Saturday, 16 March 2013 11:03

የትራንስፖርት ችግር በአጭር ጊዜ አይፈታም

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

በከተማ አውቶቡሶች ከመደበኛው ተጓዥ በላይ ከጫኑ ለሾፌሩና ለረዳቱ ኮሚሽን ይከፈላል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየው የትራንስፖርት ችግር ለዘመናት የቆየና የተወሣሰቡ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሊፈታ ይችላል ተብሎ እንደማይገመት ተገለፀ፡፡ ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈለቀ ኃይሌ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ላይ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ይስተዋላል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍና ህብረተሰቡ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እንዲችል የማድረጉ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን በጊዜያዊነት ሊፈታ የሚችልና የትራንስፖርት አቅርቦቱን የሚያሻሽሉ አንዳንድ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በከተማ ውስጥ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት አውቶብሶች በሙሉ አቅማቸው እንደማይሰሩ የገለፁት ቢሮ ሐላፊው፤ ይህም በመለዋወጫ እቃዎች እጥረትና በቴክኒሽያኖች ለስራ ዝግጁነት ማጣት ምክንያት ይፈጠር የነበረ ችግር ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ጥረት ተደርጐ በአሁኑ ወቅት 720 የሚደርሱ የከተማ አውቶቡሶችን አስተካክሎና ዝግጁ አድርጐ ወደ ስራ እንዲሰማሩ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በ20 የመንገድ መስመሮች ላይ የዋጋ ተመንን ዝቅ በማድረግ የአጭር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የገለፁት ኃላፊው፤በእነዚህ እርምጃዎች የከተማ አውቶቡሶች በቀን ያጓጉዙት የነበረውን 360ሺ መንገደኛ አሁን ወደ 500ሺ ከፍ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ የአውቶቡስ ሹፌሮችንና ረዳቶችን ለማበረታታትና ለስራቸው ፍላጎትና ታታሪነት እንዲያድርባቸው ለማድረግ በማሰብም በመደበኛነት ከሚያጓጉዙት ተጓዥ በላይ በሚያሳፍሩበት ወቅት ኮሚሽን ወይም ማበረታቻ ለመክፈል የሚያስችል አሰራርም በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደተጀመረ አቶ ፈለቀ ገልፀዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ከአቅም በላይ በመጫን በህብረተሰቡ ጤናም ሆነ በአገር ንብረት ላይ ጉዳት አያስከትልም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ይህ እንዳይሆን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋና የሰራተኛው ኃላፊነት ዋናውን ቦታ እንደሚይዝ ጠቁመው “ሠው ከሚጉላላ ተጨናንቆ ቢጓጓዝ ይሻለዋል” ብለዋል፡፡ 25 አውቶቡሶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የከተማ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ ይንቀሳቀስ የነበረው አሊያንስ ትራንስፖርት፤ እስከ ዛሬ ድረስ ስራ ለመጀመር ያልቻለበትን ምክንያት አስመልክተው አቶ ፈለቀ ሲናገሩ፤ ኩባንያው ለቢሮው ጥናቱን ባቀረበበት ወቅት 100 አውቶቡሶችን በቅድሚያ ለማስገባትና ስራ ለመጀመር አስቦ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የቻለው 25 አውቶቡሶችን ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ለ100 አውቶቡሶች ተደርጐ የነበረውን ጥናት ወደ 25 አውቶቡሶች ለማውረድ የጥናት ክለሳ ስናደርግ ቆይተናል፡፡

ይህም ብዙ ጊዜ ወስዶብናል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አውቶቡሶችን ሊያስከፍሉ የሚችሉት የዋጋ ታሪፍ ተወስነው በመጠናቀቁ በ5 መስመሮች በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ በከተማ ውስጥ ከ60 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ እንደሆነ የገለፁት ኃላፊው፤ የነዚህ መንገዶች ግንባታ በተለያዩ ስፍራዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡ ይህንን የትራፊክ መጨናነቅ ለማስቀረት በዋና ዋና መንገዶችና ጎዳናዎች ላይ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በከተማው የተለያዩ ስፍራዎች፣ የተሰሩ ሕንፃዎች ለመኪና ማቆሚያ ሰርተዋቸው የነበሩትን ቦታዎች ለካፌና ለተለያዩ የንግድ ስራዎች በማዋል የመኪና ፓርኪንግ አገልግሎቱን በመንገዱ ግራና ቀኝ ላይ እንዲሆን ማድረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ፈለቀ፤ እነዚህ ሰዎች የህንፃዎቹን የመኪና ማቆሚያ ቦታ ወደ ትክክለኛው አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው ልዩ ልዩ ስፍራዎች ላይ እየተከናወኑ ካሉት የመንገድ ግንባታዎች መካከል ወደ ስድስት ያህሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ ሐላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 4264 times