Saturday, 16 March 2013 12:17

“የሚባላው ነብር ከጓዳ ሳይወጣ የሚበላው ፍየል ተክለፍልፎ መጣ!”

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አዕዋፋት ተሰብስበው እያደኑ ስለሚይዟቸው ጠላቶቻቸው ይወያያሉ፤ አሉ፡፡ ዋና ሰብሳቢያቸው ንሥር ነው፡፡ ንሥር ያቀረበው ሃሳብ የሚከተለው ነበር፡- “እንደምታውቁት የምንወያየው የጠላቶቻችንን ፈሊጥ ተረድተን ራሳችንን ለማዳን ምን እናድርግ በሚለው ላይ ሲሆን ለዚህ አስፈፃሚ የሚሆነንን ተወካይ በመጨረሻ ለመምረጥ ነው፡፡ የምንመርጠው ተወካይ

1ኛ/ ባላንጣዎቻችን ጋ ሄዶ ማሳመን የሚችል

2ኛ/ለመወዳደርና ለመመረጥ አቅም ያለው

3ኛ/ከነሱ ጋር ተግባብቶ ውስጣቸውን ጥሩ አድርጐ ለማየትና ለኛ ሪፖርት ለማድረግ የሚችል

4ኛ/ በአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ሊርቃቸውና ሊያመልጥ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡

ሰብሳቢው ንሥር ባቀረበው ቅድመ - ሁኔታ ላይ ሁሉም ተስማሙ፡፡ በዚህም መሠረት የተለያዩ አዕዋፋት ለምርጫ ቀረቡና በከፍተኛ ድምጽ የተመረጠችው ቆቅ ሆነች፡፡ ቆቅም ባደረገችው ንግግር፤ “ወንድሞቼ እህቶቼ፤ አዕዋፋት ሆይ! እናንተን እወክል ዘንድ ስለመረጣችሁኝና ዕምነታችሁን ስለጣላችሁብኝ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደምታውቁት በአሁኑ ጊዜ መመረጥ ከፍተኛ ፈተና ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ሀ) ባላንጦቻችን ከመቼውም የላቀ አንድነት ያላቸው ሰዓት በመሆኑ፤ ለ) በውድድሩ እንድንሳተፍ ያደረጉን ተሳትፎ እንዲኖረንና ሌሎቹ ጫካ ነዋሪ እንስሳት ስለደግነታቸው እንዲያደንቋቸው ስለሆነ፤ ሐ) ወዳጅና ጠላታቸውን ለመለየት ቢያንስ ከእኛ አንዱ በመካከላቸው እንዲገኝ ብለው ስላሰቡ፤ ይመስለኛል። ሆኖም ካለመሳተፍ መሳተፍ የበለጠ ጥቅም ይኖረዋልና እናንተን መስዬ፤ እናንተን አክዬ እና እናንተን ሆኜ ለመቅረብ ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህንንም ለማሳካት ሦስት ዘዴዎችን ለመጠቀም እሞክራለሁ፡፡

1ኛው ወቅታዊነት ነው፡፡ 2ኛው ከእነሱ የሰፋ አስተሳሰብ ይዞ፣ ቀድሞ መገኘት ነው፡፡ 3ኛው እነሱን አለመናቅና ሊበልጡኝ የሚችሉበት አንዳንድ ጉዳይ እንደሚኖር ማመን ነው፡፡ ሁሉም በቆቅ ሃሳብ ተስማሙና አጨበጨቡላት፡፡ በመጨረሻ እርግብ እንድትናገር እድል እንዲሰጣት ጠየቀች፡፡ ተፈቀደላት፡፡ እርግብም፤ “ወንድሞቼ፣ እህቶቼ አዕዋፋት ሆይ! ቆቅ በመመረጧ እንደማናችሁም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ሆኖም አንድ ቅር ያለኝ ነገር አለ፡፡ ይኸውም፤ ቆቅ፤ “ቆቅ” የሚለውን ስሟን ይዛ የትም አትደርስም የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ ስለዚህ ስሟን ብትቀይር ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ማን እንበላት ካላችሁም እኔ “ዋ-ኔ” የሚል ስም ቢሰጣት መልካም ነው እላለሁ አለች፡፡” ሁሉም መስማማታቸውን በክንፋቸው በማጨብጨብ ገለፁ፡፡ እርግብም ቀጥላ “አሁን የሚያዋጣን ዛሬ ከባላንጦቻችን መወዳጀት ነው” አለች፡፡ “ለነገስ?” ብለው ጠየቋት፡፡ “ለነገማ የሆዳቸውን ስናውቅ እንወስናለን!” አለች፡፡

*** ከጥበብ ሁሉ የሚልቀው ወቅትን ማወቅ ነው፡፡ ወቅትን አለማወቅ አቅምን ካለማወቅ እኩል ነው፡፡ “እያንዳንዱ ድል አንድ አንድ ጠላት እንደሚወልድ አትርሳ” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ ስለዚህም አሸነፍኩ ብሎ ዘራፍ ማለት ከመሸነፍ አንድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ድልን በማጭበርበር የምንቀዳጅ ከሆነም ዕድሜ ልካችንን እንቅልፍ እንዳይወስደን ያደርገናል፡፡ ፖለቲካ ብዙው እጁ ሸፍጥ ነው፡፡ ሁኔታዎችን ለራስ እንደሚመች ለማድረግ ማናቸውንም ዘዴ መጠቀም ይጠይቃል፡፡ ደራሲና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በአንደኛው ቴያትሩ እንዳለው፤ “አብዮትኮ ኳስ ጨዋታ ነው፡፡ አቀበለ፣ ተቀበለ፣ ይዞ ሄደ - መታ - ፎሪ ወጣ፤ አብዮቱ ከሸፈ ይባላል፤ ወይም ቀጥሎ ደግሞ “ይዞ ሄደ! አብዶ ሰራ! መታ! - ጐል! አብዮቱ ግቡን መታ!! ይባላል፡፡

ይሄው ነው አብዮት ማለት - ኳስ ጨዋታ ነው፡፡ መቼ እንደምናቀብል፣ መቼ ወደፊት እንደምንሄድ፣ መቼ አብዶ (ምሣ) እንደምንሠራ ካላወቅን ፖለቲከኛ መሆን አንችልም፡፡ ይህንን ምንጊዜም መርሳት የለብንም፡፡ “የጐጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ” በሚለው መጽሐፉ፤ ደራሲ ግርማ ጌታኹን፣ እንዲህ ይላል … “ወለተ አልፋ አመተ አልፍን ወለደች፡፡ ከዚህ የሚአሳዝን ታሪክ አለበት፡፡ በአገር ላይ ያለ ወንድ ሁሉ በጦርነት አልቆ ወንድ ተወዶ ሳለ፤ ወለተ አልፋና ዓመተ አልፋ ዲማ ገበያ ሲሄዱ፣ ዝያ የሚባል ውሃ ሞልቶ አንድ ወንድ ጐዳነኛ ወስዶት ከዛፍ ላይ ሰቅሎት አዩ፡፡ “ሰው ነህ ግንድ” አሉት፡፡ እርሱ ግን የውርጭ ድደን ጥርሱን ገጥሞት መናገር ቸግሮት ነበርና ከዛፉ አውርደው ፀሐይ ቢአሞቁት፤ ዘመድ ላይ ከጃራ ሹም የመጣሁ ነበርሁ፡፡

ግን ውሃው አዋረደኝ ተፋኝ አለና ተናገረ፡፡ የዚህ ጊዜ እናትና ልጆች የኔ ባል ይሁን የኔ ባል ይሁን ተባባሉበት፡፡ ተያይዘው ከዲማ መነኮሳት ከነአባ ተጠምቀ መድኅንና ከነአባ ዮሐኒ ዘንድ ለፍርድ ሄዱ፡፡ እኒያም ሲፈርዱ አንች ባል አግብተሺ ቤት ሠርተሺ እርስዋን ወልደሻል፡፡ እርሷ ባል ሳታገባ ሳትወልድ ልታረጅ ነውና ለርስዋ ይሁን፡፡ አንች ብታገኝ አግቢ፤ ብታቂ መንኩሺና ተቀመጪ፣ ብለው ፈረዱ ይባላል፡፡” ወንድ ሁሉ ካገር የሚጠፋበት ዘመን አያድርስብን፡፡ እናትና ልጅ በአንድ ባል የሚጣሉበትን ጊዜ አይጣልብን! ድፍረትን ከሀፍረት ሳንነጥል የምናይበት ዐይን ይስጠን - በተለይ በምርጫ ወቅት፡፡ ዘራፍ ማለት፣ አለሁ አለሁ ማለት፣ ያለ እኔ ማን አለ ማለት፣ ካለፈው አለመማር፤ ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን፤ “የሚባለው ነብር ከጓዳ ሳይወጣ የሚበላው ፍየል ተክለፍልፎ መጣ” የሚለውን አገርኛ ግጥም አንርሣ!

Read 5484 times