Print this page
Sunday, 03 March 2013 08:29

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(5 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ - ፯

ዛሬ ቺካጎ ገብቻለሁ፡፡ ለስደተኛ ጋዜጠኛ ወዳጅ ጓደኞቼ ምስጋና ይግባቸውና ዘላለም ገብሬ የተባለው ጋዜጠኛ ወዳጄ ቺካጎን የረገጥኩ ዕለት ማምሻውን ነበር ከተማውን ሊያስጎበኘኝ ካረፍኩበት ሆቴል መጥቶ የወሰደኝ፡፡ እንደአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዘላለምም ከተማ ማስጎብኘትን የጀመረው ከሐበሻ ሬስቶራንት ነው፡፡ የትም ብትሄዱ የትም፣ ትላንት ከአዲስ አበባም ኑ ወርም አሜሪካ ቆዩ ኢትዮጵያዊ ወዳጅዎት እያንከወከወ የሚወስዶት እንጀራ ከሚገኝበት ምግብ ቤት ነው፡፡
የዘላለም ምርጫ በከተማው አለ የተባለው ‹‹ዳይመንድ ባህላዊ ሬስቶራንት›› ነው፡፡ ወደ ምግብ ቤቱ ስንዘልቅ ያለመፈናፈኛ በፈረንጆች ጢቅ ብሎ ሞልቷል፡፡ ከአስተናጋጆቹ ውጭ ያሉ ተመጋቢ ኢትዮጵያውያን ለዓመል ያህል ናቸው፡፡ ዐረፍ ብለን የልብ የልባችንን እየተጨዋወትን ለመመገብ ቤቱ አመቺ አለመሆኑን የተገነዘበው ዘላለም በቅርቡ ወደተከፈተ ሬስቶራንት ይዞኝ ሄደ፡፡ የገባንበት ቤት አዲስ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ ከአንድ ጠረጴዛ በስተቀር ሌሎቹ ሌጣቸውን ተደርድረዋል፡፡ ከዘላለም ጋር እራታችንን እየተመገብን የባጥ የቆጡን ስንቀባጥር ቆየን፡፡ በወሬያችን መካከል የደወለለት የቅርብ ጓደኛው ሲሳይ በስተመጨረሻ ተቀላቀለን፡፡
ከሲሳይ ጋር የተጀመረው ዝግ ያለው ጨዋታችን በሳቅ ለመታጀብ ደቂቃ አልወሰደበትም፡፡ ሲሳይ ጥርስ አያስከድኔ የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ ከአገሩ ከወጣ ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ዋና ሥራው ደግሞ ታክሲ መሾፈር ነው፡፡ የአሜሪካንን ኑሮ በትጋት እየተወጣ ያለው ሲሳይ ከላይ ታች ከመሮጡ ይልቅ አልለመድ ብሎ ያስቸገረው ቋንቋዋ ነው፡፡
‹‹ዱሮ አገር ቤት እያለሁ ከአሜሪካ በሚመጣ ሰው እንግሊዘኛ እቀና ነበር፡፡ እዚህ ስመጣ ደግሞ ከአገር ቤት በሚመጣ ሰው መቅናት ጀምሬያለሁ›› አለኝ ሲሳይ በቋንቋ ምክንያት ያየውን አበሳ ሊያጫውተኝ ሲጀምር፡፡ ‹‹መቀመጫዬ አሜሪካ ከኾነ በኋላ ይህንን እንግሊዘኛ እንደምንም እየሰባበርኩ አዲስ አበባ ከሚገኙ ከአንዳንድ ውብ ልጃገረዶች ጋር ቻት ለማድረግ ሞክሬ ነበር፡፡ እሱንም ቢሆን ማጣደፍ ሲጀምሩኝ ተውኩት›› አለኝ እየሳቀ፡፡
የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ በኾነበት አገር በቋንቋ እንደልብ ለመግባባት የሚያዳግታቸው ኢትዮጵያውያን የቋንቋ እጥረት እንዳለባቸው ሲሸፋፍኑ እንጂ በአገራቸው ሰው ፊት ችግር አለብኝ ብለው ሲናገሩ ስሰማ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ሲሳይ ድብቅ የሚባል ነገር የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ዘላለም የጓደኛውን ትረካዎች እየሰማ መሳቁን ተመልክቼ የሲሳይን ወሬዎች ቀልድ እንጂ እውነት የሆኑ ናቸው ብዬ ለመቀበል አዳገተኝ፡፡
በወሬ በወሬ ስለቤተሰብ ሲነሳ ሲሳይን እዚህ አዲስ አበባ የማውቀው የአንድ ድምፃዊ ወዳጄ ወንድም ኾኖ አገኘሁትና እንዲህ በቀላሉ የምንላቀቅ አልሆን አልን፡፡ የከረመ ድካሜ ግን በዚያን ምሽት ከዚያን በላይ ሊያቆየኝ ስላልቻለ ግብዣውን በይደር ማስተላለፌ ግድ ሆነብኝ፡፡
****************
የጉብኝቴ ነገር አላገጣጥም ብሎኝ የሲሳይ ግብዣ ሲገፋ ሲገፋ ቆይቶ በአንደኛው ምሽት እራት ለመብላት ጊዜ ተገኘ፡፡ አሁን ግን ግብዣው እንደቀድሞው ምግብ ቤት ሳይሆን በሲሳይ ቤት የተዘጋጀ ነበር፡፡ የኢትዮጵያዊ መኖሪያ ቤት ወደሚገኝበት ሕንጻ ጎራ ሲባል በሕንጻው ግቢ፣ መግቢያ ፣መውጫና አሳንሳር ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ በዘላለም መሪነት የሲሳይ መኖሪያ ቤት ወደሚገኝበት ሕንጻ ስንዘልቅም እንደተለመደው ሁሉ በአገራችን ልጆች ተወርሮ አገኘነው፡፡ የአንገት ሰላምታ እየሰጠን በአሳንሰር ወጥተን ወደ ሲሳይ ቤት በኮሪደሩ መሄድ ስንጀምር አፍንጫችን በወጥ ሽታ ታወደ፡፡ ሁሌም ሐበሾች በሚገኙበት ሕንጻ ውስጥ ከአንደኛው ቤት በወጣ የወጥ መዓዛ ኮሪደሩ ሊታወድ ይችላል፡፡
ሲሳይ በሩን የከፈተልን ነጭ በነጭ ለብሶ በሰንደቅ ዓላማ ቀለም የተሠራ ነጠላ አጣፍቶ ነበር፡፡ ለአክብሮቱ አመስግኜው ሶፋ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ የተሟላ ባህላዊ የቡና ሥነ ሥርዓት ማካሄጃ ቁሳቁሶች ከፊት ለፌቴ ተደርድረዋል፡፡ ጀበናው ከእነ ማስቀመጫው፣ ስኒ በረከቦት ቀርቦ ቤቱ በቡና ሽታ ታውዷል፡፡ አቀራረቡን ተመልክቼ ሲሳይ የትዳር አጋር ልትኖረው እንደምትችል ገመትኩ፡፡ በቤቱ ውስጥ ከእርሱ ውጪ ማንንም ባለማየቴ ግን በግምት ያለፍኩትን ጥያቄ ጠየኩት፡፡ ትዳር እንደሌለው ነገረኝ፡፡ ስኒውን እና ጀበናውን እያየሁ ‹‹ቡናውን ማን ሊያፈላው ነው?›› ስል ጠየኩት፡፡ ‹‹አንዲት ልጅ ትመጣለች›› አለኝ ‘ገባኝ’ በሚል ስሜት ወደ ሌላ ጨዋታ ተሸጋገርን፡፡
የፆም ዕለት በመሆኑ የተዘጋጀው የፆም ምግብ ነው፤ ሠሪው ደግሞ ሲሳይ፡፡ ምግቡን እያጣጣምን ሞያውን አደነቅንለት፡፡ እራት በልተን እንደጨረስን ሲሳይ የቀረበው ስኒ እና ጀበና አጠገብ ሄዶ ቁጭ አለ፡፡ ‘ምንም ዘመናዊ ሰው ነኝ’ ብልም ወንድ ልጅ ስኒና ጀበና ስር ተቀምጦ ያፈላውን ቡና ለመጠጣት ፈቃደኛ አልነበርኩምና እራሴው ለማፍላት ጠየቅኩ፡፡ ሲሳይ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ መቼም ሰው ቤት ተጋብዞ እምቢ አይባል ነገር!
ቡናው እስኪደርስ ዓይኖቼን ወደ ግድግዳዎቹ ላኳቸው፡፡ በርካታ ፎቶዎች ተሰቅለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሲሳይ ከአሜሪካኖች ጋር የተነሳቸው ፎቶዎች ነበሩ፡፡ ዐይኔ ያረፈበትን የተመለከተው ሲሳይ ሁሉም የየራሳቸው ታሪክ እንዳላቸው ነገረኝ፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ ከያዙ ሁለት ወጣቶች ጋር የተነሳውን ሳመላክተው በተዝናና ስሜት ‹‹ማናጀራቸው ነኝ›› አለኝ፡፡ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ልብስ ከለበሱ ሌሎች ጋር የተነሳውን ስመለከት ደግሞ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ አሠራር የሚያስተምራቸው እንደሆኑ ነገረኝ፡፡ ይሄኔ ሲሳይ ከታክሲ ሥራ ውጪ ዘርፈ ብዙ ባለሞያ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ቆይታችንን ያዋዛ ዘንድ የተከፈተው ፊልም ይህንኑ አረጋገጠልኝ፡፡
ፊልሙ አንድ የግለሰብ ቤት ውስጥ በሚገኝ ወጥ ቤት የተቀረጸ ነው፡፡ ወደ ስድስት የሚሆኑ የውጭ ዜጎች እየተንጫጩ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ ይሠራሉ፡፡ አስተማሪው ሲሳይ ነው፡፡ ጮኽ ብሎ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ መጀመሪያ ላይ እየቀለደ መስሎኝ ነበር፡፡ ንግግሩ በተመሳሳይ ሁኔታ እየቀጠለ ሲሄድ እና ልብ ብዬ ስመለከት የትውውቃችን ዕለት ስለቋንቋ አንስቶ ሲያወራ የነበረው ቀልድ እንዳልነበር ገባኝ፡፡
ሲሳይ ለፈረንጆቹ ሲያስረዳ የሚታየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቀጥሏል፡፡ ከሲሳይ አንደበት በማስረዳት መልክ የሚወጡት ቃላት በአጭሩ ሲገለጹ፤ “ካም፣ “ጎ”፣ “ስታንድ አፕ”፣ “ሲት ዳውን”፣ “ኢት”፣ “ብሪንግ ዛት”፣ “ ዚስ…. ሽሮ”፣ “ዛት…ሚት” የመሳሰሉ በግርድፉ የሚያግባቡ ቃላትን ነው፡፡ በሌሎቹ የአሜሪካ ግዛቶች በነበረኝ ጉብኝት ኢትዮጵያውያን በገበያ ቦታ እና በሥራ ቦታቸው በግርድፉ ሲግባቡ ብመለከትም እንደሲሳይ ፈረንጁን ሁሉ አሰልፈው ከዚህም ከዚያም በተሰበሰቡ ቃላት ሲመሩ ስላላጋጠመኝ ተገርሜ ዘላለምን ጠየቅኩት፡፡ ሳቅ ብሎ ጥያቄውን ወደ ሲሳይ ወረወረው፡፡
‹‹እየቀለድክ ነው?›› አልኩት፡፡
‹‹ምን እቀልዳለሁ፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ የእኔ እንግሊዘኛ ሆዴ ውስጥ ገብቶ ቦርጭ ነው የሚሆነው›› አለኝ፡፡
‹‹ ታዲያ እንዴት ነው አስተማሪ የሆንኸው?››
‹‹እነዚህኞቹ እውነተኛ ተማሪዎች አይደሉም፡፡ በፊት ዳይመንድ ሬስቶራንት እሠራ ነበር፡፡ አብዛኞቹን እዚያ ነው የተዋወቅኳቸው፡፡ በቃ አንዳንድ ጊዜ ቤቴ እጋብዛቸው እና እያሳየኋቸው አብረን ምግብ እንሠራለን›› አለኝ፡፡ እያቀያየረ የከፈተልኝን በርካታ ፊልሞች ተመለከትኩ፡፡ ከፊልሞቹ መካከል ያስገረመኝ በዳይመንድ ሬስቶራንት ተከናውኖ ነበረ ያለኝን የአንድ ዝግጅት ማስታወሻ ምስል ነው፡፡
በፊልሙ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ የውጭ ዜጎች ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያን የአገር ባህል ልብስ ለብሰዋል፡፡ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ ይበላሉ፣ ጠጅ ይጠጣሉ፣ በአማርኛ ዘፈን ልባቸው እስኪጠፋ ይጨፍራሉ፡፡ በተለይ ‹‹ያምቡሌ›› የተሰኘው የብርሃኑ ተዘራ ዘፈን ሲዘፈን የሚቀመጥ ፈረንጅ የለም፡፡ ተያይዘው እየዞሩ ይጨፍራሉ፡፡ ጭፈራው ሲፋዘዝ ‹‹ያምቡሌ….ያምቡሌ›› እያሉ ጮኸው መልሰው ያስከፍታሉ፡፡ ሲሳይ አብሯቸው ይጨፍራል፤ ዲጄም ሆኖ ያገለግላል፡፡
እንደነገሩኝ ከሆነ ሲሳይ እንዲህ ያለውን ዝግጅት በየዓመቱ ያዘጋጃል፡፡ የታዳሚው ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ የእርሱ ሥራ ማስተባበር ነው፡፡ በዕለቱ የሚገኙት እንግዶች የበሉ፣ የጠጡበትን ገንዘብ የሚከፍሉት እራሳቸው ናቸው፡፡ ሲሳይ ይህንን የሚያደርገው በዋናነት ባህሉን ለማስተዋወቅ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ በተጨማሪም ሰዎችን የማግባባት እና የማስተባበር ተሰጥኦ ስላለው በጣም በርካታ የውጭ ዜጎች በጓደኝነት ለማፍራት ችሏል፡፡
ይህንን ተሰጥኦውን ወደ ሞያ በመቀየር የዝግጅት አስተናባሪ (ኢቬንት ኦርጋናይዘር) ሆኖ የመሥራት ፍላጎት አለው፡፡ ለጊዜው ወጪ እንጂ ገቢ ባያገኝበትም መንገዱን ጀምሮታል፡፡ ቋንቋ ደግሞ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ‹‹አይ ቋንቋዋን በደንብ ባውቃትማ የአሜሪካን ሕዝብ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ልብስ አስለብሼ አሰልፌ እነዳው ነበር›› ሲል ይቆጫል፡፡ ከዚህ በኋላም የመልመድ ተስፋው ተመናምኗል፡፡
ከቡና ግብዣው በኋላ ‹‹ግሎባል ኢንስትሩመንት ኦፍ ቼንጅ›› በሚል ድረ-ገጽ ላይ ስለእርሱ የተጻፈውን አሳየኝ፡፡ ድረ ገጹ ‹‹…ሲሳይ ከስምንት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ የመጣ ስደተኛ ነው፡፡ ቺካጎ ተቀምጦ ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ የሚመጡ ወጣት ስደተኞችን ያግዛል፡፡ሲሳይ ከሰዎች ጋር መገናኘት ያስደስተዋል፡፡ የ‹‹ሆውሊንግ ፖፒስ ባንድ›› አባልና ማናጀር የሆነው ሲሳይ ለትርፍ ያልተቋቋመው ‹‹የላይፍ ሰከንድ ቻንስ ፋውንዴሽን›› አባል ነው…›› በማለት የሲሳይን በጎ ምግባሮች ይዘረዝራል፡፡ ያለ በቂ ቋንቋ ዕውቀት ከእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ጋር ተግባብቶ የተጠቀሱትን ተግባራት ማከናወን ከቻለ የበለጠ ለመሥራት ቋንቋውን ማሻሻል እንዳለበት ነገርኩት፡፡ ቋንቋውን ለማሻሻል ያልሞከረው ነገር እንደሌለ እየማለ ነገረኝ፡፡ ይህ ችግር ደግሞ የእርሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን አገር ቤት እያሉ ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው ዕድሉን ሲያገኙ ‹‹እዛው እማራለሁ›› ብለው ስለሚወጡ ከገቡ በኋላ ነገሮች እንዳሰቡት አያገኙትም፡፡ በተለይ ዩኒቨርስቲ ካልተገባ ቀስ እየተባለ በሥራ አካባቢ ያሉ የመግባቢያ ቋንቋዎች ከመልመድ ውጭ ጥንቅቅ ያለውን መልመድ በቀላሉ የሚቻል እንዳልሆነ አጫወተኝ፡፡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እርሱ እና እንግሊዘኛ ያላቸውን ትስስር ነገረኝ፡፡
****************
ሲሳይ አዲስ አበባ እያለ መርካቶ ውስጥ በአንድ የቆዳ ውጤቶች መሸጫ ቤት ውስጥ በሽያጭ ሠራተኝነት ይሠራ ነበር፡፡ ‹‹ሥራውን የምንሠራው ለሁለት ነው፡፡ እኔ ሰው ለማግባባት የተፈጠርኩ ይመስለኛል፤ ሽያጭ ይሆንልኛል፡፡ ግን ፍጥን ፍጥን የምለው ኢትዮጵያውያን ሲመጡ ነው፡፡ ፈረንጆች ከመጡ ለሥራ ባልደረባዬ ትቻቸው ፊቴን ዘወር አድርጌ ከቦታው እጠፋለሁ፡፡ አለቃችን የእኔ ፈጣን መሆን እንጂ ይቺን አያውቅም፡፡ አብሮኝ የሚሠራው ደግሞ ለቤቱ ከእኔ የቀደመ ሠራተኛ ነው፡፡ የድርጅቱን የሒሳብ ሥራም ይሠራል፤ ጎበዝም ነው፡፡ አንድ ቀን ከባለቤቱ ጋር ተጣሉ እና ሊያባርረው ሆነ፡፡ ችግሬን ስለማውቅ እንዳያባርረው ብለምነውም አልሆነልኝም ተባረረ፡፡ ባለቤቱ ቁልፉን ለእኔ ሰጠኝ እና በጠዋት መጥቼ እንድከፍት አዝዞኝ ወጣ፡፡
ጠዋት እንዲሁ እየተጨነቅኩ ሱቁን ከፈትኩ፡፡ ገና ጠራርጌ አስተካክዬ ሳልጨርስ ሁለት ፈረንጆች ዘው ብለው ገቡ፡፡ ሴት እና ወንድ ናቸው፡፡ ልጁ የላከብኝ ነው የመሰለኝ ደነገጥኩ፡፡ እንዳልኩሽ ከዱሮም ከረር ያለው እንግሊዘኛ ካልሆነ ቀለል ያለው የሚባለው ይገባኛል፡፡ የሚያጥረኝ አስተካክሎ መመለሱን ነው፡፡ አንዱን የቆዳ ጃኬት መርጠው ዋጋ ጠየቁኝ፡፡ መለስኩ፡፡ ‹‹ከምንድነው የሚሠራው አሉኝ?›› የት ልግባ? አሰብ አደረግኩና መላ አካላቴን ለምልክትነት እየተጠቀምኩ ‘ቱ ሺፕ’ አልኳቸው ‘ዋን ትራንስፖርት’ አልኩ በእጄ የመንገድ ምልክት እያሳየሁ ‘አናዘር ቱ’ አልኩና መሬት ላይ ተንበርክኔ ‘በአአ’ የሚል የበግ ድምጽ አሰማሁ ጃኬቱን በእጄ እየነካሁም ‘ዚስ ፍሮም በአአ’ አልኳቸው፡፡ እንደጉድ ሲመለከቱኝ ቆይተው ፍርስ ብለው ስቀው ጃኬቱን ገዝተው ሄዱ፡፡ በኋላም ብዙ ጓደኞቻቸውን ይዘው እየመጡ የቤቱ ደንበኛ ሆኑ›› አለኝ፡፡ ሲሳይ ለማስረዳት የፈለገው ጃኬቱ ከበግ ቆዳ መሠራቱን ነበር፡፡ የበግ እና የመርከብ ልዩነትን ለማስረዳት የተጠቀመበት ዘዴ ነበር፡፡
****************
ሲሳይ አሜሪካ ሲገባ ኑሮውን በቺካጎ ነበር ያደረገው፡፡ ከሠራቸው በርካታ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ፓርኪንግ ነው፡፡ ‹‹ዕድሌ ሆኖ ሥራውን ገና ሳለምደው እንደተቀጠርኩ አካባቢ ዋናው ጠባቂ ሁሉን ነገር አሳይቶኝ መጣሁ ብሎ ሄደ፡፡ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደድኩ ጭንቀቴን ለማውጣት እሞክራለሁ ከጥቂት ቆይታ በኋላ እንደው አንዲት ቅጥን ያለች ፈረንጅ በብስጭት እየተወራጨች ወደኔ መጣች፡፡ አኳኋኗን ዐይቼ የሚከተለው ቁጣ እና ስድብ መሆኑ ገብቶኛል ‘ኋት?’ አልኳት፡፡ ትሳደባለች፡፡ “መኪናዬን አስጫርኸው” ማለቷ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ምንም አለመሆኑን እንዴት ብዬ ላስረዳት? ሞከርኩ አልሆነልኝም፡፡ ልትረዳኝ አልቻለችም፡፡ ብቻ ትሳደባለች፣ ትጮሀለች፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ የት ልሂድ? ንድድም አለኝ፡፡ ለራሴ ለሥራውም ለአገሩም አዲስ ነኝ፡፡ በቃ ሥራው ጥዬ መሄድ አማረኝ፡፡ ‘ግን መኪናውስ ምን ሲሆን ተጫረ’ ብዬ ‘...ካም…’ እያልኩ ይዣት መኪናው ወዳለበት ሄድኹ፡፡ ነጭ መኪና ነው፡፡ ውድ ይመስላል፡፡ እንዳለችው ኮፈኑ ላይ የተጫረ ይመስላል፡፡ ምን ሊጭረው እንደሚችል ግራ ገብቶኝ በእጄ ነካ ነካ ሳደርገው ፍርፍር እያለ ተነሳ፡፡ ጠጋ ብዬ ሳየው ለካ ‘የወፍ አር’ ነው፡፡ ሌላ ነገር አለመሆኑ ደስ ብሎኝ ‘...ዚስ…’ ብዬ ለማስረዳት ስጀምር ከየት ላምጣው፡፡ ለካ ‘የወፍ አር’ ምን እንደሚባል አላውቅም፡፡ ቀና ብዬ በጣቴ ወደ ዛፉ እያሳየኋት ‘…ዚስ በርድ… ቱፍ…’ አልኳት፡፡ ሳቋን ማቆም አልቻለችም፡፡ እኔ ለማስረዳት እሞክራለሁ እርሷ በሳቅ ትንፈቀፈቃለች፡፡ በስተኋላ ንዴቷ በሳቅ አለፈላት፡፡ እኔም ተገላገልኩ›› አለኝ፡፡
****************
ሲሳይ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ገጠመኞቹ ማብቂያ የላቸውም፡፡ “ዳይመንድ ሬስቶራንት በምሠራበት ወቅት ነው፡፡ ዩኒፎርሜን እንደለበስኩ አንዱ ሶፋ መሰል መቀመጫ ላይ ፈልሰስ ብዬ ተቀምጫለሁ፡፡ ለካ አንድ 40 የሚሆኑ እንግዶች ቦታ አስይዘው ገብተው ተቀምጠዋል፡፡ እኔ የሥራ መጀመሪያ ሰዓቴ ገና ስለነበር ዞርም ብዬ አላየኋቸውም፡፡ እንደዚያ ቀብረር ብዬ የተቀመጥኩትም ለዛ ነው፡፡ እነርሱ በሥራ ሰዓት እንደዚያ የሚቀመጥ ሰው አይወዱም፡፡ በየሬስቶራንቱ አይተሸ እንደሆነ መስተንግዶ እንደ አገር ቤት አይደለም፡፡ ጠብ እርግፍ ተብሎ ነው እንግዳ የሚስተናገደው፡፡ በኋላ እንደገባኝ ከሆነ የእኔን እንደዚያ መቀመጠጥ ያላስደሰተው አንዱ ተነስቶ ወደእኔ መጣና ረዘም ያለ ነገር ተናገረ፡፡ እኔ ከመካከሉ የገባኝ “…ሆም ስፔሻል...” የሚለው ብቻ ነው፡፡ በወቅቱ የወንዶቹ መጸዳጃ ቤት በሩ ተበላሽቶ ስለነበር እነርሱ ደግሞ ለመጸዳጃ ቤት ያላቸውን ግምት ስለማውቅ በሩ የተስተካከለ መጸዳጃ ቤት የፈለገ መሰለኝ ‘...ካም…’ ብዬ ሴቶች መጸዳጃ ቤት ወሰድከት እና ‘...ዩዝ…’ አልኩት፡፡ ግራ በመጋባት ስሜት ጭንቅላቱን ነቅነቅ አደረገና በትዝብት አየት አደረገኝ፡፡ እኔ አልገባኝም አሳይቼው ምልስ አልኩ እና ቦታዬ ቁጭ አልኩ፡፡ ለካ ተመልሶ መጥቶ ለቀሩት አውርቶላቸዋል ቤቱ በሳቅ አውካካ እርሱ ማዘዝ የፈለገው ቤቱን “ልዩ ምግብ” ነበር፡፡
ሲሳይ ከፈረንጆቹ የሙዚቃ ባንዶች ጋር መሥራቱ፣በቤቱ እና በሬስቶራንት የኢትጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የሚያደርገው ጥረት በከተማው በሚተላለፍ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ላይ እንዲቀርብ አስችሎታል፡፡ ፕሮግራሙ ሲተላለፍ የቀዳውን ከፍቶ አስደመጠኝ ለመረጃ ያህል ሲዲውን እንዲሰጠኝ ጠየኩት፡፡ ‹‹ይሄማ እንጀራዬ ነው ትንሽ ቀደም ብትይ ሌላ አዘጋጅልሽ ነበር›› አለኝ፡፡ ገልብጬ ልልክለት እንደምችል ብነግረውም ሥራ ይዞት ሊወጣ መሆኑን ጠቅሶ ነፈገኝ፡፡ ሲሳይ አርብ እና ቅዳሜ የታክሲ ሥራውን ከቀን ይልቅ ማታ መሥራት ይመርጣል፡፡ ያን ዕለትም ግብዣው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሥራው ለመውጣት መዘጋጀት ጀምሯል፡፡የሲዲው እና የታክሲ ሥራው ቁርኝት አልገጥም ብሎኝ ጠየኩት፡፡
‹‹የታክሲን ሥራ አሰልቺ ከሚያደርግብኝ ነገሮች አንዱ የማሳፍራቸው ሰዎች ጭቅጭቅ ነው ‹‹ከየት ነው የመጣኸው?›› ስትነግሪያቸው ኢትዮጵያን የሚያውቋትም የማያውቋትም የማያባራ ጥያቄ ይደረድራሉ እንዲሁ ስንተባተብ ውዬ አመሽ ነበር አሁን ግን ‹‹.. ከየት ነው የመጣኸው ?›› ሲሉኝ ‹‹…ሚ….ዌይት …..›› እልና ሲዲውን ክፍት ሳደርገው ስለ እኔ በሬዲዮ የተሠራው ሙሉ ታሪክ መተረክ ይጀምራል ይሄኔ ‹‹…ሲሳይ ሚንስ ሚ….አይ ከም ፍሮም ኢትዮጵያ›› እልና እሱን ጋብዤ እገላገላለሁ፡፡›› አለኝ፡፡
ሲሳይ ጓደኞቹንም የጎንዮሽ ይነቁራል፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ እኮ የእኔ ቢጤ ናቸው፡፡የተወሰኑ ቃላትን ቅላጼ አሳምረው እየደጋገሙ ሲያወሩ የቻሉ ይመስላቸዋል፤ለነገሩ እኛ ጎጃም እየኖርን እንዴት እንለምዳለን ቀኑን ሙሉ የምናወራው በአማርኛ እንግሊዘኛው ሆዴ ውስጥ መቀበር ይነሰው እንዴ›› አለኝ፡፡ ‹‹ይልቅ እንግሊዘኛው ከሆዴ ወጥቶ መናገር እንድችል አገር ቤት ለሚገኝ ሁነኛ ታቦት ተሳይልኝ››በሹፈት መልክ ዘላለማዊ ፍላጎቱን ነገረኝ፡፡ (ይቀጥላል)

 

Read 5238 times Last modified on Friday, 15 March 2013 07:29