Monday, 25 March 2013 11:17

ደቀ መዛሙርቱ ኮሌጁ ‹‹የትምህርት ሳይሆን የንግድ ማእከል ኾኗል›› አሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በመንፈሳዊ ኮሌጁ ትምህርት ተቋርጧል፤ ተማሪዎቹም ምግብ መመገብ አቁመዋል

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት÷ ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለደቀ መዛሙርቱ መብት መከበር ከመቆም ይልቅ ገንዘብ ለመሰብሰብና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣሉ ያሏቸው ሁለት የአስተዳደር ሓላፊዎች ከሥልጣን እንዲወገዱ ያቀረቡት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ ትምህርት ማቆማቸውንና ምግብ ከመብላት መከልከላቸውን አስታወቁ፡፡ በጥያቄያቸው ያመለከቷቸው በርካታ የኮሌጁ ችግሮች ላለፉት ዐሥራ አራት ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ መኾናቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ÷ የመምህራኑ አቅም ማነስና የትምህርት ጥራት መውደቅ፣ የምግብ መበከልና የአስተዳደሩ በጥቅም ትስስርና በሙስና መዘፈቅ ሊታገሡት ከሚችሉት በላይ በመኾኑ ፓትርያሪኩና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ይኹንና ፓትርያሪኩን በአካል አግኝቶ ለማነጋገር አልያም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሓላፊዎችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ከኮሌጁ ሓላፊዎች ጋራ በጥቅም ተሳስረዋል ያሏቸው አካላት እንደፈጠሩት በሚያምኑት መሰናክል አለመሳካቱን አስታውቀዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከኮሌጁ አስተዳደር ጋራ የገቡበት ውዝግብ ከተቀሰቀሰ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲኾን ትምህርት መቋረጡም ተዘግቧል፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጸው አስተዳደሩ÷ ደቀ መዛሙርቱ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ያቋረጡትን ትምህርት እስከ ረቡዕ ቀትር ድረስ በአስቸኳይ እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡ ደቀ መዛሙርት ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱ ከኾነ ደግሞ በዚያው ዕለት ንብረትና መታወቂያ እያስረከቡ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል፡፡

‹‹ለሁለት ሰዎች ሲባል ሁለት መቶ ተማሪ አይባረርም፤ ብቃት የሌላቸውና ኮሌጁን እንደ ርስት በዘመድ ይዘው የጥቅም ማግበስበሻ ያደረጉት አካዳሚክ ዲኑና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ይነሡልን፤›› የሚሉት ደቀ መዛሙርቱ በበኩላቸው÷ ችግሮቻቸው በመሠረቱ ደረጃ በደረጃ መፈታት እንደሚገባቸው ቢቀበሉም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱት ግን የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ሲነሡ ብቻ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚያስረዱት÷ በተጠቀሱት የኮሌጁ አስተዳደር ሓላፊዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ምእመኑ ‹‹የገንዘብ ምንጭ ብቻ ኾኗል፤ አገልጋይ ጠፍቷል፡፡›› ደቀ መዛሙርቱ÷ ኮሌጁን እንደ ግለሰብ ቤትና እንደ ዘመድ ርስት ይቆጥራሉ በሚሏቸው ጥቂት ሓላፊዎች መካከል አለ የሚሉት የጥቅም ትስስር በትምህርት ጥራትና በመብታቸው ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ የሚገልጹት ‹‹ኮሌጁ የትምህርት ሳይሆን የንግድ ማእከል ኾኗል፤›› በሚል ነው፡፡

ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አባላት እንዳስረዱት÷ የተለያዩ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች ለኮሌጁ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ከእነርሱም በላይ በዋናነት ሁሉም አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው አምስት ከመቶ ፈሰስ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ ሕንጻውን በማከራየትና የመማሪያ ክፍሎቹን ለተለያዩ ኮሌጆች በመፍቀድ ከፍተኛ ገቢ ይሰበስባል፡፡ ይኹንና ደቀ መዛሙርቱ በሜዳ ላይ የሚማሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ በየመርሐ ግብሩ ከተዘረጉት ኮርሶች ብዛት ጋራ የሚመጣጠኑ መምህራንን መቅጠር እየተቻለ የመምህራን ምደባው አራትና አምስት ኮርሶችን በሚይዙ ጥቂት መምህራን መካከል የተወሰነ ነው፡፡ የመምህራኑ ዕውቀት ‹‹ሙሉዕ በኩለሄ›› እስካልኾነና መምህራኑ ከተጨማሪ ሓላፊነቶች ጋራ ከሚያጋጥማቸው የዝግጅት ማነስ የተነሣ ምደባው የትምህርት ጥራቱን የሚጎዳው ይኾናል፡፡ ይህም በትምህርት አሰጣጡና በምዘናው ላይ በሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ የተነሣ አቤቱታ የሚያቀርቡ ደቀ መዛሙርትን የሚያሸማቅቁ፣ ከዚህም አልፎ በመማሪያ ክፍሎችና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሳይቀር የሚደበድቡ መምህራን መኖራቸውን ነው ደቀ መዛሙርቱ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት፡፡

በተማሪዎች አቀባበል ወቅት ኮሌጁ የሙሉ ጤንነት ምርመራ እንደሚያደርግላቸው የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ በሂደት ግን በካፊቴሪያው ጥንቃቄ የጎደለው የምግብ ዝግጅት የተነሣ ጤንነታቸው የተጎዳና በቂ ሕክምና የማያገኙ ደቀ መዛሙርት ቁጥር ጥቂት እንዳልኾነ ደቀ መዛሙርቱ ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡ በቤተ መጻሕፍት አገልግሎትና በመረጃ ቴክኖሎጂ ረገድ የሚሰጠው አገልግሎትም አንፋውን ኮሌጅ የሚመጠን እንዳልኾነ ነው ደቀ መዛሙርቱ የሚናገሩት፡፡ ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተቀሩት ሁለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋራ ሲነጻጸር አንጋፋ ቢኾንም ዛሬ ከአስተዳደሩ ድክመት የተነሣ የሚገኝበት ደረጃ ከዘመናዊነት የራቀ ነው፤›› ይላሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ይህ የኮሌጁ ኹኔታ የሚያሳስባቸውና በጉዳዩ ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሚመክሩ መምህራን ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸውና ስለላ እንደሚካሄድባው ተመልክቷል፡፡

በኮሌጁ ሰፍኗል የሚሉትን ሙስናና የአሠራር ብልሽት የሚቃወሙት የአገርንና የሕዝብን ሀብት ከማዳን አንጻርም በመኾኑ መንግሥትም ሊያግዘን ይገባል፤ ‹‹ችግራችንን የማይፈቱልን ከኾነ ችግር ባይፈጥሩብን›› በማለትም በግል እየጠሩ ያስፈራሩናል፤ ይዝቱብናል ያሏቸውን የፖሊስ አባላት ይጠይቃሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጻፉትን ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ በግልባጭ ማሳወቃቸውን የገለጹ ሲኾን ለጥያቄዎቻቸው በቂ ምላሽ እስኪያስገኙ ድረስ ውርጩን፣ ረኀቡንና እንግልቱን ተቋቁመው ለመቆየት መወሰናቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ላይ የኮሌጁን ሓላፊዎች አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንን በስልክ ለማነጋገር የሞከረን ቢኾንም ዲኑ በአካል ካልቀረባችኹ በስልክ ምላሽ አልሰጥም ብለውናል፡፡ የዝግጅት ክፍሉ በነበረበት የጊዜ እጥረት ዲኑን በአካል አግኝቶ ሊያነጋግራቸው አልቻለም፡፡

Read 3663 times