Saturday, 16 March 2013 11:05

“እንደ ጎረቤቴ ሳይሆን እንደ ቤቴ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ! ጿሚዎች እንዴት ይዟችኋል! ለነገሩ እኮ እዚህ አገር ጾም …አለ አይደል…እንደ ሁሉ ነገር ‘የጭብጫቦ’ ነገር እየመሰለ ነው፡፡ እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…የጋብሮቮዋ ሚስት ባሏን… “ሾርባ ውስጥ ምን ያህል እንቁላል ልክተት?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ ባልም “ዛሬ በዓል ስለሆነ ግማሽ እንቁላል ክተች” አላትላችሁ። እናማ….ግማሽ እንቁላል ስለመጠቀም ልናስብ በሚገባን ዘመን…አለ አይደል… ይሄ “ከማን አንሼ…” የሚሉት የማይለቀን ነገር እያስቸገረን ነው፡፡ ሁሉም ነገር “ከማን አንሼ…” ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡ ልክ ነዋ…እንቁራሪቷ እኮ በ“ከማን አንሼ…” ነው በሬውን አክላለሁ ብላ ‘ጧ!’ ብላ ያረፈችው፡፡ እናላችሁ… ብዙ ነገር ‘በሬውን የማከል’ ሙከራ አይነት እየሆነ ነው። ምን መሰላችሁ…ድሮም እንዲህ አይነት የ“ከማን አንሼ…” ነገር ነበር፡፡

ዘንድሮ ግን በጣም ነው የበዛው፡፡ በስነጥበብ በሉት፣ በንግድ በሉት፣ በጉርብትና በሉት፣ በ‘ቦተሊካ’ በሉት…“ከማን አንሼ…” አገር እያመሰ ነው፡፡ እናላችሁ…ይሄ የ“ከማን አንሼ…” ነገር በሆድም እየመጣ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በቅበላ ‘ዊክኤንድ’ ከተማዋን ነገሬ ብላችሁልኛል? የምር…የነበረው ነገር እኮ የማህበራዊ ኑሮ ጠበብቶችና ኤኮኖሚስቶች አይነቶቹ ባለሙያዎች እንኳን ሊያብራሩት የሚያስቸግር ነበር። በማግስቱ ጾም የሚገባ ሳይሆን በማግስቱ “ነገ ይንጋ እንጂ ሁልሽም በሰማይ ቤት ፍርድ ትቀርቢያታለሽ…” የተባልን ነው የሚመስለው፡፡

(“አሁን ያለንበትን የሴልፊሽነት ዘመን የሚያሳይ ነው…” ያልከው ወዳጄ…አሪፍ ሀሳብ ነው ያነሳኸው፡፡) እኔ የምለው…መቼም እዚህ አገር “እንሠራዋለን…” እየተባለ የማይፎከርበት ነገር የለም አይደል… ባንክ ገንዘብ እንደሚቀመጥ ሁሉ በጾሙ ወራት ‘የዳሌን ወርድና ቁመት ጠብቀን የምናቆይበት’…አለ አይደል…‘ተቀማጭ ሥጋ’ ሰውነት ውስጥ (እንደ እህል ጎተራ) የማስቀመጫ ጥበብ እየተሞከረ ነው እንዴ! አሀ…ግራ ገባና! እናማ…የየሉካንዳ ቤቱና የቁርጥ ቤቱ ሰልፍ እኮ የዚህ የአዲሱን የመብራት፣ ውሀ ምናምን ክፍያ ሰልፍ ሊመስል ምንም አልቀረው! ስሙኝማ…አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ይሄ ሁለት ዲጂት፣ ምናምን ዲጂት ዕድገት አይነት ነገር የሚሉን ይሄን፣ ይሄን ሁሉ እያዩብን ሳይሆን አይቀርም፡፡

እናማ…ድፍን አዲስ አበባ ውስጥ በቀደም የነበረውን ሰልፍ ያየ ይቺን አገር የማያውቅ ሰው “ይሄ ሁሉ ሰው ሥጋ እየተመገበ ቸገረን፣ አንጀታችን ደረቀ ምናምን የሚሉት ማንን ለማሳሳት ነው!” ሊል ይችላል፡፡ ጾምን…አለ አይደል…ዘና ብሎ መቀበሉ ምንም ችግር የለውም ነው፡፡ ግን የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ ወደ አንድ ቤተሰብ የወር በጀት እየተቃረበ ባለበት ጊዜ ‘ለሥጋ መጋፋት’ የሆነ የማይመች ነገር አለው። አንዳንዴ እኮ ለእኛ ብቻ ብለን ሳይሆን ለሌላውም ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ 2012 የሚሉት የዓለምን መጨረሻ የሚያሳየው ፊልም አይታችሁልኝማል? እናማ…አንዳንድ ጊዜ ነገረ ሥራችን ልክ እዛ ፊልም ላይ እንዳለው ይቺ የእኛዋ የዓለም ክፍል በማግስቱ የሚያበቃላት ይመስላል፡፡

በ‘አገር ሰላም’፣ በችግረኝነቷ ክፋት ‘ሴሌብሪቲ’ ነገር በሆነች አገር… ይሄ ሁሉ የሥጋ ሰልፍ አስቸጋሪ ነው፡፡ (‘መስገብገብ’ የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ሙከራዬን ልብ በሉልኝማ…) አንዳንዴ እኮ “በእንትን ከአፍሪካ አንደኛ…” “በእንትን በዓለም ብቸኛ…” ምናምን እንደምንለው…አለ አይደል… “ጾም ሲገባ በየሉካንዳ ቤቱ በሚጋፋው የሰው ብዛት ከዓለም ምናምነኛ…” የሚል ነገር መጨመር የፈለግን ይመስላል፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ… በኮሚኒስት ሩስያ ጋዜጦቹ ሁልጊዜ ራሳቸውን በሁሉም ነገር ቀዳሚ ያደርጋሉ። እናማ… “በኦሎምፒክ ምርጦቹ ስፖርተኞች የሩስያ ስፖርተኞች ናቸው…” “በጠፈር ላይ የመጀመሪያው ሰው ሩስያዊው ዩሪ ጋጋሪን ነው…” “በዓለም ላይ ምርጡ ታንክ በሩስያ የተሠራ ነው…” “ከዓለም ሰፊዋ አገር ሩስያ ነች…” “ከዓለም ቀዝቃዛው ክረምት በሳይቤሪያ ነው…” “እጅግ የተዋጣላቸው ኑክሌር መሣሪያዎች የሩስያ ናቸው…” እና በሩስያ ሁሉም ነገር ምርጥ ነበር፡፡ እናላችሁ…አንድ ጊዜ የዓለም በጣም አጫጭር የሆኑ ሰዎች ውድድር ይደረግና አገራት እጅግ አጭር የሚሏቸውን ተወዳዳሪዎቻቸውን ያመጣሉ። ታዲያማ…በውድድሩ መክፈቻ ላይ የሩስያው አምባሳደር እንዲህ የሚል ንግግር አደረጉ…“ክቡራንና ክቡራት የዓለም ትልቁ አጭር ሰው ሩስያዊ ነው፡፡”

እናማ “ከዓለም አንደኛ…” “ከዓለም ብቸኛ…” ምናምን የሚል አባዜ እዚህ ያደርሳል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን ‘ዓይነ ደረቅነት’ ለሁላችን ‘ኮመን ኮርስ’ አይነት ነገር ከመሆኑ በፊት እዚህ አገር ‘ይሉኝታ’ የሚባል ነገር ነበር፡፡ እናማ…ይሉኝታ ሲበዛ ጥሩ ባይሆንም አንዳንዴ ደግሞ ሌላውን ላለማስከፋት፣ አደብ ለመግዛት፣ ማህበራዊ ኑሮን ላለመረበሽ ምናምን አሪፍ ነው፡፡ እናማ…ያን ጊዜ ጾም ለ‘ባላንስድ ዳየት’ የመጣ “አንጸባራቂ ዕድል…” ባልነበረበት ዘመን ሽፍንፍንፍ የሚሉት ምግብ ነበር፡፡ እንግዲህ ያን ጊዜ በጾም ወቅት የሥጋ ተዋጽኦዎችን ሲበላ የታየ ሰው…አለ አይደል…ከአገር ክህደት ያላነሰ አይነት ‘ወንጀል’ ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ እናማ…መብላት የፈለገ ሰው ሳያየው ለመብላት ሆቴል ገብቶ ምን ያዛል መሰላችሁ…“ሽፍንፍን!” እናላችሁ…ቋንጣ ፍርፍር እየፎከረች “ዱታው ዘራፍ…” እያለች ሳይሆን አደብ ገዝታ፣ ጨምታ፡ በእንጀራ ተሸፋፍና ‘አይዴንቲቲዋን’ ሰውራ ትመጣለች፡፡

ሰውየውም ያማረውን ምግብ ይበላል፣ ሌላው ሰው የሚያስከፋውን ነገር አያይም፡፡ ስሙኝማ…ይቺን ነገር አውርተናት ከሆነም እንድገማትማ፡፡ ሰውየው ሉካንዳ ይሄድና “ባለ ሉካንዳ እባክህ ለውሻ የሚሆን የአምስት ብር ሥጋ ትሰጠኛለህ…” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ እናማ የሥጋ ዋጋ እዛ ላይ በናረበት ዘመን ‘የአምስት ብር ሥጋ’ በመጠየቁ ባለ ሉካንዳው ይናደዳል፡፡ እናላችሁ… ምን ቢለው ጥሩ ነው…“በወረቀት ልጠቅልልህ ወይስ እዚሁ ትበላዋለህ?” (ምን ያድርግ ከዚህም እየቀነጠበ፣ ከዛም እየቀነጠበ ትከሻውን ልክ የበሬውን አሳክሎ!) እናማ…በቅበላ ቀናት ጠቅለሎ የሚወስደውም፣ እዛው ተቀምጦ የሚበላውም ሰው ብዛት ሲታይ…አለ አይደል… “ይሄ ሁሉ ሰው እንዲህ እንደ ልቡ ብሩን የሚመነዝረው ገንዘቡን ከየት ነው የሚያመጣው?” ያሰኛል፡፡ እናላችሁ…መቼም ዘንድሮ በየጓዳችን እየኖርናት ያለናትን ኑሮ በዝርዝር ባይሆንም እንኳን በጥቅሉ ሁላችንም እንተዋወቃለን፡፡

እንደምንም በምኑም በምናምኑም ከወዛው ፊታችን ጀርባ ያለውን እውነተኛ ታሪክ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እናማ… ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ…” ሆኖ ሳለ ይሄ የአደባባይ “ግነን በሉኝ…” ልማድ ሆኖብን ነገራችን ሁሉ ‘ቲራቲር’ ሆኖ ቀረ፡፡ እናማ በዚች፣ በዚች እንኳን ማንንም መሸወድ የማይቻልበት ዘመን ስለሆነ ራስን መሆንን የመሰለ ነገር የለም፡፡ የበቀደሙ የሥጋ ቤት ግፊያ ለአብዛኞቻችን ፊትን በአደባባይ ማውዛት ነው፡፡ እናማ…ሁሉ ነገር በልክ ቢሆን አሪፍ ይሆናል፡ አንድ ቀን በአደባባይ ወዛ ብለን ለመታየት አንድ ወር ሙሉ ለምን አመድ ይነዛብናል! እግረ መንገዴን…“እባክህ ለደሞዝ የምመልስልህ ብር ካለህ…” ልትሉ እያኮበከባችሁ ያላችሁና በቀደም ሉካንዳ ቤት ስትጋፉ የነበራችሁ ወዳጆቻችን… ለጊዜው ለወዳጅ ብድር የመስጠት አገልግሎት ማቆማችንን እወቁልንማ፡፡ (እኔ የምለው …ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ከአበዳሪነት ወደ ተበዳሪነት ወረደ ልበል! አይደለም ብር የሚያበድር ሲጋራ ‘የሚያስወጋ’ ወዳጅ ማግኘት እንኳን አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ነው፡፡) አንድ ሰውዬ ጫካ ውስጥ እየተጓዘ ሳለ ከጀርባው የአንበሳ ድምጽ ይሰማል፡፡ እናላችሁ… “አምላኬ ይህ የሚጮኸው አንበሳ በልቶ የጠገበና ከእንግዲህ ምንም መብላት የማይፈልግ እንዲሆን አድርግልኝ…” ሲል ይጸልያል፡፡ አንበሳው ደግሞ ምን ብሎ ቢጸልይ ጥሩ ነው፣ “እንዲህ እርቦኝ ሳለ የምበላውን ምግብ አጠገቤ ድረስ ስላመጣህልኝ ምስጋና ይግባህ፡፡” ቢርበንም፣ በልተን ብንጠግብም “እንደ ጎረቤቴ ሳይሆን እንደ ቤቴ አኑረኝ!” ብለን ለመጸለይ ያብቃንማ! ደሀና ሰንብቱልኝማ!

Read 2957 times