አሰራር የመንግስትን ድክመቶች የማያጋልጥና ለእርምት አስተዋጽኦ የሌለው እንደሆነ በማመልከት ትችት ቀርቧል፡፡ “Building Democratic Developmental State Prospect and Challenges” በሚል ርእስ አቶ በረከት ስምኦን ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ፤ የድርጅቱ አባላትና የውጭ አገራት ተጋባዥ እንግዶች ተወያይተውበታል፡፡ በኢኮኖሚ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በመተካካት ሂደት ላይ የተካሄዱት ውይይቶች ጠንካራ ትችቶች የተሰነዘሩባቸው ናቸው፡፡ የግብርና ምርት የሚፈለገውን ያህል እድገት እያሳየ አለመሆኑንና የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት አቶ በረከት ስምኦን፤ ይህም ከአመራር ብቃትና ድክመት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ መሆኑን በጥልቀት በመፈተሽ በአብዛኛው ለመድረክ የሚቀርቡ ሪፖርቶች መድረኩን ለማስደሰት ሲባል የሚቀርቡ እንደሚመስሉ ጠቅሰው፤ ስለሁኔታው ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት አርሶ አደሩ ያለበትን ችግር ወረድ ብሎ ማየት ተገቢ ይመስለኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ለአነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ መገለፁ የሚታወስ ሲሆን፤ እንደ ግብርናው ሁሉ በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍም በተመሳሳይ ሁኔታ እድገቱ እያነሰ ከመምጣቱ ባሻገር፤ በዘርፉ ከተሰማሩት ሰዎች መካከል ውጤታማ ለመሆን የበቁት የታሰቡትን ያህል አይደሉም ተብሏል፡፡ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በጣም አሳሳቢ ቢሆንም በመልካም አስተዳደር በኩል ደግሞ ከዚህም በጣም ያነሰ ውጤት እንደተመዘገበ የጠቀሱት አቶ አዲሱ ለገሰ፤ በዚህም ረገድ ተጠያቂው የድርጅቱ አመራር ነው ብለዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ጊዜ የማይሰጥ ችግር መሆኑን ጠቅሰው የተናገሩት ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የህዝቡ እሮሮ (የመረረ ጥያቄ) ምላሽ ማግኘት እንዳለበትና ቸል ማለት አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሌላው ርዕስ የመተካካቱ ጉዳይ ሲሆን፤ የድርጅቱ ከፍተኛ የአመራር አባላትም ጠንከር ያለ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

“ከአቶ መለስ መስዋእትነት በኋላ ትልቁ ፈተናችን፣ የእርስ በርስ መተማመናችንን ማጠናከር ነበር” ያሉት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ስዩም መስፍን፤ የመተካካት ሂደቱን የሚያረጋግጥ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ከመካከለኛው የአመራር ደረጃ ወደላይኛው የአመራር ደረጃ ብቃት ያለው የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ ችግሮች እንዳሉ አቶ ስዩም ተናግረዋል፡፡ በመተካካቱ ሂደት ላይ ሰፊ አሰተያየት የሰጡት አቶ በረከት፤ ነባሮቹ መሪዎች በጣም ከመድከማቸው በፊት ገለል ማለት ይኖርባቸዋል፤ በተለይ በአመራር የፊት መስመር ላይ የሚገኙ መሪዎች እስኪጃጁበት ድረስ ቦታውንና ወንበሩን ይዘው መቀመጥ የለባቸውም” ብለዋል - ነባር መሪዎች፡፡ ሥልጣን በጊዜ ለወጣቱ ትውልድ ማስረከብ አለባቸው ያሉት አቶ በረከት፤ ወጣቱ አመራር መስመሩን ተረክቦ በታማኝነት መቀጠል ይኖርበታል፤ ነባሩም ከፊት መስመር ገለል ብሎ ከጐን ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የመተካካቱ ሂደት እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥልና እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

በቅርቡ አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች በየራሳቸው ግምገማ አካሂደው የመተካካት እቅዶችን እንደተገበሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ እንደየድርጅቶቹ ባህርያት ሂደቱ ሊለያይ እንደሚችልና በጋራ የሁሉንም ለመገምገም እቅድ እንደተያዘ ተገልጿል፡፡ ድርጅቶቹ አጋር እየተባሉ የሚቀጥሉት ጉዳይ እስከመቼ እንደሚቀጥል ግልፅ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ጐልተው ከወጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ በሆነው የሃይማኖት አክራሪነት ዙሪያ ውይይት ያካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ፤ የሃይማኖት አክራሪነት በርካታ ጥፋቶችን እንደሚያስከትል ተገልጿል - በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ቡድኖች በሦስት መሰረታዊ ጥፋቶችን ለመፈፀም እንደሚንቀሳቀሱ በመዘርዘር አክራሪ ቡድኖች፣ ሃይማኖታዊ መንግሥትን ለማስፈን ይሞክራሉ፤ የሌሎችን ሰዎች ሃይማኖታዊ ነፃነት ይጥሳሉ፤ አሸባሪነትን ያስፋፋሉ በማለት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ተናግረዋል፡፡

በውስጣችን ያሉ አንዳንድ የአመራር አካላት ለሃይማኖት አክራሪነት ሽፋን በመስጠት የድርጅቱን መሰረታዊና ዝቅተኛ መስፈርት ንደዋል” ያሉት ዶ/ር ሽፈራው፤ “ዋናው ትግላችን መቀጣጠል ያለበት በራሳችን ውስጥ ነው፡፡ የአመራሮቻችንን ጥራትና ታማኝነት በሚገባ መፈተሽ ይገባዋል” ብለዋል፡፡ ጉባኤው በሚዲያ ተቋማት ዙሪያ በተለይም በመንግስት ሚዲያ ላይ ባካሄደው ውይይት፣ ሚዲያው ተግባሩንና ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም የሚል ሃሳብ ተስተጋብቷል፡፡ “የሚዲያ ስራዎቻችንን የምንመራበት ጥርት ያለ አስተሳሰብ የለንም” ያሉት አቶ በረከት፤ የአገራችን የሚዲያ ብቃትም ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ ሚዲያው ተግባሩና ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ያሉት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ህላዌ ዮሴፍ፤ በመንግሥት እጅ የተያዙት ሚዲያዎች በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጡና እርምት እንዲወሰድባቸው በማድረጉ ረገድ የራሳቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ሚዲያዎች ተግባር የመንግስትን መልካም ጐን መዘገብና ማሰራጨት ብቻ ነው ወይስ የህዝብን ጥያቄ መዘገብም ይኖርባቸዋል ሲሉ የጠየቁት አቶ ህላዌ፤ የመንግስት ሚዲያዎች የህዝብ ንብረት ናቸው ብለዋል፡፡ ለአራት ቀናት በባህርዳር ሲካሄድ በቆየው ጉባኤ፤ ከአራቱ የኢህአዴግ ድርድቶች ዘጠኝ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አባላት የመረጡ ሲሆን፤ ለሁለት አመት ተኩል ድርጅቱን በሊ/መንበርነት እንዲመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም በምክትል ሊቀመንበርነት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተመርጠዋል፡፡ በጉባኤው ላይ የኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከአስራ ሦስት አገራት የተጋበዙ የፓርቲ አመራሮች በእንግድነት ተገኝተዋል፡፡

Read 5290 times Last modified on Saturday, 30 March 2013 14:24