Saturday, 23 March 2013 13:50

የጐረቤት አገር ስደተኞች፣ የኑሮ ውድነቱን እያባባሱብን ይሆን?

Written by  ሰለሞን ጓንጉል
Rate this item
(1 Vote)

ከሶማሊያና ከኤርትራ ስደተኞች ጋር ተፎካክሮ ቤት መከራየት ከባድ ነው “የግርማ በዳዳ አስጨናቂ ጥያቄ” በሚል ርእስ አልአዛር የተባሉ ፀሐፊ፣ በጥር 11 ቀን 2005 የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ያቀረቡት ጽሑፍ አትኩሮቴን ቆንጥጦ አነበብኩት፡፡ በየአመቱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአራቱም አቅጣጫ እየተሰደዱ፣ ቁጥር ስፍር የሌለው ግፍና ሰቆቃ ይደርስባቸዋል፡፡ እውነታው ያፈጠጠ ቢሆንም፣ ለማመን እየተቸገርኩ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ “11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት” ከምታስመዘግብ ሃገርና ስለ“ሰላማዊነትዋ” ከሚነገርላት ሃገር ሸሽቶ የማምለጥ ችኮላ ለምን አስፈለገ? ሞትን የሚያጋብዝ እጅግ አደገኛ የስደት ጉዞን ምን አመጣው? እላለሁ፡፡ እድገትና ስደት አብረው የሚሄዱ ነገሮች ሊሆኑልኝ አልቻሉም፡፡ የሚወራውና የሚታየው ነገር… በጣም እየተራራቀ አልጣጣም ብሏል፡፡

የተራራቁትን ነገሮች የሚያቀራርብ አልተገኘም፡፡ ስደቱም ቀጥሏል፡፡ ስደተኛው ግርማ ከብዙዎች ኢትዮጵያውያን ስደኞች አንዱ እንደሆነ የነገሩን የአዲስ አድማሱ ፀሐፊ፤ ወደ የመን በስደት አቅንተው ኤደን ባስቲን ከተማ ደርሰው መከራቸውን የሚያዩ ኢትዮጵያውያን ብዙ እንደሆኑ በጽሑፋቸው አስነብበውናል፡፡ በእርግጥ የሌላ አገር ስደተኞችም አሉ፡፡ ነገር ግን በባስቲን ሰፈር ውስጥ ከሚርመሰመሱት ስደተኞች ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው፡፡ ፀሐፊው በአካል ተገኝተው በተመለከቷት የየመንዋ ባስቲን ከተማ ውስጥ፣ አብዛኞቹ የሃገሬ ሰዎች የእለት ምግባቸውን ለማግኘት በየአውራ ጐዳናው ላይ ተሰማርተው አላፊ አግዳሚውን ሲለምኑ የሚውሉ ናቸው፡፡

በየመን በሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል መ/ቤት ውስጥ ያሉት የግድግዳ ቻርት ምን እንደሚያሳዩም ፀሐፊው ገልፀውልናል፡፡ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ ብቻ 230 ሺሕ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተው፣ በሰንአ በኤደንና በሃራድህ ከተሞች እየኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች “የኢኮኖሚ እድገቷ ሽቅብ እየሄደ ነው” በሚባልላት ሀገር ውስጥ መኖርን ጠልተው ለመሄድና ያን ሁሉ የስደት መከራ ለመቀበል ያስገደዳቸው ተአምር ምን ይሆን? በዚህ ጥያቄ እየተብሰለሰልኩ፣ ከተቃራኒው የጉዞ አቅጣጫ ጋር ባነፃፅረውስ ብዬ አሰብኩ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ እና በሕጋዊ መንገድ ሃገራቸውን ጥለው እንደሚሰደዱት ሁሉ፤ ከጐረቤት ሃገሮችም በርካታ ስደተኞች በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መ/ቤት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፣ ባለፉት 2 አመታት ብቻ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር በእጥፍ ገደማ ጨምሯል፡፡ በሁለት አመት፣ 100ሺ በላይ የሶማሊያ ዜጐች በስደት ወደ አገራችን ገብተዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ዜጐችም እንዲሁ፡፡

ትንሽ የማይባሉ ኤርትራውያንም በአፋር እና በትግራይ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ በጥቅሉ 370ሺ የሚደርሱ ስደተኞች ኢትዮጵያን መጠለያቸው አድርገዋል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ሶማሊያውያን ናቸው - 210ሺ ገደማ፡፡ 85ሺ ሱዳኖች እና 60ሺ ደግሞ ኤርትራውያን፡፡ እነዚህን ስደተኞች የሚያስተናግዱ መጠለያዎች አምስት ሲሆኑ፤ ስድስተኛ መጠለያ እንዲከፈት እየታሰበበት ነው፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሁለት አመታት ያሻቀበው የስተደኞች ቁጥር ነው፡፡ በአማካይ በየሳምንቱ ከአንድ ሺ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ ወደ ከተሜው ነዋሪ የሚቀላቀሉ ስደተኞችም ቁጥራቸው እንዳሻቀበ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ባለፈው አመት ብቻ በየወሩ እስከ 1ሺ የሚደርሱ ኤርትራውያን ከካምፕ ውጪ ወደ ከተሞች እየገቡ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተቀላቅለው መኖር ጀምረዋል፡፡ “Out of camp scheme” ይሉታል፡፡

ስደኞች ከካምፕ ውጪ እንዲኖሩ ታስቦ የተተገበረ ፕሮግራም ነው፡፡ በእርግጥም ስደተኞቹ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት፣ ከተጨናነቀ ካምች ተገላግለው የተረጋጋ ኑሮ እንዲመሩ እድል አግኝተዋል፡፡ ምንም እንኳ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለያዩ የአፍሪካና የአረብ አገራት ውስጥ ፍዳቸውን የሚያዩ ቢሆኑም፤ ኢትዮጵያ ግን ከጐረቤት አገራት ለሚመጡ ስደተኞች ብዙም አስቸጋሪ አይደለችም፡፡ እንዲያውም ምቹ እንደሆነች አምናለሁ፡፡ በከተማችን ውስጥ እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱና በነጻነት ኑሯቸውን የሚመሩ የሶማሊያ እና የኤርትራ ስደተኞችን መመልከት ይቻላል፡፡ ከጦርነት እና ከእስር ስጋት ርቀው እንደልባቸው ዘና ብለው ሲኖሩ ሳይ በሃገሬ እኮራለሁ፡፡ “እኛ በእነርሱ ሀገር ብንሆን ይሄን ያህል ነጻነት እናገኝ ይሆን?” ብዬም እጠይቃለሁ፡፡ ቢሆንም ግን፤ የጐረቤት አገር ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት ሕይወታቸውን ሲኖሩ እያስተዋልኩ እደሰታለሁ - ደስታዬ ብዙም አይቆይም እንጂ፡፡

ከተማ ውስጥ ተቀላቅሎ የመኖር ነፃነታቸው፣ በእኛ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ያሳስበኛል፡፡ ከተጽእኖዎቹ መካከልም ቀረብ ብሎ የሚታየኝ የኑሮ ውድነቱ ነው፡፡ ለቤት ኪራይ መናር፣ ለምሳሌ ለኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች መወደድ አንድ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ፣ ለአንድ አመት ገደማ ያህል በኖርኩበት የጐፋ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም፣ በርካታ የኤርትራና የሶማሊያ ዜጐች ተከራይተው ይኖራሉ፡፡ ተከራይተው ከመኖራቸው ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ ቅር የሚያሰኘኝ የመኖሪያ ቤቶቹ ኪራይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየ ጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ የኪራይ ዋጋ በየጊዜው የሚንረው ደግሞ፣ ከስደተኞቹ አኗኗርና የመክፈል አቅም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሰብሰብ ብለው ደባልነትን የወደደ አኗኗርን ይመርጣሉ፡፡

ለአራት እና ለአምስት ሆነው በደባልነት ስለሚኖሩም የተጠየቁትን ለመክፈል አይቸገሩም፡፡ እኖርበት ከነበረ ቤት አጠገብ፣ አንድ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም እንዴት እንደተከራየ አስታውሳለሁ፡፡ የቤቱ ባለቤቶች፣ ጽዳቱን ጨምረውና የተወሰነ የቤት እቃ አክለው፣ በራሳቸው ውሳኔ “የገስት ሃውስ ደረጃ” ሰጡትና ለተጠቃሚ አቀረቡት፡፡ በርከትከት ብለው የመጡ የኤርትራ ስደተኞች፣ በጋራ ኪራዩን እንችለዋለን ብለው ገቡበት - በወር ስድስት ሺህ ብር፡፡ ወደ አውሮፓ ወይም ወደ አሜሪካ እስኪሄዱ ድረስ ለመቆያነት ያህል ኪራዩን ተጋርተው ቢከፍሉ፤ ኪሳቸውን ላይጐዳ ይችላል፡፡ የሶማሊያ ስደተኞች አኗኗርም ተመሳሳይ ነው - ሰብሰብ ብለው ኪራዩን እየተጋሩና እየከፈሉ ይኖራሉ፡፡ ችግሩ ምንድነው? የእኔ ቢጤው ተከራይ፤ ቤት ፍለጋ ሲዞር… ያው 6ሺ ብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ የሌሎች ሰዎችን ምሳሌ ከማቅረብ ይልቅ፣ የኔውኑን ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡

ከአመት በፊት እዚያው ጐፋ መብራት ሃይል አካባቢ፣ ባለ አንድ መኝታ ቤት ተከራይቼ መኖር የጀመርኩት በ1600 ብር ኪራይ ነው - የስድስት ወር ቅድሚያ ክፍያ ነበረው፡፡ ውል ተፈራርመን የተስማማነው ለአንድ አመት ስለነበር፤ የቤት ኪራይ ጉዳይ እኔንና አከራዬን በክፉም በደጉም አላነጋገንም፡፡ ንግግራችን የተጀመረው የውሉ ዘመን ሲያልቅ ነው፡፡ አከራዬ ዘና ብሎ “የግቢው ዋጋ ንሯል፡፡ አንተም መጨመር አለብህ” አለኝ፡፡ ቅር አላለኝም፡፡ ቅሬታዬ የመጣው የጭማሪውን መጠን ስሰማ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የስድስት መቶ ብር ጭማሪ፡፡ ድርጊቱ ቢያበሳጨኝ መኖሪያውን ለቀቅኩ፡፡ በለቀቅኩ በነጋታው ጭማሪውን ከፍለው የተከራዩት የኤርትራ ስደተኞች ናቸው፡፡ ስደተኞች ሁልጊዜም በአንድ ሃገር ኑሮ ላይ አሉታዊ ውጤት ያስከትላሉ እያልኩ አይደለም፡፡ ከየአገሩ እየተሰደዱ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች የአገሬውን ኑሮ ከመጉዳት ይልቅ እንደሚጠቅሙ ይታወቃል፡፡

“በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ስደኞች የኑሮ ውድነቱን እያባበሉ ይሆ?” ብዬ ስጠይቅ፤ መነሻዬ ጥላቻ አይደለም፡፡ አሊያም፣ “ይህቺ ሃገር ለኢትዮጵያውን ብቻ መሆን አለባት” ከሚል መጥፎ ጽንፍ አይደለም፡፡ በፍጹም፡፡ ጥያቄዬን የሰማ ባለሙያ ነገሩን እንዲያጠናውና ለመፍትሔ እንዲታትር ለመጋበዝ ነው፡፡ የቤት ኪራዩ ጭማሪ አከራዮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አልዘነጋሁትም፡፡ ግን ተከራዮችስ? የጐፋ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየምን በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ በጀሞ እንዲሁም በጐተራ አካባቢ የሚገኙ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የሚታየው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡ የውጭ ሀገር ዜጐች፣ ነጮችም ጭምር ሳይቀር ተከራይተው ይኖራሉ፡፡ ባለ ሁለት መኝታ ቤትም እስከ 4500 ብር ይከራያሉ፡፡ ቤቶቹ ለማን እና ለምን እንደተገነቡ ሳይዘነጋ፤ ጉዳዩ ጥናት ቢደረግበት አይከፋም፡፡

Read 2139 times