Saturday, 16 March 2013 11:28

የ97 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምርጫና የ2007 የኬኒያ ምርጫ አጭር ንጽጽር

Written by  ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

ከዘንድሮ የኬኒያ ምርጫ ምን እንማራለን? ግንቦት 30 ቀን 1997 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ላይ የተጠራው የቅንጅት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተጭበረበሩ የምርጫ ውጤቶችን ለማጣራት በቅንጅት ቢሮ ተሰይሟል፡፡ እንደተለመደው የኮሚቴው አባላት ወጣ ገባ በማለት በእጅ ስልክ የሚያካሂዱት የመረጃ ልውውጥ ስብሰባውን በወቅቱ ለመጀመር አዳጋች አድርጎታል፡፡ በዚሁ መልክ አንዱ አመራር ሲወጣ ሌላው ሲተካ ቆይቶ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ስብሰባው ተጀመረ፡፡ አጀንዳው ተነቦ ውይይት ከመጀመሩ በፊት በኮምፒዩተር የተጻፈ መልዕክት የያዘች አነስተኛ ወረቀት ለቅንጅት ሊቀመንበር ደረሳቸው፡፡ ወረቀቱን በጥሞና ካነበቡ በኋላ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ጎናቸው ለነበረው ተሰብሳቢ ወረቀቱን በማቀበል የመልዕክቱን ይዘት ማብራራት ጀመሩ፡፡

“ነገ ማክሰኞ ሁሉም ኢትየጵያዊ የስራ ማቆም አድማ እንዲያደርግ የሚጠይቅ በቅንጅት ስም የተበተነ የጥሪ ወረቀት ነው፡፡” አሉና ለሰከንዶች ትንፋሽ ወስደው በማስከተል “ሕዝባችንን ዘገየንበት መሰለኝ እንደተለመደው ቆራጥ አቋም በመውስድ ቀደመን” አሉ፡፡ የመድከምና የመታከት ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ በመቀጠልም “ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ስለሆነ ልንነጋገርበት ይገባል…” ብለው ሃሳባቸውን ሳይጨርሱ አንድ ጊዜ የኮሚቴው አባላት ከዳር አስከዳር አጉረመረሙ፡፡ ግራ መጋባትና ማልጎምጎሙ ሲበረታ ሰብሳቢያችን “አንድ ጊዜ እንደማመጥ ! እንደማመጥ እንጂ!” ማለታቸው ተከትሎ የተፈጠረውን ጸጥታ በመጠቀም አንድ የኮሚቴ አባል እጅ ሳያወጣና ለመናገር ሳይፈቀድለት መናገር ጀመረ፡፡ “የጥሪውን ወረቀት ቀደም ብዬ አይቼዋለሁ፡፡

ጥሪውንም ያደረገው ሃይል አይታወቅም፡፡ ለመሆኑ እኛ ባላደረግነው ጥሪ ጊዜ ልንነጋገር ይገባል? አይገባም፡፡ ለጥያቄው መልስ በመስጠት ወደ ጀመርነው አጀንዳ እንመለስ” አለ፡፡ ሌላው የኮሚቴ አባል ቀጠለ፡፡“ አሁን አቶ እገሌ የተናገሩት ትክክል ነው፡፡ ሕዝቡ ቁጣውን መግለጽ መብቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ የገደበው ይበቃል፤ እኛ ተደራቢ ሆነን ልንገድበው አይገባም!” ተቀባብለው ሃሳብ ሰጡ፡፡ ብዙዎቻችንን ያልገባን አንዳች ደስ የማይል ጉዳይ ነበር፡፡ ከመቅጽበት ተናጋሪዎቹ ላይ ከግራና ከቀኝ ርብርብ ተካሄደባቸው፡፡ “ምን ለማለት ፈልጋችሁ ነው!! የስራ ማቆም አድማ የተጠራው በኛ ስም ነው፡፡ ለምን የማታውቁ ትመስላላችሁ፤ ይህን የሚያደርገው ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል”፡፡ “በኛ ስም የተጠራ ነገር ግን እኛ የማንመራው አድማ አደጋውና መዘዙ ብዙ ሊሆን ይችላል”፡፡ “በስማችን እስከተጠራ ድረስ ሕዝቡ እንዳይወናበድ ማድረግ አለብን”፡፡ ግብግቡ ለሰላሳ ደቂቃና ከዛም በላይ ቀጠለ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አንደኛው ድምጽ ተሸነፈና ሌላኛው በልዩነት እስከመጨረሻው ቀጠለ፡፡ ውዝግቡ የታሪክ ተወቃሽነትና በሕዝብ አደራ ተጠያቂነት ክስ ታጅቦ ቀጠለ፡፡ ጉዳዩ ሊውል ሊያድር የማይችል በመሆኑ በመጨረሻ ማስተባበያ ለሕዝብ እንዲሰጥ በድምጽ ብልጫ ተወስኖ ማስተባበያውን የሚሰጡ ሰዎች ተመረጡ፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ ግን ይህ አልነበረም፡፡

አሳሳቢው ጉዳይ በአንድ በኩል በርካታ ወሳኝ ሰዓቶች በውዝግብ በማለፋቸው ማስተባበያው በጀርመን ድምጽ ለመተላለፍ ባለመቻሉና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ዘገባው ወደ ሕዝብ ጆሮ እንዳይደርስ በማፈኑ ሕዝብና ቅንጅት እንደተቆራረጡ ማምሽታቸው ነበር፡፡ ከረፈደ በኋላ ማስተባበያውን በቪኦኤ ለመስጠት ቢሞከርም በጣቢያው ላይ በተደጋጋሚ ይደረግ በነበረው ጃሚንግ ምክንያት ሳይተላለፍ ቀረ፡፡ መረጃ የተነፈገው ቀላል የማይባል ሕዝብ ጥሪው ከቅንጅት የመነጨ፣ በስርዓት የሚመራና የተቀነባበረ መስሎት ከስራ በመቅረት በየአካባቢው ወደሚገኘው አደባባይ ወጣ፡፡ ልዩ የጥበቃ ሃይሎች እንቅስቃሴውን ከጅምሩ ለማስቀረት በማሰብ ገና ጎህ ከመቅደዱ በከፈተው ተኩስ ሰላሳ አምስት ሰዎች ተገደሉ፡፡ በርካታዎች ቆሰሉ፣ ቁጥሩ የማይታወቅ ሰልፈኛ ታፍሶ ታሰረ፡፡የምርጫው ሂደት ከወዲሁ ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ደም ተጀመረ፡፡ አስደንጋጭም አሳሳቢም ነበር፡፡ ገና ከጅምሩ ለንግግርም ሆነ ለመደማመጥ እድል መስጠት ያልቻለው የ97 ምርጫ ፈተናው መጀመሩ ነበር፡፡

ቅንጅት በውስጣዊ አንድነቱ መላላት ምክንያት አግባብ ያለውን ውሳኔ በወቅቱ አስተላልፎ አደጋውን መታደግ አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል ከዘገየም በኋላ ቢሆን ከቅንጅት የተላለፈውን “አደጋውን በጋራ የመከላከል ጥሪ” ገዢውም ፓርቲም ሆነ መንግስታዊ መገናኛ ብዙኃን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው፣ ጉዳዩ ከሰው ልጅ ሞት በፊት መፍትሔ በመስጠት መፍታት ሲቻል፣ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተወደሰውና የሕዝብ ንቁ ተሳታፎ የታየበት ምርጫችን በሰላሳ አምስት ሰዎች ሞት “የመጀመርያው ምርጫ ተጭበርብሯል” ጥያቄ ተደመደመ፡፡ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ሕዝብን ከማንኛውም ያልለተፈለገ ጉዳት ለመከላከል ሲባል የመንግስትነት ሚናውን ተጠቅሞ ቅንጅትን ወደ መድረክ ከመሳብ ይልቅ የታጠቀ ሃይሉን ተገን አደርጎ ሰዓት ቆጠራ ውስጥ በመግባቱ፤ በሌላ በኩል ቅንጅቶች ካለፈው ስህተታችን ተምረን ውስጣዊ ልዩቶቻችንን በማጥበብ ያለቅድመ ሁኔታ ለውይይትና ለድርድር በራችንን በመክፈት የጥሪያችንን ጥቅምና ጉዳት በቅጡ ከማስላት ይልቅ በድጋሚ ሕዝብን ከለላ አድርገን ጥቅምት 20 ቀን 1998 ዓ.ም የጠራነው ሕዝብዊ አድማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጎ በአሳዛኝ ውድቀት ሁለተኛው ምዕራፍ ተዘጋ፡፡ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር ፡፡ ኡኡታችን ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ቀረ ኬንያ እ.ኤ.አ ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ ሞይ ኪባኪን አሸንፌያለሁ በማለት ቃለ መሐላ ፈጸሙ፡፡

በምርጫው ተሸንፈሃል የተባለው ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት ውጤቱ የተጭበረበረ ነው በማለት የብሄርና የጎሳ መስመርን ተከትሎ በቀሰቀሰው ሕዝበዊ አመጽ ከፍተኛ የሆነ ግድያና የንብረት ውድመት ተከተለ፡፡ በተለይ የኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት መሪ በሆኑት በራይላ ኦዲንጋ ትውልድ ቦታ፣ በናይሮቢ ቁጭራዎች (slums) እና በሪፍት ቫሊ ክልሎች ውስጥ የተቀጣጠለው አመጽ የኩኩዩ ጎሳዎችን ለከፍተኛ ጥቃት ዳረገ፡፡ ሁከቱ ማንንም አልማረም፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም የኦዲንጋ ደጋፊዎች የነበሩት የሎዎና የካሊንጄ ጎሳዎች የአመጹ ሰለባ ሆኑ፡፡ ሂደቱ በመቀጣጠልም በሞምባሳ የተፈጸመውን የሙስሊም መሪ ግድያ መንስኤ በማድረግ በርካታ ሙስሊሞች አመጹን ተቀላቀሉት፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በምርጫው የተካሄደውን ማጭበርበር በመቃወምና የራሳቸውንም አጀንዳ በማከል ሰልፍ ወጡ፡፡ አጠቃላይ ሂደቱን ተከትሎ ፖሊስ ባካሄደው መጠነ ሰፊ ጫናና አፈና በርካቶች ተገደሉ፡፡ ዓለምን ባስደነገጠ ደረጃ ፖሊሶች በጋዜጠኞች ካሜራ ፊት ዜጎቻቸውን ተኩሶ እስከመግደል ግዴለሽ ሆኑ፡፡ በዚህ ድርጊታቸውም በአጠቃላይ ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ዜጎች ሕይወት ተቀጠፈ፡፡ የግንቦት 7 ቀን 1997 ምርጫን ተከትሎ ሰኔ 1 ቀን 1997 ከቅንጅት ድርጅታዊ እውቅና ውጭ በሕዝብ ተነሳሽነት የተለኮሰው ምርጫ ተጭበርብሯል አድማ፤ የምርጫው አጠቃላይ ሂደት ገና ሃያ አምስት ቀን ሳይሞላው የተካሄደ ነበር፡፡ የኬንያው ደግሞ የምርጫው ሂደት ገና ሃያ ስድስት ቀን እንኳን አላስቆጠረም ነበር፡፡ ማንም ሊረዳው በሚችል ደረጃ መታዘብ እንደሚቻለው የቀኖቹ ማጠር የሚሰጠው ትርጉም ቢኖር ለሰላም፣ ለሃገርና ለሕዝብ ደህንንነት ሲባል ድርድርና ውይይት ምንኛ እድል ተነፍጎት እንደነበረ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ አጀንዳ ባለመሆኑ በጥልቀት ባልገባበትም ምርጫ 97 እና የኬኒያ የ2007 ምርጫዎች በርካታ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ሆኖም ግን የሁለቱም ጎረቤት ሃገሮች ምርጫዎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር በሁለቱም ምርጫዎች ላይ ከፍተኛ ድምጽ መጭበርበር የተካሄደባቸው መሆኑ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግስት የሕዝብ ግንኙነቷ ጄንዳይ ፍሬዘር የኬኒያን ምርጫ አስመልክታ በወቅቱ የተናገረችው በሁለቱም ሃገሮች ለነበረው ሂደት በመረጃነት ሊጠቀስ የሚበቃ ፍሬ ሃሳብ ነው፡፡

“ኬንያዊያኖች በፖለቲካ መሪዎቻቸውና በዴሞክራሲያዊ ተቋማቶቻቸው ሲጭበረበሩ ኗረዋል” የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው እውነትም አፍሪካውያንን የፖለቲካ መሪዎቻችንና የዴሞክራሲያዊ ተቋሞቻችን ሲዋሹንና ሲያጭበረብሩን መኖራቸውን ነው፡፡ በምርጫ ዘጠና ሰባት የነበረውን ድምጽ ማጭበርበር በሚመለከት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ሆነ በአሜሪካኖቹ ዘንድ ጠንካራና ግልጽ አቋም ባይወሰድም በወቅቱ የዴሞክራቶች ሴናተርና የኢትዮጵያ አፍቃሪ የነበሩት ጥቁሩ አፍሪካዊው ዶናልድ ኤም ፔይን የተናገሩት ስለሂደቱ ጠቋሚ ነበር፡፡ “… ቅንጅት መንግስት ለመሆን የሚያስችለው ድምጽ ባያገኝም በርካታ ወንበሮችን መጭበርበሩን ግን እናምናለን፡፡” የሚል ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን በነጻና በገለልተኛነት መንፈስ ሕዝብን የማገልግል አቅም ማጣትን በሚመለከት ብቻውን ርዕስ የሚሆን ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይ ጽሁፌ ልመለስበት እሞክራለሁ፡፡

ለተሞክሮ ያህል ግን የምርጫ ቦርድን ለጊዜው ትተን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃኑ የሰኔ አንዱን አድማ አስመልክቶ ቅንጅት ለማስተባበል የወሰደውን አቋም ሳያስተላልፉ በመቅረታቸው አደጋውን ለመከላከል አጋዢ ለመሆን አለመፈለጋቸው ሁነኛ ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህ ርዕስ መንስኤ የሆነኝ ኢትዮጵያና ኬኒያ አሳዛኝ በሆነ መንገድ ከተጠናቀቀ ምርጫዎቻቸው ምን ተማሩ የሚለው ጥያቄ ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ ኬንያ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስም ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ ጅምሮ በሃገሪቱ ባልታየ ሁኔታ ዓለምን ያሸበረ፤ ብሄርና ጎሳን መሰረት አድርጐ የተካሄደ የእርስ በርስ መተላለቅን ካስተናገደች በኋላ ኬንያዊያን ከእንቅልፋቸው በመንቃት እራሳቸውንና ተጨባጭ ሁኔታውን በጥሞና ለመገምገም እድል እንዳገኙ የዘንድሮው ምርጫ ምስክር ነው፡፡

ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለውም በልዩነት ሃሳቦችና በተቃዋሚዎች ላይ ስልታዊ አፈና በማካሄድና ምህዳር በማጥበብ የሕዝቡ ሉዓላዊነትና ይሁንታ የሚረጋገጥበትን ምርጫን ተአማኒነት ያለው ማድረግ እንደማይቻልና በዚህ መንገድም ዘለቄታ ያለው መፍትሄ መፍጠር እንደማይችል ተገንዝበዋል፡፡ አሸናፊውም ተሸናፊውም ከነውጤታቸው በሰላም ለቀጣይ ሂደት ተዘጋጅተዋል፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ተጽእኖ ውጭ በመሆኑ የተጠረጠረው በተፎካካሪው ሳይሆን በተሸናፊው ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ኬንያዊያን ምርጫ 2007ን ተከትሎ የተከሰተው ምስቅልቅ ቀን ቆጥሮ ዘመን ተሻግሮ ዳግም በተለያየ መልክ እንዳይከሰት መፍትሔ ሰጥተዋል፡፡ መፍትሔው ግን መንግስታዊና ሕጋዊ ብቻ አልነበረም፡፡

ፍትሀዊና ሚዛናዊም ጭምር ነበር፡፡ በብሔራዊ መግባበት መንፈስ ውስጥ ሆነው ይቅር ለአምላክ ተባብለዋል፡፡ በወቅቱ የጋራ መንግስት ከመመስረት ጀምሮ ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን በሰላማዊ ጐዳና ለማራመድ የረዳቸውን ሕገ መንግስታዊ መሻሻል አድርገዋል፡፡ በእርስ በርስ መተላለቃቸው የተደናገጠውንም የዓለም ሕብረተሰብ በተቃራኒው እጅግ ባስደመመ የድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት፣ የተማከለ ስልጣንን በተዋረድ ያደላደለ ክፍፍል ከማድረጋቸውም በላይ የሃገራቸውን ቢል ኢፍ ራይትን ማጽደቅ ችለዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ በዚህ ወር ባካሄዱት ምርጫ ሕዝቡ የተጫወተው ሚና እጅግ አስደናቂ ነበር፡፡ እጅግ ጨዋነትና ስነስርዓት በተሞላው ትዕግስት በውስጡ አሳድሮ ለሚቀጥለው አምስት አመታት ለሚመራው መንግስት ይሁንታውን በፍላጎቱና ያለጎትጓች ሰጥቷል፡፡

ከሁለቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጡትን የማነሳሳትና ለአመጽ የማቀባበል ቅድመ ዝግጅቶች ተቋቁሞ፤ ነጻና ገለልተኛ የሆነው የምርጫ ቦርድ የሚገልጠውን ውጤቱን በትዕግስት ጠብቋል፡፡ ውጤቱ በ50.03 ፐርሰንት በኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊነት መጠናቀቁ ከተረጋገጠም በኋላ ኬንያዊያን እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ ለማንኛውም ሃይል ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሳይሆን የሃገራቸውን ሰላም፣ የራሳቸውንና የቀሪውን ዜጋ ደህንነትና ማስከበር ችለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ የተቻለው ኬንያዊያን ከሌሎች ዜጎች የተለየ ሰብእና ስላላቸው ወይም ሌላ እኛ ያልደረስንበት ስውር ምክንያት በመኖሩ አይደለም፡፡ ዋናው ቁም ነገር እራሳቸውን ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብትና ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተገዢ ማድረግ መቻላቸው ብቻ ነው፡፡

የሚያካሂዱት ምርጫ መገለጫው ወቅቱን የጠበቀ መሆኑ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተረድተዋል፡፡ ግልጽነት የተሞላበት፣ ያለ ተጽእኖ በነጻነት የሚካሄድና በሁሉም ዜጎች ዘንድ ተአማኒነትና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማድረግ ለሃገራቸው ዘለቄታዊ ሰላምና እድገትን ለማምጣት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ተረድዋል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋሞቻቸውም ታማኝነታቸውን ለመንግስት ሳይሆን ለሕዝብና ለስርዓቱ እንዲሁም ለሕሊናቸው ማድረግ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስንመለስ ምርጫ 97 ትልቅ የሆነ መስዋእትነት አስከፍሎን ከባድ ጠባሳን አሳድሮ አልፏል፡፡ ከዛ ሂደት የተማርነው ነገር ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ ግን የምናገኝው መልስ ከኬንያውያን ተሞክሮ ፍጹም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግሩን በጋራና በጥልቀት ፈትሸን በችግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ለችግሩ መንስኤ በነበሩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ አልቻልንም፡፡ በዚህም ምክንያት ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አልተቻለም፡፡ በተቃውሞም ሆነ በገዢ ፓርቲው ጎራ ተሰልፈው ለመብታቸው የታገሉ ዜጎች በሙሉ እኩል ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ተዘንግቶ ጉዳዩ የአሸናፊናነትና የተሸናፊነት መልክ እንዲይዝ ተደርጎል፡፡

አሸናፊው ገዢ ፓርቲ ተፋራጅ፤ ተሸናፊዎቹ ተፈራጅ ሆነዋል፡፡ መንስኤዎቹና አጠቃላይ ሂደቱ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ችግሮቹ ብቻ ተነጥለው እንዲወጡ ተደርጎ ሂደቱ በፍርድ ቤትና አስተዳደራዊ መንገድ እንዲታይ በመደረጉ ሕዝብ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማቱ፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ መማር የሚገባንን መሰረታዊ ትምህርት መማር ሳንችል ቀርተናል፡፡ ገዢው ፓርቲ ለችግሩ ብቸኛው መፍትሔ ዴሞክራሲውን ማስፋት፣ የሁሉንም ተቀናቃኝ ሃይሎች ንቃተ ሕሊና ማሳደግና አቅምን ማጎልበት መሆኑን ለመቀበል አዳግቶታል፡፡ ይልቁንም ከማን እንደሆነ ባይታወቅም ዴሞክራሲውን መከላከል በሚል አደናጋሪ አቋም በመዳከር ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተከታታይ ምህዳሩን የሚያጠቡ እርምጃዎችን መውሰድን መርጧል፡፡ ምህዳሩ የበለጠ ሰፍቶ በመማማርና በመተራረም ቀጣዩን ምርጫ ሕጋዊ፣ ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ባለመቻሉም ምክንያት መድብለ ፓርቲም ሆነ የልዩነት ሃሳብ እንዲዳከሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የስርጭት ሰዓታቸው ቢያድግም ዲሞክራሲውን ከማጎልበት ይልቅ አዞና ዝንጀሮ ማሳየትን ከፍተኛ ዋጋ በመስጠታቸው የውይይትና የክርክር መድረኮቹ በዛው ልክ ጠበዋል፡፡ ዜጎች አማራጭ ሃሳብ የማዳመጥ እድላቸውን በዛው ልክ ተነፍገዋል፡፡

እንደ ጸረ ሽብርተኛነት ያሉ የማያፈናፍኑ በርካታ ሕጎችም ባለፉት ጥቂት ዓመታት መደንገጋቸው ይበልጥ የሃሳብ አፈናውን አጠናክረውታል፡፡ ከዚህ ሂደት የተገኘው ፋይዳ ቢኖር ገዢው ፓርቲ ብቸኛው የልማቱ፤ የዴሞክራሲውና የተቋማቱ ተጠቃሚና የመገናኛ ብዙሃን ተዋናይ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ዛሬም በፍጥጫና በጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ እየዳከርን እንገኛለን፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ምን ይፈጠራል በሚል ስጋት ዜጎቻችን የሚሳቀቁበት ሁኔታ አልተቀረፈም፡፡ ተመዝገብ ፤ አትመዝገብ፡፡ ምርጫው ነጻ ነው፤ ነጻ አይደለም፡፡ ምረጥ፤ አትምረጥ፡፡ የሚሉት ገመድ ጉተታዎች ሕዝቡ በምርጫ ላይ ሊኖረው የሚገባውን እምነት እንዲያጣ እየገፋፉት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ የምርጫና የመድብለ ፓርቲ ስርዓታችን ምን ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡ ምናልባት ተቃዋሚዎች ወይም ሕዝቡ በከፊልም ይሁን በሙሉ በምርጫው አተካሮ ተሰላችቶ ከሜዳው በመውጣት ምርጫው ኢህአዴግ ከኢህአዴግ ጋር የሚወዳደርበት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ሕዝቡ ተቃዋሚዎችንና ገዢውን ፓርቲ አግልሎ ትግሉን ሊረከበው ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎች ክስተቶችን መተንበይ ይቻላል፡፡ ፋይዳው ግን ይህ አይደለም፡፡

አዲስ ስርዓት ለመገንባት አብዛኛውዜጋ ዝግጁ አይደለም፤ ፍላጎትም የለውም ፡፡ ይህ ማለት ግን ያለው ስርዓት አሳታፊ እንዲሆን አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡ የምርጫ ስርዓታችንን ለማደስ ዛሬም እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምርጫ 2007 እየደረሰ ነው፡፡ እንደ ኬንያውያን አለምን ለማስደመም ይቻላል፡፡ አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መደርደር ይቁም! የሃያ አንድ ዓመት የምርጫ ጉዞአችንን እንፈትሽ፡፡ ዛሬ የት ነው ያለነው ፡፡ የት መድረስ ነበረብን፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምቻለው ነገር ግን ኢህአዴግ ከተሳትፎ ወደ ውድድር ከውድድር ወደ ፉክክር የሚወስደውን መንገድ እስካሁን እንዳልመረጠ ብቻ ነው፡፡

Read 3221 times