Saturday, 16 March 2013 12:14

ኢትዮጵያዊው ኢንቨስተር ከራሽያ ማፍያዎች ጋር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ባለፈው ሳምንት በራሽያ ሰባት ሬስቶራንቶች ስላሏቸውና በቢሾፍቱ ---ሪዞርትን ስለከፈቱ ኢትዮጵያዊ ዶ/ር---- ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አቅርበን ነበር፡፡ በቦታ ጥበት የተነሳ ኢንቨስተሩ ከራሽያ ማፍያዎች ጋር የነበራቸውን አስገራሚ ገጠመኞችና ውጣ ውረዶች ሳናቀርብ ቀርተናል፡፡ ዛሬ ይሄን ታሪካቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ከኢንቨስተሩ ጋር ቃለምልልሱን ያደረገችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ናት፡፡ እስቲ ከራሽያ ማፍያዎች ጋር ስላሳለፉት ውጣ ውረድ ያጫውቱኝ----- ራሽያ ውስጥ ከ1990-2000 ዓ.ም ድረስ ትልቅ ቀውስ ነበር፡፡ ለአስር ዓመት አገሪቱን ማፍያዎች የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር፡፡ ብዙዎቹ ከሶሻሊዝም መፈረካከስ በኋላ ሃያ ዓመትና ከዛ በላይ ወህኒቤት ታስረው የተለቀቁ ናቸው፡፡ ፓፓ ወይም ‹‹የማፍያ አባት›› በመባል የሚታወቁ ሲሆኑ ሁሉም በሥራቸው ሁለት መቶና ሶስት መቶ ሰዎች ያደራጃሉ፡፡ ከተማውን በሙሉ እነዚህ ሰዎች ተከፋፍለውት ነበር፡፡

በየሰፈሩ አንድ አንድ የሰፈር አለቃ ይኖራል፡፡ በአንደኛው ፓፓ ግዛት ሌላው ጣልቃ በመግባት ለመበጥበጥ ቢሞክር የሰፈር አለቆች አደብ ያስገዙታል፡፡ ማንኛውም በቢዝነስ ውስጥ የተሰማራ ሰው ለእነሱ በየወሩ የተጣለበትን ክፍያ (ደሞዝ) ይከፍላል፡፡ ማነው ክፍያውን የሚወስነው? ሚር X የተባለ የማፍያው ቡድን አለቃ (ፓፓ ይሉታል) የንግድ ቦታሽ ድረስ ይመጣና ‹‹ከማን ጋር ነው የምትሰሪው?›› ብሎ ይጠይቅሻል፡፡ (ከየትኛው የማፍያ ቡድን ጋር ማለቱ ነው) ስሙን መናገር አለብሽ፡፡

ፓፓ ከሌለሽ በየቀኑ ተመላልሶ የሚሸጠውን፣የሚወጣ የሚገባውን አይቶ፣ አጥንቶና ሰልሎ በወር 5ሺ ዶላር ወይም 10 ሺህ ዶላር ክፍያ ሊመድብብሽ ይችላል፡፡ በየወሩ የተመደበብሽን ገንዘብ ባትከፍይ ቤትሽ በቦንብ ሊፈነዳ ወይም በእሳት ሊቀጣጠል ይችላል፡፡ በጥይት ሊገሉሽም ይችላሉ፡፡ ማንም የሚደርስልሽ የለም፡፡ መንግስት የለም ማለት ነው? እንደሌለ ቁጠሪው፡፡ እነሱ ከመንግስትና ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ነገሩ ሳይገባሽ ለፖሊስ ወይም ለመንግስት ብታመለክቺ ጥይት በጭንቅላትሽ ላይ ይለቁብሻል፡፡ አንዳንዴ ለምሳሌ--አንቺ ካዛንቺስ የምትሰሪ ከሆነ----የልደታው ፓፓ (ንጉስ) ይመጣና ‹‹ለእኔ ይሄን ያህል መክፈል አለብሽ›› ብሎ ይወስንብሻል፡፡ ያኔ የፓፓሽን ስም ትጠሪያለሽ--- ካመነሽ ይሄዳል፡፡ ካላመነ ‹‹ደውልልኝ በይው›› ብሎ ስልኩን ትቶ ይሄዳል፡፡ ተደዋውለው ‹‹የእኔ ነው›› ከተባባሉ ነገሩ በዚያው ያልቃል፡፡ በቃ አንቺ ጋ አይደርሱብሽም ማለት ነው ፤ ለአንደኛው ብቻ ትከፍያለሽ፡፡

በዚህ ዓይነት ቢዝነስ ማስፋፋት አስቸጋሪ አይሆንም? አዎ!! ቢዝነስሽ እየሰፋ ሲመጣ ቢዝነስ በከፈትሽበት ቦታ ሁሉ ችግር ይገጥምሻል ----እንደአዲስ ክፍያ መጠየቅሽ አይቀርም፡ ለፓፓሽ ታሳውቂና እነሱ ተነጋግረው ስምምነት ያደርጋሉ፡፡ ይኼ የአንቺ ጉዳይ አይደለም፡፡ “እኔ ግዛት ውስጥ የአንተ “ቢዝነስማን” መጥቶ ስለሚሠራ፣ለአንተ ከሚከፍልህ አስር ሺህ ዶላር ውስጥ ሁለት ሺ ዶላሩን ለእኔ ትከፍለኛለህ፣ የእኔ ግዛት ነው›› ተባብለው እነሱው ይስማማሉ፡፡ አንቺ ፓፓሽ የወሰነብሽን ብቻ ነው የምትከፍይው፡፡ ማፍያዎቹ በቢዝነሳችሁ የሚያግዟችሁ--- የሚሰሩላችሁ ነገር አለ? በሬስቶራንቱ ውስጥ ጉልቤ ወይም ዱርዬ መጥቶ ሂሳብ አልከፍልም ካለ ደውለን እንነግራቸዋለን፣ መጥተው አንገቱን አንቀው አስከፍለውት ይሄዳሉ፡፡ ሌላ ችግር እፈጥራለሁ የሚል ካለም አንዱ የማፍያ አባት ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ የሚደርሱ ወታደሮች ስላሉት ችግር የለም፡፡ መጥተው አፍንጫውን ሰብረውት ይዘውት ይሄዳሉ፡፡

የገባሻትን ቃል ከጠበቅሽ ለደህንነትሽ ስጋት የለብሽም፡፡ እኔ እና አንቺ ስንሰራ ለምሳሌ ‹‹ስጋ አቀርብልሃለሁ›› ብለሽ ከእኔ መቶ ሺህ ብር ብትወስጅና ብትክጂኝ “ለፓፓ” እንጂ ለመንግስት ወይም ለፖሊስ ሪፖርት አታደርጊም፡፡ ፓፓው ቤትሽ መጥቶ ‹‹ያደረግሽው ነገር ጥሩ አይደለም፤ የእኛን ልጅ ሃቅ አጥፍተሻል፤ ስለዚህ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት መቶ ሺ ብር ታመጪያለሽ›› ተብሎ ይበየንብሻል፡፡ ቅጣት መሆኑ ነው? አዎ ቅጣት ነው፡፡ ‹‹ይሄን ባትፈፅሚ ልጅሽን አታገኚውም፤ ባልሽ ከስራ አይመጣም፤ አንቺም ላትኖሪ ትችያለሽ›› በማለት አስጠንቅቀውሽ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ከየትም ታመጫታለሽ፤ ክህደት የሚባል ነገር አይወዱም፡፡ ነገር ግን አንቺን ለማስጠቃት ሆን ብዬ “መቶ ሺ አበድሬው አልመለሰልኝም›› ብዬ ብዋሽና አጣርተው ቢደርሱበት በተመሳሳይ ቅጣቱ በእኔ ላይ ይጣላል፡፡

ህግ አስከባሪ ማፍያዎች ማለትም ይቻላላ ..? ህግ አስከባሪዎች ናቸው (ሳቅ) ለምሳሌ ለመንግስት መክፈል ያለብሽን ታክስ ካልከፈልሽ አይለቁሽም፡፡ የተከራየሽውን ቤት ኪራይ በወቅቱ መክፈልም አለብሽ፡፡ በቢዝነስ ሥራ ውስጥ ከመንግስት የሚጠበቅብኝን ሁሉ መፈፀም አለብኝ፡፡ ስንት የማፍያ አባቶች ነበርዎት፤ያሳለፉት ውጣ ውረድ ምን ይመስላል? ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ፡፡ የአንድ ቀበሌ ማፍያ አለቃ ድንገት ይመጣና ‹‹የአንተን የማፍያ አለቃ አላውቅልህም፤ ለእኔ ትከፍለኛለህ፡፡ ለእኔ ካልከፈልከኝ በግንባርህ ጥይት ነው የምለቅብህ›› ብሎ ይሄዳል፡፡ ወይንም ደግሞ ‹‹ነገ ጠዋት መቶ ሺህ ብር ይዘህ እንድትመጣ፣ እዚህ ቦታ መጥቼ እወስዳለሁ›› ሊልሽ ይችላል፡፡ ይሄኔ ለፓፓሽ ደውለሽ ትነግሪዋለሽ፡፡ እሱም ወይ ችግሩን በቀላሉ ተነጋግሮ ይፈታዋል አሊያም ደግሞ “አውቃቸዋለሁ፤እነሱ ጭንቅላታቸውን ያማቸዋል፤ ከእነሱ ጋር ያለኝን ችግር እስክፈታ ከአካባቢው ዞር ብትይ ይሻላል›› ብለው ይመክሩሻል፡፡

ችግሩ እስኪፈታ መኖርያ ቤት መቀየር አለብሽ፡፡ ሶስት አራት ጊዜ እንዲህ ፈትነውኛል፡፡ አንድ ጊዜ ምን አጋጠመኝ መሰለሽ.. ‹‹ጋጊስታን›› የሚባሉት እቤቴ መጡና.. ጋጊስታን ምንድን ናቸው? ተባራሪ ማፍያዎች ናቸው፡፡ እኛ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ባሌ..እንደምንለው በየክፍለአገሩ ይኖራሉ፡፡ ‹‹እኛ ክልል መጥተህ በመስራትህ ለእኛ መክፈል ይገባሃል›› ይሉኛል፡፡ ‹‹እኔ እኮ የእራሴ ሰው (ፓፓ) አለኝ--- ለምን አትነጋገሩም?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ያንተን ፓፓ አናውቅም! ትከፍላለህ ትከፍላለህ›› ብለው አፋጠጡኝ፡፡ ጉድ ፈላ! እንደነዚህ አይነት ማፍያዎች ከተለያየ ቦታ መጥተው ዘርፈው ነው የሚሄዱት፡፡ ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ አንዴ ቦጭቀው ይሄዳሉ፡፡ ለፓፓዬ ደወልኩና ነገርኩት፡፡

‹‹አንተ ጋ መጡ?›› አለኝ፡፡ ፓፓዬ አውቋቸዋል፡፡ ‹‹አዎ›› አልኩት፡፡ ‹‹ሌላም የገደሉት ሰው ስላለ ችግሩን እስክፈታው ሌላ አካባቢ ሂድና ቤት ተከራይተህ ተቀመጥ›› አለኝ፡፡ ሶስት ወር ሌላ አካባቢ ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡ እነሱ ሲፈላለጉ፣ ሲቀጣጠሩ፣ ሲነጋገሩ ቆዩ - ‹‹የእኛ ነው፤ የእናንተ አይደለም፡፡ እኛ ነን በፊት የምናውቀው…ከየት ነው ያገኛችሁት፤ እኔ ነኝ አባቱ፤ አይደለህም›› የሚለውን ከተነጋገሩ በኋላ አንድ ቀን መጡና ይዘውኝ ሄዱ፡፡ “ንግግራችን ላይ አንተ መገኘት አለብህ” ብለው ነው የወሰዱኝ፡፡ አንድ ትልቅ ሬስቶራንት ምድር ቤት ውስጥ ነበር ውይይታቸው የተካሄደው፡፡ እኔን መሃል አደረጉኝና በግራና በቀኝ ሃያ ሃያ ሆነው ተቀመጡ - ‹‹የእኔ ልጅ ነው፤ የእኔ ልጅ ነው›› ክርክር ያዙ፡፡ ‹‹እናንተ የእኔ አባት ልትሆኑ አትችሉም፡፡

የወለደኝ ለገሠ ደምሴ የሚባል አባት አለኝ›› አልኳቸው (ሳቅ) እነሱ ግን ‹‹እኔ ነኝ መጀመሪያ ያየሁት›› ማለታቸው ነው፡፡ ከዛ እኔን የሚጠይቁኝን ከጠየቁኝ በኋላ ‹‹ውጣ›› አሉኝ፡፡ ለእኔ ጠባቂ ሰጥተውኝ፤ታጅቤ መኪና ይዤ ስለነበር ተሰባሰቡና “ከእርሱ ፀጉር አንድ ፀጉር ብትወድቅ ነፍስ ይጠፋል፤እንዳትተኩሱ መኪናውን አስነስቶ ይሂድ” ብለው ተናገሩ፡፡ (ይሄ ሁሉ እንግዲህ በጠራራ ፀሐይ መንግስት ባለበት ነው የሚካሄደው) ጠቡ ወደ መታኮስ የሚያመራበት ጊዜ የለም…? ብዙ ጊዜ ማፍያዎች ሲጣሉ አካፋና መዶሻ መኪና ላይ ጭነው ወደ መቃብር ሥፍራ ነው የሚሄዱት፡፡ እዚያ ይተኳኮሳሉ፤ይገዳደላሉ፡፡ የተረፉት አካፋቸውን ከመኪና ላይ አውርደው የሞተውን ቀብረው ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ መቃብር ቦታ ከሄዱ ጠንከር ያለ ጠብ ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ማፍያዎች ቤተሰብ፣ ልጆች--- ምናምን የላቸውም እንዴ? በህጋቸው መሠረት ማፍያ ሚስት የማግባት መብት የለውም፣ ንብረት ማፍራት አይችልም፤ ከእናት አባቱ ጋር መኖር አይችልም፡፡ ክልክል ነው፡፡ የውስጥ ህግና ደንብ አላቸው፡፡

Read 2972 times