Saturday, 23 March 2013 13:39

“የፊተኛውን ባልሽን በምን ቀበርሺው? በሻሽ፡፡ ምነው ቢሉ? የኋለኛው እንዳይሸሽ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በዱሮ ዘመን፤ ከዕለታት አንድ ቀን፤ በአንድ አካባቢ የሆነው ታሪክ ዛሬ እንደ ተረት ይወጋል፡፡ ወቅቱ ጅብ በጣም የሚፈራበትና ከሰው ጋር እየተጋፋ ገና በደምብ ሳይመሽ የሚመጣበት፣ በረት የሚሰብርበት፣ አጥር የሚጥስበት ነበር ይባላል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ቤት ውስጥ እስከመግባትና ሰው እስከመብላት ደርሶ ነበር አሉ፡፡ በዚያን ዘመን ቀኛዝማች ቢሰውር የሚባል አንድ ክፉ ሹም ነበር ይባላል፡፡ ማዕረጉም የአካባቢው ምክትል ሹም ነው፡፡ ከወንድነት ይልቅ ትዕቢተኛነት? ከአስተዳዳር ችሎታ ይልቅ በጨካኝነት ሰዎችን የመግፋትና የማሰቃየት፣ ከመስጠት ይልቅ የመንጠቅና የመዝረፍ ባህሪ የተጠናወተው የአምባው ምክትል ሹም ነው፡፡ አንድ ማታ ቤቱ አውሬ ገባ፡፡ ቀኛዝማች ቢሰውር ከሚስቱ ጋር እንደተኛ ነው፡፡ ያ ህይወት ያለው የእንስሳ ሸክም እላያቸው ላይ ተከመረ፡፡ የቀኛዝማች ሚስት ነቅታ ብሩክታዊትን ከዘንዶ እንዳዳነ ሁሉ ባሏ ካላዳናት መበላታቸውን ተገንዝባ እንስሳው ሳይሰማ ባሏን ጐሸም ታደርገዋለች፡፡

ባል ሆዬ እንዳልሰማ ጭጭ ይላል፡፡ ደገመችና ጐሸም አደረገችው፡፡ ቀኛዝማች ምኑ ሞኝ ነው እንቅልፍ ድብን አድርጐ እንደወሰደው ሁሉ ፀጥ! ሚስት ፍርሃቱም እያየለ መጣና በጣም ጐነተለችው፡፡ ይሄኔ ባል ልምዝግ አድርጐ ቆነጠጣትና፤ “አርፈሽ ተኚ!” ይላታል፡፡ እንቅልፍ በዐይናቸው ሳይዞር ያንን አውሬ እንደታቦት ተሸከሙት፡፡ ነጋና የጠዋት ብርሃን በበሩ ቀዳዳ ገባ፡፡ እንደምንም ብርድ ልብሱን ገልጠው ሲያዩ ከቤት ለመውጣት በሩን እየገፋ ያለው ለካ አንድ በመንደሩ በአውደልዳይነቱ የሚታወቅ ትልቅ ውሻ ነው! ሚስት ከት ብላ ሳቀች! “አይ ወንድ! አይ ጀግና ባል! አይ ማዕረግ!” እያለች የምፀት ሳቋን ማቆም አቃታት፡፡ “እኔኮ ውሻ መሆኑን በፊትም አውቄዋለሁ!” አለ ባል ቢሰውር - የምንተፍረቱን፡፡ የቢሰውር ሚስት ጠዋት ከአንዲት ውድ ሚስጥረኛ ጓደኛዋ ጋር ደጅ ሲወጡ የሆነውን ሁሉ አጫወተቻት፡፡ ወዲያው መንደሩጋ ወሬው ተዳረሰ፡፡ አገሩ አወቀ፡፡

ቢሰውር የአገር መሳቂያ ሆነ! ወትሮም አገር ይጠላው የነበረው ቀኛዝማች ቢሰውር በየቤተክርስቲያኑ፣ በየገበያው፣ በየእድሩ፣ በየሰንበቴው ሰው ፊት መቆም የሰውን ዐይን ማየት አቃተው፡፡ ተረቡ፣ ሽሙጡ፣ አሽሙሩ፣ ውስጠ-ወይራው መቆሚያ መቀመጫ አሳጣው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሹመቱን የሰጡት ንጉሥ ከሰሙ ሊከተል የሚችለውን በማሰብ ሥጋት ገደለው፡፡ ስለምንም ሲወራ የሱ ታሪክ እየመሰለው መበርገግ ሆነ ሥራው! እረኛ እንዲህ ሲል ዘፈነ፡- አህያ መጣች ተጭና እንሥራ አያ ቢሰውር ውሻ አስፈራራ፡፡ አህያ መጣች ጢሻ ለጢሻ ወንዱ ቢሰውር አዘለ ውሻ!!” ሰውም አውቆ ንጉሥ እንደሰሙ እያረገ በአሽሙር እየነገረ ያስበረግገዋል፡፡ ቀኛዝማች ቢሰውር አንድ ምሽት ከቤቱ በታች ባለ ወርካ ላይ በጠፍር ራሱን ሰቅሎ ተንጠልጥሎ ተገኘ! *** የገዛ ጭካኔያችን ሰለባ ከመሆን ያድነን፡፡

ከሹመት ጀግንነት ይሰውረን! እላያችን ላይ የሚከመር ጅብ መሳይ ውሻን የመሰለ ፈታኝ ወቅት አያምጣብን፡፡ “አረረም መረረም ማበሬን ተወጣሁ!” ከሚል እሳቤ ያውጣን፡፡ ስለስብሰባ ብዙ ተበሏል፡፡ “ስብሰባዎች በአስመስጋኝ ሁኔታ ማጠር አለባቸው፡፡ ለዚህ ዘዴው ተሰብሳቢዎቹ (meetes) ቆመው እንዲሰበሰቡ ማድረግ ነው፡፡ በመጀመሪያ አያምኑም፡፡ ከዚያ በኋላ ትዕግሥታቸው ያልቅና ጥለው ለመሄድ ይቀላቸዋል” ይለናል ሮበርት የተባለ የንግድ መሀንዲስ፡፡ ሩሲያዊው ፀሀፊ ብላዲሚር ቮይኖቪች “ስብሰባ ማለት፤ በርካታ ሰዎች አንድ ላይ ታድመው፤ አንዳንዶች የሚያስቡትን ነገር የማይናገሩበት፤ አንዳንዶች ደግሞ በእርግጥ የሚሠሩትን የማይናገሩበት መድረክ ማመቻቸት ነው” ይለናል፡፡

ከዚህ ያውጣን! የአሜሪካን ኮሜዲያን ደግሞ “ኮሚቴ ማለት በየግላቸው ምንም ለመሥራት የማይችሉ ሰዎች በቡድን ሆነው ምንም ሊሠራ እንደማይቻል ለመወሰን የሚሰበሰቡበት መድረክ ነው” ይለናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡ ሮስፔሮት የተባለ ፖለቲከኛ ደግሞ “እኔ የመጣሁበት አካባቢ እባብ ስታይ ግደለው ነው የሚባለው፡፡ ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ ውስጥ ግን፤ እባብ ስታይ መጀመሪያ ማድረግ ያለብህ ስለ እባብ የሚያማክር ባለሙያ (Consultant) መቅጠር፡፡ ከዚያም ስለ እባብ ዓመት ሙሉ ማውራት ነው!” ይለናል፡፡ ይሄንንማ አይጣልብን፡፡ “ተሰበሰቡ ተሰበሰቡና ያንኑ ነገር ደጋግመው አውርተው፤ ቀና ቀና ያሉት ጐብጠው፤ ጐልማሶቹ አርጅተው ደማቸው ተንዠርግጐ መቋሚያ ይዘው ከጐባኤው አዳራሽ ወጡ” ይለናል የፈረንሣይ ኮሜዲያን፡፡

አንዳንዴ ምነው አለምን የሚመሯት ኮሜዲያን በሆኑ ያሰኛል፡፡ “አሁንስ ህይወት የተራዘመ ስብሰባ መሰለችኝ” ይላል ደራሲ በአሉ ግርማ፤ የዌልሹ ፀሀፊ-ተውኔት ግዋይን ቶማስም “አባዬ ኑሮዬኮ ስብሰባ ነበረ፡፡ አሁንማ የሌለሁበት ኮሜቴ አጀንዳዎች እንደው በመንገድ ሳልፍ እንኳ ይጠቅሱኛል!” ይለናል፡፡ ፍሬያማ ካልሆኑ ስብሰባዎች ያድነን፡፡ ለጉባኤ ስንሰበሰብ ጠቅለል ባለ አገላለፅ ልብ ማለት ያለብን የፖለቲካዊ አሰርቱ - ቃላት ሀሳቦች አሉ፡፡ “አይ መሬት ያለ ሰው! እኔ ዘንድ ሆነህ ባየኸው!” አንዱ ነው፡፡ “የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ!” ሁለተኛው ነው፡፡ “የዘመድ ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ አለ” ሦስተኛው ነው፡፡ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው!” አራተኛው ነው፡፡ “ዱታ ነኝ ብሎ ለያዥ ለገራዥ ማስቸገር ኋላ ማጣፊያው እንዲያጥር ያደርጋል፡፡

ፉሎው ሲወልቅለት ጊዜ፤ ማን ይቻለው? እንዳይባል እንደፈረስ ሁሉ ልጓም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም በእኩል ዐይን ይገምገም፡፡” ይሄ አመስተኛው ነው፡፡ “ጠላት ናቸው ስንቀርባቸው የእኛው ናቸው” ስድስተኛው ነው፡፡ “ችላ እንዳትባል፣ መቼም ወላድ ናት እንዳይደግፏት፣ የረከሰች ናት ውሻ የት ትግባ፣ ምጥ ሲያጣድፋት?” የሚለውን የኦሮሚኛ አባባል አንርሳ የሚለው፡፡ ሰባተኛው ነው፡፡ እንደ ጥንቱ ምንዝር ለአለቃ፣ የበታች ለበላይ የሚያመጣው፣ የጫንቃ ጠላ የለም፤ ብሎ ከልብ ማመን ስምንተኛው ነው፡፡ “ድንበር ጠብቅልኝ አልኩ እንጂ ሚስቴን ጠብቅ ብዬሃለሁ ያለውን ባላገር ብሶት አለመርሳት ዘጠነኛው ነው፡፡ “ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፡፡ ሹሞችም ሲሻሩ ተራ ህዝብ ናቸው” ይሏልና ከሥልጣን መሰናበት ከሀገር መሰናበት አይደለም የሚለው ዘጠነኛው ነው፡፡ ዐሰርቱ ቃላትን በልቦናችን ያሳድርብን!! “የፊተኛውን ባልሺን በምን ቀበርሺው? በሻሽ፡፡ ምነው ቢሉ? የኋለኛው እንዳይሸሽ!” የሚለው ብርቱ ብሂል በፊተኛውም ሆነ በኋለኛው ጉዳያችን ላይ ዐይናችሁን ክፈቱ ይለናልና ሁሉንም ልብ እንበል!!

Read 3749 times