Saturday, 23 March 2013 14:32

ኮፍያው

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ነገሩ የተጀመረው በኮፍያ ነው - ለምሳ ቤት መጥቶ ሲወጣ፣ በሩ አካባቢ ባገኘው ኮፍያ - ጥልፍልፍ የቴኒስ መጫወቻ (የራኬት) ምስል በላዩ ላይ ያለበት ኮፍያ፡፡ ኮፍያውን አንስቶ መኪናው ውስጥ ከተተውና ወጣ፡፡ ወደ ቢሮው ከገባ በኋላ የኮፍያውን ነገር ሊረሳው አልቻለም፡፡ “የማን ኮፍያ ነው?” የሚል ጥያቄ በአእምሮው ውስጥ አንቃጨለ፡፡ “አንድ ወንድ ጥሎት የሄደው ነው” … የሚል ምላሽ ከአእምሮው ስርቻ መልሶ አስተጋባ፡፡ ሀሳቡን ለማባረር ራሱን በሥራ ለመጥመድ ሞከረና አቃተው፡፡ ሥራ መሥራት ሲያቅተው ወደ ሚስቱ ደወለ፡፡ ሚስቱ፣ ቤት ነው የምትውለው፡፡ ከተጋቡ ገና አራት ወራቸው ነው፡፡ ስሟ ሶፊ ቢሆንም “ምጥን!” ይላታል፤ ሲያቆላምጣት - በዚህ አጠራሩ እሷ ባትስማማም፡፡ ምጥን ያለች ናት፤ አይኗ የተመጠነ፣ እጆቿ የተመጠኑ ውበቷ የተመጠነ፡፡ ትርፍ የሚባል ነገር የላትም፡፡ ጥርሷ ያምራል ግን ትንሽ አፍንጫዋ … የሚሏት አይነት አይደለችም፡፡ ሁሉ ነገሯ ያምራል፡፡

ስልኩን አነሳች፡፡ ትንሽ አወሩ፡፡ “ዛሬ፣ ቤት ማን መጥቶ ነበር?” አላት ባለቤቷ አበራ - እንደዘበት፡፡ ለአፍታ ዝም አለች፡፡ “ዛሬ … ዛሬ … ማንም አልመጣም … እኔ ምልህ …” ብላ ወደ ሌላ ወሬ አመራች፡፡ “ኮፍያው የማን ነው?” ሊላት ፈለገ፤ ግን ቃላቱ ከአንደበቱ ሊወጡለት አልቻሉም፡፡ እየዋሸችኝ ነው? ለምን ትዋሸኛለች? ሰውነቱን አንዳች ነገር ሲወረው ተሰማው፡፡ ትንሽ አውርተው ስልኩ ተዘጋ፡፡ ቢሮው ውስጥ እንዳለ ፈዞ ቆመ፡፡ እሱና እሷ ብቻ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ አንድ ኮፍያ እንዴት ሊገኝ ይችላል? ኮፍያ መቼም እግር የለው፣ የሰው ግቢ ውስጥ ዘሎ የሚገባው! የአንድ ሰው … የአንድ ወንድ ጭንቅላት ላይ ሆኖ መግባት አለበት ወደ ግቢው፡፡ ያንን ኮፍያ ያደረገው ጭንቅላት የማነው? የብዙ ሰዎች ምክር በአእምሮው መጣ፡፡

ለምን አታገባም? በልጅነትህ እናትህ አንተን እና አባትህ ጥላችሁ ስለሔደች ነው? እናትህ ምን አይነት ጨካኝ ብትሆን ነው በገዛ ጓደኛው አባትህን ከድታው የሄደችው? አባትህ ግን ምን አይነት ሞኝ ቢሆን ነው? እድሜ ዘመኑን ሲሰማው የነበረ ንግግር፣ ምክር እና ጥያቄ፡፡ በመጨረሻ ሶፊን ሲያገኝ የሴት ጥላቻው እንደጉም በኖ፣ ትዳር መያዙን የሰሙ ሁሉ ማመን አልቻሉም ነበር፡፡ “ምን አስነክታው ነው?!” ብለው ነበር ያዳነቁት፡፡ ከሶፊ ጋር በትዳር ሲኖሩ ለጥርጣሬ የሚያበቃ አንዳችም ድርጊት አይቶባት አያውቅም፡፡ ሁሌም ግን እንደሰለላት ነው፡፡ … ሁሌም አይኖቹ ለጥርጣሬ የሚሆን ነገር ለማግኘት በንቃት ይቃብዛሉ፡፡ ሶፊ ላይ ግን ምንም ነገር አግኝቶ አያውቅም - ኮፍያውን ግቢው ውስጥ ወድቆ እስኪያገኝ ድረስ፡፡ ኮፍያውን ካገኘ በኋላ ነው ስጋት እንደደራሽ ያዋከበው - የፈራው ደርሶ በነፍሰ ስጋው እየተጫወተች እንዳይሆን ሰጋ፡፡ ምን ነበር አባቱ የሚለው? “አጥንት ቢሰበር ወጌሻ ይጠግነዋል፡፡ የተሰበረን ልብ ግን ከሞት በቀር የሚያድነው የለም! በተለይ በሴት የተሰበረ ልብ …” ነበር የሚለው፡፡

ልቡ በሴት እንዳይሰበር ስንት አመት ነበር የተጠነቀቀው? እናቱ ከውሽማዋ ጋር ስትሔድ የአባቱ ብቻ ሳይሆን የእሱም ልብ ነበር የታመመው፡፡ ስቃዩን ያውቀዋል! እና ሶፊ … ከቢሮው ተስፈንጥሮ ወጣና ሲበር ወደ መኪናው ሔዶ ኮፍያውን አወጣው፡፡ የማን ኮፍያ ነው!? ወደ አፍንጫው አስጠጋው፡፡ የወዝ ሽታ አፍንጫውን ሰነፈጠው፡፡ አሽቀንጥሮ ከጋቢናው ወንበር ላይ ጣለው፡፡ “ጎረምሳ ይሆናል፣ ወይ ደግሞ መላጣ! መላጣ ነው በዚህ የሙቀት ወር ኮፍያ የሚያደርገው - መላጣውን ለመሸፈን፡፡ ለዚህ ነው የኮፍያው አስቀያሚ የወዝ ሽታ ያልጠፋው፡፡ ከኔ ግን በምን አባቱ በልጦባት ነው?”… የኮፍያውን ባለቤት አሰበው፡፡ መላጣ … ምናልባትም ቴኒስ ተጫዋች፡፡ “ወይኔ!” ብሎ የመኪናውን ኮፈን በቡጢ ነረተው፡፡

“ቀደም ብዬ ለምሳ ቤት በመሔዴ ደርሼባቸው ያ መላጣ ተደናግጦ ይሆናል ኮፍያውን ጥሎ የፈረጠጠው፡፡ ይኼ መላጣ!” አለ በንዴት፡፡ “ግን ለምን መላጣ መረጠች? ስንት ባለጎፈሬ ሞልቶላት! ምናልባትም እኮ መላጣነቱን ይሆናል የወደደችው!” በሆዱ ወፈ ሰማይ ጥያቄ ፈለፈለ፡፡ ለሶስት ቀን እያደባ፣ ሰአት እየቀያየረ ባለኮፍያውን በአሳቻ ሰአት ሊያጠምደው ሞከረ፤ አልቻለም! ሌሊት እየተነሳ ከቤቱ ጓሮ ዞሮ አካባቢውን መረመረ፡፡ መላጣው ሰውዬ አጥር እየዘለለ ሊሆን ይችላል የሚገባው፡፡ የአጥር ጥግ ሁሉ አሰሰ - አንድም ዱካ የለም፡፡ “መላጣ ሰው እንዴት እንደምጠላ!” … ሰው መሰላችሁ!?” ይል ጀመር ለጓደኞቹ፡፡ ጓደኞቹ የጋራ አለቃቸውን በሾርኒ እያማው ስለሚመስላቸው ይስቃሉ፡፡ አለቃቸው መላጣ ነው፡፡ “ከአስር መላጣ አንድ ሾጣጣ!” አለ አንድ ቀን አፉ እንዳመጣለት፡፡ መላጣና ሾጣጣ ምን እንደሚያገናኛቸው ጓደኞቹ አልጠየቁትም - ዝም ብለው ሳቁ የጋራ አለቃቸውን እያሰቡ፡፡

በነጋታው አለቃው ጉዳዩን ሰምቶ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠው፡፡ መላጦችን የሚጠላበት አንድ ተጨማሪ ምክንያት አገኘ፡፡ ከሶስት ቀን በኋላ ሚስቱ በእንቅልፍ ልቧ ስትዘባርቅ ሊሰማት ወስኖ ለተከታታይ ሁለት ቀናት አጠገቧ ተገትሮ አደረ፡፡ በሁለተኛው ቀን አጠገቧ እንደቆመ ነቃች፡፡ “ምነው!” አለችው በእጁ የያዘውን አውራ ጣቷን እያየች፡፡ ደንግጦ ለቀቃት፡፡ “አውራ ጣቱን የተያዘ ሰው፣ ሲያዝ ቀን የሰራው ይዘከዝካል” ብለው ሰዎች እንደመከሩት አልነገራትም፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በአምስተኛው ቀን፡ ከአምስት ቀን በኋላ ለምሳ መጥቶ ማዕድ ቀርቦ እየበሉ ሳለ ጥያቄ አነሳላት፡፡ “ስለ መላጣ ሰው ምን አስተያየት አለሽ?” አላት እንደዘበት፡፡ ጥያቄው ግራ ያጋባት ይመስል አይኗን እያስለመለመች አየችው፡፡ “ስለመላጣ ነው ስለሰላጣ?” … ጠየቀችው ለምሳ የቀረበውን ሰላጣ እያየች፡፡ “ስለ መ.ላ.ጣ?... ማለቴ እኔ አሁን መላጣ ሰዎችን እጠላለሁ…” አላት ሳቀች፡፡ “እኔ ደሞ መላጣ ሰው እወዳለሁ! አባቴ እኮ መላጣ ነበር፡፡ አንተም ቶሎ ብትመለጥ ደስ ይለኛል፡፡ የመላጣው ሰውዬ ባለቤት ብባል ደስ ይለኛል … ኸኸኸኸኸኸኸኸኸኸኸ” አስረዝማ ሳቀች ሶፊ፡፡ “እና አባትሽን እንዲያስታውስልሽ ነው መላጣ የጠበስሽው?” በሆዱ አጎረምርሞ ዝም አለ፡፡ ያ መላጣ እዚሁ ሰፈር ውስጥ ይሆናል እኮ የሚኖረው! ጎረቤቶቹን አሰባቸው፡፡ መላጣ ከመካከላቸው አለ እንዴ? ከቤታቸው ፊት ለፊት ያሉትን ሰውዬ አሰባቸው፡፡ እሳተ ጎመራ እንደቦደሰው ተራራ፣ መሀል አናታቸው ላይ ብቻ ነው ጸጉር የሌለው፡፡

እሳቸው ደሞ ኮፍያ አያደርጉም! ሌሎቹ ጎረቤቶቹ ደሞ አርቴፊሻል ፀጉር ካልተጠቀሙ በስተቀር ከመከም ጎፈሬ ናቸው፡፡ ቴኒስ የሚጫወት ከመካከላቸው አሰበ፤ ማንም ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ጎረቤቶቹ ከሜዳ ቴኒስ ይልቅ ለፈረስ ጉግስ የቀረቡ ናቸው፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በስድስተኛው ቀን፡ ፀጉር ቤት ሔዶ “አንድ ዘመድ ሞቶብኛል!” ብሎ ፀጉሩን ተላጨ፡፡ መላጣ ሆኖ የዛን ቀን ወደቤት ቢገባም ሚስቱ ሶፊ ግን የተለየ ስሜት አልሰጣትም፡፡ “እሷ የምትወደው የተፈጥሮውን ራሰ በራ ይሆናል!” ብሎ ተናዶ ራቱን ሳይበላ ተኛ፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በሰባተኛው ቀን፡ ጓደኛውን ማትያስን ደውሎ ጠራው፡፡ ከሶፊ ጋር ሲጋቡ አንደኛ ሚዜው ነበር፡፡ ራሰ በራ ባይሆንም በቅርቡ ራሰ በረሀ የመሆን እድል አለው ሲል አሰበ፡፡ ራሰ በራ በሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን በእጩ ራሰ-በራዎች መቅናት ጀምሯል፡፡ “ማቲያስ እንቢ የማትለኝ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ!” ብሎ እግሩ ስር ወደቀ፡፡

ማቲያስን በግድ እሺ ካሰኘ በኋላ ከእግሩ ስር ተነሳ፡፡ “ሚስቴን ላምናት አልቻልኩም፡፡ በኔ ላይ የደረበችብኝ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍንጭ አግኝቻለሁ፡፡ ሰውዬው መላጣ ይመስለኛል…” ብሎ ስለኮፍያው ነገረው፡፡ “እና አንተ ሌላ ፍላጐት እንዳለው ሰው ሆነህ ቅረባት፡፡ ማለቴ… በቃ ልታወጣት እንደምትፈልግ…” አለው ማትያስን በመለማመጥ፡፡ ማትያስ በንዴት ጥሎት ሄደ! ኮፍያውን ባገኘ በስምንተኛው ቀን፡ ማትያስን አፈላልጐ አገኘው፡፡ እንባ አውጥቶ ለመነው፡፡ “የአባቴን ቁስል እያወክ!” በግድ…በግድ አሳመነው፡፡ እቅድ ነደፉ፡፡ እሱ ለመስክ ሥራ እወጣለሁ ብሎ ሊሄድ፤ ማትያስ ደሞ የእሱን መውጣት ተከትሎ እሷን ሊፈታተን፡፡

ኮፍያውን ባገኘ በሃያኛው ቀን፡ ማትያስ “ዝም ብለህ ነው! ሚስትህ ንፁህ ናት! ይኸው ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ እቤታችሁ እያመሸሁ ተፈታተንኳት፡፡ እሷ ግን እንዴት ክብሯን የምትጠብቅ መሰለችህ?” አበራ፤ “አይምሰልህ ሴቶችን አንተ ስለማታውቃቸው ነው፡፡ ውጪ ራት ጋብዛት፡፡ ለኔ እንዳትነግረኝ አደራ ብለህ ንገራት!” ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ስድስተኛው ቀን፡ ሶፊ ስልክ ደውላ “አቤ…ቆየህ እኮ በጣም… ዛሬ ጓደኛህ ማትያስ ራት እንብላ አለኝ፡፡ እኔ ግን ደስ አላለኝም፡፡ አበራ ልቡ እየመታ “ሶፊ ደሞ ምን ማለትሽ ነው? ማትያስ ማለት እኔ ማለት ነው እያልኩሽ፡፡ እራት በልታችሁ መመለስ ነው፡፡

ምን ችግር አለው?…” ነዘነዛት፡፡ ተስማማች፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ሰባተኛው ቀን፡ ማትያስ፣ “አበራ ሚስትህ በጣም ታማኝ ናት! አንተ በሰጠኸኝ ገንዘብ እራት ጋብዣት እስከ ስምንት ሰአት ድረስ አብረን አመሸን፡፡ ግን… እኔንጃ በህይወቷ ሙሉ እንዳንተ የምትወደው ሰው እንደሌለ አረጋግጫሁ!” አበራ ንድድ አለው፡፡ በቃ የሴቶችን ልብ ማግኘት ከባድ ነው ማለት ነው? አባቱም እናቱን ታማኝ ናት ብሎ በደመደመበት ሰአት ነበር ጥላው የጠፋችው፡፡ አእምሮው የእናቱን ድርጊት እንደፊልም ማጠንጠን ጀመረ፡፡ ሶፊማ በፍፁም ልታታልለኝ አትችልም! “እና ካሁን በኋላ ተልእኮዬን ጨርሻለሁ?” አለ ማትያስ፡፡ “አንድ የመጨረሻ እድል ማቲ…” ለመነው ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ስምንተኛው ቀን፡ ማትያስ ሶፊ ቤት ሲጫወት አመሸ - የሰአቱ መንጐድ እንዳልተገነዘበ መስሎ፡፡ እኩለ ሌሊት ተጠጋ፡፡

በቤቱ ወስጥ እሱና ሶፊ ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ በጣም መምሸቱን ሲያረጋግጥ “በጣም ስለመሸ እዚሁ ባድር…” የሚል ሰበብ አቀረበ፡፡ ኮፍያውን ባገኘ ሃያ ዘጠነኛው ቀን፡ አበራ ራሱ ለማትያስ ደወለ፡፡ “እሺ?” አለ አበራ “ምን እሺ አለ?” ማትያስ ቀዝቀዝ አለ፡፡ የሆነ ነገር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ አበራ ልቡ መታ፡፡ በአንድ በኩል ሚስቱ ስታታልለው ስለያዛት ደስታ፣ በሌላ በኩል ክህደቷ እንደወላፈን ገረፈው፡፡ “እኔ እኮ ነግሬሃለሁ! ሴቶች ከሀዲ ናቸው! ያ መላጣን ማውጣቷ ሳያንስ አንተንም! የማላውቃቸውን ስንት ወንዶች… ስንት ወንዶች…” የአበራ ድምፅ በለቅሶ ሻከረ፡፡ “ባክህ ዝም በል! ምንም የሆነ ነገር የለም! ትላንትና ማታ ሚስትህ ባለጌ ብሆንባትም አክብራ ሶፋ ላይ አስተኝታ፣ መኝታ ቤቷን ቆልፋ ነው የተኛችው!” ማትያስ ስልኩን ጆሮው ላይ ዘጋው፡፡

አበራ እልህ በልቡ ተንተከተከ፡፡ ከማትያስ ጋር እንደተመሳጠሩ ወይ ጠርጥራ በነፍሰ ስጋው እየተጫወተች ነው እንጂ… አእምሮው ውስጥ ያሉ ድምፆች አስተጋቡ - “የሴቶችን ልብ ማመን አትችልም! ልባቸውን ወንድ ያኘዋል ማለት ዘበት!” ሲፈራ ሲቸር ማቲያስ ጋር ደወለ፡፡ ያሳለፈውን ህይወት እየተረከ ማትያስ እንዳያዝንለት አደረገ፡፡ ማትያስ በጣም ተጨነቀ፡፡ “እሺ አሁን ምን አድርግ ነው የምትለኝ?” “ሚስቴን ማመን እፈልጋለሁ! ያን ለማድረግ የመጨረሻ! የመጨረሻ! አንድ ነገር ብቻ ተባበረኝ! ከዛ በኋላ አላስቸግርህም ማትያስ አማራጭ አልነበረውም “የተቆለፈ ልብ በአልኮል ይከፈታል! ያኔ የተደበቀ ማንነት ይወጣል!” አለ አበራ ኮፍያውን ባገኘ በሰላሳኛው ቀን፡ ማትያስ ሁለት ሰአት ላይ ወደ ሶፊ መጣ፡፡ ራት በልተው ሲጨርሱ ይዞ የመጣውን ሻምፓኝ ከፈተ፡፡ ሶፊ አልጠጣም አሻፈረኝ አለች፡፡ ማትያስ ለአበራ ደውሎ ነገረው፡፡ አበራ ለሶፊ መልሶ ደወለ “ሶፊዬ ማትያስ ማለት እኔ ማለት ነው፡፡ እሱ እኮ ብቸኝነት እንዳይሰማሽ ነው፡፡ ለኔ ስትይ እሺ በይው…” ለመናት፡፡

ሶፊ አንደኛውን የሻምፓኝ ብርጭቆ ተቀብላ ተጐነጨች… ደገመች… ኮፍያውን ባገኘ ሰላሳ አንደኛው ቀን ጠዋት፡ አበራ ጠዋት ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በሩን ከፍቶ ሊገባ ሲል የግቢውን ቆሻሻ የሚደፋው ልጅ ከበሩ መግቢያ ላይ አገኘው፡፡ እድሜው ከዘጠኝ አመት አይበልጥም፡፡ “ጋሼ፤ ቆሻሻ አለ?” “የለም!” ብሎት አልፎት ሊገባ ሲል፣ ልጁ እየተቅለሰለሰ ጠጋ አለው፡፡” “ጋሼ ይቅርታ! ባለፈው ቆሻሻ ልወስድ ስገባ ያቺን ኬፕ… ማለቴ ኮፍያ ግቢ ውስጥ ረስቻት ወጣሁ፡፡ ባለፈው መኪና ውስጥ አይቻት ልጠይቅዎት ስል ሄዱ፡፡ በኋላ ፊልድ ሄደዋል አሉኝ…” አበራ አናቱን በዱላ የተመታ ያህል ደነገጠ፡፡

“ያንተ ነው?” አለ ልጁ ላይ እያፈጠጠ፡፡ ልጁ በድንጋጤ እንደተዋጠ ጭንቅላቱን ላይ ታች ወዘወዘ፡፡ “እና መላጣ ምናምን ስል የበረው በራሴ ፈጥሬ ነው?” አለ አበራ ሳይታወቀው እየጮኸ “ምናሉኝ ጋሼ?” ልጁ ግራ ተጋብቶ ጠየቀው፡፡ ልጁን ችላ ብሎ ወደ ግቢው ሲገባ ማትያስ አይኑ እንደቀላ ወደ በሩ ሲመጣ አየው፡፡ ቆሞ ጠበቀው፡፡ “ያው ደስ ይበልህ! ያሰብከው ሁሉ ሆነልህ! በመጠጥ አደንዝዘህ የምትፈልገውን ፈፅመናል!...” ማትያስ በንዴት ባሩድ የተቃጠሉ ቃላቶቹን እንደጥይት ተኮሳቸው፡፡ “ከሌላ ወንድ ጋር እስክታያት መቼም ቢሆን አርፈህ እንደማትቀመጥ እርግጠኛ ነበርኩ! ሚስት ያገባነው ለበቀል ነበር!” ብሎት ሄደ፡፡ ሚስቱን እጅ ከፍንጅ በመያዙ እርካታን ጠብቆ ነበር፡፡ እርካታ የለም! ፈፅሞ እርካታ ውስጡ የለም! ንፁህነቷ እየጐላ የእሱ መሰሪነት እየገዘፈ መጣበት፡፡

ቤት ሲገባ የሶፊ ሻንጣ ለጉዞ ተዘጋጅቶ ተቀምጧል፡፡ አንገቷን ደፍታ ከሶፋው ላይ ተቀምጣለች፡፡ ቀጭን እንባ በፊቷ ላይ ይወርዳል፡፡ በቆመበት ቁልቁል አያት! መግቢያ ቀዳዳ አጥታ ስትሽቆጠቆጥ በእርካታ ተሞልቶ እንደሚያስተውላት ነበር ያሰበው፡፡ መሳሳቱ ወለል ብሎ ታየው! እንደ አልማዝ የጠነከረ ታማኝነቷን እሳት ሆኖ ማቅለጥ ቢያቅተው፤ በውሃ ሸርሽሮ በድን አካሏ ቃል ኪዳን እንዲሰብር ማድረጉ መልሶ አንገበገበው…

Read 3979 times