Sunday, 03 March 2013 08:26

የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ ‘ማንበብ’…

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“በህዝብ ጥያቄ የተደገመ…” የሚሉት ነገር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ ማንበብ፡፡ ሁልጊዜ ግርም የሚለው ነገር ምን መሰላችሁ… እኛ በቅርበትም በርቀትም የምናውቃቸው ሰዎች አንዳቸውም “ጥያቄ አቅራቢዎች ውስጥ አለሁበት…” ሲሉ አለመስማታችን፡፡ እኔ ይሄኔ…በቃ…“የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ እየተነበበ ነው” እንላለን፡፡ (ጥያቄ አለን…“አህዛብ እንጂ ህዝብ አይደላችሁም” ካልተባልን በስተቀር እንዴት ነው “እንዲደገም…” የሚጠይቁት ውስጥ የማንገባሳ! ቂ…ቂ…ቂ…)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ሰውየው… የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ነው፡፡ እናላችሁ… ተማሪዎቹን ስለ ውሸት ሊያስተምራቸው ይፈልጋል፡፡ ትምህርቱን ለመጀመርም እንዲያነቡ የሰጣቸውን መጽሐፍ ከፍ ያደርግና “እዚህ መጽሐፍ ላይ ሀያ አምስተኛውን ምዕራፍ ያነበባችሁ ስንት ናችሁ?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ክፍሉ ውስጥ ያሉ ሁሉ እጃቸውን ያነሳሉ፡፡
አስተማሪውም ምን ቢላቸው ጥሩ ነው…“ሥራዬ ከባድ ይሆናል ማለት ነው፡ መጽሐፉ ውስጥ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ የለም፡፡”
እናላችሁ…እንዲሀ አይነት የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡ ሰዎች ብቻ ሳንሆን ‘የሰማይ ስባሪ’ የሚያካክሉ ተቋማት፣ ‘የሰማይ ስባሪ’ የሚያካክሉ ‘ፐርሰናሊቲስ’…ምን አለፋችሁ…ከዳር ዳር የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አነበብኩ…” ማለት በጋራ የተሰጠን ባህሪይ እየመሰለብን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ “ለምንድነው ህብረተሰባችን ውስጥ እንዲህ መተማመን የጠፋው?” ብላችሁ ጠይቃችሁ አታውቁም፡፡ እንደዚህ አይነት ህብረተሰብን ከስረ መሰረቱ ሊነቅሉ የሚችሉ ነገሮችን ጥናት አካሂዶ መፍትሄ የሚጠቁመን ይጥፋ! የምር አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ያለመተማመን የግለሰቦች፣ የቡድኖች ምናምን ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ወደ አገር ደረጃ ከፍ ሲል አሪፍ አይደለም፡፡ በብዙ ነገር “በእነሱ ቤት እኮ እኛን ማታለላቸው ነው!” እየተባባልን ነው፡፡
እንዲህ የሆንነው ለምን መሰላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ስለሄድን፡፡
ለምሳሌ መግለጫዎች ምናምን ስንሰማ ወይም ስናነብ “እሱን እንኳን ተዉት፣ ምን ያላልንበት ዳገት የለም አለች እንስሳዋ…” ምናምን ማለት ከጀመርን ውለን አደርን፡፡ አሀ..ልክ ነዋ…ብዙ ነገሮች ከቃላተ ጋጋታና ከ‘ዘመኑ አማርኛ’ ባለፈ ከመግለጫው አዳራሽ እንደተዋጣ ሁሉም ነገር ‘የሀላፊ ጊዜ ግስ’ ሆኖ ይቀራላ!
በተበለጨለጨ አዳራሽ ‘የተብለጨለጩ መገለጫዎች’ ሲሰጡን ለማመን እየተቸገርን ያለነው የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡
(በዚህ መሀል የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ… ‘እውነት ሊሆኑ የሚችሉ’ ነገሮች ሜዳ ላይ እየቀሩ መሆናቸው፡፡)
ለምሳሌ…ይሄ “በህዝብ ጥያቄ የተደገመ…” የሚሉት ነገር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ ማንበብ፡፡ ሁልጊዜ ግርም የሚለው ነገር ምን መሰላችሁ… እኛ በቅርበትም በርቀትም የምናውቃቸው ሰዎች አንዳቸውም “ጥያቄ አቅራቢዎች ውስጥ አለሁበት…” ሲሉ አለመስማታችን፡፡ እኔ ይሄኔ…በቃ…“የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ እየተነበበ ነው” እንላለን፡፡ (ጥያቄ አለን…“አህዛብ እንጂ ህዝብ አይደላችሁም” ካልተባልን በስተቀር እንዴት ነው “እንዲደገም…” የሚጠይቁት ውስጥ የማንገባሳ! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡
አንዳንዴ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ይሄ “በህዝብ ጥያቄ የተደገመ…” ዝም ብሎ ምክንያት መፍጠሪያ አይነት ነገር ይመስለኛል፡፡ “ይህ ፕሮግራም ጠቃሚ ነገሮች ስላሉበት ያዩት እንዲደግሙት፣ ያላዩት እንዲያዩት ተደግሟል…” ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ እኮ ‘ዋር ኤንድ ፒስ’ ‘ክራይም ኤንድ ፐኒሽመንት’ ምናምን መዘርዘር አያስፈልግም፡፡
እናላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እዚህ አገር አዲስ አሠራር ሁሉ ሳይሳካ በሌላ አዲስ አሠራር ለምን የሚተካ ይመስለኛል መሰላችሁ…ገና የወጡ ‘ናሙና’ ሳይቀመስ እምቢልታና መለከቱ ስለሚበዛ!
ለምሳሌ አንዳንድ ሰው በአጭር ጊዜ መልኩ ምናምን ተለዋውጦ ስናየው “የእግዚአብሔር ሥራ ነው…” ምናምን ቢለን ምንም አናምነውም፡፡ እዚህ አገር አፍንጫ፣ ‘ብሬስት ምናምን’ አይነት ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ተለምዷላ!
መልክን የመለወጥ ነገርን ካነሳን አይቀር…ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ነገር ስሙኝማ…የሆነች መካከለኛ ዕድሜ ላይ የደረሰች ሰው የልብ ድካም ይገጥማትና ሆስፒታል ትሄዳለች፡፡ እናላችሁ… እየታከመች ሳለች በመንፈሷ እግዚአብሔር ይታያታል፡፡ ይሄኔ እያስተዛዘነች “አምላኬ፣ በቃ አለቀልኝ ማለት ነው?” ትለዋለች፡፡ እሱም፣ “አይ ያንቺ ጊዜ ገና ነው፡ ምድር ላይ ገና 43 ዓመት፣ ከ2 ወር ከ8 ቀን ይቀርሻል” ይላታል፡፡ሲሻላትም ራሷን ለመለወጥ ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ለማድረግ ሀኪም ቤት ትሄዳለች፡፡ አፍንጫዋ ሰልካካ ተደረገ፣ ሾል ያለ አገጯ ተስተካከለ፣ ‘ብሬስቶቿ’ ሞላ እንዲሉ ተደረጉ፣ የጸጉሯ ቀለም ተለወጠ…ብቻ ሙሉ ለሙሉ ሌላ ሰው ሆነች፡፡ ህክምናው አልቆ ልክ ከሆስፒታሉ ስትወጣ ግን መኪና ይገጫትና ትሞታለች፡፡
ከዛም እግዜሐር ፊት ስትቀርብ ምን ትላለች…“ገና አርባ ሦስት ዓመት አለሽ አላልከኝም ነበር እንዴ! ለምንድነው ከመኪናው ፊት ስበህ ያላወጣኸኝ?” ትለዋለች፡፡ እግዜሐር ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው… “ሙሉ ለሙሉ ተለውጠሻል፣ አንቺ መሆንሽን አላወቅሁማ!” አላት፡፡
እናማ… ይሄ ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት አበሳም አለው ለማለት ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ ድንብርብሩ እየወጣ እንደገና የውሸት አፍንጫና አገጭ እየበዛ ሲሄድ “የእግዚአብሔር ሥራ…” የሆነውን ሁሉ እየተጠራጠርን ነው፡፡እናላችሁ…የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ያለመተማመን የባህሪያችን ዋና መገለጫ እየሆነ ነው፡፡
እኔ የምለው…መቼም የዘንድሮ ነገራችን ቢወራ፣ ቢወራ ፈቀቅ የማይል ሆኗል፡፡ በብዙ ነገሮች በአለባባስ በሉት፣ ከሰዎች ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ በሉት፣ በምግብ ‘አመራራጥ’ በሉት…እዚቹ እኛዋ ሀበሻ አገር ሆኖ የፈረንጅነት የክብር ዜግነት አለኝ ሊል ምንም የማይቀረው የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የሚል መአት አለላችሁ፡፡
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የዜግነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሩሲያዊው፣ ፈረንሣዊውና እንግሊዛዊው አዳም የምን አገር ዜጋ እንደሆነ ይከራከሩ ነበር፡፡ፈረንሣዊው፣ “ያለምንም ጥርጥር አዳም ፈረንሣዊ ነው፡፡ ከኢቭ ጋር እንዴት በስሜት ፍቅር እንደሚሠራ አታዩትም!” አለ፡፡እንግሊዛዊው ደግሞ፣ “የነበረቻቸውን ብቸኛ አፕል ለሴቷ ሰጣት፡ በእርግጥም እንግሊዛዊ እንጂ የሌላ አገር ዜጋ ሊሆን አይችልም፣” ይላል፡፡
ሩስያዊው ይህን ሁሉ ከሰማ በኋላ ምን ቢል ጥሩ ነው…“አዳም የሌላ አገር ዜጋ ሳይሆን ሩስያዊ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከአንዲት አፕል ሌላ ምንም ሳይኖራቸውና ራቁቱን ወዲህ ወዲያ እያለ ብርድ እየቀፈቀፈው መንግሥተ ሰማያት ነኝ ብሎ የሚያስብ ሩስያዊ ብቻ ነው፡፡” አሪፍ አይደለች!
“አንድ ቁራሽ ዳቦ እንክት ያደርግና
አንድ ጣሳ ውሀ ግጥም ያደርግና
ተመስገን ይለዋል ኑሮ ተባለና…” የምንለው አይነት የእኛ አገር ጉድ እንደ ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሩስያን ነገር ካነሳን ይቺን የተስማማችኝን ቀልድ ስሙኝማ…ስታሊን ይሞትና ገሀነም ይወርዳል፡፡ እሱ እዛ በወረደ በጥቂት ቀናት ውስጥ አንድ ሌሊት መንግሥተ ሰማያት በር ላይ ቅልጥ ያለ ጩኸት ይሰማል፡፡ ለሽ ያለ እንቅልፍ ላይ የነበሩት መላዕክት ተደናግጠው ይነቃሉ፡፡ ቅዱስ ዼጥሮስ በሩን ሲከፍት ደጅ የሰይጣን መአት ሜዳውን ጥምቀተ ባህር አስመስሎታል፡፡ “ምን ሆናችሁ! ደግሞ እዚሀ ምን ልትሠሩ መጣችሁ?” ይላቸዋል፡ እነሱም “እኛን ከገሀነም እንደመጣን የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች ቁጠረን፣ የፖለቲካ ጥገኝነት ይሰጠን፣” ይሉታል፡፡ እሱም ምክንያታቸውን ሲጠይቃቸው ምን ቢሉት ጥሩ ነው… “ስታሊን የሚባል ሰው መጥቶ ገሀነምን በአንድ እግሯ አቁሟታል፣ የእሱን ጭቆና መቋቋም ስላልቻልን በመንግሥተ ሰማያት ጥግኝነት ይሰጠን” አሉ ይባላል፡፡እናላችሁ…የግብረ ገብ ጉዳይ ያገባናል ማለት የሚገባቸው አንዳንድ ተቋማት… እንኳን እኛን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መመለስ ቀርቶ…አለ አይደል… ለራሳቸውም ‘ራዳሩ ሲጠፋባቸው/ሲያገኙ፣ ሲጠፋባቸው/ሲያገኙ’…አንዳንዴ ራሳቸው አቅጣጫ የሚያሳይ ያጡ ይመስላል፡፡ ረናማ…አሌ የሚለን እየጠፋ የሌለ ሀያ አምስተኛ ምዕራፍ “አንብቤያለሁ…” የምንል ሰዎች እየበዛን ነው፡፡
መልካሙን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3724 times